Saturday, 13 August 2011 09:28

ስደት የሚቀርበት ጊዜ ናፈቀኝ

Written by  ትዕግስቱ በለጠ
Rate this item
(0 votes)

የናይሮቢ መሐል ሰፈሮች በቱሪስት የተጨናነቁ ናቸው፡፡ የሕንጻው ውበትና ጥራት ከአውሮፓ ትናንሽ ከተሞች ጋር ያመሳስላቸዋል፡፡ በበርካታ ዘመናዊ መኪኖች የተሞላውን ጠባብ የኬንያ መንገዶች እያቆራረጥኩ ለሣምንት የከረምኩበትን ..ዳውን ታውን.. ትቼ በርካታ ሶማሌያውያን እና ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መኖሪያ ናት የተባለችውን ..ኢስሊ..ን ለመጎብኘት መንገድ ጀመርኩ፡፡

የድሬውን ..አሸዋ.. - ናይሮቢ አገኘሁት
በስም እንጂ በካርታ እንኳን ለይቶ የማያውቃትን ካናዳ በመናፈቅ ኬንያን እንደመሸጋገሪያ ቆጥሮ መቼ እንደሚሳካ የማያውቀውን የጉዞ ..ፕሮሰስ.. መጠበቅ ከጀመረ ስድስት ዓመት ያስቆጠረ ወዳጄ እና ወዳጆቹ በምቾት አንፈላሰው እያሽሎከሎኩ በሚወስዱት ታክሲዎች አሳፍረው ያስጎበኙኝ ጀመር፡፡ በእነዚህ ታክሲዎች ተሳፍሬ መጓዝ ስጀምር ዲፕሎማት የሆንኩ እየመሰለኝ እንደመኩራራት ይቃጣኝ ነበር፡፡ ላገሬ ላዳ ታክሲዎች ማዘኔም አልቀርም፡፡  
ቀደም ሲል እንግሊዞች በኋላም ኬንያውያን ያሳመሯቸውን መስታወት አልባ ህንፃዎች እና የንግድ አካባቢዎች እየራቅናቸው ጥቅጥቅ ወዳሉት እና ወዳረጁት ህንፃዎች ስንቃረብ መድረሻዬ አሰጋኝ፡፡ እግረ መንገዳችንን ታዋቂ የንግድ ስያሜ ያላቸው ጫማዎች እና ቁሳቁሶች በርካሽ ዋጋ የሚሸጡባቸውን ቦታዎች ለማየት የስደተኛው ወዳጄን ትረካ እየሰማሁ ቀጠልኩ፡፡ ስደተኛው ትረካውን ቀጥሏል፡፡ ..ኢትዮጵያ እኮ በጣም የምታስጠላ አገር ነች፡፡ ናይል ፐርች ኢትዮጵያ ስንት ነው? . . . ፖምስ . . .ፓፓያስ . . . ሙዝስ . . . እሺ ወይንስ . . .?.. አሉ የተባሉ የምግብ ዓይነቶችን ከነዋጋቸው ርካሽነት ጭምር እየዘረዘረ በየመንገዱ እንደሚሸጡ ነገረኝ፡፡ ከምግብ ዓይነት ጀምሮ የማይጠራው የዕቃ ዓይነት የለም፡፡ ነጋዴ መሰለኝ፤ ስደተኛነቱን ተጠራጠርኩት፡፡
ወደተባለው የንግድ ስፍራ ሰተት ብለን መግባታችንን እነሱ ሳይነግሩኝ አውቄው ነበር፡፡ ከፍ ብሎ በተሰራ መደብ ላይ ፕላስቲክ እና የማዳበሪያ ጣሪያ የለበሱ ሱቆች ተደርድረዋል፡፡ የተለያዩ ልብሶች ለዕይታ ምቹ ሆነው በዓይነት ተሰቅለዋል፡፡ በርካታ ስኒከር ጫማዎች መደቡን ሞልተውታል፤ ማሰሪያቸው ተፈቶ ታጥበው የተሰጡ ጫማዎች ቁጥርም ቀላል አልነበረም፡፡ ቦታውን የት እንደማውቀው  ለማስታወስ ሞከርኩ፤ ልክ ነኝ አውቀዋለሁ፡፡ ግን ኬንያ ሳይሆን ድሬዳዋ ..አሸዋ.. ተብሎ በሚጠራው ሰልባጅ ተራ፡፡ ሁለቱም ቦታዎች አንድ ናቸው፡፡ የተጠቃሚዎቹም ዜግነት አንድ ነው፡፡ ታዲያ ምን አዲስ ነገር አለ? ማየት ሳያስፈልገኝ ወደ ኢስሊ አመራሁ፡፡
