Saturday, 13 August 2011 11:22

ሰው፣ ስም፣ ሰላምታእና ማህበራዊ ኑሮ

Written by  ስብሃት ገ/ እግዚያብሔር.
Rate this item
(1 Vote)

.....እግዚአብሔር አምላክም የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ሁሉ ከመሬት አደረገ፤ በምን ስም እንደሚጠራቸው ያይ ዘንድ ወደ አዳም አመጣቸው፤ አዳምም ህያው ነፍስ ላለው ሁሉ በስሙ እንደ ጠራው ስሙ ያው ሆነ..
(ኦሪት ዘፍጥረት፤ ምእራፍ ሁለት፣ ቁጥር አስራ ዘጠኝ)
አንድ
የተከበራችሁ አንባብያን
ሰው ገና ሲወለድ ቀዳሚው ጥያቄ ..ወንድ ነው ሴት?.. ነው፡፡ (..አፍንጫው ልክ የሴት አያቱን..፣ ..ቅንድቡ መገናኘቱ ቁርጥ አጎቱን.. ወዘተ ይባላል በጎን በቅንፍ)
ከፆታው የሚቀጥለው ጥያቄ ..ስሙ ማን ይሁን?.. ነው፣ ብዙ ያወያያል (አመል ያለባቸውንም ያጨቃጭቃል) እኛ ለጊዜው ማህበረሰቦች የጂኦግራፊ አቀማመጣቸውንና የመልክ የባህላቸውን ያህል ስም ሲያወጡም ያንኑ ያህል እንደሚለያዩ እያየን እንዝናና፤ ካጋጠመንም እንደነቅ!

ከክሪስቶፈር ኮለምበስ በፊት አዲሱ ዓለም ውስጥ ይኖሩ የነበሩት Red Indians የወንድ ስም Sitting Bull, Red Cloud, Eagle Eye, Gallopping Stallion.  የሴት ስም Fleeing Antelope, Graceful Deer, White Dove.
Tibet አገር ከተወለድክ ስምህ የተወለድክበት ቀን ስም ነው፡፡ ለምሳሌ Tuesday Lobsang Rampa የሚባሉት ሰው የተወለዱት ማክሰኞ እለት ነው፡፡
ሰው ብቻም አይደለም ስም ያለው፡፡ የቤት እንስሳታችን ሁሉ የተውኦ ስም አላቸው፡፡ ታላላቅ የጦር ጀግኖቻችን የፈረስ ስማቸው የታወቀ ነው - ምኒልክ አባ ዳኘው፣ መኰንን አባ ቃኘው፣ ኃይለሥላሴ አባ ጠቅል፣ የአፄ ዮሐንስ አባት ..አባ ፈንቅል.. እያለ ይሄዳል፡፡
ከልጅነታችን ጀምሮ ስለለመድነው ከምንም አንቆጥረውም እንጂ እንዲህ ብለን ..በአርምሞ.. እናስብ እስቲ ..ስም.. የሚባል ነገር ባይኖር ኖሮ፣ አብረን የመኖሩ ጉዳይ ምን ይውጠው ነበር?
ሁለት
..እግዚአብሔር ሰጠ፤ እግዚአብሔር ነሳ፤ yእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን፡፡.. (መጽሐፈ ኢዮብ)
እኛ ባለንበት ስማችንን ሲጠሩ አቤት እንላለን (ወይም እንገላመጣለን)፡፡ ሌላ የሚገርም ነገር አለ፤ ይኸውም እኛ በሌለንበት ስማችን የራሱ ምትሀት ወይም ተአምር አለው፡፡ ለምሳሌ ያህል የሚከተሉትን ነጥቦች እንመልከት፡-
..የልጆች ጊዜ.. የሚባለው የአባባ ተስፋዬ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ውስጥ፣ ልጆቹ አድገው ሀኪም ወይም ፓይለት ወይም ሌላ የሚመኙትን ከሆኑ በኋላ ምን እንደሚሠሩ ሲጠይቁ፤ ..ወላጆቼን እረዳለሁ.. ካሉ በኋላ ..ሌላስ?.. ሲሏቸው፣ ..ያገሬን ስም አስጠራለሁ.. ይሆናል መልሳቸው፡፡
እንግዲህ እቺ አገር ስምዋ መጠራቱ ምን ይጠቅማታል? እንዲያውስ ስሟን የሚጠራ ማን ወይም እነማን ናቸው? ለአገሪቱስ ምን ልዩነት ያመጣል? ለነሱስ?
