Saturday, 13 August 2011 09:39

የኖህና የሳባ ተረት

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ alemayehugelagay@yahoo.com
Rate this item
(7 votes)
  • ከወገብ በላይ ጣዖት፣ ከወገብ በታች ታቦት

ተረታችን ታሪካችንን ተጭኖት በዕውነት ሳይሆን በህልም መሰል መማለል ውስጥ የምንኖር ሕዝቦች ከሆንን ቆይተናል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ወደ ንቃት ከማምራት ይልቅ የበለጠ እንዲጫጫነን በሚያደርጉ የተረት እሹሩሩዎች እየተባበልን እንገኛለን፡፡ ከታሪክ ሊቃውንት ይልቅ ..የተረት አባቶች.. በገነኑባት በዚች አገር መግባባታችን በአፈ ታሪክ ተወርሮ የኋላ ምስላችን እንደ ልጆች ትረካ ከሳይንሳዊው ዓለም የማይደባለቅ አስቂኝ ቀልድ ሆኗል፡፡

ሰሞኑን ..የኢትዮጵያ የ5ሺህ ዓመት ታሪክ - ከኖህ እስከ ኢህአዴግ.. የሚል መጽሐፍ በፍስሐ ያዜ ካሳ ተጽፎ ገበያ ላይ ውሏል፡፡ መጽሐፉ በ456 ገፆች ዳጎስ ያለ ቢሆንም የተነሳበት ዓላማ በቁምጥ ስለቀረበት ገና ክፍል ሁለት እንደሚታተም አስታውቋል፡፡ ከታሪክ ጋር መጠነኛ ትውውቅ ያለው ሰው ገና የመጽሐፉን ርዕስ በማየት ብቻ የተምታታ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገባ ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቱም በሳይንሳዊ ጥናት የኢትዮጵያን ታሪክ (ከክርስቶስ ልደት በፊት) ከ200 ዓመታት አሳልፎ መመልከት ስላልተጀመረ ነው፡፡ ..ቅድመ አክሱም ዘመነ መንግሥት.. በሚባል የሚታወቀው ያ ወቅት የታሪክ ምንጩ አነስተኛ እንደሆነ በተደመደመበት በዚህ ጊዜ 2ሺህ 800 ዓመታት ወደዚያ አስፈንጥሮ የሚጥል ምን መረጃ ተገኘ ብሎ መጠየቅ የግድ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኖህን ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ምን እንደሚያገናኘው መገመት እጅግ አዳጋች ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የሚያዳግተን ሁኔታውን ከሳይንሳዊው ታሪክ አንፃር ካየነው ብቻ ነው፡፡
