Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 20 August 2011 10:13

ጠ/ሚኒስትሩ፤ ፌስቡክንና ትዊተርን መዝጋት እፈልጋለሁ ያሉት መቼ ነው?

Written by 
Rate this item
(0 votes)
  • የእንግሊዝ መንግስት በኢራን፣ በሊቢያና በታሊባን ተተችቷል

የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን፤ የእንግሊዝን ሁከት ከግብፅ ጋር አያይዘው ዘግበዋል
በለንደን ኧሊንግ በተባለው አካባቢ የተጀመረው ነውጠኛ ሁከት (riot) ፤ ቅዳሜና እሁድ ተባብሶ ሰኞ እለት የከተማዋ ስምንት አካባቢዎችን አዳርሷል፡፡ ሰፈር ውስጥ ያገኙትን መኪና እየከሰከሱና እሳት እየለቀቁበት፤ ያጋጠማቸውን የንግድ ሱቅ ሰብረው እየገቡ ይዘርፋሉ - አይፎንና ብላክቤሪ ሞባይል ስልኮችን፤ ስኔከር ጫማና መነፅር፤ ሻምፑ እና መጠጥ ሳይቀር... ያገኙትን ከዘረፉ በኋላ ያጋዩታል፡፡

ፀጉር በማስተካከል የሚተዳደሩት የ89 አመት አዛውንት አሮን ቢበር፤ የሚዘረፍ ብዙ ነገር አልነበራቸው፡፡ ፀጉር ማስተካከያ፤ እንደ ጌጣጌጥ ወይም እንደ ኤሌክትሮኒክስ ሱቅ አይደለም፡፡ ነውጠኞቹ ግን የሚዘረፍ ነገር ባያገኙ እንኳ፤ በዝምታ አያልፉም፡፡ በእሳት ያያይዙታል፡፡ በየበሩ ደጃፍ የሚቀመጠው የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቆርቆሮም አይቀራቸውም - እንዲያውም በሱ ነው የሚጀምሩት፡፡ አዛውንቱ አሮን ቢበር፤ አሁን የፀጉር ማስተካከያ ሱቃቸው በእሳት አመድ ከሆነ በኋላ፤ ህይወታቸውን እንዴት መምራት እንደሚችሉ አያውቁም - ከዚህችው ስራ ውጭ ሌላ መተዳደሪያ የላቸውም፡፡ የ68 አመቱ ጡረተኛ ሪቻርድ ቦው ግን የባሰ አጋጥሟቸዋል፡፡
በቪዲዬ የተቀረፀው ምስል እንደሚያሳየው፤ ሪቻርድ ቦው በብቸኝነት ከሚኖሩባት ቤታቸው ብቅ ሲሉ፤ ሰፈሩ ሰላም አልነበረም፡፡ ከወዲህ ወዲያ በሚወረወሩ ድንጋዮችና ተቀጣጣይ ጠርሙሶች አማካኝነት የመስኮት መስተዋት እየተሰባበረ ነው፤ እዚህም እዚያም እሳትና ጭስ ይታያል፡፡ ከቤታቸው አቅራቢያ ያለው የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቆርቆሮም በእሳት ተያይዟል፡፡ ነውጠኛው ሁከት የተለኮሰበት ሰፈር ነው፤ በመጀመሪያው ቀን፡፡
አዛውንቱ ሪቻርድ ቦው፤ የተቀጣጠለውን እሳት እያዩ ዝም ማለት እንዳልቻሉ፤ የተቀረፀው ቪዲዮ ይመሰክራል፡፡ በአዛውንት አቅማቸው ወደ እሳቱ ሲራመዱ ይታያል፡፡ መራመድ ብቻም ሳይሆን፤ እሳቱን ለማጥፋት ይጣጣራሉ፡፡ በዚህ መሃል ነው፤ በርከት ያሉ ነውጠኞች አዛውንቱን የከበቧቸው፡፡ ቪዲዮው ላይ የነውጠኞቹ ፊት አይታይም፤ ፊታቸውን በጨርቅ ሸፍነዋል፡፡