የስማቸው መጠራት ልዩ እሴት እንዳለው የሚቆጥሩ ሰዎች አሉ፡፡ አንድ ሰውዬ እንዲህ ሲሉ ትዝ ይለኛል ..የቁልቢው ገብርኤል ስሜን የሚያስጠራ ልጅ እንዲሰጠኝ ለዓመቱ በእግር ከድሬዳዋ እስከ ቁሉቢ እየሄድኩ እንደተሳልኩ ነው፡፡ ከፈለገ ለምን የመጨረሻ ከሀዲ ከይሲ ጨካኝ አረመኔ አይሆንም!? ብቻ ስሜን ያስጠራልኝ!..
ስም ማጥፋት ምንድነው? ..ለመሆኑ ስም ይጠፋል እንዴ? ከጠፋስ የት ይሄዳል?.. የስም ማጉደፍ ዘመቻ ማካሄድ ምን ማለት ነው? ሀሜትና ይሉኝታ ባህል በሆነበት አገር ይህ ጉዳይ ከባድ ሳይሆን ይቀራል ወይ?
እዚህ ባህል ውስጥ ይሉኝታ የህሊናን ሚና ይጫወታል ቢባል ምን ያህል እውነት ይሆን?
ሦስት
ስም ባይኖረን ኖሮ፣ በማህበረሰብ መኖር ምንኛ ባስቸገረን ነበር!? እንዲሁም ከናታችን ቋንቋ ጋር ሰላምታን ያስተምሩናል፡፡ ..እማማን ሳማቸው! አባባን ሳሚያቸው!.. እየተባልን፣ ሲስሙን ከነንፍጣችን መልሰን እንስማቸዋለን፤ ስንፈራ ስንቸር፡፡
ሰላምታ ባይኖር ኖሮ ከሰው ጋር ስንገናኝ እንዴት እንጀምር ነበር? የምናውቀው ሰው ከሆነስ እንደምንም እናድበሰብሰዋለን እንበል፡፡ ከማናውቀው ሰው ጋር ስንገናኝስ? ቆመን መፋጠጥ? ንግግሩን ማናችን ይጀምር? ምንስ ብሎ ይጀምር? ..ላም እሳት ወለደች፡፡ እንዳትልሰው እሳት ሆነባት፣ እንዳትተወው ልጇ ሆነባት.. የተባለው ሁኔታ ውስጥ የምንገኝ አይመስልም?
ቅድም የልዩ ልዩ ማህበረሰቦችን ስሞች እያየን እንዳደረግነው፣ አሁን ደግሞ የተለያዩ የሰላምታ አይነቶችን እያየን እንዝናና፣ ካጋጠመንም እንደነቅ!
ለክፍለ ዓለማችን የባህልና የስልጣኔ ምንጭ ከሆነችው ከፈርኦናዊት ግብ እንጀምር፡፡
ተራው ሰው ከፈርኦን ጋር ሊተላለፍ ሲሆን፣ ገና ፈርኦን ብቅ ሲል እንዳየ፣ በግምባሩ ተደፍቶ ጭንቅላቱ ላይ አፈር ይነሰንሳል፡፡ እና ፈርኦን ካለፈ በኋላ፣ የአንድ ባለሟል ድም ..መነሳት ትችላላችሁ.. ሲል፣ ተነስተው አፈሩን አራግፈው ወደ እለት ጉዳያቸው ይራመዳሉ፡፡ መሳፍንቱና መኳንንቱ (እንዲሁም ሚስቶቻቸው) ካጋጠሙትም ያው በግምባሩ ተደፍቶ ጭንቅላቱ ላይ አፈር መነስነስ ነው፣ የትህትና ትህትና ለማሳየት፡፡
መሳፍንቱንና መኳንንቱ ከፕሮቶኮል ስነ ሥርዓት ውጪ ከፈርኦን ጋር ሊተላለፉ የሆነ እንደሆነ፣ በግምባራቸው መሬት ተደፍተው ጭንቅላታቸው ላይ አፈር መነስነስ ይኖርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ፈርኦን ሲባል አባቱ Horus ነው፡፡ (ፀሐይን እንደ ሰረገላው ከምስራቅ ወደ ምእራብ የሚነዳ አምላክ እሱ ነው) አሜን!
ይህም በርቀት Voltaire የተናገረውን ያስታውሰናል “If God did not exist, He would have to be invented”
Anthropologist ሊቃውንት እንደሚነግሩን፣ የትም አገር ቢሆን ማንም ዜጋ ከንጉስ ጋር ሲተላለፍ፣ ተሽቀዳድሞ በማጐምበስ (በመስገድ፣ እጅ በመንሳት) ትሁት ታዛዥ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት፡፡
ንጉስ በማንም ዜጋ ላይ የህይወትና የሞት ሥልጣን ያለው መሆኑን እናስታውሳለን፡፡ እንዲሁም እቺን በአምስት ዓመቱ የጠላት ዘመን ብቸኛ ወንድ ልጅ ያላት ሴት በጭንቀት ሰዓት የገጠመችውን እናስታውሳለን፡፡
..ጌታው ሞሶሎኒ የዝጌር ታናሽ ወንድም
የዛሬን ማርልኝ ሁለተኛ አልወድም..
በየዘመኑ በየአገሩ የነበረውንና ያለውን ወታደራዊ ተጠንቀቃዊ ሰላምታ እናስብ፡፡
ለማሳረግያም አለችላችሁ ሰላምታ እንደ ቄጠማ የለመለመች፣ እንደ ጌረዳ የተዋበች፣ ለሰጪዋም ለተቀባይዋም ፀጋን የምትለግስ፡፡ Namaste ይሏታል ህንዶቹ፣ መዳፍና መዳፋቸውን እያነካኩ፣ አንገታቸውን በትህትና እየደፉ፡፡ ሲተረጎም “I bow to the Divinity within you” (እርስዎ ውስጥ ለሚኖረው መለኮት እሰግዳለሁ) በነሱ እምነት እያንዳንዳችን ውስጣችን ወይም ነፍሳችን መለኮት ነው፡፡ በርቀትም ቢሆን እኛ ክርስትያን እያንዳንዳችን yእግዚአብሔር ዘለአለማዊ ትንፋሽ ነን ብለን ከምናምነው ጋር ይቀራረባል፡፡ ናማስቴ!
አራት
የተከበራችሁ አንባብያን፡-
የጽሑፋችን አርእስት እንደ¸ያመለክተው ..ሰው፣ ስም፣ ሰላምታ.. አብቅቷል፤ በቅንፍ ..እና ማህበራዊ ኑሮ.. ወደ ሚለው መሸጋገራችን ነው፡፡ አብሮ መብላት መጠጣቱን በቸልታ አልፈነው ወደ ፆታዊ ግንኙነት ጎራ እንል ዘንድ ተጋብዛችኋል፣ እኔ አስጎብኚ guide ሆኜ የዛሬ ወጣት ፍቅረኞች ወገብና ትከሻ ተቃቅፋችሁ በመንገድ ስትዘዋወሩ የዚያን ጊዜዎቹ ቢያዩዋችሁ ዓይናቸውን ማመን ያቅታቸዋል፤ ስምንተኛው ሺ የደረሰ ይመስላቸዋል (ደርሶ ይሆን እንዴ ምናልባት? ለጨዋታችን ምንም ልዩነት አያመጣም፡፡)
እንበል አንዲትዋ ላይ ዓይንህን ጣል አረግህባትና፣ እሷ ላይ ተተክሎ ቀረ፡፡ ልብህ ከጊዜው እንጉርጉሮ ጋር ያዜማል፤
..ዓይን የተፈጠረው ሁሉን ለማየት ነ-ው፣ ሁሉን ለማየት ነው
አንቺን አይቶ ሌላ (አዬ-!) አላይ አለኝ ምነው?..
