Saturday, 20 August 2011 11:04

..እርግማንና ምርቃት´በእውነተኛ

Written by  ከጌታሁን ሽፈራው
Rate this item
(3 votes)
  • በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመርኩዞ የተፃፈ

ባለፉት አስራ አምስት ቀናት መንፈሱ ክፉኛ ታውኮ ነበር፡፡ በተለይ ትላንት ሌሊት በህልሙ ጣዕረሞት ሲያስጨንቀውና ሲያሰቃየው ነው ጐህ የቀደደው፡፡ ከእንቅልፉ እንደነቃ ሻወር ወሰደና ድካሙን ለማስታገስ ሞከረ፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት ለምርቃት አድርጐት የነበረውን ግራጫ ገበርዲን ኮትና ሱሪውን ከመሰል ሸሚዙ ጋር ለብሶ የመመረቂያ ጋዋኑን እንደያዘ ማንም ሳያስተውለው ከቤቱ ወጣ፡፡ መኪናውን አስነሳና በአካባቢው ከሚገኝ አነስተኛ ፀጉር ቤት ገብቶ ፀጉሩን፣ ፂሙን ከተስተካከለና ከአንዲት ካፌ ገብቶ ቡናውን ከጠጣ በኋላ ራሱን አነቃቅቶ በዝግታ እየነዳ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቅጥር ግቢ በማምራት ከተመራቂ እድምተኞቹ ጋር ተቀላቀለ፡፡

ምንም እንኳን ያለፉትን ጊዜያት ጭንቀት በተሞላበት ሁኔታ ቢያሳልፍም ዛሬ ግን ያ ሁሉ ፈተና የተወገደ መስሎ ተሰማው፡፡ ከሰባት ሺ በላይ የሚሆኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የምርቃት ስነስርዓት የሚያካሂዱበት የዩኒቨርስቲ ቅጥር ግቢና አካባቢው በተመራቂዎችና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ተጨናንቋል፡፡
ዳንኤል በማኔጅመንት በዲግሪ መርሃግብር ከሚመረቁት ተመራቂዎች መካከል አንዱ ነበር፡፡
ዳንኤል ይህንን የመመረቂያ ጋዋን ሲለብስ የዛሬው ለሁለተኛ ጊዜው ነው፡፡ ያኔ ከሁለት ዓመት በፊት መነሳነሱን ለብሶ ከዚህ ቅጥር ግቢ በወዳጅ ዘመድ ታጅቦ ሲወጣ ከተሰማው ስሜት ይልቅ ዛሬ በብቸኝነት ያደረገው ሥርዓተ ምርቃት እጅግ የተሻለ ነበር፡፡ የባለፈው ሁለት ዓመት የምርቃት ከበርቻቻ ከአሁኑ ጋር ሲለካ ከንቱና ፋይዳ ቢስ መሆኑ ተሰምቶታል፡፡
ፊቱ በደስታ እንዳበራ መኪናውን አስነሳና ወደሚጠብቁት ጓደኞቹ ዘንድ አመራ፡፡ ዛሬ ቁርጠኛና ጽኑ መሆኑን በጓደኞቹ ፊት ያስመሰክራል፡፡ እስካሁን በትግዕስት አምቆ የቆየውን ምስጢር ይነግራቸዋል፡፡ የእነኚህ እርኩስ ጓደኞቹን ተንኮልና ክፋት ሊነግርና ሊያሳፍራቸው አስቦ እንጂ ከነርሱ ጋር የዛሬውን ደስታ እንዲጋሩት አስቦ አይደለም ሊያገኛቸው የፈለገው፡፡ ከዚህ ቀደም የነበረው ወዳጅነቱ ብልጠት ላይ የተመረኮዘ የይስሙላ ወዳጅነት ነው በተለይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ፡፡ ዛሬ መመረቁን አምነው እጅ ይሰጣሉ፡፡ ከእንግዲህ ግን ዓይናቸውን አያይም፡፡ የነርሱ ክፋትና ምቀኝነት ለዚህ ታላቅ ድል ታላቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ..ምቀኛ አታሳጣኝ.. የሚባለው ተረት በርሱ ላይ እንደሰራ አሁን ተገንዝቦአል፡፡