ታሪክ የራሱ የሆነ የምርምር ዘዴ ያለው ሳይንስ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የታሪክ እሳቤ ፈልሳፊ የነበረው ሔሮዱቱስ ..ኢስቶሪ.. ሲል የሰየመው (በእንግሊዝኛ ሒስትሪ) በግሪክ ..ምርምር.. የሚል ፍቺ አለው፡፡ ያልተመረመሩ ትውፊቶችን ሆነ ተረቶችን ታሪክ ውስጥ ማካተት (ወይም ታሪክ ብሎ ማቅረብ) የዘርፉ የመጨረሻ ነውር ተደርጐ ይቆጠራል፡፡ የታሪክ ዋነኛ ግብ ማዝናናት ወይም ሥነ ምግባራዊ ትምህርት መስጠት ሳይሆን እውነትን ፈልጐ ማግኘት ነውና በተቻለ መጠን ከተረትና ከትውፊት ቢዳ ይመረጣል፡፡ በግልጽ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ታሪክ ሳይንሳዊ ይዘት ሊኖረውና የምርምር መልክ ሊላበስ የሚችለው ወደ ኋላ በማፈግፈጉ ሳይሆን ወደ ፊት በመቅረቡ ነው፡፡ በቅድመ አክሱም ጭል-ጭል ይል የነበረው የታሪክ ምንጫችን እየጐላና እየተጠናከረ የሚመጣው በሰለሞናዊው ዘመን (1270-1527) በኩል አድርጐ በጐንደር ምስረታና በጐንደር መሳፍንት ዘመን (1527-1855) አልፎ ወደዚህኛው አስተዳደር እየቀረቡ የተመጣ እንደሆን ብቻ ነው፡፡ እንደ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፣ ፕሮፌሰር ታምራት ታደሰ፣ ፕሮፌሰር መርእድ ወልደአረጋይና ፕሮፌሰር ሁሴን አህመድ ያሉ የታሪክ ሊቃውንት በምርመራቸው ወደ ኋላ ብዙ እርቀው የማይጓዙት የቅርብ ታሪካችንን ያህል የጥንቱ ታሪክ አስተማማኝነት ስለሌለው ነው፡፡ እንደ አባ ጋስፓረኒ፣ መላኩ በጎሰው፣ በላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ፣ ያሬድ ግርማ እና ተክለ ፃድቅ መኩሪያ ያሉት ፀሐፊዎች በታሪክ ሊቃውንት እንደ ..ተረት አባት.. የሚቆጠሩት ወደ ኋላ ዘመን እርቀው በመሄዳቸውና ያልተመረመረ ተረትና አፈ ታሪክ በማብዛታቸው ነው፡፡
..የኢትዮጵያ የ5ሺ ዓመት ታሪክ ከኖህ እስከ ኢህአዴግ.. ደራሲ ፍስሐ ያዜ ልቦናውን እምነቱንና ምርምሩን በሁለተኞቹ ፀሐፊያን (..የተረት አባቶች..) ላይ በመጣሉ ከእነሱ እጣ-ፈንታ ፈቅ ብሎ ለሳይንሳዊው ታሪክ ተጠቃሽ ሊሆን የሚችል መጽሐፍ ለማቅረብ ሳይታደል ቀርቷል፡፡ በተለይ የመጽሐፉ 26 ምዕራፎች ላይ ፀሐፊው ለተድበሰበሱ ተረቶች፣ ለተጭለመለሙ አፈ ታሪኮችና ዓይን ላወጡ ትውፊቶች ቀልቡን በመስጠቱ የጥንቶቹን የኢትዮጵያ ..ታሪክ.. ፀሐፊዎች ስህተት ለመድገም ተገድዷል፡፡
የፍስሃ ያዜ ..የታሪክ.. መጽሐፍ የመጀመሪያ ስህተት የሚመስለኝ በታሪክ ህልውናው ያልተረጋገጠውን ኖህን መነሻ ማድረጉ ነው፡፡ ..ከጥፋት ውኃ በኋላ የኖህ መርከብ በጣናው አራራት ተራራ አረፈችና ቤተሰቡ ጥቂት ዘመን ቆይቶ ሴምና ያፌት ከኢትዮጵያ ተነስተው ወደ እስያና አውሮፓ ሄደው (ኖኅና) ካም እዚሁ (ቀሩ).. የሚለውን የፍስሃ ያዜ ..የምርምር.. መዳረሻ ትተን በመጀመሪያ የኖህን ህልውና እንፈትሽ፡፡ ለመሆኑ ኖህ የተሰኘ ሰው በዚች ምድር ላይ ነበር?
