Sunday, 31 July 2011 14:10

የህይወት ጨዋታ ምናባዊ ወግ

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(4 votes)

ዳማ ጨዋታ ለጥንት ሰዎች የሚሆን ብቻ ሳይሆን የጥንት ሰውነትን የሚያመለክት ጨዋታ ነው፡፡ . . .ዳማ ላይ ሴት አልተካተተችበትም፡፡ ሁሉም ወታደር ወንድ ነው፡፡ . . .እንደ ዘመነ መሳፍንት ስርዓት ሁሉም ወታደር ተፋልሞ የሰሌዳው ወይም የኃይሉ መጠነኛ ጫፍ ሲደርስ ንጉሥ ይሆናል፡፡ . . .በዘመነ መሳፍንት በአንድ ሀገር ላይ ብዙ የመሳፍንት ንጉሦች ይገኛሉ፡፡ ተራው ወታደር መሳፍንቱን ሊነካው ባይችልም መሳፍንት እና መሳፍንት ግን ይጋጠምና ይበላላል፡፡ . . .ይህ የመሳፍንት ዘመን ነበር፡፡ ዳማም ለዚህ ዘመን ተገቢ የሆነ ጨዋታ ነው ወይም ነበር፡፡

አንድ ሀገር በአንድ ንጉሥ የምትተዳደርበት ስርዓት ሲመጣ ከዳማው ይበልጥ የቼዙ ጨዋታ እና ህግ እውነታውን መምሰሉ አያጠራጥርም፡፡ . . .የቼዙ ጨዋታ ነጩዋ ንግሥት ኃያል የነበረችውን ንግሥት ኤልሳቤጥ ልታስታውሰን ከቻለች፣ ጥቁሯ ንግሥት ደግሞ የአድዋ ድል ጀግና እቴጌ ጣይቱ የማትሆንበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ . . .ቤተ መንግሥቶች (Castles) ከበኪንግሀም ፓላስ እስከ ፋሲል ግንብ በጥቁር እና በነጭ ግዛት ተመስለው ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ . . .ንጉሡ፤ ሻርልማይን ወይም አፄ ሚኒልክ ሊሆን ይችላል፡፡ ሁለቱም ታላላቅ ድል የተቀዳጁ ናቸው፡፡ . . .ቼዝ የንጉሥ ዘመን የስዩመ እግዚአብሔር በደም እና በዘር ተራው ከምርጡ የሚለይበት ነው፡፡ . . .እርግጥ እንዳንድ ተራ እግረኛ ወታደር እንደ መይሳው ካሣ የሰሌዳው ጠርዝ በኃይለኝነት እና ቆራጥነቱ በልጦ ሲነግስ ይታያል፡፡ በነጩ ጠጠሮች ተርታም ናፖሊዮን ቦናፓርት ይሄንኑ ገድል ፈጽሟል፡፡. . .
ቼዝ የዘውድ ስርዓት ጨዋታ ነው፡፡ ዳማው በቼዝ እንደተሻሻለው አሁን ለምንኖርበት ዘመን የሚሆን የተሻሻለ የሰሌዳ ጨዋታ ያስፈልገናል ብዬ ሳስብ ቆየሁ (እዛች የተለመደችዋ ወንበር ላይ ቁጭ ብዬ)
መሻሻል የሚመጣው ከነበረው ጨዋታ ወይም ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት መሆን እንዳለበት መግለጽ አያስፈልገኝም፡፡ ፡ ፡፡  እንደዚህ እንደሚከተለው ለማስተካከል ደፈርኩ (የሆነ ድም ..ደፋር.. ሲለኝ አይሰማችሁም?)