መኪናውን በጥንቃቄ እየነዳ ኦሎምፒያ አካባቢ ከሚጠብቁት ጓደኞቹ ቤት ሲደርስ 6፡15 ሆኖ ነበር፡፡
ከስፍራው እንደደረሰ ጓደኞቹ አልአዛር፣ ሱራፌልና ያፌት አራት በአራት የሆነችውን የጳውሎስን ቤት አስጊጠው ፍቅር በተሞላበት ድባብ ..እንኳን ለዚህ ክብር አበቃህ.. በማለት በእቅፍ አበባ ተቀበሉት፡፡
ዳንኤል በኩራት ስሜት አበባውን ተቀብሎ ወደ ቤቱ ውስጥ ዘለቀ፡፡ የቤቱ ግድግዳ ..እንኳን ለዚህ ክብር አበቃህ.. የሚል ጽሑፍና ዳንኤል የመመረቂያ ጋዋኑን እንደለበሰ በስቲከር ላይ በተነሳው ፎቶ አሸብርቋል፡፡ ይህ ፎቶግራፍ ከሁለት ዓመት በፊት የተነሳው ፎቶ ነበር፡፡
ከዮሴፍ ከቅርብ ጓደኛው በስተቀር በነርሱ እጅ መግባቱ በጣም አስገርሞት ይበልጡኑ ትክ ብሎ ተመለከተው፤ ያው እንደቀድሞው ዓይነት ፎቶ ነበር፡፡ ..ይህን ፎቶ ከየት አመጣችሁት.. አለ በንዴትና በአግራሞት፡፡ ከዚህ በኋላ ምንም እሹሩሩ አያስፈልጋቸውም ብሎ አሰበና፡፡ ሆኖም የሰማው ማንም አልነበረም፡፡ ፎቶግራፍ በእነርሱ እጅ እንዴት ሊገባ እንደቻለ ያብሰለስል ጀመር፡፡ ጥቂት እንደቆየ ከደጅ የመኪና ሞተር ድምጽ ተሰማ፡፡ ወዲያው ዮሴፍ ጳውሎስና ፓስተር ዴቭ እነርሱ ወዳሉበት ክፍል ገቡ፡፡ ጳውሎስና ዮሴፍ ሞቅ ያለ ሰላምታና መልካም ምኞታቸውን ገለለት፡፡ ፓስተር ዴቭ ግን እጁን እንደያዘ ቆየና ..እግዚአብሔር የእርግማን ቀንበሩን ሰብሮልሃል.. ካለው በኋላ ..ስላንተና ስለቤተሰብህ ሁኔታ እንደሰማሁ የእግዚአብሔር እርዳታ እንደሚያስፈልጋችሁ አሰብኩ፡፡ በምንም መልኩ የአባት ሃጢያትና በደል በልጅ መከፈል እንደሌለበት በሚገባ እረዳ ነበር፤ ስለሆነም አባትህንና ጉዳዩ የሚመለከተውን ተበዳይ አነጋግሬ ችግሩን ለመቅረፍ ሙከራ አድርጌ ነበር፤ ሆኖም በወቅቱ አልተሳካልኝም፡፡ ስለዚህ ላንተ ፀሎት ማድረግ ጀመርኩኝ፤ ጓደኞችህን አነጋገርኩኝ ያቋረጥከውን ትምህርት በምን አይነት ግፊትና የእግዚአብሔር ሃይል መቀጠል እንዳለብህ አሰብኩ፡፡ ጥረቴና ፀሎቴ በእግዚአብሔር ድጋፍ ተሳካ፡፡ ሁሉም ነገር በጽኑ እምነትና ፀሎት እንደሚሸነፍ በማወቅህ ደስ ብሎኛል፡፡ በመጨረሻም ልመናችን ያንተን ልብ አደላደለ፤ የአባትህንም ደንዳና ልብ ሰበረ፡፡.. አለና የሆቴል ቤት ምርቃት የሚል አንድ ወረቀት አውጥቶ ሰጠው፡፡
ዳንኤል ወደ ፓስተር ዴቭና ወደ ጓደኞቹ በመገረም መመልከት ጀመረ፡፡ ሁሉም በፍቅር ዓይን እንደሚመለከቱት አስተዋለ፡፡