የዘፍጥረቱ ኖህ በህይወት የነበረ ሰው ነው ብሎ ለመከራከር የሚያስችለው ብቸኛው መረጃ (መረጃ ከተባለ) በብሉይ ኪዳኑ ውስጥ የተካተተው ታሪኩ ብቻ ነው፡፡ ከዕምነት ባሻገር የኖህን ህልውና በሳይንስ ለማረጋገጥ የተሞከረው የከርሰ ምድር ጥናት (archeology) ሁሉ መደገፊያ የእውነት ቅስት እያጣ አልቆም ብሎ በመውሸልሸል አስቸግሯል፡፡ ከጥፋት ውኃ በኋላ ከጥንቷ ኡራርቱ (የአሁኗ አርሜኒያ) ውስጥ በአራራት ተራራ ላይ አረፈ የተባለው መርከቡ፣ ስብርባሪው እንደተገኘ ቢነገርም ትክክለኛ የኖህ መርከብ ስለመሆኑ በምርምር ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ ለምሳሌ በ1955 ዓ.ም. ፈረንሳዊው ፌርናንድ ናቫራ 5ሺህ ዓመት የሞላቸው ሦስት የመርከብ ስባሪ እንጨቶችን ተራራ ጫፍ ላይ በበረዶ ተሸፍኖ ቢያገኝም ሳይንስ የኖህ ስለመሆኑ ማረጋገጫ አጥሮት እስካሁን ነገሩ በእንጥልጥል ይገኛል፡፡
በተቃራኒው ደግሞ ኖህ የሚባል ሰው በህይወት አልነበረም፤ ታሪኩም ሀሰተኛና የአፈ ታሪክ ቅጂ ነው ለማለት የሚያስችሉ አንዳንድ የከርሰ ምድር ጥናት ውጤቶች እየተገኙ ነው፡፡ ከእነዚህ ሳይንሳዊ ግኝቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የባቢሎናውያኑ የንጉስ ጊልጋሜሽ አፈ ታሪክን የድንጋይ ላይ ጽሑፍ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን በእንግሊዛውያኑ የከርሰ ምድር ተመራማሪዎች ጢግሪስ ውስጥ የተገኘው ይሄ የጊልጋሜሽ አፈ-ታሪክ በጀብዱ ግጥሞቹ ውስጥ የኖኅን ታሪክ ምንጭ ይዞ መገኘቱ ምሁራኑን አስደምሟል፡፡ 4000 ዘመን ዕድሜ ያለው ይሄ የግጥም ትረካ ፍፁም ከኖኅ ጋር አንድ የሆነ ታሪክ ያለውን ሰው ኡትናፒሽቲም (utnapishtim) ይለዋል፡፡ ይሄ ሰው ከጥፋት ውኃ በኋላ የዘላለማዊነትን ምስጢር አማልክቶች ስለነገሩት ነበር ንጉሱ ጊልጋሜሽ ሞትን በመፍራት ወደሱ የሚሄደው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ኡትናፒሽትም ስለጥፋት ውኃ ገጠመኙ ይናገራል፡፡ አማልክቶቹ በሰው ልጅ ክፋትና ጥፋት ተበሳጭተው አለምን በውኃ ሙላት ለማጥለቅለቅ ይወስናሉ፡፡ ነገር ግን አማልክቱ ኢአን (Ea) ከልቡ በማገልገል የሚታወቀው ፃድቁ ኡትናፒሽቲም መካከላቸው አለ፡፡ ስለዚህ ኢአ የኖኅን አምላክ ትዕዛዝ በመሰለ (በሆነ) አገባብ እንዲህ ሲል ኡትናፒሽቲምን ያዘዋል፡፡..ኦ አንተ የሹሩፓክ ሰው፣ የኡባርቱቱ ልጅ ሆይ፤ ስለቤትህ እንባህን አፍስስ፤ መርከብንም አን፤ ከህይወት በኋላ ስላለው ነገር እንጂ የሐብትህን ነገር ከጭንቅላትህ አውጣ፡፡ የንብረትህን ጉዳይ ንቀህ ተውው፤ ህይወትህን ብቻ አትርፍ፡፡ ከምድር ፍሬም ሆነ ህይወት ካለው በሙሉ አንድም ሳታስቀር ዘሮቹን ወደ መርከብህ አስገባ፡፡ መርከቢቱን እንደምን አድርገህ እንደምታንጽ ምክርን ከኛ ¬g¾lH””..