እንግዲህ ምን ትሆን? ከላይ እንደተገለው የስምና የሰላምታ ጉዳይ አስቸጋሪ ሆነብህ፡፡ ዘልለህ ..ወደድኩሽ ሞትኩልሽ.. እንዳትላት ድፍረት ጠፋ፡፡ ፍቅር አሳብዶህ ድፍረቱን ቢሰጥህም እንኳ አይሳካልህም፡፡ ሴቶቹ እንደሆኑ፣ ክፋታቸው ብቻቸውን ሆነው በመንገድ አይታዩም - ቢያንስ ሁለት ናቸው፡፡
አማላጅ ሊያስፈልግህ ነው፡፡ ኧረ ጉዳዩ ከባድ ስለሆነ የአማላጅ አማላጅ ይፈልጋል! በለስ ከቀናህ ወንድምህ ወይም ጓደኛህ እህቷን ወይም ጓደኛዋን ያውቃል፡፡ የአማላጁ ሚና ለውቢቱ ደብዳቤ ማቀበል ነው፡፡
..ደብዳቤው ውስጥ ምን እላታለሁ?.. እያልክ አትጨነቅም፡፡ ደብዳቤ ፀሐፊዎች አሉ፡፡ ባይገርምህ ደሞ፣ የፍቅር ደብዳቤዎች (ማንም ለማንም ቢጽፋቸው) ሁሉም ቃል በቃል አንድ ናቸው - ያቺኑ ፎርሙላ ይከተላሉ፡፡ ግጥሞቹን በቃል ስለማላስታውስ፣ መንፈሳቸውን (ወይም መአዛቸውን ወይም ቃናቸውን) ብቻ ልጠቁም፡-
ሰማዩ ብራና ሆኖ ባህሮቹ ቀለም ቢሆኑ፣ ያንቺ ውበት ተጽፎ አያልቅም
መነኰሳትም፣ ፃድቃን፣ መልአክትም ቢያዩሽ፣ በፍቅርሽ ይደነዝዛሉ
ለኔ ፍቅርሽ ላሳበደኝ ምስኪን ከርታታ እዘኚልኝ፣ በአዛኚቱ እመቤታችን እማፀንሻለሁ ለደብዳቤዬ መልስ እንድትልኪልኝ... ከደብዳቤው በታች ስእል አለ፡፡ ፍላጻ (arrow) ልብ ውስጥ ተሰክቶ ያሳያል፡፡ ፍላጻው ፍቅሯ ከሷ ተወርውሮ ልብህ ውስጥ ተሰክቷል ማለት ነው፡፡
...እንበል በቀኝ ጐንህ በተነሳህበት ገዳም ቀን ደብዳቤዋ ደረሰህ፡፡ የተልእኮህ አንደኛ ደረጃ ተፈመ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በነዚያው አማላጆች መሀረብህን ትልክላታለህ፡፡ አንድ ሁለት ጊዜ አልቀበልም እያለች መሀረብህ ይመለስልሀል፡፡ አንድ ቀን ትቀበለዋለች፣ አማላጆች የላከልህ የፍቅር አምላክ ቀንቶሀል፡፡
በሦስተኛ ደረጃ እንግዲህ እሷ መሀረቧን እንድትልክልህ የበፊቱ የአማላጅ ቀስተኛ ጋጋታ ይሰለሳል፡፡ ይሄ በወቅቱ ዘፈን እንዲህ ይገለጻል፡-
ወለቤ ወለቤ! ነይ መሀረቤ
ወለቤ ወለቤ! ነይ መሀረቤ
የመሀረቡን - ላኪ መልሱን
የመሀረቡን - ላኪ መልሱን
መሀረቡንማ - ወሰደው ለማ
መሀረቡንማ - ወሰደው ለማ
ይሄ ለማ የተባለው እድለኛ ምኞቱ ተሳካለት፡፡ ይሄ ሁሉ ውጣ ውረድ ሲሳካ የት ለመድረስ ነው? ከንፈር ለከንፈር ለመሳሳም ብቻ! ከዚያ አያልፍም፣ የሰርጋችሁ እለት ..ብር አምባር ሰበረልዎ!.. ሊዘፈንላችሁ ካልሆነ፡፡
አምስት
ጠጅ ነጋዴ (..ኮማሪት..) ከሆነች ሴት ጋር ለማድረስ እንዴት ነው? ያው በአማላጅ መሄድ ይኖርብሃል፣ ወድያውም ንግድ ቤቷ ገብተህ የማር ጠጅህን እየጠጣህ (ስኳር በዚያን ዘመን ውድ ነው ማር ይረክሳል) ሞቅ እያለህ ሲሄድ ሴቲቱ የበለጠ እያማረችህ ትሄዳለች፡፡
