Sunday, 31 July 2011 14:08

ወዴት እንደግ?

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

ወደ አክሱምና ላሊበላ ወይስ ወደ አፄ ምኒልክ?
..ስለ አክሱም፣ ላሊበላ፣ ሐረር፣ የፋሲል ግንብና ስለመሳሰሉት ታሪካዊ ነገሮች በአገር ውስጥና በውጭ ባለሙያዎች በርካታ ጥናቶች ተሰርተዋል፡፡ እኛ ..እንደገና.. የተሰኘውን  የቴሌቪዥን ዘጋቢ ፊልምን ለማዘጋጀት ስንነሳ ቀድመው ከተሰሩት የተለየ ነገር የማምጣት ዓላማ ኖሮን ሳይሆን ቁጭት ለመፍጠርና የተመልካቹን ስሜት ለማነሳሳት ነው የሞከርነው፡፡ ተሳክቶልናል ብለን እናምናለን፡፡..

አላቲኖስ የፊልም ሰሪዎች ማህበር በየሳምንቱ ሐሙስ በፑሽኪን የባህል ማዕከል በሚያቀርበው ዝግጅት ለሐምሌ 14 ቀን 2003 ዓ.ም የጋበዛቸው ሁለት እንግዶች ነበሩ ከላይ የቀረበውን ምስክርነት የሰጡት፡፡ በ..እንደገና.. ዘጋቢ ፊልም ላይ በዳይሬክተርነትና በፕሮዲዩሰርነት የተሳተፉት ይርጋ መንግሥቱና መስከረም ጌታቸው ለ50 ደቂቃዎች የተላለፈውን የቴሌቪዥን ዘጋቢ ፊልም ለማዘጋጀት የስድስት ሳምንት ጊዜ እንደወሰደባቸውም ገልፀዋል፡፡
በዕለቱ ዘጋቢ ፊልሙ በስክሪን እንዲታይ ከተደረገ በኋላ በውይይቱ ወቅት ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል ዘጋቢ ፊልሙን ለመስራት መነሻ ምክንያታችሁ ምን ነበር? ቦታዎችንና ሰዎችን እንዴትና በምን መመዘኛ መረጣችሁ? ለርዕሰ ጉዳዩ የሚመጥኑ ባለሙያዎችን ከየዘርፉ ለምን አልጋበዛችሁም? ሥልጣኔዎቻችን ወደዚህኛው ዘመን መሻገር ያልቻሉበት ምክንያት ለምን አልተነገረም? ዘጋቢ ፊልሙ በመንግሥታዊ ተቋም ባይሰራ ምን የተለየ ነገር ይኖረው ነበር? የቀድሞ ዘመን ሥልጣኔዎቻችን ተያያዥነትና ቀጣይነት ባለው ሁኔታ የተገኙ ናቸው ወይ? ከባለፉት መንግሥታት መጥፎውን ብቻ ሳይሆን ጥሩ ነገሮችን መጥቀስ ለምን አልቻላችሁም? ዶክመንተሪ ከፊቸር ፊልም የሚለይበት አንዱ ግብ ያለው መሆኑ ነው፡፡ ዘጋቢ ፊልማችሁ ተደራሽነቱ ማንን ግብ ያደረገ ነው? ሕፃናት፣ ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች?...