ኖኅ በፈጣሪው እንደታዘዘ ሁሉ አትናፒሽቲም እንደዚያ ያደርጋል፡፡ ከጥፋት ውሃም ተርፎ የኖኅ መርከብ አራራት ተራራ ላይ እንዳረፈች yኡትናፒሽትም ኒሲር (Nisir) ተራራ ላይ ትቆማለች፡፡ የኡትናፒሽቲምን ትርክት እንዳለ ማቅረብ የኖኅን ታሪክ መድገም ነው፡፡ ታሪኩ ብቻ ሳይሆን ገለጻውና የመርከቡ መዋቅር አቻ ለአቻ የሚቆምና የሚገናዘብ ተመሳሳይ መሆኑ ተመራማሪዎቹን አስደምሟል፡፡ ከማስደመም አልፎ የዘፍጥረቱ ኖኅ ከዚህ ጥንታዊ የጀብዱ ግጥም በፀሐፊው በሙሴ የተቀዳ እንጂ በህይወት ያልኖረ ሰው እንደሆነ ጥርጣሬ አሳድሯል፡፡ ምክንያቱም የጊልጋሜሽ የጀብዱ ግጥም ሙሴ የኖኅን ታሪክ ከመጻፉ ቢያንስ በአንድ ሺህ ዓመት ስለሚቀድም ነው፡፡ የጊልጋሜሽ ታሪክ ሳቢነትና ማራኪነት ያለው የጥበብ ሥራ በመሆኑ አብዛኞቹ ጥንታውያን ህዝቦች ወደራሳቸው ቋንቋ መልሰውትና በድንጋይ ላይ አስቀርውት ተገኝቷል፡፡ ሒቲትያኖች (Hittites) እና ግብጻውያኖች የጊልጋሜሽን አፈ-ታሪክ ቀድተው ከያዙት ህዝቦች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እንደነዚሁ ሁሉ እስራኤላውያንም በሙሴ በኩል የጊልጋሜሽን አፈ-ታሪክ የራሳቸው ለማድረጋቸው እንደጣሩ የብሉይ ኪዳኑ የኖኅ ታሪክ ዋነኛ ማስረጃ ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ከረፈደ ተነስተን የጊልጋሜሽን አፈ ታሪክ በኖኅ በኩል አጠላልፈን የራሳችን ለማድረግ በመጣጣር ላይ እንዳለን የፍስሃ ያዜ መጽሐፍ ማሳያ ነው፡፡ መጽሐፉ ኖኅ አርሜኒያ ሳይሆን ጣና ውስጥ ያለው አራራት ተራራ ላይ መርከቡን እንዳሳረፈ ለማሳመን ብዙ ይደክማል፡፡ ከዚያም ኖኅና ቤተሰቦቹ ጎንደር ጭልጋ ውስጥ እንደነበሩና የኖኅ ባለቤት ..እሜቴ አይከል.. የሞቱበት የጭልጋ ከተማ አሁን ድረስ በስማቸው እንደተሰየመ ያብራራል፡፡ ..ኖኅ ከዚያ ወዲህ ለ350 ዓመታት ቤተሰቡን ሲመራ በተመሳሳይ አገላለጽ ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር ኖሮ ሲሞትም ልጁ ካም ተተክቶ ቤተሰቡንና አገሩን መምራት፣ መግዛት ቀጠለ፡፡..
የዚህ ሁሉ አዙሪታም ተረት ፋይዳው ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ ኃይማኖት ርዕዮተ-ዓለም በነበረበት በጥንቱ ዘመን ቢሆን የህዝባችንና የታሪካችንን እንዲሁም የሥልጣኔያችንን ምንጭ ከእስራኤላውያን ጋር በመቋጠር በአለም ፊት የተለየ ግምትና ትኩረት ለማግኘት ነው ይባል ነበር፡፡ አሁን ግን የዓለም ርዕዮተ ዓለም ኢኮኖሚ ከሆነ ሰነባብቷልና ይሄ ሁሉ የተረት ጥምጥም ለቅስና እንደማያበቃን መገመት ደግ ነበር፡፡
