Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 06 August 2011 15:42

የምናብ ውጤት ነው!

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ከሦስት አሰርት ዓመታት በፊት የሆነ ነው፡፡ ጉንሳዩሉስ የተባለ ወጣት ቄስ በአሜሪካ ቺካጐ ግዛት የሚታተሙ ጋዜጦች ላይ በቀጣዩ እሁድ በዓይነቱ ለየት ያለ ትምህርት እንደሚሰጥ የሚገል ማስታወቂያ አስነግሮ ነበር፡፡ወጣቱ ቄስ በማስታወቂያው ላይ እንደጠቆመው የሚሰጠው ትምህርት ርዕስ ..አንድ ሚሊዮን ዶላር ቢኖረኝ ምን አደርግበት ነበር..ይላል፡፡ ማስታወቂያው የበርካታ አሜሪካውያንን ቀልብ ትኩረት የሳበ ሲሆን ፊሊፕ ዲ. አርሞር የተባለ ዕውቅ የግዛቷ ባለፀጋ ይገኝበታል፡፡

በሰንበተ እሁድ ብዙ ታዳሚዎች በተሰበሰቡበት ወጣቱ ቄስ ትምህርቱን ጀመረ፡፡ ..አንድ ሚሊዮን ዶላር ቢኖረኝ ምን አደርግበት ነበር.. በሚል ርዕስ ገንዘቡ ቢኖረው ኖሮ ምን ያደረግ እንደነበር ማብራራት ገባ፡፡ ገንዘቡ ቢኖረኝ ኖሮ ታላቅ የቴክኖሎጂ ት/ቤት እከፍት ነበር አለ - ወጣቱ ቄስ፡፡ ወጣት ወንዶችና ሴቶች በንድፈ-ሃሳብ ደረጃ ሳይሆን በተግባር ማሰብ የሚችሉበትን ክህሎት የሚያዳብርላቸው ድንቅ ት/ቤት እከፍታለሁ -  በተግባር እየሠሩ የሚማሩበት፡፡ ..አንድ ሚሊዮን ዶላር ቢኖረኝ ኖሮ ይሄን ዓይነቱን ት/ቤት እከፍት ነበር.. ሲልም የዕለቱን አጭር ትምህርት ቋጨ፡፡ ያልተለመደ ዓይነት ትምህርት ስለነበር ብዙዎቹን ማስገረሙ አልቀረም፡፡ ከአቅሙ በላይ ተመኝቷል በሚል ሃሳቡን ..የቀን ቅዠት.. ያለውም አይጠፋም፡፡ ግን የሰባኪው ምኞት ፈጽሞ ቅዠት አልነበረም፡፡ ሰባኪው ከስብከት መስጫ ስፍራው ሳይነቃነቅ ፈሊጥ ዲ.አርሞር የተባለው ማስታወቂያውን ከጋዜጣ ላይ ያነበበው የግዛቷ ባለፀጋ ቀርቦ አነጋገረው፡፡ ..አንተ ጐረምሳ፤ አደርገዋለሁ ያልከውን ሁሉ ታደርገዋለህ ብዬ አምናለሁ፡፡ ነገ ጠዋት ወደ ቢሮዬ ጐራ ብትል የምትፈልገውን 1ሚ. ዶላር እሰጥሃለሁ.. አለው፡፡
ወደ ተግባር ሊቀየር የሚችል ዕቅድ የሚፈጥሩ ወይም የሚነድፉ ሁሉ በካፒታል - (በመስሪያ ገንዘብ) እጥረት ወይም እጦት ብቻ ከግባቸው አይደናቀፉም ይላል - |Think and Grow Rich” የተባለው መጽሐፍ ደራሲ ናፖሊዮን ሂል፡፡