እዚያም ጫት አለ  
የኢስሊ ገበያም አዲስ አልሆንብሽ አለኝ፤ መንገዱ በሰዎች ተጨናንቋል፡፡ መጀመሪያ የገባነው መጋረጃ ተራ ነበር፡፡ የሶማሊያውያኑ ቁጥር ከፍ ቢልም ኢትዮጵያWÃnùN ጨምሮ ሁሉም ከልብስ መስፊያ መኪናቸው ጋር ይነጋገራሉ፡፡ በየሱቆቻቸው መስኮት ላይ የቆሙም አልጠፉም ..እሙዬ፣ እንብላ፣ እዚህ ጋም ቆንጆ መጋረጃ አለ፣ ሰላም በይና!.. አማርኛ ወደሚናገሩት ሁሉ አንገቴን ሳዞር በመቆየቴ ነው መሰለኝ ስወጣ ህመም ቢጤ ተሰማኝ፡፡
ጫት ተራው የቀለጠ ነው፡፡ ልክ እንድ ድሬ አፋቸው ድረስ ጢም ተደርገው የተሞሉ ትልልቅ የጫት መያዣ ላስቲኮች ተደርድረዋል፡፡ የጫት ላስቲኩን ከፊታቸው አስቀምጠው ገበያ የሚጠብቁት ነጋዴዎችም ጉንጫቸውን በጫት ወጥረው ቀንበጥ ቀንበጡን ከላይ እያደረጉ ያስተካክሉታል፡፡
አስቀድመው ጫታቸውን የሸመቱት ደግሞ በየሱቆቻቸው በረንዳ ላይ ምንጣፍ አንጥፈው ጫታቸውን እየቀረጠፉ ጨዋታውን አድርተውታል፡፡ ግን አልቀናሁም ..የጫቱስ ነገር እኛም ቤት አለ.. ብዬ አሽሟጥጫቸው አለፍኩ እንደውም kኢትዮጵያውያን የኮረጁ ሁሉ መሰለኝ፡፡  
ያማለለኝ የኤሌክትሮኒክስ ገበያ
በኤሌክትሮኒክስ እቃዎች መሸጫ ሱቆች ውስጥ ሞባይል፣ ካሜራ፣ ቪዲዮ ካሜራ . . . የሌለ ነገር የለም፡፡ ገበያው የስስት አይደለም፡፡ በመልክም በዓይነትም አንድ ዕቃ ይዞ እሱኑ ከዲስፕሌይ ላይ አውጥቶ መሸጥ እዛ አልተለመደም፡፡ ሲያዩት እራሱ የሚያስደስቱ በርካታ አማራጮች አሉ፡፡ ዋጋውስ ቢሆን... ከኢትዮጵያ ገበያ በመቶ እጥፍ ቅናሽ ነው፡፡ በቻይና ዕቃ ምሬት በኬንያ የለም፡፡
የቅጅ መብት ነገር?
በኢትዮጵያዊ ስም የተሰየመችው አነስተኛ ኪዮስክ መሰል ሙዚቃ ቤት ከውጭ በተሰቀለው ስፒከሮች አካባቢውን በአማርኛ ዘፈን አናውጣዋለች፡፡ ስደተኛው ወዳጄ የሙዚቃ ቤቱን ባለቤት ያውቀው ነበርና ለሰላምታ ወደ ውስጥ ዘለቅን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ዓይቻቸው የማውቃቸው እና የማላውቃቸው የተለያዩ ፖስተሮች ዙሪያውን ተለጥፈው ለቤቷ ድምቀት ሰጥተዋታል፡፡ ባለቤቱ በሥራ ተወጥሯል፤ ፊትለፊቱ የተቀመጠው አሮጌ ኮምፒዩተርም ሥራ በዝቶበታል፡፡ ጠረጴዛው ላይ ተደርድረው ከተቀመጡት ባዶ ሲዲዎች እያነሳ ከኮምፒዩተሩ ውስጥ ባወጣው ምትክ ይከታል፡፡ አጠገቡ ከተቀመጠው ላስቲክ ውስጥም ጫት እያወጣ ወደ አፉ ይከታል፡፡ ..የማንን ዘፈን ላድርግልህ?