Saturday, 06 August 2011 15:39

የተስፋ ትዝታ

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(1 Vote)

ሳሚን ለመዳኘት የኳንተማ ሜካኒክስሀሳብን መጀመሪያ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ የኳንተም ሜካኒክስ ቲዎሪ ፈጣሪ የሚባሉት ፊዚሲስቶች ራሳቸው ..ስለ ኳንተም ማንም የሚያውቅ የለም.. ይላሉ፡፡ ስለ ሳሚ ለማወቅ የተነሳም ሰው ካለ ማወቅ የሚችለው ማወቅ ከፈለገው በጣም ያነሰ፣ ትንሽ፣ ኢምንት፣ ቅንጣት፣ ደቃቅ፣ ቀኒጥ. . . መሆኑን ተቀብሎመሆን አለበት፡፡
ሳሚ ከስሙ በስተቀር ሌላው ነገሩ በሙሉ ግልጽ አይደለም፡፡ ግን በሙሉ ግልጽ የሆነ ምንስ ማንስ አለ፡፡ ሳሚ በሆነ ዓመተ ምህረት. . . ከሆኑ አባት እና እናት ነው የተወለደው መቼም ለመወለድ አባት እና እናት ማስፈለጉ አይቀርም ብዬ ነው እንጂ. . . እኔ ስለወላጆቹም ሆነ ስለመወለዱ አንድም የማያውቀው ነገር የለም፡፡

እኔ ፀሐፊው ያላወቅሁትን ደግሞ ማንም ሊያውቅ የሚችል አይመስለኝም ምን ይሻላል?!. . .፤ በእነ በዓሉ ግርማ ዘመን እንዳሉት ደራሲዎች ሁሉንም ነገር ከውስጥ እና ከውጭ በሁሉም ቦታና ጊዜ ተገኝቼ የማውቅ እና የማይአይደለሁኝም፡፡ . . . ደራሲዎች ሞተው አልቀዋል፡፡ እኛ የቀረነው ፀሐፊዎች ነን፤ ለማወቅ የምንሞክረው እንጂ አውቀን የተፈጠርን አይደለንም፡፡ አውቀን ብንፈጠርስ ምን የምንፈጥረው ነገር. . . ፈጥረንስ የምንፈይደውአለን?
. . .እና ሳሚ ከሆኑ አባት እና እናት ነው የተወለደው፤ በሆነ ዓመተ ምህረት. . . ከአብዮቱ ዘመን በኋላ የተወለደ ቢሆን ነው ስሙን ሳሚ ብለው የሰየሙት፡፡ ምናልባት ስሙ ራሱ በዓመታት ጥሪ ብዛት ሟሙቶ ለዝቦ ሳሚ ሆነበት እንጂ በትኩሱ ተጋግሮ ከአክንባሎው ሲወጣ ..ሳምሶን.. ሊሆን ይችላል፡፡ ሳምሶን መሆኑን እርግጠኛ ልሆን ይቅርና ሳሚ መሆኑንም ያመንኩት አንድ ሰው ሲጠራው ሰምቼ ነው፡፡ . . .ሳሚ ራሱ ስለራሱ ቢነግረን የተሻለ ነበር፤ ሳሚ ግን አብዷል፡፡ ማንንም አያናግርም. . . ማንንም አያይም. . . አንድ የግርግዳ ጥግ ተለጥፎ በጣም ሩቅ የሆነ ነገርን ይመለከታል፡፡
. . .ሳሚን ለመረዳት የኳንተም ሜካኒክስን ንሰ ሀሳብ አስቀድሞ መረዳት ያሻል፡፡ ኳንተም ሜካኒክስን ለመረዳት እስካሁን የተረዳኸውን ነገር በሙሉ አለመረዳት ያስፈልጋል፡፡ ያወቅኸውን ለመርሳት ያላወቅኸውን ገብቶህ ማስረዳት መጀመር ግዴታ ይሆናል፡፡