አዛውንቱ በዙሪያቸው ካፈጠጡባቸው ነውጠኞች ጋር መጋፈጥ ባይችሉም፤ ወደኋላ አላሉም፡፡ ለነገሩ ልሩጥ ቢሉም ማምለጥ አይችሉም፡፡ ጭምብል ካጠለቁት ነውጠኞች መካከል አንዱ፤ እጁን ወረወረ፡፡ የተወረወረው ቦክስ አዛውንቱ ፊት ላይ ሲያርፍም ቪዲዮው ውስጥ ይታያል፡፡ አዛውንቱ የኋሊት ሲወድቁና አናታቸው ከአስፋልቱ ጋር ከተላተመ በኋላ አልተንቀሳቀሱም፡፡ ራሳቸውን ስተዋል፡፡ በመጨረሻ ሆስፒታል ተወስደው፤ ለሶስት ቀናት በህክምና ሲያሳልፉም፤ ራሳቸውን አያውቁም - ህይወታቸው እስካለፈበት እለት ድረስ፡፡
ኧሊን በሚባለው አካባቢ የተጀመረው ሁከት፤ ወዲያውኑ አልቆመም፡፡ ከቀን ወደ ቀን፤ ሌላ ተጨማሪ ሰፈር በነውጠኞች እየታመሰ፤ ሁከቱ ስምንት ያህል የከተማዋ አካባቢዎችን አዳርሷል፡፡ በርሚንሃም፤ ማንችስተርና ሊቨርፑልን ጨምሮ በስድስት ከተሞች ውስጥም፤ በርካታ ሰፈሮች የነውጡ ሰለባ ሆነዋል፡፡ የትኛውን ሰፈር፤ የትኛውን መንገድና የትኛውን የገበያ ቦታ እንደሚያጠቁ በሞባይል ሜሴጅ፣ በፌስቡክና በትዊተር መልእክት የሚለዋወጡ ነውጠኞች፤ ከየአቅጣጫው እየተጠራሩ ይሰባሰባሉ፡፡ አንዳንዶቹ ከደርዘን አይበልጡም፡፡ አንዳንዶቹ እስከ ሃምሳ ይደርሳሉ፡፡
ቁጥራቸው ቢያንስም ቢበዛም፤ እግራቸው የረገጠውን አካባቢ በድንጋይና በተቀጣጣይ ጠርሙስ ቀውጢ ያደርጉታል - መዝረፍ፣ መስበር፣ ማቃጠል፡፡ የእሳት ማጥፊያ መኪኖችና ሰራተኞች ወደየአካባቢው ለመድረስ ቢሞክሩም አልቀናቸውም - የድብደባ ኢላማ ሆነዋልና፡፡ የተጎዱ ሰዎችን ለመርዳትና ወደ ህክምና ለመውሰድ የመጡ አምቡላንሶችም፤ በጤና አልተመለሱም፡፡
ነውጠኞቹን ለማስቆም ወይም ለመበተን የተሰማሩ ፖሊሶችስ? እዚህኛው ሰፈርና ወዲህኛው መንገድ ላይ ሁከት የፈጠሩትን ነውጠኞች ለመበተን ፖሊሶች ሲሰማሩ፤ ነውጠኞቹ ይሮጣሉ፤ የተበተኑም ይመስላሉ፡፡ ግን፤ እዚያኛው ሰፈርና ወዲያኛው መንገድ ላይ ሌላ የዝርፊያና የቃጠሎ ሁከት ለመፍጠር ጊዜ አይፈጅባቸውም፡፡ እንደገና ፖሊሶች ሲመጡባቸው፤ ነውጠኞቹ ቦታ እየቀየሩ.... በቃ ፖሊስ፤ ሁከቱን በፍጥነት ለመግታት አልቻለም፡፡ ጭራሽ በነውጠኞች የሚተራመሱ ሰፈሮች በመበራከታቸው የተቆጡ ተቺዎች ፖሊስ ላይ ጣታቸውን መቀሰር ጀምረዋል - የከተማዋ የፖሊስ ኮሚሽን ተጨማሪ ፖሊሶችን በፍጥነት ለማሰባሰብና ለማሰማራት አልቻለም በሚል ወቀሳ፡፡ ሌላ አይነት ትችትና ወቀሳ የሚያቀርቡም በርካታ ናቸው፡፡ ፖሊስ፤ ነውጠኞቹን ፊት ለፊት እየተጋፈጠ አይደለም በማለት ቅሬታቸውን የሚገልፁ ሰዎች፤ ፖሊስ የውሃ መርጫ መኪኖችን ከመጠቀም ታቅቧል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በቡድን የተሰባሰቡት ነውጠኞች ፖሊስ ሲመጣባቸው፤ አንዳንዶቹ በፍጥነት ወደ ሌላ ሰፈር እየሄዱ ሲበጠብጡ፤ ሌሎቹ ደግሞ እዚያው በያሉበት ሆነው ፖሊስን መጋፈጥ ጀምረዋል፡፡ በእርግጥም ፖሊስ ሊቋቋማቸው አልቻለም፡፡ ነውጠኞቹ፤ ድንጋይና ዱላ፣ ስለታማ ብረቶትና ተቀጣጣይ ጠርሙስ ይጠቀማሉ፡፡ የፕላስቲክ ዱላም ሆነ ውሃ መርጫ መኪኖችን እንዳይጠቀሙ የተደረጉት ፖሊሶች፤ ነውጠኞቹን ለመበተንና ለማሰር ይቅርና ራሳቸውን ከጉዳት ለመከላከል ተቸግረዋል - በርካቶችም ተድብድበዋል፤ በስለታማ ብረት ተጎድተዋል፡፡ ፖሊሶች የፕላስቲክ ዱላና የውሃ መርጫ መኪና እንደማይጠቀሙ መከልከላቸው ተገቢ ነው ወይ በሚል ለአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትርዋ ጥያቄ ሲቀርብላቸው፤ ተገቢ መሆኑን በመግለፅ ምላሽ ሰጥተዋል - የአገራችን ፖሊስ አሰራር እንደዚያው ነው በማለት፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ታዲያ ፖሊሶች ነውጠኞቹን እንዴት መቋቋም ይችላሉ?ነውጠኞቹ የትኛውን ሰፈር በየትኛው ሰአት እንደሚረብሹ እቅድ እያወጡ በፌስቡክና በትዊተር ሲጠራሩ ምንም ማድረግ አይቻልም ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችና ትችቶችም ተሰንዝረዋል - ነውጠኞቹ በፌስቡክና በትዊተር እንዳይጠቀሙ ጊዜያዊ ቁጥጥር ማድረግ ወይም በተወሰነ መልኩ ብቻ ለአጭር ጊዜ አገልግሎቶቹ እንዲቋረጥ ማድረግ አይቻልም ወይ በማለት፡፡ ነውጠኞችን ለመቆጣጠር በሚል ሰበብ፤ መንግስት yኢንተርኔትÂ የሞባይል አገልግሎት እንዲቆጣጠር በጭራሽ መታሰብ የለበትም በማለት ቁጣቸውን የገለፁም ነበሩ - የፕሬስ ነፃነትን፣ የመናገር ነፃነትን ይጥሳል በማለት፡፡ ለማንኛውም፤ መንግስት yኢንተርኔትNÂ የሞባይል አገልግሎትን ሊያደናቅፍ ቀርቶ፤ ...ለማደናቀፍ ሊሞክር ቀርቶ፤ እናደናቅፍ ብሎ ሊወስን ቀርቶ፤ እንሞክር ወይ የሚል የውሳኔ ሃሳብም በወቅቱ አልቀረበም፡፡ ሁከቱንና ነውጡን በተመለከተ የፓርላማ ኮሚቴ ባዘጋጀው ምርመራ፤ የመንግስት ባለስልጣናትን ጠርቶ ቃላቸውን እንዲሰጡ ሲያደርግ የተገኘው መረጃም ይህንን ይመሰክራል፡፡ ቃላቸውን ከሰጡት ባለስልጣናቱ መካከል አንዱ የለንደን ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ናቸው፡፡
