Saturday, 06 August 2011 14:17

ፈሪሐ እግዚአብሔር ወይስ ዲሞክራሲ?

Written by  በዕውቀቱ ስዩም
Rate this item
(3 votes)

በገዳማም አገር
የክንፍ ድም ይሰማል ተርገብጋቢ ነገር
የመላክ አይደለም፣ ተመአት የሚያድን
ያሞራ ነውንጂ የሚበላ በድን
ሰሞኑን ሃይማኖት ፖለቲካን የተካው ይመስላል፡፡ የታሠሩ ጋዜጠኞች ጉዳይ በቅጡ ሳይነሳ በኑፋቄ የተጠረጠሩ ዲያቆናት ጉዳይ በዓለማዊ መጽሔቶች ገጽ ውስጥ ሰፊ ሽፋን ተሰጥቶት እናነባለን፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድም ብዙም በማይሰማበት በዚህ ሰዓት የምእመናን ማኅበራት በስሜት የነደደ መግለጫ ሲሰጡ እንሰማለን፡፡ ከፓርላማው ውሳኔ ይልቅ የሲኖዶሱ ውሳኔ ትኩረት ይስባል፡፡

የእኛ ህልውና ባልተረጋገጠበት ሁኔታ የእግዜሩን ህልውና ለማጣራት እየተሞከረ ይመስላል፡፡ ምን እያደረግን ነው? ምናልባት የአደባባይ ተሳትፎ በሌለበት የአደባባይ ተሳትፎ እያደረገን እንደሆነ እንዲሰማን የፈጠርነው ሐሳዊ ትርኢት ይሆን? እየኖርን ነው፣ እየተከራከርን ነው፣ እየደገፍን ነው፣ እየተቃወምን ነው የሚለውን የምናሳይበት የመጨረሻ ምልክት ይሆን?
ሃይማኖት ርዕሰ-ጉዳይ አይሆንም ማለቴ አይደለም፡፡ አንድ ግዙፍ ገዳም በሆነችው አገራችን ይቅርና በዓለማውያን አገሮች እንኳ ሃይማኖትን ቸል ማለት የሚቻል አይደለም፡፡ ግን አንገብጋቢ ጥያቄዎቻችንን የሚያስዘነጋ መሆን የለበትም፡፡ አንገብጋቢ ጥያቄዎቻችን ሁለት ናቸው፡፡ ዳቦ እና ዳቦውን በአግባብ የምንካፈልበት ሥርዓት፡፡
መራራውን ሀቅ ለመጋፈጥ የሚፈልግ ሰው ካለ ዳቦና ዲሞክራሲ ከእምነት ኃይሎች እንደማይፈልቁ ማወቅ አለበት፡፡ ያገራችን ገበሬ የሞፈር አቆራረጥንና የበሬ አጠማመድን ከቅዱሳት መጻሕፍት አልተማረውም፡፡ እንዲያውም ገበሬ የእምነት ሹሞችን እንደ ጥገኛ ሕዋስ እንደ¸መለከታቸው የሚያሳየን ..ካህንና ሽመላ ያልዘራውን ይበላ.. የሚለው ተረቱ ነው፡፡ የእምነት ሹሞች በገበሬው ህይወት ላይ ከዚህ ያለፈ ሚና ካላቸው ሚናው ከልካይነት ነው፡፡ በዚህ ቀን አትሥራ፣ በዚህ ቀን አትብላ እያሉ ይከለክሉታል፡፡ ውጤቱ ምን ሆነ? እያየነው፣ እየሰማነው፣ እየዳሰስነው ነው፡፡ እንዲህ ስንናገር ..ከቁስ ዕድገት ይልቅ የመንፈስ ዕድገት ይቀድማል.. እያሉ የሚያዳክሙን ብዙ ሰዎች አይጠፉም፡፡ እኒህን ብዙ ሰዎች የአዲስ አድማስ የቅርብ አምደኛ ዶክተር ፍቃዱ አየለ ይወክሏቸዋል፡፡ በበኩሌ ዶክተር ፍቃዱን ከልቤ ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ፡፡ በእምነት ስም ታላቂቱን አገራችንን ትንሽ ያደረጓትን አመለካከቶች እንድንመረምራቸው ወደ ዓለማዊው መድረክ ያመጡልን እርሳቸው ናቸው፡፡
ዕድገት ከቁስ ሳይሆን ከመንፈስ መጀመር አለበት ከሚለው ስህተታቸው እንጀምር፡፡
