Saturday, 20 August 2011 10:49

ለእርስዎ ተረት ለብዙሃኑ እውነት ሆኖ ይቀጥል

Written by  ፍሰሐ ያዜ
Rate this item
(2 votes)

የኖህን ምድር ላይ መኖር መጠራጠርም መካድም መብትዎ ነውና፤ ምድር ላይ አልኖረም ወደማለት አምርተዋል፡፡ ስለዚህ የፈጣሪን ህልውናም ይጠራጠራሉ፤ ይህም መብትዎ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ የግል መብትዎ እንጂ እንደ ትልቅ እውቀት ቆጥረው፤ ፈሪሀ ፈጣሪ ባደረበት ማህበረሰብ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ በሚነበብ ጋዜጣ ላይ የግል አቋምዎን ደንጉረው፤ እምነቱ ሕይወቱ የሆነውን ህዝብ ማደናገር ከፀሐፍት ስነምግባር ውጪ መሆኑን ማወቅ ነበረብዎ፡፡ይህ ጽሑፍ ባለፈው ሣምንት ነሐሴ 7/2003 ዓ.ም በዚሁ ጋዜጣ በጥበብ ዓምድ     ስር ..የኖኅና የሳባ ተረት.. በሚል ርዕስ

ለቀረበው ጽሑፍ የተሠጠ መልስ ነው፡፡ፀሐፊው አለማየሁ ገላጋይ የነበሩ ሲሆን አነሳሳቸውም በቅርቡ ለህትመት በቅቶ ወደ አንባብያኑ የደረሰውን ..የኢትዮጵያ የ5ሺ ዓመት ታሪክ፤ ከኖኅ እስከ ኢህአዴግ.. የሚለውን መጽሐፍ መዳሰስ ነበር፡፡ 
በመጀመሪያ ደረጃ መጽሐፉ እርስዎን አይመለከትም፡፡ ምክንያቴንም በመሃፉ በገጽ 20 አስፍሬያለሁ፡፡ .....ሁሉም የሰው ልጆች በጥፋት ውሃ ጠፍተው ኖኅና ቤተሰቦቹን ከተረፉ በኋላ በእነርሱ አማካኝነት ዓለም በሰው ልጆች ተሞልታለች፡፡ በዚህ ብንግባባ ምርጫዬ ነው፡፡ በዚህ ካልተግባባን በሙሉው መጽሐፍም ስለማንግባባ ከዚህ እምነት ውጪ የሆነ አንባቢ ካለ ንባቡን ያቋርጥል በትህትና ዝቅ ብዬ ሳይሆን ቀና ብዬ እጠይቀዋለሁ.. ብያለሁ፡፡
እኔ ይህን ስል እርስዎ ማቴሪያሊስት እንደመሆንዎ መጠን ያን ጨለምተኛ አስተሳሰብዎን ለራስዎ ሊይዙት ይገባ ነበር፡፡ ሳይሆን ቀረና የልማድዎን ለማድረስ ያንኑ ዱልዱም ብዕርዎን ከወረቀት አዋደው የእርስዎን ተረት እውነት፣ የብዙሃኑን እውነት ተረት አድርገው መተረት ጀመሩ፡፡
ሲቀጥሉም .....ለመሆኑ ኖኅ የተሠኘው ሰው በዚች ምድር ላይ ነበር? የዘፍጥረቱ ኖኅ በህይወት የነበረ ሰው ነው ብሎ ለመከራከር የሚያስችለው ብቸኛው መረጃ (መረጃ ከተባለ) በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተካተተው ታሪኩ ብቻ ነው.. አሉ፡፡ እርስዎ ይሄን ይበሉ እንጂ ከዚህም ያለፉ መረጃዎች አሉ፡፡
መጽሐፌ ላይ ስለዘረዘርኳቸው አሁን አልደግማቸውም፡፡ ያም ቢሆን እርስዎ ..መረጃ ከተባለ.. ብለው ያጣጣሉት መጽሐፍ ከመረጃነት ባለፈ የብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ የህይወት ማንዋል መሆኑ በደንብ ይታወቃል፡፡