ነውጠኞቹ ፌስቡክና ትዊተርን፣ እንዲሁም የሞባይል ሜሴጅን በስፋት ይጠቀሙ እንደነበር የተናገሩት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ እነዚህን አገልግሎቶች በተወሰነ አካባቢና በተወሰነ መልኩ ማቋረጥ ቢቻልስ? የሚል ሃሳብ መጥቶልኝ የነበረ ቢሆንም፤ ወዲያውኑ ውድቅ አድርጌዋለሁ ብለዋል፡፡ ነውጠኞችን ለመቆጣጠር በሚል ሰበብ፤ yኢንተርኔትNÂ የሞባይል አገልግሎትን መቆጣጠርና ማደናቀፍ ህጋዊነት ይኖረዋል ብዬ አላስብም ያሉት ም/ኮሚሽነሩ፤ እናም አገልግሎቶቹን የመቆጣጠር ሃሳብ ለውሳኔ ሰጪዎች አላቀረብኩም ብለዋል፡፡የውሃ መርጫ መኪናስ? ፖሊሶች ህግ በሚፈቅድላቸው መሰረት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ እየተደረገ ነው በማለት የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትርዋ ቢናገሩም፤ ፖሊስ የውሃ መርጫ መኪኖችን እንዲጠቀም ፈቃድ አላገኘም፤ ወይም አልታዘዘም፡፡ ነውጠኞቹ ፊታቸውን የሸፈኑበት ጭንብል በግድ እንዲያወልቁ ማድረግም አልተቻለም - ህጉ ይፈቅዳል ወይስ አይፈቅድም፤ ሰብአዊ መብትን ይጥሳል ወይምስ አይጥስም የሚለው ጥያቄ ገና እልባት አላገኘም ነበር፡፡ በለንደን ከተማ ተጨማሪ ፖሊሶችን በማሰማራት፤ እንዲሁም ቀንደኛ ነውጠኞች የተባሉትን ይዞ ወደ ፍርድ ቤት ለማቅረብ በመሞከር ነው፤ ሁከቱን ለማርገብና ለማስቆም የተቻለው፡፡
ቀንደኛ ነውጠኛ የተባሉትን ይዞ ለፍርድ ቤት ማቅረብ ሲባል፤ እንዲሁ መንገድ ላይ የተገኘውን በአፈሳ እስር ቤት ማጎር አይደለም፡፡ እንደአገራችንና እንደብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት ያለክስ በፍርድቤት ቀጠሮ እያመላለሱ ማቆየትም የለም፡፡ በዚያ ቀውጢ ሁከት ውስጥ፤ ፖሊሶች ማስረጃ እያሰባሰቡ ነበር፡፡ ፖሊስ ሰዎችን የሚይዘው በአፈሳ ሳይሆን በማስረጃ ከሆነ፤ ወዲያውኑ ክስ አዘጋጅቶ ከነማስረጃው ለፍ/ቤት ለማቅረብ አያቅተውም፡፡ ሁከቱ ሳይቆምም፤ በፖሊስ ከተያዙት 2700 ገደማ ተጠርጣሪዎች መካከል፤ እስከሰኞ ድረስ 1200 ያህሉ ላይ ክስ ተመስርቶባቸዋል - ለ68 አመቱ ጡረተኛ ሪቻርድ ቦው መሞት ተጠያቂ ነው የተባለው ወጣት ጭምር፡፡በዚህ መንገድ፤ ሁከቱና ነውጡ ከቆመ በኋላ ነው፤ ብዙ ጥያቄዎች ጎልተው መውጣት የጀመሩት፡፡ የጥፋቱ መንስኤና መጠን እንዲሁም የመንግስትና የፖሊስ እርምጃ ምን ይመስል ነበር?