. . .ስለ ሳሚ ለማወቅ ሲወለድ ጀምሮ እስካሁን ያለበት ነጥብ በጊዜ ውስጥ ሊኖር የሚችሉትን ታሪኮች በሙሉ ማሰባሰብ ያስፈልጋል፡፡ ሳሚ የእነዚህ ታሪኮች ጥርቅም ውጤት ነው፡፡ . . . እኔም ሳሚን ለመረዳት ሲወለድ ጀምሮ እስከ አሁን ያሉትን የማላውቃቸውን ታሪኮቹን አሰባስቤ፤ አገጣጥሜ ለመጻፍ ተነሳሁ፡፡ . . .ታሪኮቹን ለማሰባሰብ በመሞከር አይደለም የምሰበስባቸው፤ ለመገጣጠም በመሞከር አይደለም የምገጣጥማቸው. . . ለመጻፍ በመሞከር አይደለም የምጽፋቸው፡፡ . . .ስለዚህ ለማንበብ በመሞከር መረዳትም ሆነ ማንበብ ይሄንን ታሪክ አይቻልም፡፡
ሳሚ የሚለጠፍበት ግርግዳ በቀጭኑ ሽንጡ ቅርጽ ተልጣለች፡፡ የሽንጡ እና የትከሻው ወርድ ቢለካ እኩል ነው፡፡ የዓይኑ እና የራስ ቅሉ መጠን. . . ከራስ ቅሉ ላይ የተላጨው ፀጉሩ ከዓይኑ ላይ ጥቁረቱ ቢታከልበት፤ ዓይኑ እና ራስ ቅሉ በመጠን እኩል ይሆናሉ፡፡ አፍንጫው ንጽጽር አያስፈልገውም፤ ተራ ነው፤ ÃStnFsêL፡፡ በአፉ ሲተነፍስ አይታይም፡፡ አፉን አይከፍትም፡፡ በአፉ እንደሌላው ሰውአይገለገልበትም፡፡ አፉ እንደ ሌላው ሰው ያገኘውን ነገር ሁሉ እየከተተ የሚያመነዥግበት፣ ያገኘውን ነገር ሁሉ. . . የሚነጭበት፣ የሚያገጥጥበት. . . ወሬ የሚጐነጭበት መሳሪያው አይደለም፡፡ በጭንቅላቱ የሚጉመጠመጠው እና ወደ ውጭ ግን የማይተፋው የሆነ. . . ጠረኑ ደስ የማይል የሆነ. . . ቁሻሻ ውሃ. . . እንደ ትዝታ የመሰለ ነገር ሳይኖረው አይቀርም፡፡ አፍህን ከፍተህ ትፋ ብሎ የመከረው ሰው ያለም አይመስለኝም፡፡ እስከማላውቀው ድረስ አይመስለኝም፡፡
በጣም ሩቅ ያለ ነገርን ዓይኑን ሳያንቀሳቅስ ቀኑን ሙሉ ሲመለከት ይውላል፡፡ ቀኑን ሙሉ ሲመለከት የዋለውን ነገር ሲመለከት ያድራል፡፡ ፊቱ ላይ ግን ምንም ድካምም ሆነ መሰልቸት አይታይበትም፡፡ ፊቱ ገርጥቷል፡፡ አጥንታም እጆቹን ከፊትለፊቱ ይዘረጋቸዋል፤ የተጣጠፉት እግሮቹ ላይ፡፡ . . .እጆቹ. . . ልጆቹ ይመስላሉ፡፡ እግሮቹ ደግሞ ችግሮቹ፡፡ ልጆቹን በጥንቃቄ ነው ያስቀመጠው፤ ችግሮቹን ደግሞ በቸልታ፡፡
