Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Monday, 08 August 2011 09:51

20ኛው ፕሪሚዬር ሊግ ሳምንት ይጀመራል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በእንግሊዝ እግር ኳስ የ2011 -12 የውድድር ዘመን የሊጉ ሻምፒዮን ማን. ዩናይትድ ከኤፍ ኤካፕ  ሻምፒዮኑ ማን. ሲቲ ጋር ነገ በዌምብሌይ በሚያደርጉት የኮሙኒቲ ሺልድ የዋንጫ ጨዋታ ሊከፈት ነው፡፡ በሌላ በኩል የላቀ የሻምፒዮናነነት ፉክክር እንደሚደረግበት የሚጠበቀው 20ኛው ፕሪሚዬር ሊግ ከሳምንት በኋላ ይጀመራል፡፡ በፕሪሚዬር ሊጉ የ20 ዓመታት ታሪክ ማን. ዩናይትድ ለኮምኒቲ ሺልድ ዋንጫ 14 ጊዜ የተጫወተ ሲሆን ማን ሲቲ በበኩሉ ከ38 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያው ነው፡፡

ባለፉት 6 ዓመታት የውድድር ዘመኑን የመክፈቻ የዋንጫ ጨዋታ ያሸነፈ ቡድን በሻምፒዮናነት መጨረሱ የታየ ሲሆን የነገው የኮሚኒቲ ሺልድ ፍልሚያ ሁለቱ የማንቸስተር ከተማ ክለቦች ትንቅንቃቸውን የሚጀምሩበት ይሆናል፡፡
በሊጉ የሻምፒዮናነት ትንቅንቅ ማን. ዩናይትድ ቼልሲ፣ አርሰናልና ማን ሲቲ ቅድሚያ ግምት ቢኖራቸውም የሁለቱ የማንችስተር ከተማ ክለቦች ፉክክር ግን በአዲሱ የውድድር ዘመን ከፍተኛ ትኩረት የሚስብ እንደሚሆን እየተነገረ ነው፡፡
..በፕሪሚዬር ሊግ 20ኛው ዓመት 20ኛውን የሻምፒዮናነት ክብር ማግኘት እንፈልጋለን.. ያሉት ሰር አሌክስ ፈርጉሠን ይህን የተናገሩት በጉራ ስሜት አለመሆኑን ገልፀዋል፡፡ ማንቸስተር ዩናይትድን ወጣቱን ግብ ጠባቂ ዴቪድ ዲኒያ ከስፔኑ አትሌቲክ ማድሪድ፣ ተከላካዩን ፊል ጆንስ ከብላክበርን እንዲሁም የክንፍ ተጨዋቹን አሽሊ ያንግን ከአስቶን ቪላ በማስፈርም ተጠናክሯል፡፡ በእነዚህ ዝውውሮች 80 ሚሊዮን ዶላር አውጥቷል፡፡ ዘንድሮ በኦልድትራፎርድ መስራት ከጀመሩ 25ኛ ዓመታቸውን የሚይዙትና 70ኛ ዓመታቸውን የሚያከብሩት ሰር አሌክስ ፈርጉሠን ለ12ኛ ጊዜ የሊግ ዋንጫውን በሻምፒዮኑን ለማንሳት ትኩስ ፍላጐት እያሳዩ ናቸው፡፡
በማንችስተር ሲቲ በኩል  አዲሱ የውድድር ዘመን ከፍተኛ ተስፋ ተሰንቆበት የሚጀመር ነው፡፡ ክለቡ ባለፈው የውድድር ሲሆን ከ35 ዓመታት ያለዋንጫ ቆይታ በኋላ ታላቁን የኤፍ ኤካፕ ድል አግኝቷል፡፡ በሊጉ ደረጃ ሰንጠረዥም 3ኛ ሆኖ በመጨረስ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ውድድር ተቀላቅሏል፡፡ የአውሮፓ የተጨዋቾች የዝውውር ገበያውን በከፍተኛ ወጭ የተቆጣጠረው ማን ሲቲ በክረምቱ የዝውውር ገበያ 92 ሚሊዮን ዶላር አውጥቷል፡፡ ክለቡ ባለፉት 3 የውድድር ዘመናት በአቡዳቢው ሼክ መንሱር ከ1 ቢሊዮን ዶላር ፈሰስ ሆኖበት በተሟላ ሁኔታ የተደራጀው ክለቡ ባለው ጥንካሬ ከ3 በላይ ዋንጫዎችን (በሊግ፣ በሻምፒዮንስ ሊግ፣ በኤፍ ኤካፕ) ቢያነጣጥር የሚደንቅ አደለም፡፡
20ኛውን የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በተጠናከረ አቋም ለመሳተፍ ኃያላኖቹ 5 እና 6 ክለቦች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም የሊጉ ተወዳዳሪ ክለቦች በተጨዋቾች ግዢ ከፍተኛ ትኩረት አድርገው ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡ በዝውውር መስኮቱ ሊዘጋ የ3 ሳምንት ዕድሜ እየቀረው የሊጉ ተወዳዳሪ 20 ክለቦች በዝውውር ገበያው 638.8 ሚሊዮን ዶላር አውጥተዋል፡፡ ማን ሲቲ ማን ዩናይትድና ሊቨርፑል በገበያው ንቁ ተሳትፎ ካደረጉ ክለቦች ዋናዎቹ ቢሆኑ በድምሩ ከ250 ሚሊዮን ዶላር በላይ ፈሰስ አድርገዋል፡፡