፣ ምን ዓይነት ፊልም ይሻልሃል ኮመዲ፣ ትራጀዲ፣ . . .?.. ገበያተኞቹን ይጠይቃል፡፡ እነሱም ይመልሳሉ፡፡ የተወሰነውን አስከፍተው ያያሉ፤ ዋጋ ይደራደራሉ፡፡ አስቀድተው ይወስዳሉ፡፡ የኮምፒዩተሩ ጠረጴዛ ከተደገፈው ግድግዳ ላይ ከተለጠፉት ፖስተሮች መካከል አንዱ በትልቁ እንዲህ ይላል ..ኦርጅናል በመግዛት ለራሳችንና ለባህላችን ታማኝ እንሁን!!.. ፖስተሩን ሲለጥፈው ምን እንደሚል አላየው ይሆናል በሚል ላሳየሁ ሞከርኩ፤ ፈገግ ብሎ አየኝና ሥራውን ቀጠለ፡፡ ኮፒ እያደረገ ይሰጣል፤ በምትኩም በርካታ ሽልንጎች ይቀበላል፡፡ እሱም ሥራው ቀጠለ፤ እኔም ቤቱን ለደንበኞቹ ለቅቄ መጣሁ፡፡ ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች የቅጂ መብት ትግላቸው ኬንያንም ሊጨምር ይገባል ስል አሰብኩ፡፡
ዝንቦች የከበቡት ሬስቶራንት  
በዘነበው ዝናብ ይሁን በፈነዳ ቱቦ የጨቀየውን፣ የኢስሊ ጎዳና ተጠንቅቀን እየረገጥን፣ ሲያቅተንም በጭቃ እየቦካን በቆሻሻ የተሞሉትን መንገዶች እያቆራረጥን፣ ከአማርኛ ተናጋሪዎች ጋር ሰላምታ እየተለዋወጥን፣ ከሶማሊያውያኑ ጋር በፈገግታ እየተግባባን ወደ ሐበሻ ምግብ ቤት አመራን፡፡
ወደ ምግብ ቤቱ የሚያስገባውን ደረጃ ስንጀምር ኢትዮጵያ የማውቀው የመፀዳጃ ቤት ሽታ አፍንጫዬን ሰነፈጠኝ፡፡ አንድ ሳምንት በቆየሁባቸው ሌሎች በኬንያውያን ሬስቶራንቶች እንዲያ ያለ ነገር አልሸተተኝም ነበርና የኢትዮጵያWÃnù ለምን እንዲህ ሊሆን እንደቻለ እያብሰለሰልኩ ወደ ፎቆ ወጣሁ፡፡ ቁርጥ እና ጥብስ የቤቱ ምግብ ነበር፡፡ አንዱን አዘን እጄን ልታጠብ ስሄድ መታጠቢያው ውሃ የለውም፡፡ ጎኑ ላይ ከተቀመጠው ባልዲ በጆግ እየጠለቁ መታጠብ የግድ ነበር፡፡ የለመድኩት ስለነበር ግር ሳይለኝ እኔም ጠልቄ ታጠብኩ፡፡
በኬንያ መቼም የምግብ ችግርም ሆነ ስጋት የለም፡፡ በየመንገዱ የሚበላ ነገር አይጠፋም፤ በተለይ ፍራፍሬ፡፡ ምግቦቹ ሥራ አያበዙም፤ መላጥ የሚያስፈልጋቸው ፍራፍሬዎች በሙሉ ታጥበው፣ ተልጠው እና በላስቲክ ታሽገው በኬንያ ጥቂት ሽልንግ በየመንገዱ ይሸጣሉ፡፡ የኬንያ ደሀ ፖምና ፓፓያ እየበላ ነው የሚደኸየው፡፡ ባለፈው ሰሞን በምግብ እህል ላይ ሁለት የኢትዮጵያ ብር ጨመረ ብለው የቀለጠ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው ነበር አሉ፡፡ ሰላማዊ ሰልፉን ተከትሎ ደግሞ ቅናሽ ተደርጎላቸዋል፡፡ የባቄላ አሹቅ እንኳን በቅጡ ሳይበላ ..አደገ.. የተባለው የአገሬ ገበሬ አሳዘነኝ፡፡  