በዘመናችን ንጉሥ ብሎ ነገር የለም፡፡ ንግሥት ግን አለች፤ የቁንጅና ወይም የፋሽን ሾው ንግሥት ማለቴ ነው፡፡ . . .ንግሥቲቱ አንድ ጊዜ አግብታ ለዘለዓለም ከጐኑ በሞት በስተቀር የማትለየው ባል አያስፈልገኝም፡፡ ፡፡ በንጉሱ ትዕዛዝ ስር መኖር የሚያስገድዳት ህግ የለም፡፡ ምክንያቱም ንጉሥም ሆነ የቀድሞው የዘውድ ሥርዓት የለም፡፡ የድሮው የጨዋታ ባህል በአንድ ባህርይ እንድትመራአያስፈልገኝም፡፡ ፡፡ የድሮው የጨዋታ ሐሪሶት አሁን የለም፡፡ አሁን ጐራው ተቀይሯል፡፡ በጥቁሩ የቼዝ ጠጠሮች ተርታ ወንዶች ተሰልፈዋል፡፡ የተለያዩ ዓይነት ወንዶች፡፡ ሴት አስገድዶ ደፋሪ ወንዶች በድሮዎቹ ወታደሮች ፋንታ ተደርድረዋል፡፡ በቼዝ ፈረሶቹ ፋንታ የቼዝ መኪናዎች ቆመዋል፡፡ በቼዝ ጳጳሶቹ ፋንታ የጐልድ ኩዌስት ወይም የሊደር ሺፕ ጳጳሳት ቆመዋል፡፡ በቤተ መንግሥት ፋንታ ቤተ ህዝብ ወይም ኮንዶሚኒየም ተገትሮበታል፡፡ . . .ይህ የወንዶች ተርታ ነው፡፡ እንደ ጥንቱ የጥቁር ጠጠሮች ሊቆጠሩ ይችላሉ፡፡
በነጮቹ ጠጠሮች ፋንታ የሴት ሰራዊት ነው ከወንዶቹ ጋር ተፋጥጠው የቆሙት፡፡ ከአሥራ ስድስቱ የጥንት ዘመን የቼዝ ጠጠሮች ስምንቱ ወታደር እንደነበሩት፤ የአሁኑ ዘመን ስምንቱ ደግሞ ሴተኛ አዳሪ ናቸው፡፡ ከአሥራ ስድስቱ ስምንቱ፡፡ ቤተ መንግሥት የላቸውም ሴቶቹ ጠጠሮች፡፡ ከወንዶቹ ጋር ተጫውተው ኮንዶሚኒየማቸውን አና መኪናዎቻቸውን መውረስ ነው የሚፈልጉት፡፡ ፈረሶቻቸው ውበታቸው ናቸው፡፡ ጳጳሶቻቸው የሴት የበላይነትን የሚሰብኩ ናቸው፡፡ ንግሥታቸው የሴቶቹን እንቅስቃሴ አቀናብራ የያዘች ናት፡፡ ስሟ ቪነስ ነው፤ የፍቅር መርዝ ያለበትን ፍላጻ ከ..ኤሮስ.. ተቀብላ በአንድ እጇ ወድራለች፡፡ ወድራለች እንደጡቷ፡፡
እንግዲህ ፍልሚያው በወንድ እና በሴት መሀል ሆኗል፡፡ ይህ የአዲሱ ዘመን ቼዝ አደረጃጀት ነው፡፡ ጨዋታውም ሴትን መማረኪያ ..ቼዝ.. የሚለው ቃል ብቻ ሳይሆን የወንድ ማንበርከኪያውም ቋንቋ ..ቼክ.. አብሮ ታክሎበታል፡፡ ንብረቱን ሸጦ ሊያስረክባት ወይም እንዲያስረክባት አድርጋ ካንበረከከችው በኋላ የገንዘቡ መጠን የተገለበትን የባንክ ወረቀት እንዲሰጣት ስትጠይቀው ..ቼክ.. ትለዋለች፡፡ የባንክ ወይም ባንክ ተወስዶ የሚመነዘር ..ቼክ..፡፡