ቀናት ይከታተላሉ፤ በዚህ ሁኔታ፤ እየገረጣ እንጂ በጭራሽ እየደከመው አይመጣም፡፡ . . . ቤተሰቦቹ ቀኑን ያውቁታል፤ መጨነቅ y¸jM„bTN፡፡ ከቀኑ ቀድመው መጨነቅ አይጀምሩም፡፡ መጨነቅ ሲጨርሱ. . . እሱ ከሀኪም ቤት ወደ ቤቱ ተመልሷል ማለት ነው፡፡ መጨነቅ የሚጀምሩት እንደዚህ እንደ አሁኑ ግርግዳው ጋር ተቀምጦ ሲቀር እና የተወሰኑ ቀናት ሲያልፉ. . . እሱም ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ማድረግ ሲያቆም ነው፡፡
በሩቁ አተኩሮ የሚመለከተውን ነገር መመልከቱን እንዳያቋርጥ በመፍራት ተነስቶ ሽንት ቤት መሄዱን ያቆማል፡፡ . . . ሽንት ቤት ሄዶ እስኪመለስ በሩቅ፣ በሙሉ አትኩሮት የሚያየው ነገር ሊያመልጠው ይችላል፡፡ ዓይኑን ከተከለበት ነገር ላይ ከነቀለ ነገርየው እንደ ወፍ በርሮ ያመልጠዋል፤ መሰለኝ፡፡ . . .ምግብን መመገብ ያቆማል እጆቹን እንደ ልጆቹ. . . መዳፍ ወደ ላይ አድርጐ ገልብጦ ያስቀምጣቸዋል፡፡
. . .ቤተሰቦቹ ወደ ሆስፒታል ሊወስዱት ሲመጡ፤ ከአራት አቅጣጫ አድብተው ካልሆነ ያመልጣቸዋል፤ (መሰለኝ). . .፡፡ ከተቀመጠበት ሳይንቀሳቀስ ከአራቱም አቅጣጫ የመጡበትን አጥማጆቹን ከአራቱም አቅጣጫ ውጭ ወደ ሆነ፣ መቁጠር የሚያስቸግር አቋራጭ ያመልጣቸዋል፡፡ . . .ስለዚሀ አድብተው ከአራት አቅጣጫ አራት ጊዜ አራት በሆነ የእጅ ብዛት የሳሚን ሁለት እጆች እና ሁለት ችግሮች. . . ከተጣጠፉበት ዘርግተው. . . ከተዘረጉበት አጣጥፈው ባዘጋጁት ገመድ፣ ቃጫ፣ መጫኛ. . . ወዘተ ተብትበው ያስሩታል፡፡ እጆቹ ሲያዙ ዓይኖቹ ሩቁን ትተው ወደ ቅርቡ ይመለሳሉ፡፡ ሳሚ እጆቹን ይመለከታል፤ እንዳይገናኙ በጥንቃቄ ተለያይተው የተቀመጡ የነበሩት እግሮቹ አንድ ላይ ተጨባብጠው፣ ተቆላልፈው. . .፡፡ እጆቹ ተለያይተው የተቀመጡ የነበሩት እግሮች አንድ ላይ ተጨባብጠው፣ ተቆላልፈው. . .፡፡ እጆቹ ተለያይተው ሲቀመጡ ነው ነጻ የሚሆኑት፤ ተጨባብጠው ከተቆላለፉ. . . ከታሰሩ ይሞታሉ፡፡ እጆቹ. . . ልጆቹ በገመድ ተሳስረው ሲሞቱ በሩቅ አይኑ በሃዘን ተውጦ ቅርቡን ያያል፡፡. . .
ቤተሰቦቹ አስረው የሚወስዱት ለምን እንደሆነ እነሱም ራሳቸው አያውቁትም፡፡ እብድ፤ እብድ መሆኑ እንዲታወቅ ልብሱን ማውለቅ እንዳለበት ይጠበቃል፤ በተለምዶ፡፡ ..እብድም ወደ ሀኪም ቤት ሲወሰድ መታሰር እንዳለበት ይጠበቃል.. እኔ እነሱን ሆኜ ብጠየቅ የምመልሰው ነው፡፡ እመልሳለሁ እንጂ እኔ ሳሚን ብሆን ግን አልመለስም፡፡ እኔን እንደ ሳሚ እጄን አስረው እብድ ሀኪም ቤት ቢወስዱኝ የተወሰድኩበት ቦታ እቀራለሁ እንጂ ቤት አለኝ ብዬ በወጥመድ ወደተያዝኩበት ስፍራ አልመለስም፡፡
