Saturday, 13 August 2011 09:35

አህያ እና ጥናት

Written by  አንተነህ ግዛው
Rate this item
(7 votes)

የጋማ እንስሳት ጥበቃና እንክብካቤ ባለስልጣን የአመቱን በጀት ሊዘጋ የቀናት ዕድሜ ቀርቶታል፡፡
በበጀት አመቱ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በርካታ ተግባራትን ቢያከናውንም ከተያዘለት አመታዊ በጀት አስራ ስድስት በመቶውን ብቻ ነበር የተጠቀመው፡፡
ይህ ደግሞ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን ዋና ዳይሬክተር ስጋት ውስጥ ጥሏቸዋል፡፡ በጀቱን ጥቅም ላይ አለማዋልና ተመላሽ ማድረግ የሚጠላ አለመሆኑን ያውቃሉ፡፡ ግን ደግሞ ለአመቱ ከተመደበው በጀት 84 በመቶውን ተመላሽ ማድረግ ያልታሰበ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ጠርጥረዋል፡፡

..ይሄን ያህል በጀት ተመላሽ ማድረግ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ተገቢውን ስራ እንዳላከናወነ እንዲሰማቸው ሊያደርግ ይችላል.. ብለው አሰቡ ዋና ዳይሬክተሩ፡፡
ስለዚህ የበጀት አመቱ ከመጠናቀቁ በፊት የተወሰነውን ገንዘብ በሆነ ምክንያት...የሆነ ስራ ፈጥሮ ወጪ ማድረግ እንደሚገባ ወሰኑ፡፡
ውሳኔያቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ጊዜ አላባከኑም፤ ምክንያቱም በጀት ሊዘጋ አስር ቀናት ብቻ ናቸው የቀሩት፡፡
በባለስልጣኑ ..የአህዮች ሁለንተናዊ ደህንነት ጥበቃ ወሳኝ የስራ ሂደት ባለቤት.. ወደ ሆነው አቶ ያየህ ስልክ ደወሉ፡፡
..በል እንግዲህ እስኪ ጉድህን እንየው.. አሉ ዋና ዳይሬክተሩ፡፡
..የምን ጉድ ነው እሱ?.. ግራ ተጋብቷል አቶ ያየህ፡፡
..በጀት አነሰኝ እያልክ ስትነጫነጭ አልነበር?.. ጠየቁት፡፡
..በዚህ አስር ቀን ውስጥ አንድ ፕሮጀክት ቀርፀህ ተጨባጭ ውጤት ያለው ስራ ሰርተህ ማሳየት አለብህ፡፡ የበጀት ችግር የለም፡፡ የጠየቅከውን ያህል ይመደብልሃል፡፡ ጥያቄ ካለህ ወይም ማብራሪያ ከፈለግህ አሁኑኑ ቢሮዬ ድረስ መምጣት ትችላለህ፡፡..
አቶ ያየህ አለቃው ያሉትን ሲሰማ ለማመን ተቸገረ፡፡
ኮስታራ አለቃው የበጀት አመቱ ከመጠናቀቁ በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ የማይሆን ቀልድ የቀለዱ ነበር የመሰለው፡፡ እየቀለዱ አለመሆኑን ለማረጋገጥ ወደ ቢሯቸው ሄደ፡፡ ደጋግሞ ያስያዛቸው ዕቅዶች በበጀት እጥረት ምክንያት ውድቅ ተደርገውበታል፡፡ ለምሳሌ፤ በሁለኛው ሩብ አመት ..የወፍጮ ቤት አህዮች እና የፓርኪንግ ችግር.. በሚል ጉዳይ ዙሪያ ጥናት ለመስራት አቅዶ ..በጀት የለም.. ተብሎ ሃሳቡ ውድቅ ተደርጐበት ነበር፡፡
አሁን የበጀት አመቱ ሊጠናቀቅ አስር ቀናት ብቻ ቀርተውት ..በጀት ሞልቷል.. መባሉ ግራ አጋባው፡፡
ወደ ዋና ዳይሬክተሩ ቢሮ አምርቶ ባደረገው ውይይትም የበለጠ ግራ ተጋባ፡፡ ትዕዛዛቸውን የመፈፀም ግዴታ እንዳለበት አስረግጠው ነገሩት፡፡