አምስት ምሽት ያህል እንዲህ ከተመላለስክ በኋላ እስከ ነገ ስትሰናበታት በሞቅታ ደፍረህ መሀረብህን ትተህላት ልትሄድ ትችላለህ፡፡
እስካሁን ያጫወትኳችሁ አብዛኛው ሰው የሚፈጽመውን ሥነ ሥርዓት ነበር፡፡ የማቀርብላችሀ የእውነት ታሪክ ነው፡፡ ዘመኑንም፣ ገፀ-ባሕርያቱንም እንደ ካሜራ ላንድ አፍታ ብልጭ አድርጎ ያሳየናል፣ በተጨማሪም አጤ ምኒልክን የገዛ ህዝባቸው ለምን ..እምዬ ምኒልክ.. ወይም ..እንቅልፌ ምኒልክ.. የሚል የቅል ስም እንዳወጣላችሁ ይታያችሁ ይሆናል፡፡
ሰውየው ከኮማሪቷ ጋር አብሮ ለማደር ሦስት ጠገራ (ወይም ማርትሬዛ) ብር ከፈላት፡፡ ፍቅር መቸስ እንደ ወፍ ዘራሽ ፍሬ የትም ይበቅላልና፤ ጧት ሲነቁ ሁለቱም ፍቅር ይዟቸዋል! ጠጅ ቤቱን ዘጋችው፣፣ በንግዱ አጠራቅማው የነበረውን አንድ መቶ ጠገራ ብር ..ባሏ.. እንዲነግድበት ሰጠችው፡፡
ፍቅራቸው እየሞቀ፣ ትዳራቸው እየለመለመ አስራ አንድ ዓመት ኖሩ፣ ፍሬ ባይሰጣቸውም ፍቅር የለገሳቸውን አንድዬ እያመሰገኑ፡፡ ነጋዴ ባል ሲበዛ በለገ፡፡
ዳሩ ምን ይሆናል፣ ገነት ውስጥ ሲኖሩ ..ዘመድ.. የሚባል እባብ ተላከባቸው፡፡
..አንተን የመሰለ የተከበረ የጨዋ ዘር፣ ምን ጐደለኝ ብሎ ከኮማሪት ጋር ተቆራኝቶ ይኖራል? ኧረ ወዲያ ተዋትና የምትመጥንህን ጨዋ ሴት ታገባለህ! ለዚች ሴትዮህ ካዘንክላት አልፎ አልፎ እየመጣህ ታጫውታታለህ.. እያሉ ጐተጐቱት፣ በዙበት፣ አሸነፉት፡፡
እንፋታ አላት፡፡ እግዜአር የሰጠንን ሲሳይ አንተ እምቢ ካልክ ንብረቴን አካፍለኝ አለችው፡፡
እንቺ ይኸው የሰጠሽኝ አንድ መቶ ብር፡፡ ያን ሁሉ ንብረት አብረን አይደለም ወይ ያተረፍነው? ብትለው፣ የነገድኩት እኔ! አሻፈረኝ አለ፡፡
ወረዳ ፍርድ ቤት ከሰሰችው፡፡ ዳኛው ..እንደ ሀቁ ቢሆን አንቺ ትረቺው ነበር.. አላት ..እኔ ግን በህጉ መሰረት መፍረድ ግዴታዬ ስለሆነ፣ አንድ መቶ ብርሽን ተቀብለሽ መሰናበት ይኖርብሻል..
ይግባኝ አለች፡፡ የዳኛው ስሜትም ፍርድም ያው ሆነ፡፡ አሁንም ይግባኝ፣ አሁንም ያው፡፡ እንዲህ ስትል ስትል አጤ ምኒልክ ችሎት ደረሰች፡፡ የሳቸውም ፍርድ ያው ሆነባት፡፡
እጅ ነሳችና ድምን ከፍ አድርጋ ..ይግባኝ ለሀብተ ጎርጊስ!.. አለች፡፡ ሰው ጉድ አለ፤ አጉረመረመ፡፡ አንዳንዱ ነቀፋት፣ ጥቂቱ ኃይለኛ ቅጣት በየነባት፡፡
አጤ እጃቸውን አነሱ፤ ፀጥታ ሆነ፡፡ ..ልቀቁዋት አባ መላ ጋ ትሂድ.. አሉ ..መላ ያገኝላት ይሆናል..
አባ መላ ችሎት ከሳሽና ተከሳሽ ቀረቡ፡፡ ፍርዳቸው ያው ሆነ!
ሰውየው የድል ስሜት እየታየበት እጅ ነስቶ ሊወጣ ሲል፣ ..ቆይ.. አሉት፡፡ ቆመ፡፡ ..አስራ አንድ ዓመት አብራችሁ ኖራችሁ፡፡ ለመጀመሪያው አዳር ስንት ከፈልካት?..
..ሦስት ብር..
..እንግዲያው አስራ አንድ ዓመት ውስጥ ስንት ሌሊት እንዳለ ስሌቱን ሰርተህ፣ ለያንዳንድዋ ሌሊት ሦስት ብሯን ከፍለህ አሰናብታት..