. . .ሀኪሞቹ ለሳሚ የኤሌክትሪክ ንዝረት በህብለ ሰረሰሩ እና በጭንቅላቱ ይሰጡታል፡፡ መስጠቱ ለብዙ ሳምንታት ይቀጥላል፡፡ . . .ዶክተሩ እንደሚለው ..በጭንቅላቱ የሀሳብ ግዛት ውስጥ ገብቶ ከመነነበት አግባብቶ አሳምኖ ወደ ዓለም እንደመመለስ ነው.. ብሎ ሲገለጽ የት ሆኜ እንደሆነ ባለውቅም በጆሮዬ በብረቱ ሰምቻለሁ፡፡
ዶክተሩ እንደ ጤናን ማግኘት የሚገልው ነገርን ሳሚ በኋላ ላይ ራሱ ሲናገር እንደምንሰማው ደግሞ ጤናን እንደማጣት አደርጐ ነው፡፡ ሳሚና የዶክተሩ ስለ ጤና ትርጉም ያላቸው እይታ የተለያየ ነው፡፡ ዶክተሩ እና ሳሚ. . .፡፡ ሳሚ ጤነኛም ሆኖ ወይንም ህመም ላይ ባለበት ጊዜ ከዶክተሩ እና ከቤተሰቦቹ ጋር በጭራሽ አይስማሙም፡፡ . . .ላይስማሙ የሳሚ ጀርባ እና ጭንቅላት በፋራዴር እና ቶማስ ኤዲሰን ፈጠራ ይጠበሳል፡፡ . . .ሳሚ ዶክተሩ ሊያክመው እንደማይችል እርግጠኛ ነው፤ እርግጠኛነቱ ፊቱ ላይ በግልጽ ይነበባል፡፡
ሳሚ ወደ ቤቱ ሲመለስ እንደ አዲስ ይጀምራል፡፡ ያጠፉበትን ፍለጋውን እንደ አዲስ ይጀምራል፡፡ የነበረውን ወደ ፈለገበት ቦታ የመጓዝ ብቃት እና እውቀት ሙሉ ለሙሉ ዶክተሩ እና ኤሌክትሪኩ ስለሚያጠፉበት፤ እንደ አዲስ ከጭረት መጀመር ይኖርበታል፡፡ ወደ አለሙ መግቢያ ..ኮዶቹን.. እንደ አዲስ ማግኘት፡፡ . . .እስኪያገኝ ድረስ መፈለግ፡፡ መፈለግ፡፡ መለማመድ፡፡
. . .ከሆስፒታል ሲወጣ ወሬኛ ሆኖ ነው፡፡ ከፀጥታው ሲያገግም እንደ ሰካራም በማውራት ነው፡፡ ቤተሰቦቹ እንደ ሰካራም መለፍለፉን ይወዱለታል፡፡ ቤተሰቦቹም እንደ ዶክተሩ ናቸው፡፡ እንደ ሰካራም ማውራቱን ጤነኝነቱ ብለው ይጠሩለታል፡፡ አንድ ቦታ መቀመጥ ያቅተዋል፡፡ ከሀኪም ቤት ሲመጣ. . . መቁነጥነጥ እና እንደ ሰካራም ማውራት፤ እና እንደ በሽተኛ አብዛኛውን ሰዓት መተኛት፡፡ እንደ በሽተኛ ብዙ ሰአታት መተኛትን ጤነኝነት ብለው ነው የሚጠሩት፤ ዶክተሩ እና ቤተሰቦቹ፡፡
በልምምዱ ወቅት እየመጡ ይረብሹታል፡፡ ብላ፣ ጠጣ፣ ገላህን ታጠብ፣. . . ማለቂያ የለውም የረብሻቸው ዓይነት፡፡ እሱም ያፈረሱበትን ዓለሙን እንደገና መገጣጠሚያ መንገድ እያሰበ በረብሻቸው Yrb>§cêL፡፡ እነሱ የሚረበሹት እሱ ወደዛኛው ዓለሙ ሲገባ እና ከመረበሽ ግዛት ውጭ ሲሆን ነው፡፡ እሱ ደግሞ የሚረበሸው አሁን ነው፡፡ ቤተሰቦቹ ሰላም ሲያገኙ. . .