(ቁስ ለሚለው ቃል አቻ የሆነውና ብዙ ሰው የለመደው ..ንብረት.. የሚለው አማርኛ በመሆኑ በዚህ እንቀጥል፡፡) እኔና ቢጤዎቼ ያለ ንብረት ዕድገት የመንፈስ ዕድገት የሚባለው ትርጉም የለውም እንላለን፡፡ ይህንን ለማስረዳት ብዙ መራቀቅ አያስፈልግም፡፡ ሁለት ልብስ ያለው አንዱን ለታረዘ ይስጥ የሚለውን መንፈሳዊ ትዕዛዝ መመልከት ይበቃል፡፡ ሁለት ልብስ የንብረት መጠን ሲሆን አንዱን ልብስ ለታረዘ ይስጥ የሚለው በጐ አድራጐት ወይም መንፈሳዊነት ነው፡፡ መስጠት የምትችለው የተረፈ ምርት ሲኖርህ ነው፡፡ የሚለገስ በሌለበት ልግስና ትርጉም የለውም፡፡ ኃያላን አገሮች እኛን የሚረዱን ሀብታም ስለሆኑ እንጂ ሃይማኖተኛ ስለሆኑ አይደለም፡፡
ዶክተር ፈቃዱ ..የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው አፍሪካ የችጋርና የእርዛት ምክንያት ከጥንት እስከ ዛሬ ድረስ እግዚአብሔርN በማይፈሩ መሪዎች የመዳሸቅ ዳፋ ነው.. ብለውናል፡፡ እውነት? እንዲህ ዓይነቱ የዋህነት የሚመነጨው ፈሪሐ እግዚአብሔር የካህንነት እንጂ የመሪነት መስፍርት አለመሆኑን ካለማወቅ ነው፡፡ አንድ አገር አለቃ የሚመርጠው እንዲመራው ነው ወይስ እንዲቀድስለት? ከማል አታቱርክ ለዛሬዋ ቱርክ ታላቅነት እና ዲሞክራሲÃêEnT መሠረት የጣለ መሪ ነው፡፡ ግን አታቱርክ አማኝ አልነበረም፡፡ በይፋ ከተናገራቸው ንግግሮች አንዱን ልጥቀስ፣ ..እኔ ሃይማኖት የለኝም፡፡ መንግሥቱን ለማናት ሃይማኖትን ተገን የሚያደርግ መሪም ደካማ ነው፡፡ ሕዝቡን በወጥመድ ለመያዝ እንደመሞከር ይቆጠርበታል፡፡ ሕዝቤ yዲሞክራሲNÂ የሳይንስን ንሰ ሐሳብ ይማራል፡፡ ምልኪ ቦታ አይኖረውም፡፡..
በተቃራኒው የአምባገነኖች ቁንጮ ተደርጐ የሚቆጠረው ኢዲ-አሚን ዳዳ በፈጣሪ አጥብቆ ያምን ነበር፡፡ ግን እምነቱ ኡጋንዳን ከማደህየት፤ ኡጋንዳዊያንን እንደ ቄራ ሠንጋ ከማረድ አላስጣለውም፡፡ እንዲያውም፣ ..አይመረመሬው.. የአምባገነኖች መሸሸጊያ የሚሆንበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ ሮበርት ሙጋቤ ዚምባቡዌን ይሄን ያህል ዘመን አጨማልቀው ከገዙ በኋላ ስልጣናቸውን ለሕዝብ ያስረክቡ እንደሆን ሲጠየቁ ..እግዜር ነው የሾመኝ እግዜር ነው የሚያወርደኝ.. ብለው ደርቀዋል፡፡
ዶክተር ፈቃዱ የበለፀጉ አገሮችን የዕድገት ምስጢር ሲነግሩን እንዲህ ብለዋል፤  ..የበለጠጉት የእምነት አገሮች የብልግና ምክንያት እግዚአብሔርN በሚፈሩ ሰዎች መመራታቸዉንና ልክ እንደ ቃሉ ሰው ለነፃነት የተፈጠረ መሆኑን የሚያምን ሕግ ባለቤት መሆናቸው ነው.. (ያሰመርኩት እኔ  ነኝ)  
ዶክተር ብልግናንና እምነትን በግድ ለማዛመድ ..የበለጠጉት የእምነት አገሮች.. የሚል የሌለ ጎራ ፈጠሩ፡፡ የበለጠጉ የእምነት አገሮች እነማን ናቸው? ስም የላቸውም? እኔ የማውቃት ..የበለጠገች የእምነት አገር.. ሳዑዲ አረቢያ ናት፡፡ የነፃነት ጣዕሙም ሆነ መአዛው ግን አልደረሳትም፡፡ የብልግናዋ ምንጭም ሃይማኖቷ ሳይሆን ለእምነት ደንታ የሌላቸው ምዕራባውያን ቆፍረው ያወጡት ዘይቷ ነው፡፡