የኖህን ምድር ላይ መኖርን መጠራጠርም መካድም መብትዎ ነውና፤ ምድር ላይ አልኖረም ወደ ማለት አምርተዋል፡፡ ስለዚህ የፈጣሪን ህልውናም ይጠራጠራሉ፤ ይህም መብትዎ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ የግል መብትዎ እንጂ እንደ ትልቅ እውቀት ቆጥረው፤ ፈሪሀ ፈጣሪ ባደረበት ማህበረሰብ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ በሚነበብ ጋዜጣ ላይ የግል አቋምዎን ደንጉረው፤ እምነቱ ሕይወቱ የሆነውን ህዝብ ማደናገር ከፀሐፍት ስነምግባር ውጪ መሆኑን ማወቅ ነበረብዎ፡፡
የኖኅን ህልውና የሚጠራጠር ካለ ይህን መጽሐፍ ማንበቡን ከወዲሁ ያቋርጥ ብዬ በመግቢያው ላይ የጠቀስኩትም ቢገባዎት እንደ እርስዎ መንታ መንገድ ላይ ቆሞ እውነት ከምድር ተቆፍራ ትወጣለች ብሎ በተስፋ የሚጠባበቅ ተቅበዝባዥ፣ ጣልቃ ገብቶ፣ ያለእምነቱና ያለርዕዮቱ እንዳይፈተፍት በመስጋት ነበር፡፡
እልፍ ስንል በእርስዎ እይታና ድምዳሜ የኢትዮጵያ ታሪክ ከክርስቶስ ልደት በፊት 200 አመት ይነሳል፡፡ በዚህ ድምዳሜ ቆመው ለመቅረት ያመችዎ ዘንድም የጥቂት የታሪክ ምሁራንን ስም በጽሑፍዎ ላይ በመበተን ከነሱ ጐራ ነኝ ለማለት ዳድተዋል፡፡ ምንም ያልወጣቸውንም አብረው ዘርዝረዋል፡፡
ምነው? ቢሉ ከዚያ ዘመን በፊት የነበረው ታሪክ አይታወቅም ነው መልስዎ፡፡ ..የኢትዮጵያ የ5ሺ ዓመት ታሪክ ከኖኅ እስከ ኢህአዴግ.. የሚለው መጽሐፍ ግን ከዚያ በፊት የነበረውን የረጅም ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ በመረጃ ተንተርሶ ይተነትነዋል፡፡ የዚህ ፍርድ የብዙሃኑ አንባቢ ከመሆኑ አንፃር የምለው ባይኖረኝም የማንበብንና የማነብነብን ልዩነት ግን ሳልጠቁምዎ አላልፍም፡፡
(በእርግጥ ..ኢትዮጵያ የ100 አመት ታሪክ ነው ያላት.. በማለት አዋቂነታቸውን ለመግለጽ የሞከሩ ምሁራንና ምሁር ተብዬ ባሉባት አገር የእርስዎ አቋም ብዙ የሚደንቅ አይሆንም፡፡)
አሁንም በእርስዎ እይታ ኖኅ ብቻ ሳይሆን 3ሺ ዓመት ያስቆጠረችው ንግስተ ሳባም ተረት ተረት ነች፡፡ ወይም ባለፈው ሳምንት ጽሑፍዎ ተረት ተረት ብለዋታል፡፡
ንግስተ ሳባ እንደነበረች እርስዎና መሰሎችዎ ኢትዮጵያውያን ቢክዱም ከኛ አገር የመረጃ ሰነድ ባለፈ እስራኤላውያን ከሠለሞን ጋር በነበራት ቁርኝት ታሪኳን ከትበው ይዘዋል፡፡ በዘመኗ ከንጉስ ሠለሞን የተበረከተላት የዴር ሱልጣን ገዳም ዛሬ ድረስ yኢትዮጵያውያን ቅርስ ሆኖ እየተጐበኘ ይገኛል፡፡