ከሳሚ ጋር የተዋወቅነው እኔና እፁብ ልንጠይቀው በሄድንበት ወቅት ነበር፡፡
..አንድ ጓደኛዬ ከሀኪም ቤት ወጥቷል ነገ ሄደን እንጠይቀው?.. አለችኝ፡፡ ..ማነው.. ብዬ xL«yQºTM፡፡ ሄድን፡፡ ሳሚን ስተዋወቀው ስለ በሽተኛ የነበረኝ የተለመደ እይታ ተዛባ፡፡ ልጁ የታመመ መሆኑን የሚጠቁም ምንም ዓይነት ምልክት አጣሁ፡፡ እንዲያውም የበሽታ አዝማሚያ ይታይብን የነበረው እኔና እፁብ ላይ መሆኑ እኔን ረበሸኝ፤ ሳሚን ሳይገርመው አይቀርም፡፡
..መቼ ገባህ... . . ..መቼ ወጣህ... . . ..ተሻለህ ወይ..
..ምንድን ነበር ችግርህ.. የምትለዋን ጥያቄ ግን በጣም በሩቁ ላለማየት ዓይናችንን አንዘዋርረን የባጥ የቆጡን አወራን. . .፡፡ ሳሚ ከመጠን በላይ ስዑል የሆነ አእምሮ የያዘ ሰው ሆኖ አገኘሁት፡፡ የምንሸሸውን ጥያቄ ራሱ አምጥቶ ይገልጽልን ጀመር፡፡ . . .እኔ እና እፁብ እንደተጋባን ማወቁ የእሱን እና የባለቤቴን የቀድሞ ታሪክ ከመተረክ አላገደውም፡፡
..ጠቅላላው የኔ ሁኔታ ከእፁብ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከእፁብ ጋር በፍቅር ውስጥ የወደቅሁት የዛሬ ሰባት ዓመት ነበር፡፡ . . .እፁብ ከእዛ ጊዜ እስከ አሁን የሰባት ዓመታት ያህል ተለውጣለች፤ ምናልባትም አድጋለች፡፡ አሁን ያንተ ባለቤት የሆነችው እፁብ ለእኔ ፍቅር በሽታ ተጠያቂ የሆነችዋ እፁብ አይደለችም፡፡ . . .እቺኛዋ አንድ ሌላ ሴት ናት፤ እኔምኮ ከሰባት ዓመት በፊት የነበርኩት ሳሚ አይደለሁም፡፡ እኔም አሁን ወንድሟ እሷም እህቴ ናት፡፡ . . .ስለዚህ አትፍራ ወርቅነህ.. አለኝ እኔን፡፡
በመቀጠል ..ስለ በሽታ ፍልስፍናዬ ልንገርህ.. ብሎ ሶፋው ላይ እግሮቹን አጣምሮ ዘና አለ፡፡ ዓይኑ የነብሱ መስኮት ብቻ ሳይሆን የነብሱ የጉዞ ገድሉ የተጻፈባቸው ናቸው፡፡ ሩቅ እያዩ ቅርብ ያወራሉ. . . ወደ ውስጥ ያዩትን ወደ ውጭ ÃN[ÆRÝlù፡፡
... . .አየህ ወርቅነህ. . . በነገርህ ላይ መልአክን ስም ያወጣዋል በሚለው አምናለሁ፡፡ መልአክን ስም. . . አንተም ስምህ አውጥቶሃል፡፡ ስምህ ወርቅ እንደ ሆንክ መስክሮልን መዳብ ወይም ቆርቆሮ ልትሆን አይቻልህም፡ . . . እና ወርቅ ነህና ታሪኬን እንድታንፀባርቅልኝ አዳምጠኝ.. ብሎ ይተርክልኝ ጀመር፡፡ሚስቴ እንደ ሀሳብ ከጊዜ በኋላ ስትለወጥ ሳሚ መለወጥ አቃተው፡፡ እሱ ግን መለወጥ ያቃተውን የፍቅር አጋጣሚውን የሚገልው እንደ በሽታ አድርጐ ነው፡፡