ያዘዝነው ትኩስ የፍም ጥብስ በበርካታ ዝንቦች ሙዚቃ ታጅቦ ከቸች አለ፡፡ እኛም በሁለት እጃችን ሥራ ያዝን፡፡ በአንዱ እጃችን እያባረርን በአንዱ ደግሞ እየጎረስን፡፡ የኢስሊ ጉብኝቴን አጠናቅቄ ..ማታቱ.. በተባሉት የኬንያውያን አውቶብሶች ወደ ዳውን ታውን ለመመለስ ስጠብቅ የጫት መረቅ በአፉ ዳርና ዳር የሚታይበት፣  የተቦጫጨቀ አዳፋ ልብስ የለበሰና አውራ ጣቱን ለተመልካች አሳልፎ የሰጠ ጫማ የተጫማ ኬንያዊ ስለመሆኑ ቅንጣት ታክል ያልተጠራጠርኩት ጠቆር ያለ ወጣት፤ ..እሙዬ ትንሽ ገፍትሪልኝ?.. ሲል ጠየቀኝ፡፡ ዓይኔ  ከሱ ይልቅ ክርር ባለው ጠራራ ፀሐይ ኢትዮጵያ ውስጥ በፒካፕ መኪና ላይ ሲጫኑ የምናውቃቸውን በርካታ ቁሳቁሶች የሞሉ ተጎታች ጋሪዎች በወገባቸው አጥልቀው እየጎተቱ የሚሄዱትን ጠንካራ ኬንያውያን ተመለከትኩ፡፡ ..ለልመና ልመና ለምን ተሰደደ?.. ስል አጉረመረምኩ ለራሴ፡፡  
ከስደተኞቹ ወዳጆቼ እንደተረዳሁት ጥቂት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ራቅ ብለው ከመኖራቸው በስተቀር አብዛኞቹ በማይመሸው ኢስሊ ከትመው ሌላ ስደት ይናፍቃሉ፡፡ ጉዳያቸውን በስደተኞች ጣቢያ አመልክተው የሚመጣላቸውን ጥሪ ይጠባበቃሉ፡፡ ጥሪው መቼ እንደሚመጣ ከፈጣሪ ውጭ የሚያውቅ የለም፡፡ ይደወልላቸዋል እንጂ አይደውሉም፡፡ ዓመት . . . ሁለት ዓመት፣ . . . አራት ዓመት እያለ ከ20 ዓመት በላይ የተቀመጠ አለ፡፡ ቤት ያለው ቤቱ፣ የሌለው ጎዳና ብቻ የትም ያድራሉ፡፡ ጠዋት እስከ ስድስት ሰዓት ይተኛሉ፡፡ ሲነቁ ይቅማሉ፡፡ መልሰው ይተኛሉ፡፡ የአብዛኞቹ የተለመደ ህይወት ይህ ነው፡፡
ሶማሌያዊያኑ ግን የኢስሊን ገበያ በበላይነት ተቆጣጥረውታል፤ ከመፋቂያ ጀምሮ አያሌ  እቃዎችን ይሸጡበታል፤ ይገዙበታልም፡፡
ፀሐያማዋን፣ በሰዎች የተጨናነቀችውንና ቆሻሻዋን ኢስሊን ለቅቄ ንፁሁን አየር መሳብ ብጀምርም ሐሳቤ ግን እዛው ኢስሊ ቀርቶ ነበር፡፡ ስደት፣ ረሃብ፣ ልመና፣ ችግር lኢትዮጵያውያን እንዲሆን ያደረገው ማን እንደሆነ ማወቅ ፈለኩ፡፡ በአገራቸው አፈር፣ በአገራቸው ቋንቋ ከአገራቸው ሕዝብ ጋር ተባብረው ብዙ በጣም ብዙ ነገር ማምረት የሚችሉት የነዚያ ወጣት እጆች እና እግሮች አንድ ቦታ ተቀምጠው፤ ተስፋ አጥቶ በገረጣው ፊታቸው ኢትዮጵያዊ መሆኔን አውቀው ፈገግታ የለገሱኝን በየመንገዱ ተኮልኩለው ያየኋቸው ወጣቶችን መርሳት አቃተኝ፡፡ እነዚህን መሰል ወጣቶች በአገሬ እንዳሉ ባውቅም እንደ ኬንያዎቹ አላሳዘኑኝም፡፡ አንድ አስተማሪዬ ..ጋዜጠኛ አገር የለውም!፣ ጋዜጠኛ ስሜት የለውም፣ አያለቅስምም፡፡ የጋዜጠኛ ሥራ ገለልተኛ ሆኖ መጻፍ ብቻ ነው.. ሲል አስተምሮኝ ነበር . . . እኔም ለዓመታት ተግባራዊ አድርጌው ነበር፡፡ ኢስሊ ያየኋቸው ወጣት የአገሬ ልጆች ግን ስሜቴን በእጅጉ ተፈታተኑት፡፡ ከመጻፍ ይልቅ ማልቀስ አማረኝ፡፡ ስደት የሚቆምበት ጊዜም ናፈቀኝ፡፡

 

Read 5484 times Last modified on Saturday, 13 August 2011 09:35