በአውሮፓ እግር ኳስ የተጨዋቾች የዝውውር ገበያ የእንግሊዝ ክለቦች በሚያወጡት ወጭ የበላይነት እንደያዙ ቀጥለዋል፡፡ የሊጉ ተወዳዳሪ ክለቦች ባንድ የውድድር ዘመን  በአማካይ ከ50-120 ሚሊዮን ፓውንድ ለተጨዋቾች ዝውውር በማውጣት ላይ ናቸው፡፡ ዴሊዮቴ የተባለው ተቋም ይፋ ባደረገው ሪፖርት ባለፉት 10 የውድድር ዘመናት ብቻ የእንግሊዝ ክለቦች  ለተጨዋቾች ዝውውር ከ2.8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ አድርገዋል፡፡
ቼልሲ ዘንድሮ ሊጉን የሚጀመረው እንደለመደው በአዲስ አሰልጣኝ ነው፡፡ ክለቡን የ33 ዓመቱ ፖርቱጋላዊ አሰልጣኝ አንደሬ ቪላስ ቦአስ በዋና አሰልጣኝነት ይመሩታል፡፡ አንድሪ ቪላስ ቦአስ ለቼልሲ አዲስ አይደሉም፡፡ የሞውሪንሆ ረዳት ሆነው ከ2004 -2007 በስታምፎርድ ብሪጅ ሰርተዋል፡፡ ከሊጉ መጀመር በተያያዘ በቼልሲ ክለብ ዙር አነጋጋሪ የሆነው ጉዳይ አዲሱ አሰልጣኝ ቪላስ ቦአስ በእድሜ እኩያዎች የሚሆኑ ተጨዋቾችን በዋና ኃላፊነት መርተው ይሳካላቸዋል ወይ የሚለው ጥያቄ ነው፡፡
አሰልጣኝና ተጨዋቾች እኩያሞች መሆናቸው ምንም ተጽእኖ እንደማይኖረው የተናገረው የክለቡ አምበል ጆን ቴሪ ነው፡፡ ..አንድሬ ዘመናዊ አሰልጣኝ ነው፡፡ በጣም የሚያስደንቀኝ ተጨዋቾችን በቀላሉ የመረዳት ችሎታው ነው፣ ያረጀ አስተሳሰብ የለውም.. ብሏል ቴሪ አንድሬ ቪላስ አንጋፋው አሰልጣኝ ካርሎ አንቸሎቲ በሁለተኛ የውድድር ዘመናቸው ክለቡን ያለዋንጫ ያስቀሩበትን ሁኔታ ለመቀየር ይችላሉ ተብሎ ይገመታል፡፡  የቼልሲው ባለቤት ሮማን አብራሞቪች ከአዲሱ አሰልጣኛቸው የፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫን ላይጠብቁ ይችላሉ፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን አጋማሽ ላይ በ100 ሚሊዮን ዶላር በጀት ፈርናንዶ ቶሬስና ዴቪድ ሊውዝን ወደ ክለቡ ቢቀላቀሉም ክለቡ በአዲሱ የውድድር ዘመን ዋዜማ በግዢ  አልተሳተፈም፡፡ ለሻምፒዮንስ ሊጉ የሚበቃ ቡድን አለኝ የሚሉት ቪላስ ቦኦስ ከሊጉ ለዚሁ የአውሮፓ ድል ቅድሚያ ይሰጣሉ ተብሎ ይገመታል፡፡
በፋብሪጋዝና ናሰሪ ክለቡን የመልቀቅ ወሬ እየተገታገተ ያለው አርሰናል በአዲሱ የውድድር ዘመን ጅማሮው በስጋት ተወጥሯል፡፡ በሁሉም ውድድሮች ያሉ ዋንጫዎችን ለመፎካከር ጥያቄ ውስጥ የገባው ክለቡ የሊግ ካፑን ለማግኘት  ቢያልም የማይደንቅ ሲሆን ያለፉትን 6 የውድድር ዘመናት ያለዋንጫ ማሳለፉ ከኃያላኑ ተርታ እያስወጣው ይገኛል፡፡ የክለቡ ደጋፊዎች በቅድመ የዝግጅት ውድድር አርሰናል ባለው አቋም ደስተኞች አይደሉም፡፡ ቲዬሪ ሆንሪ ከሚገኝበት የአሜሪካው ሬድ ቡልስ ጋር ከሳምንት በፊት የተደረገ የወዳጅነት ጨዋታ ላይ የአርሴን ቬንገር ቡድን ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ አርሴን ቬንገር አሁን አለቃቸው የሆኑትን አሜሪካዊ ቢሊዮነር ስታን ክሮንኬ ..ከእኛ በላይ አቅም ካላቸው ጋር መፎካከር አለብን.. በሚል ምሬት አምተዋል፡፡
ከሳምንት በኋላ የሚጀመረው የ2011 -12 የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫ ተቀናቃኝ እንዲሆን የተገመቱት ማን.ዩናይትድ፣ ቼልሲ፣ አርሰናልና ማን.ሲቲ ቢሆኑም በ2ኛ እርከን በተፎካካሪነት ሊቨርፑልና ቶትንሃም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በተለይ ሊቨርፑል ከተጨዋቾች ዝውውር ጋር በተያያዘ በእንግሊዛዊያን ተጨዋቾች ላይ በማተኮር ስብስቡን ሲያጠናክር ከ75 ሚሊዮን ዶላር በላይ ፈሰስ ማድረጉ ትኩረት አግኝቶበታል፡፡

 

Read 6917 times Last modified on Monday, 08 August 2011 09:53