..ፍቅር በሽታ ነው፡፡ ጉንፋን ቢይዝህ ለምሳሌ ያስያዘህን ሰው እንደ በዳይ የተያዝከውን አንተን ደግሞ እንደ ተበዳይ ልታይ አትችልም፡፡ . . .በትክክለኛ እና አመዛዛኝ እይታ ከተመለከትከው ፍቅር ብዙ ነገሩ እንደ ተላላፊ በሽታ ነው፡፡ ትክክለኛው ፍቅር የሚይዝህ ከትክክለኛዋ አንድ ሴት ብቻ ነው፡፡ ከወንድም ወደ ሴት በተመሳሳይ መንገድ በሽታው ይተላለፋል፡፡ ግን ወንዶች ላይ የበሽታው ምልክቶች እና ስቃይ የሚቆይበት ጊዜ በጣም ይለያያል፡፡ . . .አንዳንድ ወንዶች በጊዜ ያገግማሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ እድሜ ልካቸውን አያገግሙም፡፡ . . .እድሜ ልካቸውን ባያገግሙም፤ የበሽታውን ኃይል በተለያየ መንገድ በመቀነስ. . . በተለያየ ማረሳሻ ህመሙን በማድከም፣ የፍቅሩን የመርዝ ጉልበት በተለያየ ሴት ተቃራኒ መርዝ በማለዘብ በህይወት መቀጠል ይችላሉ፡፡ . . .ሌለኛዎቹ ወንዶች ደግሞ እንደኔ ዓይነቶቹ ናቸው፡፡ ምንም ዓይነት ጊዜም ሆነ ማስረሻ በሽታውን ይጨምርባቸዋል፤ እንጂ አይሻላቸውም፡፡ . . .ከጊዜ በኋላ ይሞታሉ፡፡ ወይም የሚገድላቸውን ነገር በመፈለግ ከስቃያቸው ለመገላገል ይሞክራሉ፡፡ . . .በሽታውን ያስያዘህን ሰው ጥፋተኛ ማድረግ መፍትሄ እንዳልሆነ ስለደረስኩበት የእኔን በሽታ ስቃይ ለማስታገስ እፁብ ምንም ፋይዳ የላትም፡፡ የምታገለው ከበሽታው ጋር ነው፡፡ የምታገለው በህይወት ለመቆየት ነው፡፡.. ብሎኝ ጥቂት ጊዜ ፀጥ አለ፡፡
ይህንን ዓይነት ውይይት ስሰማ የመጀመሪያ ጊዜዬ ስለሆነ ተገረምኩ፡፡ ደራሲ የመሆን ዝንባሌ እንዳለኝ ለሳሚአጫውቼዋለሀ፡፡፡፡ ለድርሰት የሚሆን ታሪክ መፍጠር እንጂ ማግኘት እንደሚቻል ግን እሱ ነው ያጫወተኝ፡፡ የራሱን እውነተኛ ታሪክ፡፡
..በጊዜ ወደ ፊት በተስፋ ተጉዞ እቅድ ማውጣት እንደሚቻለው እኔ ደግሞ በትዝታ ወደ ኋላ ሄጄ እኔና እፁብ የተገናኘንበትን ጊዜ ታሪክ በመቀየር. . . ለሰባት ዓመት የቆየሁበትን የስቃይ በሽታ ለመፈወስ እየሞከርኩ ነው፡፡ . . .ታሪክም እንደ ራዕይ ሊተነበይ ይችላል፡፡ ትንቢቱ ግን ሊከሰትም ላይከሰትም የሚችልበት በጣም ብዙ አማራጭ አለው፡፡ የተከሰተ ታሪክም ቢሆን ወደ ኋላ ተመልሰን ብንመለከተው የተከሰተበት ሁኔታ በተለያየ አቅጣጫ የመታወስ ብዙ አማራጭ አለው፡፡ . . .እኔና እፁብ ስለመጀመሪያው የተቀጣጠርንበት ቀን እንድናስታውስ እና እንድንተርክ ብንጠየቅ. . . ትረካችን እንደ እይታ አቅጣጫችን ይለያያል፡፡ ታሪኩም አንድ ብቸኛ አማራጭ ያለው በመሆን ፋንታ እንደ ትዝታው እና የትዝታው ተራኪ ብዛት ብዙ አማራጭ ያለው ይሆናል፡፡ . . .