..ይሄ ነው ይሄ ነው አልልህም፡፡ እንደባለሙያነትህ በአህዮች ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችን ከእኔ ይልቅ አንተ ታውቃቸዋለህ፡፡ ይሆናል በምትለው ጉዳይ ዙሪያ የሆነ ጥናት እንድትሰራ ነው የሚፈለገው.. አሉት ዋና ዳይሬክተሩ ኮስተር ብለው፡፡
አቶ ያየህ መጨነቅ ጀመረ፡፡
በቀሪዎቹ የበጀት አመቱ ጥቂት ቀናት ውስጥ ምን አይነት ጥናት መስራት እንደሚችል አሰላሰለ፡፡ አስቸጋሪ ሆኖ ታየው፡፡ ..አሰቃቂ ቅጣት ይቁም.. የሚለውን ..ብሮሸር.. በየጉልቱ እና በየገበያው ለህዝቡ የማደል ስራ የሚያከናውኑ ሰራተኞችን እየተዟዟረ የመገምገም ስራውን አልጨረሰም፡፡
.....የብሮሸር እደላውን የመገምገሙ ስራ እኮ አልተጠናቀቀም፡፡ እሱን ትቼ..... አለና አቋርጦ ተወው አቶ ያየህ፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ በአቶ ያየህ ንግግር ማዘናቸውን ለመግለጽ አንገታቸውን ግራና ቀኝ አወዛወዙ፡፡
..አቶ ያየህ...Think big!... ለታላቅ ነገር እየታጨህ ለምን በተራ ነገር ራስህን እንደምትጠምድ አይገባኝም፡፡ እኔ የፈለግኩህ የመስሪያ ቤቱን ህልውና በሚወስን ታላቅ ጉዳይ ላይ የሚጠበቅብህን አስተዋጽዖ እንድታበረክት እንጂ..... አሉና በቁጣ አፈጠጡበት፡፡ በዋዛ እንደማይለቁት ገብቶታል፡፡
..ካለን የስራ ሂደት ባለቤቶች ሁሉ ይህንን ስራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማከናወን የሚችል ማነው? ብዬ በቂ ጥናት አድርጌያለሁ፡፡ አንተ የተሻልክ መሆንክን አምኜ ነው የመረጥኩህ..... ብለው ሲጋራ ፍለጋ ጣታቸውን ወደ ሸሚዝ ኪሳቸው ሰደዱ፡፡
..እ...እኔኮ ያልኩት የ..ብሮሸር.. እደላ ስራው ሳይጠናቀቅ.. አላስጨረሱትም፡፡ በቀኝ እጃቸው ጠረጴዛውን ነረቱት፡፡
..እሱን ትተህ ያዘዝኩህን ብቻ ፈጽም፡፡ ለትልቅ ነገር እያጨሁህ ተራ ነገር ላይ ትልከሰከሳለህ እንዴ? ..የአህያ ስጋ አልጋ ሲሉት አመድ.. አሉ.. አሉ፡፡
..የአህያ ስጋ አልጋ ሲሉት አመድ..
አቶ ያየህ ይህን አባባል እያሰላሰለ ነበር ከአለቃው ቢሮ የወጣው፡፡ ከአህያ ጋር በተያያዘ ጥናት እንዲሰራ ነው የታዘዘው፡፡ ከተሰጠው ጊዜ አጭርነት አኳያ የተሻለው የጥናት ርዕስ ከላይ በነጠላ ጥቅስ ውስጥ የሰፈረው ከአህያ ጋር የተያያዘ የአለቃው (የህዝቡ) ምሳሌያዊ አነጋገር ሆኖ ተሰማው፡፡
..የአህያ ስጋ አልጋ ሲሉት አመድ..
አቶ ያየህ ጥናቱን በተሰጠው ጊዜ ውስጥ አጠናቀቀ፡፡
የጥናቱ ውጤት ይፋ የሚደረግበት የግማሽ ቀን አውደ ጥናት በአንድ ሆቴል አዳራሽ ውስጥ ተዘጋጀ፡፡
..አቶ ያየህ የጥናት ውጤታቸውን መድረክ ላይ ወጥተው ለአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች በፓወር ፖይንት.. አስደግፈው ያብራራሉ፡፡
የመስሪያ ቤቱ የሂሳብ ባለሙያ ወ/ሮ ያየሽ የዝግጅቱን ወጪ ከመድረክ ጀርባ ገብተው ይደምራሉ፡፡
..አህያ እና ምሳሌያዊ አነጋገሮቻችን.. የዳሰሳዊ ጥናቱ ርዕስ ነው፡፡
..ለዝግጅት ወጪ የተደረጉ ክፍያዎች..