ወንዱም አባርሮ አባርሮ ሴቲቱን ሲያጠምዳት ..አባርሬ ነው በእጄ ያስገባሁሽ.. ???? እንደማለት ሲማርካት ..ቼዝ.. ይላታል፡፡ (I chased and caught you!) እንግዲህ በዚህ በአዲስ ..ቼክ እና ቼዝ.. አዲሱ ዘመናዊ የጨዋታ ህግ የወንድ እና የሴቷን ፍልሚያ ቼክ እና ቼዙ በመሠረቱ ጨዋታ ቢመስልም ከእውነተኛው ህይወት ጋር ግንኙነት አለው፡፡ የትኛውም ዓይነት ጨዋታ መነሻው እውነት ነውና፡፡ ጨዋታውም የቀልድ ሳይሆን ለጠጠሮች የምር ነው፡፡ ጨዋታም ሳይሆን ጦርነት ነው፡፡ ጥቁሮቹ የወንዶቹ ጐን ሴቶቹን ቢችል ሚስቱ አድርጐ ቤት ማስቀመጥ፣ ካልቻለ መድፈር እና መሰወር፣ ካልሆነ ከአንድ በላይ ሴቶች ይዞ ዲቃላ ማስታቀፍ፣ አልያም በመኪናው አጓጉቶ ጠልፎ መሰወር፣ ወይም የተሻለ መኖሪያ እሰጥሻለሁ ብሎ የተሻለ የኑሮ አቅጣጫዋን ማሳጣት የእሱ ተገዢ ማድረግ (ማሰር). . . ወዘተ፤ የአጨዋወት ወይም የፍልሚያ ዘዴው ነው፡፡ ሁለቱ ተቃራኒዎች የሚፈላለጉበትን ስበት ከተፈጥሮ ተቃራኒነታቸው ያገኙት ነው፡፡ ተቀላቅለው እንዳይጫወቱ ማድረግ አይቻልም፡፡ ከተቀላቀሉ በኋላ ደግሞ መጣላታቸው አይቀርም፡፡ የተፈጥሮ ስበት አለ፤ ተባራሪውን ወደ አባራሪው የሚያስጠጋው እና y¸ÃÃZ²cW፡፡ y¸Ãb§§cW፡፡
ሴቶቹም የራሳቸው የሆነ የጨዋታውን ማሸነፊያ በቂ ዘዴ አላቸው፡፡ ወንዱን ከገንዘቡ መለያየት የሚችሉባቸው የማስከፈያ ዘዴ - ሴተኛ አዳሪዎቹ በዚህ የተካኑ ናቸው፡፡ ወንዱ ማስረገዝ እና እነሱን ዲቃላ ማስታቀፍ ወይም አርፋ የምትቀመጥ ሴት ማድረግ መፈለጉ ከአጨዋወት ዘዴው ከገባቸው፤ የእርግዝና መከላከያ እና ሌላ የተለያየ አማራጭን በመጠቀም ያመልጡታል፡፡ የተጠመደላቸውን ወጥመድ በጥንቃቄ አልፈው ወንዱን ግን ሳያውቀው ራሳቸው ባጠመዱለት ወጥመድ ውስጥ መክተት መቻል ነው ዋና አላማቸው፡፡ ዋናው ወጥመድ ..ፍቅር.. ነው፡፡ እዛ ውስጥ ተሳስቶ የወደቀ ወንድ ሴቷ የፈለገችውን ልታደርገው መብቷ ነው፡፡ ፍቅር ውስጥ የገባ ወንድ እንደታሰረ ንጉሥ ወይም እንደተበላ ጠጠር ይቆጠራል፡፡ በፍቅር የታሰረውን ጠጠር ትታ ሌላውን የወንድ ጠጠር ለማሰር መንቀሳቀስ ትችላለች፡፡