እኔ ግርግዳው ጥግ ተለጥፌ ወደ ውስጥ የምጠፋው በትዝታ ጊዜና ቦታ ተጉዤ. . . የእኔና የእፁብ ፍቅር ከጥሩ ትዝታ ወደ ገዳይ በሽታ ከመቀየሩ በፊት ያለውን የታሪክ መሹለኪያ አማራጭ በመውሰድ. . . ራሴን ከሞት እና ስቃይ መገላገል ነው፡፡ የሰባት ዓመት በህመም ያጣሁትን ታሪኬንም ማስመለስ እፈልጋለሁ፡፡ ግን ይሄንን አማራጭ በመፈለግ በምጓዝበት ጊዜ በትዝታ አራተኛው አውታር ውስጥ እቀርና. . . እዚህ እና አሁን ላይ ያለውን ሰውነቴን እዘነጋዋለሁ፡፡. . .ልክ አሁን እዚህ ሆኜ ከእናንተ ጋር ሳወራ ትዝታዬን እንደምዘነጋው ማለቴ ነው፡፡ . . .እንግዲህ እየፈለኩ ወዳለው አዲስ የትዝታ አማራጭ ስደርስ እና ልለውጠው ስቃረብ. . . በኤሌክትሪክ ንዝረት አባንነው ወደነበርኩበት ይመልሱኛል፡፡ መመለሱ በበዛ ቁጥር. . . የመጓዣው መንገድ እና ብልሐት እየከበደ . . . እያቃተኝ መምጣቱ አልቀረም፡..በትዝታ ጐዳና መጓዝ አቃተኝ ማለት ለቤተሰቦቼ እና ለሚያክመኝ ዶክተር ስኬት ነው፡፡ ጤነኛ ሆንኩ ማለት ነው በእነሱ ቋንቋ፡፡ ጤነኝነቴ ከላይ ነው እንጂ ከውስጥ የፍቅር በሽታዬ ስቃይ እያየለ. . . ከጊዜ በኋላ በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ ባዶነት መሞቴ አይቀርም፡፡ . . .ይሄንኑ ሙከራዬን ለቤተሰቦቼ ለማስረዳት ጥሬአልተሳካልኝም፡፡ ዶክተሩም እኔን ወደ ስቃይ ለመመለስ እንጂ ከስቃይ የምወጣበትን መንገድ ለመጠቆም ሞያዊ ብቃት ያለው አይመስልም፡፡..
እፁብ አይን ላይ ሀዘን ተነበበ፤ በዓይኖቼ ዓይኗን ስመረምር፡፡ የሳሚን ዓይን መርምራ የደረሰችበት እውነት ነው በዓይኗ የተነበበው፡፡ የሷን ዓይኖች መርምሬ በእኔ ዓይን የተነበበውን ደግሞ ሳሚ በዓይኑ ዓይኔን እንደ ሀኪም አጥንቶ ደርሶበታል፡፡ የደረሰበት ደግሞ በሱ ዓይኖች ላይ መነበብ ቀጠለ፡ . . .ሚስቴ እፁብ በሳሚ እብደት መስማማቷ በእኔ ዓይን ተገምግሞ በሳሚ ዓይን ተነበበ፡፡ . . .ብርሃን በተለያዩ ዓይኖች ሲገባ የተለየ ትርጉም ይይዛል፡፡ ሲወጣ ደግሞ የተለያየ ትርጉም፡፡ ብርሐን የሰው ልጆችን አንድ ዓይነት እውነት አያሳይም፡፡ ብርሃን ዓይኖችን በአንድ ቋንቋ አያግባባም፡፡
..እፁብ በአንድ ወቅት የጻፍሽልኝ ደብዳቤ መልሼ ሰጥቼሽ አስቀምጠሽልኝ ነበር፡፡ ትዝ ይልሻል፡በኤሌክትሪኩ ንዝረት ትዝታዎቼ በሙሉ ስለተደመሰሱ እንደ አዲስ ከጭረት መጀመር አለብኝ፡፡ . . .ደብዳቤ እንደሰጠሁሽ ትዝ ያለኝ እግሬ ላይ በማይጠፋ ጠባሳ ጽፌ ስላስቀመጥኩት ነው፡፡ ትዝታዎቼን ሁሉ ሲያጠፉ እንደገና ለመጀመር መነሻ ሁሌም እተዋለሁ፡፡ . . .እና ካልተሳሳትኩ አንድ ደብዳቤ አንቺ ጋር አለኝ፤ ትሰጪኛለሽ?.. ሳሚ ዓይን ላይ የመጀመሪያውን የተስፋ ብርሃን አየሁ፡፡ አይኑ ተስፋን ትዝታ አስመስሎ ነው የሚያንፀባርቀው፡፡