በዚህ መልኩ ለቀረቡት ጥያቄዎች ከሁለቱ ተጋባዦችና ከተሳታፊዎችም ሰፋ ያሉ መልሶች ተሰጥተዋል፡፡ ራሱን ከፍ አድርጎ ለማሳየት ትላልቅ ሐውልቶችን ያቆም የነበረው የአክሱማውያን ስልጣኔ የተመራበት ፍልስፍና፤ መንፈሳዊነት ተጭኖት፣ መሸሸና መደበቅን ዓላማው አድርጐ፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ካነው ፍልስፍና የተለየ ነበር የሚል መልስ በተሰጠበት መድረክ፤ የፋሲል ነገሥታትም ከቀድሞው በተለየ መልኩ የውጭ ዜጎችን አስመጥተው ሕንፃዎቻቸውን እስከ ማሠራት መድረሳቸውም ተነግሯል፡፡
kኢትዮጵያWÃN ዕውቀት፣ ፍልስፍናና ሀሳብ ጋር በተያያዘ ከዕለቱ ታዳሚዎች ከተሰጡት መልሶች አንዱ ..ብቸኛው ፈላስፋ.. ዘርዓ ያዕቆብ ኢትዮጵያዊ መሆኑ እርግጥ ቢሆንም ፍልስፍናው ከፈረንሳይ ፈላስፎች ጋር መመሳሰሉ ወይም ከውጭዎቹ የተቀዳ ስለመሆኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁራን በቅርቡ አዘጋጅተውት በነበረ መድረክ መግለጻቸውም ተነግሯል፡፡
ኢትዮጵያ ከዓለም ታላላቅ አገራት አንዷ ብትሆንም በዕድገት ቁልቁል እያደገች ለዛሬ መድረሷ የሚገባቸው፣ የማይገባቸው እንዲሁም ይገባታል ብለው በጥላቻ የሚቀበሉት የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች አሉ ያሉት የዘጋቢ ፊልሙ ዳይሬክተርና ፕሮዲዩሰሯ፤ lሥልጣኔዎቻችን አለመቀጠል ምክንያት የሆኑ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ ጉዳዮች ብዙ ናቸው፡፡ ወደዚያ ጥልቅ ጉዳይ ከመግባት ይልቅ ለፊልሙ በተመረጡ ማሳያ ቦታዎችና ተናጋሪ ሰዎችን አይቶ ተመልካቹ ..እውነትም ምን ነካን?.. ብሎ እንዲነሳሳ ነው የሞከርነው ብለዋል፡፡    
ከድል ታሪኮቻችን አድዋን በምሳሌነት መርጠናል ያሉት የመድረኩ ተጋባዦች፤ በዘጋቢ ፊልሙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማቅረብ ሞክረናል፡፡ ማንም ቢመጣ ከአገራችን ችግር አንፃር ሊናገር የሚችለው ተመሳሳይና ተቀራራቢ ነገሮችን ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው ቢማርም ባይማርም፤ ቢያውቅም ባያውቅም ዘጋቢ ፊልሙን አይቶ ..እኔስ ምን እየሠራሁ ነው?.. የሚል ስሜትና ቁጭት እንዲሰማው ነው የፈለግነው፡፡ አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ ..አክሱምን እንዴት አምጥተው ተከሉት?.. ብሎ በጥያቄ መልክ የሰጠው መልስ ስሜታዊ ገለጻ ነው፡፡ ባለሙያ ብንጋብዝ ለጥያቄው የሚሰጠን መልስ ሐውልቱ እንዴት እንደመጣ ትንታኔ በማቅረብ ነው የእኛ ፍላጐትና አነሳስ ደግሞ አትሌት ኃይሌን መሰል ሰዎች የሚሰጡትን ገለጻ የፕሮግራም ተመልካቹም እንዲጋባበት ነው፡፡