የውበት ወጥመድን በመጠቀም ወንዱ እንዲያባርራት አድርጋ ታቀርበዋለች፡፡ ውበትን በመጠቀም ወንዱን ጠጠር ከሩቅ ወደ ቅርብ የማጥመጃ ርቀት ማምጣት ይቻላታል፡፡ ውበት በሩቅ እንደሚሠራው፤ ፍቅር ደግሞ በቅርብ ርቀት ያለ ጠላትን ለመጥለፍ የሚያገለግል ወጥመድ ነው፡፡ ሴተኛ አዳሪዎቹ ጠጠሮች የወንዱን ብር ድክመቱን በመጠቀም መውሰድ ይችላሉ፡፡
ለእያንዳንዱ ተቃራኒ ጐራ ለጥቃት የሚጠቀምበትን ዘዴ ማክሸፊያ ተቃራኒ ብልሀት አለ፡፡ ሴተኛ አዳሪን ሲያይ የፍትወት መንፈሱን መቆጣጠር የሚችለው ጠጠር ብሩን ሳይበላ የተጠመደበትን ተሻግሮ የማለፍ አቅም አለው፡፡ ግን ተሻግሮ የማለፍ አቅም ያለው ወንድ ጠጠር፣ መጠጥ ከመጠን ያለፈ ከጠጣ...ወጥመድ መዝለያ አቅሙን በስካር ያጣል፡፡ አንዳንዴ ሴቷም የፍቅር ወጥመዷን ዘርግታ፣ ደንባራው ወንድ እንዲወድቅላት ስትጠብቅ ራሷ ያልጠበቀችው የወንድ የፍቅር ወጥመድ ውስጥ ትወድቃለች፡፡ . . .ያኔ የወንድ ባሪያ፣ የዲቃላዎቹ እናት፣ የጡጫው ማረፊያ፣ የቤቱ ጠባቂ፣ ከሱ ጭንቅላት እና አንገት በታች ያለች ጭን እና ማህፀን ትሆናለች፡፡ እንደታሰረች ወይም እንደተበላች ይቆጠራል፤ እንደዚህ ስትሆን፡፡
ትዝ ይለኛል አንድ በቅርብ ጊዜ የተካሄደ የዋንጫ ጨዋታ፡፡ ሴቶቹ ወንዶቹን በልተው፣ ወርሰው፣ አስረው፣ አጀዝበው፣ ጠጪ አድርገው... ጨርሰዋቸው፤ የሰሌዳው ጠጠሮች አልቀዋል፡፡ አንድ ያልተጠመደ ወንድ ብቻ ነው የቀረው፡፡ የሴቶቹ ጐን ሁለት ጠጠሮች እሱን ለማሰር ቀረቡት፡፡ አንድ የቁንጅና ንግሥት እና አንድ ግብረ አበሯ . . .ወንዱ የተጠቀመው መንገድ ለመምረጥ ብቻ ሳይሆን ጨዋታውን ለመጨረስ ጠቀመው፡፡ . . . ሁሉም ሌላ ጠጠር (ወንድ) ለማሰር የሚሞክረው ንግሥቲቱን ነው፡፡ ይሄኛውም ጨዋታውን ለመጨረስ፣ ማድረግ የነበረበት ነገር ንግሥቲቱን ለማጥመድ ወይ ለመብላት መሞከር ነበር፡፡ ግን ከተጠበቀው በስተግራ ታጥፎ...የንግሥቲቱን አስቀያሚ ገረድ መውደዱን እና በፍቅሯ ሊሞት መሆኑን በቀስታ ለንግሥቲቱ ነገራት፡፡ እና ገረዲቱን መውደዱን እንድትነግርላት ለንግሥቲቱ ተማነ፡፡ የያዘውን ፍቅር በምን መልክ እውን ማድረግ እንደሚችል የሴት ምክሯን እንድትለግሰው ጠየቃት፤ በእንባ እየታጠበ፡፡ ንግሥቲቱ ቀናች፡፡ እኔን ሳይወድ እንዴት እቺን አስቀያሚ ጓደኛዬን (የቆንጆ ሴት አስቀያሚ ጓደኛ እንደ ገረድ ስለምትታይ) ይወዳል ብላ በገነች፡፡ ጓደኝየዋን እንዴት ማጥመድ እንደሚችል እየመከረችው