ይህ የወ/ሮ ያየሽ የወጪ መዝገብ ርዕስ ነው፡፡
አቶ ያየህ የጥናት ውጤታቸውን እያቀረቡ ነው፡፡
...ያው ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት ጥንት በዚያን ጊዜ ..ሰርዶ.. የሚባል ከግራር የሚልቅ የዛፍ አይነት ነበር፡፡ የአህያ ዋነኛ ስራም በየዕለቱ የዚህን ዛፍ ግንድ እየተሸከመች ወደ ሩቅ አገር ማጓጓዝ ነበር፡፡ አህያም ታዲያ ለረጅም አመታት የሰርዶ ግንድ ስታመላልስ ኖራ በስተመጨረሻ እያረጀችና እየደከመች መጣች፡፡ በዚህ ጊዜም ንጉሱ አንበሳ ..አህያ ሆይ፤ ይሄን ያህል ዘመን የሰርዶ ግንድ ስታመላልሺ ኖረሻል፡፡ አሁን ግን ደክመሻል፡፡ መሞቻ ጊዜሽም እየደረሰ ነው፡፡ ስለዚህ አንቺ በክብር እረፊ...የሰርዶ ግንድ የማመላለሱን ሃላፊነት ለድመት እሰጣታለሁ.. ይላታል፡፡ አህያ ግን ..ይሄንን ስራ ድመት አትችለውም፡፡ እኔው በህይወት እስካለሁ ስራውን ለመስራት አሁንም ፈቃደኛ ነኝ.. ብላ እንቢ አለች፡፡ አያ አንበሶም ታዲያ በአህያ እምቢተኝነት ተናደደና ..እንዲያውም ዛሬውኑ እንድትሞች ወስነናል...ከመሞትሽ በፊት የምትናገሪው ነገር አለ?.. ሲል ጠየቃት፡፡ እሷም ታዲያ ከሞቷ በላይ ያሳዘናት ድመት በዚያ ከባድ ስራ ስትሰቃይ መኖሯ ነበርና እንዲህ ብላ ተናገረች፡፡
.....ንጉስ አንበሳ የሞት ፍርድዎን ተቀብያለሁ፡፡ ግን ባይሆን ..እኔ ከሞትኩ በኋላ ሰርዶ አይብቀል.. የእንስሳትን ጀርባም አይላጥ ብዬ እንድፀልይ ቢፈቅዱልኝ.. ብላ ጠየቀች፡፡ እንግዲህ የዚህ ምሳሌያዊ አነጋገር መነሻ ይህ እንደሆነ ነው ጥናቱ የሚያረጋግጠው...
..እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል.. የሚለው አባባል አህያን ስስታም አድርጐ ለማሳየት ተጣሞ የተነገረ አባባል መሆኑን ለመናገር እወዳለሁ...እሷ ይህንን ያለችው ..መከራ በኔ ይብቃ.. ለማለት ነው...
ወ/ሮ ያየሽ የአውደ ጥናቱን ወጪዎች እየደመሩ ነው፡፡
...ለመሰብሰቢያ አዳራሽ ኪራይ...25,000 ብር፡፡
በሌላ ጊዜ ደግሞ አያ አንበሶ ልጁን ..ድል.. ባለ ድግስ ይድራል፡፡ እየተበላ፣ እየተጠጣ ይዘፈናል፡፡ አህይት ግን ከማዕድ ቤት ወደ ሰርጉ ድንኳን ምግብና መጠጡን በማመላለሱ ስራ ተጠምዳለች፡፡ ..ምናለ አረፍ ብለሽ እህል ውሃ ብትይ.. ሲሏት በጄ አላለችም፡፡ በመካከል ላይ ታዲያ የአህይት ሁኔታ ያሳዘነው ውሾ አንድ ማንኪያ ማር እያቀበላት ..ኧረ ባይሆን ከዚህ እንኳን ቅመሺ.. አላት አሉ፡፡   
ይሄን የሰማችው ጦጢት ምን ትላለች መሰላችሁ?