ጥቂት ቆየና ስለ ፓስተር ዳንኤል የሰማውን ማሰላሰል ጀመረ፡፡ ይህ ሰው እጅግ ታላቅ መንፈሳዊ አባት እንደሆነ ያውቃል፤ አጋንንት በእግዚአብሔር ስም እንደሚያስወጣ ምዕመኖች የመሰከሩለት ሰው ነው፤ መጀመሪያ ይህን ሰው ያየበትን ቦታ አይረሳውም፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ በርሱ ምርቃት ሥርዓት ላይ ከጽዮን ሆቴል አዳራሽ ውስጥ ተገኝቶ በጆሮው ሹክ ያለውን ነገር አይዘነጋውም፡፡ ..አትጨነቅ፣ በጠንካራ እምነት ሁሉም ነገር ይሸነፋል፡፡ አንተ ግን በፀሎትህ ትጋ እምነትህን አጠንክር፡፡ ካሁን ሰዓት ጀምሮ ትምህርትህን ለመቀጠል ራስህን አዘጋጅ.. ያለው ቃል እስካሁን ድረስ ጆሮው ላይ ያንቃጭልበታል፡፡
ይህ ሰው ይህንን እንዴት ሊለኝ ቻለ? ስለኔ እንዴት ጠልቆ አወቀ? እያለ ያሳስበው ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ከሁለት አመት በኋላ ከጓደኞቹ ጋር የጠበቀ ግንኙነት በርሱ ጉዳይ መመስረቱን እያወጋው ነው፡፡
እዚህ የተገኙት የዳንኤል ጓደኞች ከሴይንት ጆሴፍ ት/ቤት ከ1ኛ ክፍል ጀምሮ እስከ 12፤ ከዚያም አልፎ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እስኪከታተሉ ድረስ ጠንቅቆ ያውቃቸዋል፡፡ በእርግጥ ዳንኤል ከሱራፌል፣ አልአዛርና ያፌት የበለጠ የሚዋደደው ከዮሴፍ ጋር ነው፡፡ ሴይንት ጆሴፍ ት/ቤት የወጣት ወንዶች ትምህርት ቤት እንደመሆኑ ሁሉም ተማሪዎች ከመሰል ጓደኞቻቸውና ከክፍል ልጆች ጋር የመቧደን ባህርይ ይታይባቸዋል፤ እየጐረመሱ ሲመጡ ይሄው ባህርይ እየጐለበተ ይበልጡኑ በስሜትና በአዋዋል የሚመሳሰሉ ልጆች ቅርርባቸውን እያጠናከሩና ከማይመሳሰሉዋቸው ጋር እየተራራቁ መሄዳቸው፣ ለስሜታቸው የሚኖሩበት ዕድሜ እየደረሰ መምጣቱን ያመላክት ነበር፡፡ ስለሆነም ከብዙ ጓደኞች መካከል ዳንኤል፣ ዮሴፍ፣ ሱራፌል፣ ያፌትና አልአዛር ይበልጡኑ ይቀራረቡ ነበር፡፡ የሴይንት ጆሴፍ ትምህርታቸውን ሊጨርሱ ገደማ ከትምህርት ውጭ እየተገናኙ አልበረካና አረቢያን የመሳሰሉት ቦታዎች ጫት ይቅሙ ነበር፡፡ የሚያመሹበት ክበብም ተመሳሳይ በመሆኑና እስከ ዩኒቨርስቲም አብረው መዝለቅ በመቻላቸው ከሌሎች ጓደኞቻቸው ይልቅ የቀረበ ትስስር መፍጠር ችለዋል፡፡
ሆኖም እንደአብዛኛዎቹ ወጣቶች በምሽት ክበብ ያጠመዱዋቸውን ሴት ወጣቶች የመነጣጠቅ ባህርይ ስለነበረባቸው አልፎ አልፎም ቢሆን መጠነኛ ግጭትና መቃቃር በመሃላቸው መፈጠሩ አልቀረም፡፡