 

አሜሪካስ? በርግጥ አሜሪካ፣ ሀብታም ናት፡፡ የነፃነት አገርም መሆኗ አይካድም፡፡ ይሁን እንጂ ..በእግዜር እናምናለን.. የሚል መፈክር ዶላሯ ላይ አትማ መዞሯ በእምነት የበለጠገች አያሰኛትም፡፡ መታወቅ ያለበት ነገር የአሜሪካ ታላቅነት የመነጨው እጅግ ምርጥ ከሚባለው የፖለቲካ ሥርዓቷ ነው፡፡ የፖለቲካ ሥርዓቷን የገነቡላት መሥራች አባቶቿ በዘመነ መባነን) አስተሳሰብ እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ ወይም በቅዱስ ቁርዓን የሚመሩ አልነበሩም፡፡ አዲሲቱን አሜሪካ ከፈጠሯት መሪዎች ዋናው በሆነው በቶማስ ጄፈርሰን አዕምሮ ላይ ተእኖ ያሳደረበት ዮሐንሰ ሎክ እንጂ ዮሐንሰ ወንጌላዊው አይደለም፡፡ ዶክተር ከላይ በጠቀስኩላቸው አንቀጽ ..እንደ ቃሉ.. ብለው የይሁዲ ሃዋርያትን ትዕዛዝ፣ ከአሜሪካ ሕገ መንግሥት ጋር እኩያ ሊያደርጉት ሞክረዋል፡፡ ልዩነቱን ባያውቁት ነው፡፡ ..ቃሉ..ማ የሚለው ሰጥ ለጥ ብላችሁ ተገዙ ነው፡፡ ... . .ስለጌታ ብላችሁ ለሰው ሥርዓት ሁሉ ተገዙ፡፡ ለንጉሥም ቢሆን ከሁሉ በላይ ነውና ለመኳንንትም ቢሆን ክፉ የሚያደርጉትን ለመቅጣት በጎም የሚያደርጉትን ለማመስገን ከእርሱ ተልከዋልና.. (1ኛ ጴጥ 2፡13) ... . .በተቀባው ንጉሥ ላይ እጅህን አታንሳ የተቀባውን የረገመ ሞት ይገባዋል.. (1ሳም 26፡9) እነዚህና መሰል ጥቅሶች የሚያሳዩት ..ቃሉ.. አብዮትን አለመደገፉን ነው፡፡
አሜሪካ ግን የተገኘችው በአብዮት ነው፡፡ ሕዝቡ አምባገነን ሹሞች ካስመረሩት መሸፈት መብቱ ብቻ ሳይሆን ግዴታው እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ “when a long train of abuses and usurpations… evinces a design to reduce (the people) under absolute despotism, it is their right, it is their duty, to throw off such government, and to provide new Guards for their future security” (የነጻነት ነጋሪት)
የአሜሪካን ሕግ ያረቀቁት መሥራች አባቶች እነ ጄፈርሰን እነ ቢኒያም ፍራንክሊን፣ ለሕገ መንግሥቱ የሚጠቅሟቸውን መሠረታዊ ሀሳቦችን የወሰዱት ከዘመነ መባነን ፈላስፎች ነው ብያለሁ፡፡ በርግጥ God ወይም እግዜር የሚለውን ቃል ያነሳሱታል፡፡ ግን የእነሱ እግዜር ከአብርሃማዊ ሃይማኖቶች እግዜር የተለየ፣ ..አንዴ ከፈጠርሁህ በኋላ ሥራህ ያውጣህ.. ብሎ ዞር የሚል የአስገኝነት ባህሪ ብቻ ያለው ሐሳብ ነው፡፡ መፍጠር እንጂ የፈጠረውን የማስተዳደር ሚና የለውም፡፡ እንዲህ ያለው እግዜር ከንቱ ውዳሴ የማይቀበልና ፀሎት የማይሰማ በመሆኑ ከተፈጥሮ ጋር መሳ ነው፡፡     