.....ተዋት እባክህ... ለአህያ ማር አይጥማትም.. ከዚያ ጊዜ በኋላ ነው እንግዲህ ይህ ምሳሌያዊ አነጋገር...
* **
...ለሻይ ቡናና ለምሳ... 10,000 ብር፡፡
***
...ጊዜው በውል በማይታወቅ በጥንት ዘመን አህያ በስራ ትጋቷ አንደኛ ሞዴል እንስሳ ተብላ ተመርጣ ነበር፡፡ በወቅቱ የእንስሳት ንጉስ የነበረው ፈረስ ለአህያ እና ለዘመዶቿ ከስፖንጅ የተሰራ ሸኮና ሸለማቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ነው እንግዲህ አህያ ቢራገጥ ጥርስ አይሳበርም የሚለው አባባል መጀመሩን ጥናቱ የሚያሳየው፡፡ የዚህ ምሳሌያዊ አነጋገር አመጣጥ ያልገባቸው ሰዎችን ግን አህያ ከትግልና ልፊያ በቀር ሞያ የሌላት እንስሳ ናት የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳላቸው በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡
***
...ለተሳታፊዎችና ለጋዜጠኞች አበል... 8500 ብር፡፡
***
...እንደሚታወቀው ማህበረሰቡ በአሉታዊ ምሳሌያዊ አነጋገሮች ፆታዊና የመሳሰሉ ጥቃቶችን ይፈማል፡፡ ለምሳሌ ሴቶች አሉታዊ መልኩ ከሚጠቀሱባቸው ምሳሌያዊ አነጋገሮች መካከል ሴት ያለ፣ ሴት አከለ የሚለውን መጥቀስ ይበቃል፡፡ መሰል የተዛቡ አመለካከቶችን ለመለወጥ ራሱን የቻለ የመንግስት አካል ተቋቁሞ እየሰራ ይገኛል፡፡ ...የእኛ ባለስልጣን መስሪያ ቤትም ይህን ተሞክሮ ወደ አህዮች ለማስፋፋት ነው ይህንን ጥናት ያደረገው፡፡ ወደ ጥናቱ ውጤት ስንመለስ...
በጥናቱ እንደተረጋገጠው አህያ በማንነቱ የሚኮራና በራሱ የሚተማመን እንስሳ ነው፡፡ ይህ ሆኖ እያለ አንዳንድ ግለሰቦች ግን አሁንም በተንሻፈፈ የምሳሌያዊ አነጋገር ትርጓሜ የአህያን ማንነት ያልሆነ ቦታ ሲሰጡት ይታያል፡፡
ለምሳሌ - በቅሎ አባትሽ ማነው? ቢሏት... ፈረስ አጐቴ ነው አለች የሚለውን ምሳሌያዊ አነጋገር እንመልከት፡፡
እውነት... በቅሎ በአባቷ በአህያ የምታፍርና የምትሸማቀቅ ሆና ነው ይሄን መልስ የሰጠችው?... ጥናቱ ግን ይህ እንዳልሆነ ነው የሚያሳየው፡፡
ነገርን ከስሩ... ውሃን ከጥሩ ይባላልና ጉዳዩን መለስ ብለን ማየቱ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡
በጥንት ጊዜ ነው... አህያ የእንስሳት ሁሉ ንጉስ የነበረበት ጊዜ ነበር፡፡ ንጉስ አህያ እንስሳትን በእኩልነትና በዴሞክራሲያዊ መንገድ በማስተዳደሩ ከሰዎች ዘንድ ሳይቀር ተደናቂነትን ለማትረፍ በቃ፡፡ በዚህ ጊዜም ሰዎች ለንጉስ አህያ አድናቆታቸውን በመግለ በተለይ የትምህርት እድል ለሌላቸው ሦስት እንስሳት ስኮላርሺፕ እድል እንደሰጡ የሚያበስር ደብዳቤ ላኩ፡፡