ወደፊት ተመሳሳይ ጥፋቶችን ለመከላከልና ለመግታትስ ምን መደረግ አለበት? የሚሉ ጥያቄዎች ላይ ውይይትና ክርክር ተጧጥፏል፡፡ ለበርካታ አስርት አመታት እንግሊዝ ውስጥ ስነምግባር ሲሸረሸር መቆየቱንና ይህም ለጥፋት መንስኤ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን፤ የፖሊስ አሰራሮችን ቀልጣፋ ማድረግ፤ በትምህርት ቤቶች ያለውን የላላ ስነምግባር ማጠናከር፤ ወንጀሎች ሲፈፀሙ በድህነትና በተበዳይነት አለማሳበብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፤ ሁከት በሚፈጠርበት ወቅት፤ በነውጥና በወንጀል ተግባር የተጠረጠሩ ሰዎችን በመለየት፤ የፌስቡክና የትዊተር አጠቃቀማቸውን ማገድ ይቻል እንደሆነ መፈተሽ ያስፈልጋል ብለዋል - ዳቪድ ካሜሮን፡፡ ይህን በሚመለከት፤ የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ምን ብለው እንደዘገቡ ሰምታችሁ ይሆናል፡፡ ዳቪድ ካሜሮን፤ የግብፅ አመፅ በተካሄደበት ወቅት፤ የፌስቡክና የትዊተር አስተዋፅኦን ሲያደንቁ ነበር የሚለው ኢቲቪ፤ አሁን ግን ፌስቡክንና ትዊተርን ለመዝጋት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል የሚል ሃሳብ የያዘ ዘገባ አሰራጭቷል - ለዚያውም እየደጋገመ፡፡ እስቲ ይታያችሁ፡፡ ዳቪድ ካሜሮን የነውጥ ተጠርጣሪዎች በፌስቡክና በትዊተር እንዳይጠቀሙ ማድረግ በሚቻልበት መንገድ ላይ ሊታሰብበት ይገባል ማለታቸው ከግብፁ ሁኔታ ጋር ይያያዛል? በግብፅኮ ሰላማዊ ሰልፈኞችንና ዜጎችን በሙሉ ለማፈን ነው፤ yኢንተርኔትÂ የሞባይል አገልግሎት የተቋረጠው፡፡ ታዲያ የዳቪድ ካሜሮን ሃሳብ፤ ከዚህ ጋር ወይም ኢትዮጵያ ውስጥ በ97 ምርጫ ቀውስ፣ ለወራት ያህል ከተቋረጠው የሞባይል ሜሰጅ አገልግሎት ጋር ይመሳሰላል? ለማመሳሰል የሚፈልጉ ይኖራሉ፡፡ ልዩነታቸው ግን ሲበዛ ግልፅ ነው፡፡ በግብፅ፤ ምርጫ እንዲካሄድና ስልጣን እንደርስት መታየቱ እንዲቀር በሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄ የሚያቀርቡ ዜጎችን ለማፈን ኢንተርኔት ተቋረጠ፡፡ በእንግሊዝ ግን፤ ለዝርፊያና ለቃጠሎ የሚዘምቱ ነውጠኞችን በመለየት፤ ለዚያውም ማስረጃውን ለፍርድ ቤት በማቅረብ፤ ፍ/ቤቱ ሲፈቅድ የነውጠኞቹን መስመር ማቋረጥ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ጥያቄ መፈተሽ አለበት ተባለ፡፡ የልዩነቱን ስፋት አያችሁ? አንደኛው ሰላማዊ ዜጎችን አፋፍሶ ሲገድል፤ ሌላኛው ደግሞ ወንጀለኞችን ለመከላከል ፍርድ ቤትን ያስፈቅዳል፡፡ እንዲያም ሆኖ፤ ዴቪድ ካሜሮን ያሰቡት እርምጃ፤ ህጋዊነቱና ውጤታማነቱ ምን ያህል አስተማማኝ ነው የሚለውን ጥያቄ በቸልታ ማለፍ አይቻልም - ለዚያውም የመናገር ነፃነትና የፕሬስ ነፃነት ከብዙ አገራት በተሻለ ሁኔታ በሚከበርበት አገር፡፡ ኢትዮጵያን በመሳሰሉ የአፍሪካ አገራት እንጂ፤ በእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለተናገሩ ብቻ፤ ነገርየው ተግባራዊ ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ በድጋፍም ሆነ በተቃውሞ ምሁራን ትንታኔ ያቀርባሉ፡፡ ፍርድ ቤቶች የመንግስት እርምጃዎችና መመሪያዎች ህጋዊ መሆን አለመሆናቸውን በተመለከተ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ይዳኛሉ፡፡ በጋዜጣ፣ በሬድዮ፣ በቲቪ፣ በኢንተርኔት አወንታዊም ሆነ አሉታዊ ዘገባና ትችት በስፋት ይሰራጫል፡፡ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ይከራከሩበታል፡፡ ዜጎች ሃሳባቸውን ይሰነዝራሉ፤ ማጭበርበርና አፈና በሌለበት የምርጫ ወቅትም ይሻላል የሚሉትን ፓርቲና ፖለቲከኛ ይመርጣሉ - ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ሆነ ሌሎች ሚኒስትሮችንና የፖሊስ ኮሚሽነሮችን እንዲህ በቀላሉ መሻር ይችላሉ፡፡ በነሱ አገር የመንግስት ስልጣን፣ ንብረት አይደለም፡፡ ታዲያ፤ በእንዲህ አይነት አገር የቀድሞው ጠ/ሚ ቶኒ ብሌር ለ13 አመታት በስልጣን ላይ መቆየታቸው እንደ ብርቅ መታየቱ ይገርማል?እንግዲህ፤ ለ41 አመታት ያለምርጫ በብቸኝነት ስልጣን ላይ የቆዩት ሙአመር ጋዳፊ ናቸው፤ የለንደን አመፅን ተከትሎ የእንግሊዝ መንግስት ላይ ትችት የሰነዘሩት፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲ ማደራጀትና በምርጫ መፎካከርን ቀርቶ፤ ትችት ያዘለ ትንታኔ የሚፅፉ ምሁራንንና በቅሬታ አቤቱታ የሚያቀርቡ ዜጎችን የሚያስር፤ ነፃ ጋዜጣና ቲቪ እንዳይኖር የሚከለክል፤ ኢንተርኔት የሞባይል አገልግሎትን በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚዘጋ፤ ተቃውሞ ለማሰማትና ምርጫ እንዲካሄድ ለመጠየቅ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ የሚሞክሩ ዜጎች ላይ ጥይት የሚዘንብና ታንክ የሚያዘምት፤ መንገድ ላይ የተገኘውን እያፈሰ የሚገድል የሊቢያ መንግስት ነው፤ በእንግሊዝ ላይ ወቀሳና ስድብ የሚሰነዝረው፡፡
ሰዎችን ለምን ኳስ ተጫወታችሁ ወይም ለምን ጨዋታውን አያችሁ ብሎ በድንጋይ የሚወግር፤ ከነጭራሹ ቴሌቪዥን የሚባል ነገር እንዳይኖር የሚያግድ፤ የመናገር ነፃነትና የፖለቲካ ምርጫ ወንጀል ናቸው ብሎ የሚያውጅ፤ ትችት የሚያቀርቡትን ቀርቶ አልደገፉኝም የሚላቸውን የሚያስርና የሚገድል የአፍጋኒስታኑ ታሊባን ነው፤ የእንግሊዝ መንግስት ላይ ውግዘት የሚያቀርበው፡፡ ከታሊባን የማይሻለው የኢራን መንግስትም እንዲሁ””የአፍጋኒስታኑ ታሊባን፤ ሊቢያና ኢራን፤ ከአለም መንግስታት ሁሉ ተለይተው፤ በለንደኑ ነውጥ ሰበብ የእንግሊዝን መንግስት ለማውገዝ የዘመቱት ለምን ይሆን? የነሱስ ይሁን፤ የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን፤ የእንግሊዝ መንግስትን ከቀድሞው የግብፅ መንግስት፤ የእንግሊዙ ጠ/ሚ ዳቪድ ካሜሮንን ከቀድሞው የግብፅ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ በሚያመሳስል መንገድ ዘገባ ሰርቶ እየደጋገመ ያሰራጨው ለምን ይሆን? ለዚያውም የተዛባ ዘገባ፡፡

Read 4967 times