እሷ ንግስት ሆዬ ራሷ በሱ ፍቅር ውስጥ ተጠምዳ መውደቋን እየቆየች ነበር የተረዳችው፤ ግን ጉዳዩ እንዳልሆነ በማስመሰል ገረዲቷ ላይ አተኮረ፡፡ በጥሩ አስመሳይ ትወናው የገረዷን የጫማ ጠረን ከመሬት ላይ እንደ ሽቶ አነፈነፈ፡፡ ንግሥቲቱ ለገረዲቱ ወጣቱ ወንድ ጠጠር ያለውን ፍቅር ንገሪልኝ ብሎ አደራ ባላት መልክ መልእክቱን አደራውን አልተወጣችም፡፡
ፍቅሩን ለማንም እንዲሆን ስለማትሻ፡፡ በስተመጨረሻ አላስችል ሲላት የፍቅሩ እስረኛ መሆኗን አፍ አውጥታ ነገረችው፡፡ . . .ወጣት ወንድ ጠጠር ንግሥቲቱን ካጠመደ በኋላ፤ ገረዲቱን ማጥመድአላስቸገረውም፡፡ ገረዲቱን እና ንግሥቲቱን በእጅ አዙር አስሮ በዚህኛው ጨዋታ ወንዶች ማሸነፋቸውን አወጀ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የቼዝ/ቼክ ጨዋታው ራሱ ከወቅታዊው የሰዎች ህይወት ጋር እየተመሳሰለ መምጣት ሳይሆን ጨዋታው እውነቱን እየሆነ መምጣት ጀምሯል፡፡ በእውነተኛው ህይወት ላይ ግን ሴቶቹ የበለጠ እያሸነፉ ነው፡፡ ከወንዶች ሥራ እየተካፈሉ መሥራት ጀምረዋል፡፡ ከወንዶቹ እኩል እየተማሩ መግባት ጀምረዋል፡፡ የወንዶቹን መኪና ቀድመው እየገዙ መንዳት ላይ ናቸው፡፡ ወንዱ ያደርግ የነበረውን ሴቶችን የማጥመድ የመጀመሪያ እንቅስቃሴ እነሱ ተግባር ላይ እያዋሉት ነው፡፡ ወንዱን አጥምደው መልቀቅ ወይም እንዳሠሩት ጥለውት መሄድ እየቻሉ ነው፡፡ ወንዱም በፍቅር ለመጠመድ እና ለመቸገር ቀላል እየሆነ መጥቷል፡፡ ሴቶቹ በተቃራኒው የሚሰበር ልብ አያስፈልግም ብለው የመጠመጃ ድክመታቸውን አስወግደዋል፡፡
በጭንቅላት ማሰብ ጀምረዋል፡፡ ለወንዱ የቀረው የጨዋታ ዘዴዎች፤ የሚያሸንፍባቸው ሳይሆን ራሱን በራሱ ጠልፎ የሚጥልባቸው ብቻ ሆነዋል፡፡ አስገድዶ እንደ መድፈር፣ ወይም እንደ መቅናት፣ በድሮው ባህል ስም ሴቶቹን እንደማውገዝ... ወዘተ የሚያራምድ የሽንፈት የጨዋታ ዘዴዎች. . .፡፡
የወደፊቱ የጨዋታው ተከታታይ ሻምፒዮናዎች ሴቶች እንደሚሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ህይወት ሴቶች ወንዶችን የሚያሸንፉበት ጨዋታ እየሆነ ነው፡፡

 

Read 5601 times Last modified on Sunday, 31 July 2011 14:18