ንጉስ አህያም ደብዳቤው በሚያዘው መሰረት በተለይ የትምህርት እድል የሌላቸው ችግረኛ እንስሳት ተመርጠው ወደ ሰዎች እንዲላኩ አዘዘ፡፡ በእድሉ ለመጠቀም የፈለጉ መሰል እንስሳትን የመመዝገብና የመምረጥ ሃላፊነቱ የተሰጣት ጥንቸል ነበረች፡፡ አመልካቾችን በመመዝገብ ላይ እያለች ታዲያ በቅሎም ለመመዝገብ ወደ ጥንቸል ሄደች፡፡
..አንቺስ ማን ነሽ?.. አለች ጥንቸል አቀርቅራ እየፃፈች፡፡
..በቅሎ.. አለች በቅሎ ፈራ ተባ እያለች፡፡
..አባትሽስ ማነው?.. ስትል ቀጠለች ጥንቸል በመሰላቸት፡፡
ይሄኔ በቅሎ ፍርሃት ገባት፡፡ ስኮላርሺፑ የተፈቀደው የትምህርት እድል ለሌላቸው ችግረኛ እንስሳት ነው፡፡ እሷ ደግሞ አህያን የመሰለ የእንስሳት ሁሉ ንጉስ ነው አባቷ፡፡ ስለዚህ አባቴ አህያ ነው ስትል አንቺማ በድሎት አንደላቆ የሚያስተምር ንጉስ አባት ነው ያለሽ ተብላ ውድቅ መደረጓ አይቀርም፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ሙስና ነካክቶት የማያውቅ አባቷ ልጁን መርጦ ላከ ተብሎ እንዲታማ ልታደርግ ነው፡፡ ጨነቃት በቅሎ፡፡ ጥቂት ቆይታ ግን ከቅርብ ዘመዶቿ የትምህርት እድል ያላገኘ እንስሳ ትዝ አላት - ፈረስ፡፡
..ንገሪኝ እንጂ... አባትሽ ማነው?.. ቆጣ ብላ ጠየቀች ጥንቸል፡፡
..ፈ... አረስ አጐቴ ነው.. ስትል መለሰች በቅሎ፡፡
ይህ የሚያሳየን ምንድን ነው?... በቅሎ ፈረስ አጐቴ ነው ያለችው በንጉስ አባቷ በአህያ አፍራ ሳይሆን ችግረኛውን ፈረስ ሰበብ አድርጋ እድሉን ለማግኘት ስትል ብቻ ነው፡፡
ምሳሌያዊ አነጋገሩ ከምን እንደመነጨ ያልገባቸው ሰዎች ግን የአህያን ማንነት አዛብተው ሲገልፁበት እንመለከታለን፡፡
***
...ለባነር እና ለስቲከር ዝግጅት... 8ሺህ 300 ብር፡፡
***
...ይሄም በጥንት ጊዜ የሆነ ነገር ነው... በዚያን ጊዜ ለእንስሳት ሹመት የሚሰጠው ስጋቸው እየተመረመረ ነበር፡፡ ሁሉም እንስሳ ከአካላቱ የተወሰነ ስጋ እየቆረጠ ለምርመራ ይልክና በውጤቱ መሰረት የሚገባውን ሹመት ያገኛል፡፡ መርማሪው አያ ጅቦ ሲሆን፣ ለስጋ ካለው ፍቅር አንፃር የእያንዳንዱን እንስሳ ስጋ በማነጋገር ችሎታው የስጋውን የቋንቋ ክህሎት ለማግሀነት ስጋውን ቆርጦ ወደ አያ ጅቦ ላከ፡፡
አያ ጅቦ ስጋዎችን ተራ በተራ እየጠየቀ የቋንቋ ችሎታቸውን ሲመዝን ዋለ፡፡ አያ ጅቦ አንድ ቃል ሲጠራ ስጋውም በተራው አያ ጅቦ ከጠራው ቃል ጋር እኩል የፊደላት ቁጥር ያለው ቃል ከጠራ ፈተናውን አልፏል ማለት ነው፡፡
..ፍርምባ.. አለ አያ ጅቦ፡፡
..ጥሬ.. አለ የዶሮ ስጋ፡፡ ፈተናውን wdq
..ሻኛ.. አለ አያ ጅቦ፡፡
..ቅጠል.. አለ yqn¤ ስጋ፡፡ ፈተናውን አለፈ፡፡
የአህያ ስጋ አልጋ ሲሉት አመድ በማለት በመስፈርቱ መሰረት አሸናፊ ሆኖ ብርቱ ሰራተኛ የሚለው ሹመት ለአህያ ተሰጠ፡፡
ውድ የአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች፣
በውድድር አልፎ ለተሻለ ስፍራ የበቃው አህያ ነው፡፡ እንግዲህ በተጣመመ ምሳሌያዊ አነጋገር ክብር የማይወድለት እንስሳ ተደርጐ የሚጠቀሰው...