ይህ አመለካከት አሜሪካውያኑ አባቶች ለምድራዊ ችግራቸው ምድራዊ መፍትሄ እንዲፈልጉለት አድርጓቸዋል፡፡ በአ„ አሜሪካ የበለጠገችው በተአምርና በቅዱሳት መፃህፍት የማይተማመኑ ሊቃውንትና መሪዎች የሕዝብን ፈቃድ አልፋና ኦሜጋ የሚያደርግ ሕግ ስላረቀቁላት ነው፡፡ አሜሪካ በፈሪሐ እግዚአብሔር የሚጠቀስ መሪ አላት ከተባለ ..ኢራቅን እንድወርር ፈጣሪ በራዕይ አመለከተኝ.. ብሎ የቃዠውና ጫማ እንደ ጥምቀት ሎሚ የተወረወረበት ቡሽ ነው፡፡
የአገራችን ችግር አንዱ ምን የእግዜር እጥረት ሳይሆን የሰውን ድርሻ ለእግዜር አሳልፎ መስጠት ነው፡፡ ..የኢትዮጵያ ሕዝብ.. አሉ ሃዲስ አለማየሁ በ1985 ባቀረቡት ንግግር ..የኢትዮጵያ ሕዝብ ከላይ ከርእሰ ብሄሩ ጀምሮ እስከ ታችኛው ሠራተኛ ድረስ ደመወዝ እየተከፈላቸው ሥጋዊና መንፈሳዊ ፍላጐቶቹን አሟልተው እንዲያቀርቡለት በየቦታቸው ማስቀመጡና መልካም ቢሰሩ በየቦታቸው እንዳሉ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ፣ መልካም ባይሰሩ ቦታቸውን መልካም ለሚሰሩ እንዲለቁ ለማድረግ የመጨረሻው ባለመብትና ባለስልጣን መሆኑን አያውቅም፡፡ ይህ የመብትና የሥልጣን ሁሉ የመጨረሻ ባለቤት እሱ ብቻ መሆኑን ባለማወቁም ለዘመናት ለእሱ መጉጃ ለገዢዎች መነገጃ ሆኖ ኖሮአል፡፡ ይህ ምድራዊ ሥልጣንን ከላይ ከተሰጡ መለኮታዊ ትእዛዛት እንደአንዱ የሃይማኖት ክፍል አድርጐ ተቀብሎና አምኖ መኖሩ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ በሐብቱ በንብረቱ በጉልበቱና በሕይወቱ ሳይቀር ለዘመናት መለኪያ የማይገኝለት መስዋእትነት ሲያስከፍለው ኖሯል፡፡..
ሲጠቃለል፡-
በአገራችን የሥነ-ሐሳብ ታሪክ ውስጥ የትኛው ሃይማኖት ይበልጣል? የሚባለው ጥያቄ ሲነሳ ሲወድቅ ኖሯል፡፡ ይሁን እንጂ በርግጥ ሃይማኖት በመሠረቱ አስፈላጊ ነው? እውነትስ አለው? ብሎ መጠየቅ አልተለመደም፡፡ ያገራችን አገልጋዮች ለዚህ ጥያቄ አለመዘጋጀታቸውን መረዳት የሚቻለው አድማስ ላይ ባነበብኳቸው ቁጣ የሰፈነባቸው ሐተታዎች ነው፡፡ እግዜር ያልተረጋገጠ መላ ምት ነው፤ ቅዱሳት መጻሕፍትም ዘመናቸውን እንጂ ዘመናችንን በማያውቁ ሰዎች የተጻፉ ድርሰቶች ናቸው ብሎ የሚያስብ ትውልድ ሲመጣ ልቡናን የሚመጥን መልስ መስጠት እንጂ መቆጣት የሚያዋጣ አይመስለኝም፡፡ ሃይማኖት ከቁጣ የማያስጥል ከሆነስ ፋይዳው ምንድነው?

Read 5139 times Last modified on Saturday, 06 August 2011 14:41