..አዎን ዛሬ ልጠይቅህ ብቻ ሳይሆን እንደ ሁልጊዜውም ያስቀመጥኩልህን ደብዳቤ ይዤ መምጣትን እንደምትጠብቅ ስለማውቅ ነው የመጣሁት.. አለችው፡፡
..ስንተኛ ጊዜህ ነው ከጭረት ትዝታህን ለመሥራት ስትሞክር.. አልኩት
..ስንተኛ ጊዜዬ ነው.. አላት እፁብን
..አስረኛ.. አለች፤ ቦርሳዋን እየበረበረች፡፡
ደብዳቤውን ከሰጠነው ጊዜ ጀምሮ ተሰናብትነው እስክንወጣ እያጠፈ እና እየዘረጋ ብዙ ጊዜ አነበበው፡፡ መጀመሪያ የማይገባ ነገርን እንደሚያነብ ሰው ዓይኑ ግርግዳ መሰለ፡፡ ቀጥሎ ግርግዳው ወደ መጋረጃ. . . መጋረጃው ወደ መስታወት፣ መስታወቱ ወደ ዓይን፡፡
የደብዳቤው አናት ላይ ..ህድማ ቅድሚት.. የሚል አርዕስት ተጽፎበታል፡፡ ወደሚቀጥለው ጉዳያችን ለመሄድ መኪና ውስጥ ከገባን በኋላ ቁልፉን ለማስነሳት እየጠመዘዝኩ ..ምን ማለት ነው የደብዳቤው አርእስት?.. ብዬ ባለቤቴንጠየቅኳት፡፡..የመጀመሪያ አንድ ሌሊት አብረን ካሳለፍን በኋላ አንተ ቤት ውስጥ ቁጭ ብዬ የጻፍኩት ነው፤.. አለችኝ፡፡ የሆነ ዓይነት በሽታን ከአንዱ ጤነኛ ወደ ሌላው የማዳረስ ኃላፊነት የተጣለበት ወባ ትንኝ በራሷ በመኩራት የምታሳየውን የከንፈር ዳር ፈገግታ እያሳየችኝ፡፡
ያኔ እኔ ቤት ቁጭ ብላ ደብዳቤውን ለእሱ ስትጽፍ የዛሬ ሰባት ዓመት በፊት፤ ሳሚ ፍቅረኛዋ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ ጓደኛዋ ነበርኩ፡፡ ዛሬ እኔ ፍቅረኛዋ ነኝ፤ እሱ ደግሞ ጓደኛዋ ሆኗል፡፡ ለእሷ ከሰባት ዓመት በፊት የነበረው ነገር ታሪክ ነው፤ ለሳሚ ደግሞ ትዝታ ነው፡፡ ..ህድማ ቅድሚት.. ለሳሚ የመጀመሪያው ትዝታው ነው፡፡ ሳሚ ለአስራ አንደኛ ግዜ ወደ ትዝታው ግዛት ገብቶ ሩቅ ሩቅ ማየት ጀመረ፡፡ እዛችው ግርግዳው ጥግ ተለጥፎ፡፡ . . .ቀናት አለፉት ከተቀመጠበት ቦታ ሳይነቃነቅ፡፡ ቤተሰቦቹ መጨነቅ መጀመር ያለባቸውን ጊዜ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ . . .መጨነቅ ጀመሩ፡፡
ከአራት አቅጣጫ. . . አራት ጊዜ አራት በሆነ የእጅ ብዛት አድብተው አፈኑት፡፡ እጆቹ ታስረው ተጨባብጠው. . . ወደ ዶክተሩ ዘንድ ወሰዱት፡፡ በፋራዴይ እና ኤዲሰን ኤሌክትሪክ አንጐሉ እንዲነፍር ተደረገ፡፡ግን ፋራዴይ እና ኤዲሰን ከአስራ አንደኛው የትዝታ ምናኔው ሊያወጡት አልቻለም፡፡ . . . ወደ መጀመሪያው ትዝታ ቦታ ላይመለስ ሰውነቱን ጥሎላቸው ሄዷል፡፡ መመለሱም ያጠራጥራል፡፡

 

Read 5556 times Last modified on Monday, 08 August 2011 14:24