አጅበውት መጥተው የነበሩት ..መካር.. ዘመዶቹ ምንተ እፍረታቸውን አማላጅ ሆነው እየተመላለሱ እየጐተጐቱ እሺ አሰኙዋት፡፡
ተናግቶ የነበረው ትዳር ተመልሶ ቀጥ ብሎ ቆመ. . .   
ስድስት
የአባ መላ የስልጣን ዘመን ግማሹ በአጤ ምኒልክ፣ ግማሹ በጃንሆይ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ይሽከረከራል፡፡ ያንን ዘመን በተመለከተ እነሆ ታሪካዊ የግርጌ ማስታወሻ፡፡ (በተክለ ጻድቅ መኩሪያ)
በ1909 ..ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ፣ ወለቱ ለዳግማዊ ምኒልክ፣ ስይምተ እግዚአብሔር´ ተብለው በዙፋን ተቀመጡ፡፡ . . .ደጃዝማች ተፈሪም ራስ ተብለው፣ ለኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽና እንደራሴ ሆነው የራስ ወርቅ አሰሩ፡፡
በሁለቱም ዘመን ጌታ ፊታውራሪ የጦር ሚኒስትር፣ ያገር ግዛት ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ሦስቱንም ነበሩ፡፡
ጊዜው የኮሎኒያሊዝም ስለሆነ፣ አውሮፓውያኖች (በተለይም ጣልያኖች) በንግድ ወይም በሌላ ሽፋን ወታደራዊ ስለላ ያካሂዱ ነበር፤ ለወደፊት ለወረራ የሚረዳ መረጃ ለመሰብሰብ፡፡ ብዙዎቹን ሽፍቶች ይገድሉዋቸዋል ለመዝረፍ፡፡
እንበል ሦስት አብረው የመጡ የኢጣልያ ዜጎች ተገደሉ፡፡ የኢጣልያ ቆንስል ለኢትዮጵያ መንግሥት ይህን ወንጀል ሲያመለክት ጌታ ፊታውራሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ይቀበሉታል፡፡ ..ይህን ብርቱ ጉዳይ ባለን አቅም ሁሉ እንከታተላለን.. ይሉታል፡፡ ከሁለት ሦስት ሳምንት በኋላ ያስጠሩታል፡፡
..ሽፍቶቹንኮ ያዝናቸው፡፡ ይምጡማ ላሳይዎት.. ብለው ወስደው የአራት ሽፍቶች ስቅላት ያሳዩታል፡፡ ወደ አገሩ መንግሥት የጌታ ፊታውራሪን ተባባሪነት እያመሰገነ ዘገባ ይልካል፡፡ (እንደ እውነቱ የሆነ እንደ ሆነ ግን፣ አራቱም የተሰቀሉት ባገራችን ህግ የተፈረደባቸው ወንጀለኞች ናቸው፡፡ ሦስቱን ጣልያኖች የገደሉዋቸው ..ሽፍቶች.. የጌታ ፊታውራሪ ታማኝ ወታደሮች ናቸው፡፡ አባ መላ አመስግነው ሸልመው ..በርቱ! ተግታችሁ ጥበቃችሁን ቀጥሉ.. ብለው ያሰናብቷቸዋል፡፡
ጌታ ፊታውራሪ በተዋጉባቸው ጦርነቶች ሁሉ ድል ያደረጉ ጀግና የጦር ኃይሎች ዋና አዛዥ ናቸው፡፡ (የግል ወታደሮቻቸው ብቻ እንኳ ብዛታቸው አንድ ክፍለ ጦር ያክላል!) ለሰራዊታቸው ምን ያህል እንደሚቆረቆሩ የምታሳይ አንዲት ታሪክ እችትላችሁ፡፡
የዘማች ወታደር ሚስት ..እምነት በማጉደል.. ከአንድ ቆማጣ ውሽማዋ ጋር ..መርፌና ክር.. እንደሆኑ ተያዙ፡፡ ጌታ ፊታውራሪ ፊት አቀረቡዋቸው፡፡ ሴትዬዋ ቆማጣ ውሽማዋን አዝላ ..እኔን ያያችሁ ተቀጡ!.. እያለች የአጤ ምኒልክን ቤተ መንግሥት የውጭ ካብ ሦስት ጊዜ ዞረችው (ጐደሎ ቀን ይሉታል እንዲህ ዓይነቱን)
ከጐደሎ ቀን ይሰውረን አሜን!

 

Read 4496 times Last modified on Saturday, 13 August 2011 11:36