እንደ ማንኛውም ሥራ ስህተቱ ከእኛ የመነጨና ተጠያቂነቱን ሌሎችም የሚጋሩት ችግሮች በዘጋቢ ፊልሙ ሥራ ወቅት ገጥመውናል ያሉት ይርጋ መንግሥቱና መስከረም ጌታቸው፤ በፕሮግራሙ የአገራችንን መንግሥታት ታሪክ ለማሳየት አይደለም የፈለግነው፡፡ የ1965 እና የ1977 ዓ.ም. ድርቅን ለማሳያነት ያመጣነው ያንን ዘመን ለመውቀስ አይደለም፡፡ ረሀብ በ1994 ዓ.ም. ተከስቷል፡፡ ድርቅና ረሀብ የብዙ ነገሮች ድምር ውጤት እንጂ በራሱ ችግር አይደለም፡፡
ዘጋቢ ፊልሙ ላይ የታዩብን ስህተቶች ከጊዜ ማጠር ጋር በተያያዘ የተከሰተ ነው ያሉት ተጋባዦች፤ ፕሮግራሙን ለመሥራት ምንም ዓይነት ጫና አልነበረብንም፡፡ ሙሉ ኃላፊነት ተሰጥቶን ነው የሠራነው፡፡ በመጨረሻ ላይ የህዳሴውን ግድብ ያመጣነው ለሀሳብነቱ ነው፡፡ ዳንኤል ክብረት ..ትልቁ ነገር መታሰቡ ነው.. እንዳለው፤ ዘጋቢ ፊልሙም ተለውጠናል፣ አድገናል ብሎ አያበቃም፡፡ ተነስተናል፣ ጀምረናል፣ እንቀጥልበት ነው የሚለው ብለዋል፡፡ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ ወጣቶች ታዳሚና ተሳታፊ በነበሩበት የሐምሌ 14ቱ የፑሽኪን ባህል ማዕከል ስብሰባ ከተነሱት ጥያቄዎች ..የቀድሞ ዘመን ሥልጣኔዎቻችን ተያያዥና ቀጣይነት ባለው ሁኔታ የተገኙ ናቸው ወይ?.. የሚለው ጥያቄና ..የዘጋቢ ፊልሙን ተመልካች ስሜታዊ ለማድረግ፣ ለማነሳሳት ነው የጣርነው.. የሚለው መልስ፤ እኔም በዚህ ጽሑፌ በርዕስነት ያቀረብኩትን ጥያቄ እንዳነሳ ምክንያት ሆኖኛል፡፡ በእውነት ግን ወዴት ነው ማደግ ያለብን? ወደ አክሱምና ላሊበላ ወይስ ወደ አ ምኒልክ? ብዙ የሚያወያይ፣ የሚያነጋግር፣ የሚያሳስብ ይመስላል፡፡አገራችን ባለፉት ጥቂት ዓመታት አንጻራዊ ሰላም ማግኘቷ ዋነኛው ምክንያት ሆኖ መሬት የነካና የሚታይ የልማት ሥራዎች ተግባራዊ መሆን ጀምረዋል፡፡ በተቃራኒው ከዕለት ማግስት እየተባባሰ ከመጣው የኑሮ ውድነት ጋር በተያያዘ የዕድገቱ መኖር አለመኖር አከራካሪ በሆነበት ወቅት ነው ..ጀምረናል በዚህ እንቀጥል.. የሚል መልዕክት ያለው ..እንደገና.. የቴሌቪዥን ዘጋቢ ፊልም የቀረበው፡፡ መሠራቱ የሚደነቅ ነው - ቢያንስ መነጋገርን ፈጥሯል፡፡
ግን ደግሞ በዘጋቢ ፊልሙ በታየው ምስል፣ በተደመጡ ንግግሮች፣ ለዝግጅቱ የተሰጡ አስተያየቶችና የመድረክ ላይ ውይይት ..ወዴት እንደግ.. የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ የአክሱም ሥልጣኔ ለላሊበላ ያሸጋገረለት ነገር አለ ወይ ተብሎ ሲጠየቅ መልሱን ደፍሮ የሚመልስ ሲጠፋ ምንድነው ሊባል የሚችለው? የሐረር ሥልጣኔ ከላሊበላ ምንም አልወሰደም ሲባልስ?...