ታሪኳ ብቻ ሳይሆን በጠበብት ሰዓሊያን ዘንድ የተሳለውና ከፎቶ ግራፍ ያልተናነሰ ምስሏ አለ፡፡ መጽሐፍ ቅዱሱን ቢክዱ እንኳ በከፍተኛ መረጃ በቀላሉ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
አስገራሚ ነው! የምኒልክ ላት የለም ብንል እና ምኒልክም ተረት ከሆነ ንጉስ ሠለሞንም ተረት ነበር ማለት ነው) የሰለሞን ቤተመቅደስም ዛሬ ድረስ እየታየ እየተዳሰሰ ተረት ነው ማለትዎ ነው፡፡ አዎ ምኒልክና ሳባ ተረት ከሆኑ ሰለሞንም ተረት ነዋ! ዛሬ ድረስ ወደ እስራኤል እየተጓዙ ያሉት ፈላሻ እና ሙራ ፈላሻዎችም ተረት ናቸዋ! በህልምዎ ነው እንዴ የሚኖሩት? ያሠኛል፡፡
የእርስዎ እይታ ወይም አቋም ሳይንሳዊ ምርምር ይፋ ያደረጋቸውን ካልሆነ በስተቀር ሌላውን አላይምም አልሰማምም፡፡ የጽሁፍ ሰነድንም ጭምር የሚል ይመስላልና አዋቂነቴን እወቁልኝን ያስከትልና በታሪክ ምሁራን ትከሻ ተከልሎ፣ ብዙ በተደከመበት ስራ ላይ ምላስ ማውጣት መሆኑን ሳስብ ዓላማዎ ግራ ግብት ይለኛል፡፡
ሳይንስንና ትውፊትን፣ ነባራዊ ሁኔታዎችንና የአርኪዮሎጂ የምርምር ውጤቶችን ወዘተ ሁሉን አጣምሬ መጓዜን አልዘነጋም፡፡ ስለዚህ ከተሳሳትኩ ልታረም ልተች፣ ስህተቱ ሊነገረኝ ሲገባ ዝም ብሎ ሂስ አይሉት ዳሰሳ፣ ህፀጽ ፍለጋ አይሉት ምን ተረት ይባልልኛል
ምናልባት ሰው የተፈጠረው በፈጣሪ እጅ ነው የሚለው ገለፃዬ ፍፁም ጥላቻ አሳድሮብዎት ከሆነ ከላይ እንደገለጽኩት ይህ መጽሐፍ የተፃፈው የፈጣሪን ህልውና ለሚቀበሉ እንጂ ለማይቀበሉ አይደለም፡፡
ቅድም ..በመግባቢያው.. ላይ ያልኩትን እንዳሠፈርኩልዎ አሁን ደግሞ በመግቢያው ላይ ያልኩትን ልንገርዎ፡፡ ምክንያቱም ከምዕራፍ አንድ ስለጀመሩና መግቢያና መግባቢያውን አንብበውታል ብዬ ስለማላስብ ነው፡፡
.....ሳይንስ መነሻችንን ሊነግረን ቢዳዳም መድረሻችንን እስካላሳወቀን ድረስ ሁሌም ከጥያቄ አይድንም፡፡ ስለዚህ ሰው ከዱዳሌብ አፈር፣ ከኮሬብ እሳት ከአዜብ ነፋስና ከናጌብ ውሃ ተውጣጥቶ ተፈጠረ፤ ከፈጣሪው ነባቢነትን፣ ልባዊነትን፣ ህያውነትን አገኘ፤ የፍጥረታት የበላይ እንዲሆንም ተደረገ፡፡ ህግ ተሠጠው ያንን ህግ ተላለፈ፣ ቅጣቱም ሞት ሆነ፡፡ አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ፤ ሞትንም ትሞታለህ ተባለ፡፡ ይሄው ዛሬ ድረስ እየሞትን ነው፡፡ ሳይንስ ሞትን እስኪያስቀር ድረስ የትኛውን መነሻ መምረጥ እንዳለብን መድረሻችን በራሱ ስለሚነግረን ብዙ ማለት አያስፈልገንም፡፡
ምንም ቢሆን ግን የኢትዮጵያን ታሪክ በተመለከተ መፈናፈኛ የለም፡፡ በከርሰምድር ጥናት ቢባል በምን ያው የሰው ዘር መገኛነቷ የተረጋገጠ ነው...፡፡.. ብያለሁ (ገጽ 8) እየሞትን አይደለም እንዴ?