የፍስሐ ያዜ መጽሐፍ በተረት አሳብሮ እኛን ከእስራኤላውያን የዘር ሐረግ ጋር ለማገናኘት የሚጥረው በኖኅ በኩል ብቻ አይደለም፡፡ የንግሥተ ሳባን የሰሎሞን ጉብኝት አፈ ታሪክ እንደ ታሪክ ቆጥሮ ለማጥራትና ለማሳመን ብዙ ይደክማል፡፡ በዚህም የሐፊው ልፋትና ውጤት ለሳይንሳዊው ታሪክ እርባና የሌለው ከተረት ወገን የሚመደብ እንዲሆን አድርጐታል፡፡ ንግሥተ ሳባ (ማክዳ) የኢትዮጵያ የጥንት ሐፊዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ጋራ ዘራችንንና አስተዳደራችንን ለማዛመድ ሲሉ የፈጠሯት ተረት ነች፡፡ የታሪክ ሊቁ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት ..ተረትና ታሪክ በኢትዮጵያ.. የሚል ጥናታቸው ላይ ይሄንኑ ጉዳይ ይጠቅሱታል፡፡
..ይህ የኢትዮጵያን ሕዝብ ታሪክ ከመጽሐፍ ቅዱስና ከእስራኤል ጋር የማያያዝ ነገር ተጨባጭ የታሪክ ማስረጃ የለውም፡፡ እንዲያውም ያሉት አስተማማኝ የታሪክ ቅሪቶች በቀጥታ ይቃወሙታል፡፡ ቀዳማዊ ምኒልክና ጓደኞቹ የእስራኤል ወጣቶች ከኢየሩሳሌም ታቦት ሰርቀው አክሱም ከተማ ቤተ መቅደስ አኖሩት በሚባልበት ጊዜ አክሱም ገና አልተቆረቆረችም፡፡ የአክሱም ከተማና የታሪክ ዘመን የሚጀምረው የቀዳማዊ ምኒልክ አባት ነው ከሚባለው ከንጉሥ ሰሎሞን 800 ዓመት ያህል ቆይቶ ነው፡፡..ይሄንን የንግሥተ ሳባ የተረት ሰርጎ-ገብነት የሚቃወሙ ብዙ ምሁራን ብዙ ብለዋል፡፡ ፕሮፌሰር ታምራት አማኑኤል ..ስለ ኢትዮጵያ ደራሲያን.. የሚል መጣጥፋቸው ላይ የንግሥተ ሳባን፣ የንጉሥ ሰሎሞንን ግንኙነት እንዲሁም የቀዳማዊ ምኒልክን መወለድና መንገስ ..አፈ ታሪክ.. ይሉታል፡፡ ..ይህን አፈ ታሪክ የሚነግሩን መጻሕፍት ባገራችን መጻፍ የጀመሩት ከሺህ 300ኛው ዓመተ ምህረት ወዲህ ነው፡፡ ...የመጽሐፍ ቅዱስ አሳብ (ኢትዮጵያዊውን) በአሕዛብነት የነበረበትን ዘመን እንዲጠየፈው የሕዝበ እስራኤልን መጻሕፍትና ሀሳብ እንዲወድ አድርጐት ስለነበር ጥቂት በጥቂት የገዛ ታሪኩን እየዘነጋ የእስራኤል ልጅ ነኝ ከማለትና የእስራኤል ሕዝብ የጻፉዋቸውን መጻሕፍት አያቶቼ የጻፉዋቸው ናቸው ከማለት ደርሰዋል፡፡..
የንግሥተ ሳባ ተረት እንደ ታሪክ መቅረቡ ማንነትን የሚያናጋ የህልውና ማዕበል እንደሆነ በመጠቆም የጻፉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ብላቴን ጌታ ህሩይ ወልደሥላሴና አለቃ አሜ ሳይቀሩ በግልጽ አውግዘውታል፡፡ ..ያዳቆነ ሴጣን. . ... ሆኖብን ዘንድሮም ጨርሶ ለመጣል ሲያሳሳን እዚህ ደርሰናል፡፡ የፍስሃ ያዜ መጽሐፍም ይሄን በሐሰት ያብረቀረቀ ተረት እንደ ከበረ ድንጋይ ተንከባክቦ ልዩ ቦታ ላይ ያስቀምጠዋል፡፡ የተረቱ ህልውና የሆኑትን ተአምሮች በማራገፍ ንግሥተ ሳባ ከዘንዶ ወገን መወለዷን፣ እግሯ የአህያ ሽሆና መሆኑንና ንጉሥ ሰለሞንን ልትጠይቅ ወደ ቤተ መንግሥቱ ስትገባ ሽሆናዋ መርገፉን ከትርክቱ ውስጥ በመንቀስ ተረቱን ለእውነት የቀረበ ታሪክ ለማስመሰል ፀሐፊው ይተጋሉ፡፡ ከንግሥተ ሳባ የሚነሳውን የነገሥታት ፉርጐ 68 በማድረስ ከቅድመ ክርስቶስ 1013 እስከ 1 ዓ.