በሐምሌ 14ቱ የፑሽኪን ባህል ማዕከል ስብሰባ፤ በዘጋቢ ፊልሙ ላይ አስተያየት የሰጠ አንድ ወጣት ..ከሁሉም ተናጋሪዎች በተለየ መልኩ ገለጻና አስተያየት የሰጡት ፕሮፌሰር እንድሪያስ እሸቴ ናቸው፡፡ የእሳቸው ገለጻዎች መተንተን ነበረባቸው.. ብሏል፡፡ በቴሌቪዥን ዘጋቢ ፊልም ላይ ፕሮፌሰሩ ..ታሪካችን ይበዛብናል፤ ይጫነናል.. ነበር ያሉት፡፡ አስተያየት ሰጪው ወጣትም ታሪካችን ለምን እንደሚበዛብን መጠየቅ ነበረባቸው ነው ያለው፡፡
በዘጋቢ ፊልሙ ላይ የፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴን ሀሳብ በሌላ አገላለጽም ቢሆን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም ደግመውታል፡፡ ..ዛሬ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሆነንም በአክሱማዊያንና በላሊበላ ዘመነ መንግሥታት የተሠሩትን ደግመን መሥራት አንችልም.. እውነታው ይህ ከሆነ ታዲያ ወዴት እንድናድግ ነው የሚፈለገው?
ዘመናዊ ሥልጣኔን ወደ አገራቸው ለማስገባት አፄ ቴዎድሮስ የተመኙትን አፄ ምኒልክ አምነውበት ለሥልጣኔ በሩን ሙሉ ለሙሉ ባይከፍቱት ኖሮ፣ ሌላው አገራዊ የዕድገት አማራጭ ምን ይሆን ነበር? ብሎ መጠየቁ ተገቢ የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተሠሩ የዕድገት ሥራዎች፣ አፄ ምኒልክ የተቀበሉትን ዘመናዊ ሥልጣኔ መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ደርግም ኢሕአዴግም በዚያው መስመር መጓዝ ነው የቀጠሉት፡፡ከዚህ በመነሳት የዘመነ መሳፍንት አገዛዝ ካከተመ በኋላ የመጡት ሁሉም መንግሥታትና መሪዎች የአክሱማዊያንና የላሊበላ ነገሥታትን ሥራ ደግመው መሥራት እንደማይችሉ እርግጠኛ ሆነዋል ማለትስ ይቻላል? አፄ ምኒልክ የውጭ ሥልጣኔ ወደ አገራቸው በማስገባታቸው እስካሁንም ድረስ ሲመሰገኑ የምንሰማው ለዚህ ይሆን? አሁን ያለው ብቸኛው የዕድገት አማራጭ አፄ ምኒልክ ባቀኑልን መስመር መጓዝ ብቻ ነው?  
ኢንጂነሪንግ፣ የሂሳብ ዕውቀቱ፣ የከርሰ ምድር ጥናት... ባልተስፋፋበት ዘመን የተሠሩት የአክሱምና የላሊበላ ነገሥታት ዘመን ሥራዎች በድንገት የተገኙ ነገሮች ሆነው ግራ እንዳጋቡን ቀጣይ ዓመታትንም እንቆጥር ይሆን? ስለ ድንገተኛ ሥራ ከተነሳ የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ በ..እንደገና.. የቴሌቪዥን ዘጋቢ ፊልም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሲናገሩ ..በድንገት ተነስተን ምን መሥራት እንደምንችል ለዓለም አሳይተንበታል.. ብለዋል፡፡ እውነታው ይህ ከሆነ ታዲያ የሚበዙብን፣ የሚጫኑን የተባሉትን ታሪኮቻችንን ለዕድገት መቀስቀሻነት መጠቀም ተገቢ ነውን? ከስሜታዊ ቅስቀሳ ይልቅ ተጨባጩ እውነት ላይ ተነጋግሮ ለዘላቂ ለውጥ የሚጠቅመንን ይዞ መቀጠሉ አይሻልም ወይ? ስለዚህ ወዴት እንደግ? ወደ አክሱምና ላሊበላ ወይስ ወደ አፄ ምኒልክ?

Read 3325 times