ወይስ የእርስዎ ሳይንስ ጦጣ መሰል የሚለው ነው?  አይ ወዳጄ! እሱማኮ ድሮ ጦጣ መሰል ነን ተብለን ተምረነው ነበር፡፡ በኋላ ግን የእነ ወይዘሮ ሠላም፣ የእነ እቴሜቴ አርዲ፣ የእነ አቶ ካዳሙ አጥንት ተቆፍሮ ሲወጣ ጦጣ መሠል አይደለንም ሰው መሰል ነን ተብሎ የትምህርት ኳርኩለሙ ተቀይሯል፡፡ ነገም ሌላ ሲወጣ ሌላ ትምህርት እንማራለን፡፡
የእርስዎ መሻት ይሄ ከሆነ ብዙ መጠበቅ ሊኖርብዎ ነው፡፡ መብትዎ ነው፡፡ ሞትን መነሻ አድርጐ ወደ እውነታው መቅረብ የሚሹ እንዳሉም አይዘንጉ፡፡
በእርስዎ አገላለጽ ..አባ ጋስፓረኒ፣ አቶ መላኩ በጐ ሰው፣ ብላቴን ጌታ ህሩይ ወልደ ስላሴ፣ ተክለፃድቅ መኩሪያ! ያሬድ ግርማ ታሪክ ፀሐፊዎች ሳይሆኑ የተረት አባቶች ናቸው፡፡.. ትልቁን ስህተትዎን ያየሁትም እዚህ ላይ ነው፡፡ አባ ጋስፓረኒ የአስመራ ካምቦኒ ኮሌጅ ዳይሬክተር የነበሩ ምሁር ናቸው፡፡ ብላቴን ጌታ ህሩይ ምንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቢሆኑ ለኢትዮጵያ ታሪክ የማይናቅ አስተዋጽኦ ያረከቱ ናቸው፡፡ ተክለፃድቅ መኩሪያ ማለት በአውሮፓ አገሩ ቤተመፃሕፍት እየተዟዟሩ በነጮች የተዘረፉብንን ሰነድ ሲያገላብጡ የኖሩና በከፍተኛ ደረጃና በልዩ ጥረት ፍሬ ነገር ያለው ታሪካችንን ጽፈው ትተውልን ያለፉ ከታላቅም ታላቅ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ የትምህርት ሚኒስትር ዲፕሎማት ሆነውም ሰርተዋል፡፡
እነሱንና ስራቸውን በማጣጣል የኛን ድንቁርና ለመጋረድ መሞከር ትልቅ የህሊና ብክነት ይባላል፡፡ የዛሬውን ዘመናዊውን የትምህርት ማዕረግ ይዞ ተጐልቶ ከሚያፈጥ ምሁር ያለ ቅድመ የማዕረግ ስም ለአገሩ ብዙ የሠራ ሰው በኔ ሚዛን ታላቅ ይሠኛል፡፡
ስለዚህ የዛሬዎቹ የታሪክ ፕሮፌሰሮች የፃፉት የቅርብ ዘመኑን ታሪክ ስለሆነ፣ ለቅርቡ ታሪክ እነሱን፣ ለፋቁ ታሪክ እነዚያን ተጠቅሜÃlhù”” እነሱን የጠቀሰ ፀሐፊ የረት አባቶች ቡድን ከተባለ እርስዎ ታሪክዎን ወይም ታሪክ የተማሩት እነሱ በፃፉት መጽሐፍ ስለሆነ የእርስዎ የማንነት ታሪክም ተረት ነው ማለት ይሆናል፡፡ እኔ ተበታትኖ ያለውን የኢትዮጵያ የታሪክ ሰነድ ገጣጥሜ ግዕዙን፣ አርኛውን፣ የሐውልቱን ጽሑፍ ወዘተ ተጠቅሜ የአገሬን ታሪክ ጽፌያለሁ፡፡ በእርስዎ እይታ የግዕዙ ሰነድ ተረት   ተረት ነው፡፡ ይግረምዎትና ግን ከዚህ በፊት በየጋዜጣው ቃለ ምልልስ ሳደርግ እንደገለጽኩት እናንተ ግዕዙን ተረት ስትሉት የውጭ ዜጐች ግን ዶክትሬታቸውን በግዕዝ ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ፡፡ ተረት ሊያነቡ? አይደለም ተረትነቱ ለእርስዎና ለመሰሎችዎ እንጂ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ተረት ሲጽፉ አልኖሩም፡፡ ተረት ለማውራት ጊዜ ያለው ማን እንደሆነም ያለፈው ሳምንት ጽሑፍዎ ያስረዳዎት ይመስለኛል፡፡
