Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 13 August 2011 11:01

ይርጋ ዱባለ በጐንደር ይዘከራል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በኢትዮጵያ፣ በእስራኤልና በአሜሪካ የሚኖሩ አድናቂዎቹና ወዳጆቹ ድምፃዊ ይርጋ ዱባለን የሚዘክር ኪነጥበባዊ ዝግጅት በጐንደር ከተማ ሊያቀርቡ ነው፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት በከተማይቱ በሚቀርበው ዝግጅት የአርቲስቱ መገልገያ ቁሳቁሶች በአዲሱ ራስ ሚካኤል ስሁል ቤተመዘክር የሚቀርቡ ሲሆን ለዚህም የይርጋ ቤተሰቦች እና የጐንደር ከተማ ባህልና ቱሪዝም ህፈት ቤት ፈቃደኛ እንደሆኑ ታውቋል፡፡ በተጨማሪም ዘንድሮ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየውን ከያኒ አስመልክቶ ጥናታዊ ሁፍ፣ የፓናል ውይይትና የቅኔ ውድድር ይካሄዳል፡፡ ድምፃዊው በህይወት ሳለ የከተማዋ የደን መመናመን አሳስቦት ያቀነቀነውን ..ጐንደር እሹሩሩ.. የተሰኘ ዜማን ምክንያት በማድረግ የችግኝ ተከላ ይኖራል ተብሏል፡፡

ሀገሬ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን እና እቴጌ ምንትዋብ አርት ፕሮሞሽን የሚያስተባብሩትን ዝክረ ይርጋን አስመልክቶ የሀገሬ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሄኖክ ስዩም ..ከያንያን አዝማሪ በሚባሉበት ዘመን መስዋእትነት ከፍለው የሀገሪቱን ማህበረሰብ ሙዚቃ በማሳደጋቸው ሀገራዊ አስተዋኦዋቸውን በማሰብ ዝግጅቱ ቀርቧል.. ካሉ በኋላ የአርቲስቱ አልባሳትና ቁሳቁስ በቋሚነት ቤተመዘክር ከፍቶ ለማስቀመጥ እንደታሰበ ጠቁመዋል፡፡
ከአርቲስት ባህሩ ቃኜ እና አርቲስት ራሄል ዮሐንስ ጋር ባቀነቀነው ..የሰው የለው ሞኝ.. በሚለው ዘፈኑ የሚታወቀው አርቲስት ይርጋ ዱባለ በኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ወቅት ባወጣው ..የፍየል ወጠጤ.. የተሰኘ ዘፈኑ ይታወቃል፡፡
ከዚህም ሌላ በፕሮፌሰር ሃይሌ ገሪማ መመረቂያ ፊልም ..3ሺህ ምርጦች..፣ እና ..ሻፍት ኢን አፍሪካ.. ፊልሞች በተዋናይነት ተሳትፏል፡፡
የድምፃዊው ቀብር ..አርበኛ እንጂ ሙዚቀኛ አይደሉም በጀግና ሥርዓት ይቀበሩ.. በሚል ውዝግብ ፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡

 

Read 6771 times Last modified on Saturday, 13 August 2011 11:03