በአገሪቱ በተግባር የተደገፈ ትምህርት የሚሰጥበት “Armour Institute of Technology” የተጀመረው በእንዲህ ያለ መልኩ ነበር፡፡ ይሄ ት/ቤት የተወለደው በዚያ ወጣት ሰባኪ ..ምናብ.. ውስጥ ነው፡፡ የእሱ ምናብና የባለፀጋው ካፒታል ባይቀናጁ ኖሮ ስለ ሰባኪውም ሆነ ት/ቤቱ ዛሬ አይወራም ነበር፡፡እያንዳንዱ ታላላቅ ፈጠራ፣ እያንዳንዱ ታላላቅ የቢዝነስ ኩባንያ፣ እያንዳንዱ ድንቅ የገንዘብ ተቋም፣ እያንዳንዱ አስደማሚ ህንፃና ድልድይ ወዘተ . . . የተፀነሰው በአንድ የሆነ ሰው ምናብ ውስጥ ነው፡፡ ያ ሰው ቀድሞውኑ ባያስበው ኖሮ ዛሬ እነዚህ የምንላቸው ሁሉ በእውን ባልኖሩ ነበር፡፡
አምፑልና ሌሎች ለሰው ልጆች ጠቃሚ የሆኑ የፈጠራ ውጤቶች እውን ከመሆናቸው በፊት በቶማስ ኤ. ኤዲሰን ምናብ ውስጥ ነበር የተፀነሱት፡፡ ዛሬ በመላው ዓለም 6ሺ ቅርንጫፎች ያሉት የዎል ማርት ሱፐርማርኬት ቀድሞ በመስራቹ ሳም ዋልተን ምናብ ውስጥ ነው የተፈጠረው፡፡ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሥር ነቀል ለውጥ ያመጣው የማህበራዊ ግንኙነት መረብ ..ፌስቡክ.. ከመፈጠሩ በፊት በወጣቱ አሜሪካዊ የኮሌጅ ተማሪ በማርክ ዙከርበርግ ምናብ ውስጥ ነበር፡፡ የአፕል ኮምፒዩተር ፈጣሪ ስቲቭ ጆብስ ቀድሞ በምናቡ ባይፈጥራቸው ኖሮ ዛሬ እነ አይፖድና አይፎን የቴክኖሎጂ ትሩፋት ሆነው ለሰው ልጆች አይበረከቱም ነበር፡፡በለጋ ዕድሜያቸው ምናባቸውን መጠቀም የተማሩ ወይም የለመዱ እነሱ የታደሉ ናቸው ይላል - ናፖሊዮን ሂል፡፡ በእርግጥ ምናብን መጠቀም ለተመረጡ ጥቂት ሰዎች የተቸረ ልዩ ስጦታ አይደለም፡፡ የሰው ልጅ በሙሉ በተፈጥሮው የሚያገኘው በረከት እንጂ፡፡ ነገር ግን ምናብ የማያድገው፣ የሚሰፋውና የሚበለጽገው ጥቅም ላይ ሲውል ብቻ ነው፡፡ ያለ ሥራ የተቀመጠ ምናብ ባለበት ሳይለወጥ ይቀመጣል - አንዳችም ፍሬ ሳያፈራ፡፡ ማንም ሁን፣ የትም ሁን፣ በምንም የሥራ ዘርፍ ተሰማራ ምናብህን በመጠቀምና በማዳበር ራስህን ጠቃሚና ምርታማ የማድረግ ሰፊ ዕድል አለህ፡፡ የትኛውም ስኬት የ..ምናብ.. ውጤት ነው፡፡ የትኛውም የዓለማችን ቢሊዬነር ቢሆን የብልግናው ሰበብ ምናቡ የወለደው የመጀመሪያው ሃሳቡ ናት፡፡ የማይክሮሶፍት መሥራቹ ቢል ጌትስ የበለፀገው በምናቡ ውጤት ነው፡፡ የሃሪ ፖተር ደራሲ ጄ.ኬ. ሮውሊንግስ የደራሲ ቢሊዬነር ልትሆን የበቃችው በምናቧ በፀነሰችው ድንቅ የፈጠራ ሃሳብ ነው፡፡ ሆሊውድን በየዓመቱ በቢሊዮን ዶላሮች የሚያጥለቀልቀው የፊልም ኢንዱስትሪ የምናብ ውጤት ነው፡፡ በየትኛውም የሙያ ዘርፍ በህክምና፣ በፊዚክስ፣ በህዋ ሳይንስ፣ በኬሚስትሪ፣ በሥነ ጥበብ ወዘተ የተገኙ ፈጠራዎችም ይሁኑ ስኬቶች የሰው ልጅ የምናብ ውጤቶች ናቸው፡፡ በምናባችን ያሰብንበት፣ያለምንበት እንደርሳለን፡፡

 

Read 6409 times Last modified on Saturday, 06 August 2011 15:58