***
...ለጥናት የሚሆኑ መረጃዎችን ለማሰባሰብ... 9ሺህ 500 ብር፡፡
***
...በአንድ የጥንት ዘመን ደግሞ አንበሳ ንጉስነቱን መከታ በማድረግ በሌሎች እንስሳት ላይ ግፍ መስራት ጀመረ፡፡ በባለ ትዳር እንስሳት መካከል ጣልቃ በመግባት ትዳር ከማፋረስ አልፎ በጉልበት ሚስትየዋን በመቀማት ዝሙት መፈፀም ያዘ፡፡ በዚህም አላበቃም... ከባሏ ነጥቆ ዝሙት የፈፀመባትን ሴት ጅብ ተብሎ ከሚጠራ አፋፍ ቁልቁል በመወርወርና በመጣል መግደል ጀመረ፡፡ እነ ቀበሮ፣ እነ ከርከሮ፣ እነ ተኩላ... ሌሎችም ከአንበሳ ጋር በመፋለም፣ ሚስታቸውን ከመደፈርና ከጅብ አፋፍ ተጥላ ከመሞት ለማትረፍ ያልቻሉ ፈሪ እንስሳት ሁሉ ሚስቶቻቸውን ተነጥቀው ዝም አሉ፡፡
አቶ አንበሳ አንድ ቀን የአህያን ሚስት ለመቀማትና የለመደውን ፈሞ ከጅብ አፋፍ ጥሎ ለመግደል አሰበ፡፡ አስቦም አልቀረም፡፡ ከባሏ ጋር ገበያ ውላ ስትመለስ ጠብቆ ጐተት አደረጋት፡፡ ይሄን ጊዜ በሚስቱ ቀልድ የማያውቀው አህያ ..እኔን ገድለህ ካልሆነ ሚስቴን አትቀማም.. ብሎ ከአንበሳ ጋር ጦርነት ጀመረ፡፡ እንደምንም ብሎም ሚስቱን ከመደፈርና ከጅብ አፋፍ ከመጣል አተረፈ፡፡ ይሄን ጊዜ ነው እንግዲህ... በነገሩ የተደነቁ ነገር አዋቂ አጋዘን የአህያን ባል ጀግንነት ለመግለ ..እሱማ እንደሌላው ባል ሚስቱን ከጅብ አፋፍ አያስጥልም.. ያሉት፡፡
..የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም.. የሚለው ምሳሌያዊ አነጋገር የመጣው ከዚህ ጋር በተያያዘ ነው...
...አሁን ጊዜው ተሰብሳቢዎች ለሻይ እረፍት የሚወጡበት ስለሆነ እዚህ ላይ ላብቃና ስንመለስ እቀጥላለሁ... ማስታወቂያ አለ፡፡
...ከክልሎች ተወክላችሁ የመጣችሁ ተሳታፊዎች የትራንስፖርት ደረሰኝ ወይም ነዳጅ የቀዳችሁበትን ሪሲት በማቅረብ ገንዘባችሁን መውሰድ ትችላላችሁ፡፡
...አህያም መብት አላት በሚለው የግጥም ውድድር ከአንደኛ እስከ አስረኛ የወጣችሁ ተወዳዳሪዎችም ከሻይ እረፍት መልስ የሽልማት አሰጣጥ ስነስርዓት ስለሚኖር ተዘጋጁ፡፡
...ቲ-ሸርትና ቆብ ያላገኛችሁ እንዲሁም ተጨማሪ የምትፈልጉ ተሳታፊዎች ከአቶ መከተ መቀበል ትችላላችሁ፡፡
አመሰግናለሁ፡፡

 

Read 7738 times Last modified on Saturday, 13 August 2011 09:39