ኢትዮጵያ የታሪክ ሊቃውንት ይኖራት ይሆናል፡፡ ነገር ግን ከአፄ ቴዎድሮስ ወዲህ ያለውንና በአዝማሪ ስንኝ ለትውልድ የሚተላለፈውን ግልጽ ታሪክ እንጂ ሌላ ጽሑፍ አናገኝም፡፡ ስለዚህ የሊቃውንቱን ሊቃውንት መነሻ ከመድረግ ውጪ ምንም ምርጫ ይኖራል? የታሪክ ሊቃውንት የኢትዮጵያን የታሪክ መነሻና መድረሻ ጽፈው ከሆነ ከጠቀስኳቸው ውጪ ቢመሩኝ ደስ ባለኝ፤ ካለ ምን ገዶኝ? በአግባቡ ተጽፎ ከነበረማ ምን አደከመኝ? መነሻዬስ ምን ሆነና ያገሬ ታሪክ ተበታትኖ በገዛ ዜጐች ተንቆ ተሸራርፎ መቅረቱ ገርሞኝም አሳዝኖኝም እንጂ ሌላ ምን ልጠቀም ነው ይሄን ያህል መስዋዕት የከፈልኩት? መቸም ለጥቅም ብሎ አይሉኝም፡፡ በዚህ መሠረት ሂደት የገንዘብ ኪሳራ እንጂ ትርፍ እንደሌለው በራስዎ ያውቁታል ብዬ አምናለሁ፡፡ አንድ ነጭ እውነት ልነግርዎ እፈልጋለሁ፡፡ የድሮዎቹን የታሪክ ፀሐፍት የተረት አባት ለማለት የሚያስችልዎ ምንም የሞራል መሰረት የለዎትም፡፡ የእነርሱ ተረት ተረት ነው የሚል ሰው ተረት ያልሆነውን ከጐኑ አስቀምጦ ማሳየት አለበት፡፡ ገሎ ነው መፎከር የሚለው ብሒል በደንብ ይገልፀዋል፡፡ የተሻለ አማራጭ አቅርቦ ነው መናገር፤ ስለዚህ እንኳን እርስዎ ሊቃውንቱ እነዚያን ፀሐፍት የማጣጣል ሞራልም መብትም ብቃትም የላቸውም ለምድነው በ1936 ዓ.ም የታተመው የተክለፃድቅ መኩሪያ መጽሐፍ ያውም ከቴዎድሮስ እስከ ሃይለስላሴ ከ74 አመታት በኋላ በ2000 ዓ.ም እንደገና ታትሞ ወዲያው ያለቀው? ..ከልብነድንግል እስከ ቴዎድሮስም.. ጭምር በ74 አመታት ውስጥ ከሚሏቸው የታሪክ ሊቃውንት የተሻለ ጽሑፍ ጠብ ማለት ተስኖት? ወይስ ለምን? ባገሩ ቋንቋ ላገሩ ሰው መፃፍ የሚቀለውና የሚሰልጠውስ ማነው? ለማንኛውም ..የኢትዮጵያ የ5ሺ አመት ታሪክ ከኖኀኀ እስከ ኢህአዴግ.. የሚለው መጽሐፍ እርስዎ እንዳሉት ሳይሆን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ መምህራን ገምግመው ጉድለት ያሉትን ሞልተው፣ ስህተት ያሉትን አርመው ያሳለፉት እንጂ በኔ ይሁንታና በኔ ገንዘብ የታተመ አይደለም፡፡ እኔም ብሆን ከአክሱም እስከ ኑብያ ናፖታ፣ መርዌ የዛሬው ጀብል ባርካ ድረስ ተጉዤ የፃፍኩት እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ የእርስዎን አንዲት ተቃውሞ ብቻ ማግኘቴንም አልሸሽግም፡፡ Only text ብዬ ባስቀመጥኩት ስልክ ቁጥርና በኢሜል የደረሱኝ አስተያየቶችም 472 ሲሆኑ አንድም ተቃውሞ አልደረሰኝም፡፡ የጠቀሷቸው ምሁራን ሳይቀሩ የኢትዮጵያ አምላክ ይጠብቅህ ባዮች ናቸው፡፡  መጽሐፉም 5ሺ ኮፒ ታትሞ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተሠራጭቶ ያለቀና ለድጋሚ ህትመት የተዘጋጀ ነው፡፡ በርካታ የታሪክ ምሁራንም ወደ እንግሊዝኛ ሊተረጉሙት ዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ በአመቱ ከታተሙ መፃሕፍት ውስጥም በሽያጭ ረገድ 6ኛ ደረጃ ላይ መገኘቱን በሚዲያ የሰሙ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ለእርስዎ ተረት ለብዙሃኑ እውነት ሆኖ ይቀጥላል፡፡ በተረፈ አራት ኪሎ ላይ ሆነው ያራት ኪሎን ታሪክ ጽፈው በማሳተምዎና አንባቢዎን በማዝናናትዎ ሳላደንቅዎ አላልፍም፡፡ ..አጥቢያ..የምትለው መፃሕፍም ጥሩ ናት፡፡ እናም በዘርፍዎ ቢቀጥሉ ለማለት ነው፡፡

 

Read 4139 times Last modified on Saturday, 20 August 2011 10:54