ም. ይጓዛሉ፡፡ የፀሐፊው ጉዞ አታካች ቢሆንም ..በድል.. መወጣታቸውን እንደመምበታለን፡፡ የተረት ክምር ለታሪክ ቋት ጠብ የሚል ነገር ባይተርፈውም ፍስሃ ያዜ ተስፋ ሳይቆርጡ እና ሳይዝሉ ባቡሩን ያስቀጥላሉ””..የኢትዮጵያ የ5ሺህ ዓመት ታሪክ ከኖኅ እስከ ኢህአዴግ.. መጽሐፍ ትርክቱ እንደ ንጋት ጀንበር የተረቱን ልመት እየገፈፈና እየጠራ የመሄድ ባህርይ አለው፡፡ በተለይ ንጉሥ ኢዛናና ሲዛና (አብርሃ ወ አብሃ) ዘመን ላይ ሲደርስ የታሪክ ፀሐይ ሙሉ በሙሉ ትወጣለች፡፡ እውነታን የማስጨበጡ ጥረት በከርሰ ምድር ጥናት ግኝቶች እየተደገፈ ፍሰቱን አሳምሮ ይጓዛል፡፡ ከመጽሐፉ አነሳስ ይልቅ የመሐፉ አጨራረስ አስር እጅ ለሳይንሳዊው የታሪክ ምርምር የቀረበ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በዚህም መጽሐፉን ..ከወገብ በላይ ጣዖት ከወገብ በታች ታቦት.. እንደሚባለው በሁለት አፈጣጠሩ ለመዳኘት እንገደዳለን””የፍስሃ ያዜ የታሪክ አጻጻፍና ትርክት በስሜት የተሞላ፣ ወገንተኝነት የሚንባረቅበትና በእልህ የተነሱ መሆኑ በሚያስታውቅ ዓይነት ነው፡፡ እንደውም አንዳንድ ጊዜ እንደ ታሪክ ፀሐፊ ሳይሆን እንደ መድረክ መሪ ..አጨብጭቡ.. ማለት ይቃጣቸዋል፡፡ ..በ.. . ጣም በፈገግታ እንደደመቃችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ምርጥ አተራረክ ነው በእውነት.. (ገጽ 58) ይላሉ፡፡ ከዚያም አልፈው አንዳንዴ በውጭዎቹ ታሪክ ፀሐፊዎች ላይ ፉከራ ያስደምጣሉ፡፡ ..አሯል ሆዴ ጨሷል ሆዴ ቢቸግረኝ እንጂ ጠላቴን መውደዴ! አለ ያገሬ ሰው ዘራፍ! አትልም!.. (ገጽ 78) ለታሪክ ተመራማሪ ሐሰትን በእውነት ገስሶ ማቅረብ እንጂ እንደጦረኛ ለማሸነፍ መነሳት ባህሪው አይደለም፡፡ ብዕሩም በጭለማው ዘመን ላይ ብርሃን የምትተፋ ባትሪ እንጂ ለመውጋት የምትሰደር ጦር አይደለችም፡፡ ፍስሃ ያዜ ከቀጣዩ መጽሐፋቸው ላይ ውግዘት፣ ፉከራ፣ ማስጨብጨብና ማዳመቅ የተቀላቀለበት አጻጻፋቸውን ሊያርሙት ይገባል፡፡ ..እንኮፈሳለን..፣ ..አድቀን እንለፍ በሙሉ ድምጽ፡፡ ግልጽ ነዋ!..፣ ..ብለን በመጠየቅ አንገት እናስደፋለን..፣ ..ፈገግም ያሰኛል..፣ ..ልክ ነን..... የሚሉ የተመራማሪ ያልሆኑ ቃላቶችም ሊያራግፉ ግድ ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን የፀሐፊውን ፍስሃ ያዜ ትጋትና ውጤት ሳናደንቅ ማለፍ ንፉግ ያሰኘናልና - ይኸው!!

 

Read 9611 times Last modified on Saturday, 13 August 2011 09:46