ዳንኤል ይበልጡኑ ከባለፀጋ ቤተሰብ በመገኘቱና የገንዘብ እጥረት ስለሌለበት፣ እነሱራፌል ደግሞ አንደበተ ርቱዕ የሆነ ምላስ ስላላቸው፣ በምላሳቸው ደልለው ያመጧቸውን ኮረዶች በገንዘብ እያማለለ ይነጥቅብናል በማለት አልፎ አልፎ መቃቃር ይከሰት ነበር፡፡ ስለዚህም ነው የዛሬ ሁለት ዓመት ዳንኤል ሲመረቅ ከቅርብ ጓደኛው ዮሴፍ በስተቀር እነሱራፌል የርሱን መመረቅ እንዲሰሙ ያልፈለገው፤ ምክንያቱም እጅግ የበለጠ ውስጥ አዋቂ ከሆኑ የቆየ ቂማቸውን ይዘው ወሬ በመንዛት ችግር ሊፈጥሩ ይችላሉ ተብሎ ስለተሰጋ ጭምር ነው፡፡ ሆኖም የተፈራው አልቀረም፡፡ አንድ ቀን ዮሴፍ፤ እነሱራፌል የዳንኤልን የምርቃት ሥርዓት ሰምተው በመገረም ተንኮል እንዳሰቡ አልበረካ አብሮዋቸው ሲቅም መስማቱን ለዳንኤል ነገረው፡፡
ዳንኤል ተበሳጭቶ ምን መደረግ እንዳለበት ዮሴፍን ሲያወያየው ..ትምህርትህን ማጠናቀቅ እንደሚገባህ ምንም አማራጭ የለውም፤ እስከዚያው ድረስ ግን ከነርሱ ጋር ያለውን ግንኙነት ጠበቅ አድርጐ በዘዴ መያዝ ያስፈልጋል፡፡ ያለዚያ ግን አንተም ሆንክ ቤተሰብህ ታላቅ ውርደት ላይ ትወድቃላችሁ.. በማለት ስጋቱን ከገለፀለት በኋላ ነው ትምህርቱንም ለመቀጠል ከነርሱ ጋር የነበረውን ወዳጅነትም ጠበቅ ለማድረግ የተገደደው፡፡
ዳንኤል ከሁለት ዓመት በፊት kዩኒቨርስቲW ቅጥር ግቢ ድረስ ከእናት አባቱና ከጓደኛው ዮሴፍ ጋር ታጅቦ በመምጣት ከሆቴሉ አዳራሽ መድረክ ላይ ተቀምጦ ነበር፡፡ የዮን ሆቴልን አዳራሽ የሞሉት ወዳጅ ዘመዶች ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉላቸው፡፡
በአዳራሹ እንኳን ደስ ያለህ ለማለት የተገኙት ዘመዶችና የአባቱ ወዳጆች ለዚያች ታሪካዊ ቀን ልዩ ትኩረት የሰጡት ይመስላል፡፡
ለዚህም ምክንያቱ የዳንኤል አባት አቶ ትዕግስቱ ከገጠር አዲስ አበባ ከፈለሱ ከልጅነት ጊዜያቸው ጀምሮ በንግድ ዓለም ከአቶ ምትኩ ጋር በሸሪክ ከአትክልት ተራ መደብ ከመያዝና አትክልት ከመነገድ አንስቶ ንግዳቸውን በማጧጧፍ የሆቴል ንግድን ጨምሮ በጋራ አራት ሱቆችን በተለያዩ ቦታዎች ለመክፈት ችለዋል፡፡ ነገር ግን አቶ ምትኩ በግላቸው በሚጥሉት ዕቁብ ባለዕዳ በመሆን ሸሪክ ከገቡበት ሱቅ ላይ ዕዳ ትተው ስለነበር አቶ ትዕግስቱ የአቶ ምትኩን ዕዳ ከድርሻቸው ላይ አንስተው ለመክፈል በመገደዳቸው የጋራ የንግድ እንቅስቃሴያቸው እየተዳከመ በመምጣቱ አቶ ትዕግስቱ የሸሪካቸውን ዕዳ በማስገመት ቀሪውን የገንዘብ ግምት ሰጥተው ሱቁን ለብቻቸው ጠቅለው ያዙት፡፡
ይህ አካሄድ ቅሬታ የፈጠረባቸው የአቶ ምትኩ ወዳጅ ዘመዶች ቅራኔውን ለመፍታት ቢሞክሩም ችግሩ ባለመፈታቱ በሀገራቸው ደንብና ባህል መሠረት በሽማግሌዎች ፊት እውነታውን በመሀላ እንዲያረጋግጡ ተገደው ነበር በመሆኑም ተበደልኩ ባይ አቶ ምትኩ፤ አቶ ትዕግስቱ የኔ ሀቅ ከሌላቸው መሀላ ያድርጉና እንለያይ በማለታቸው፣ አቶ ትዕግስቱ ..ልጆቼን ለወግ ማዕረግ አያብቃልኝ.. ብለው በሀገር ሽማግሌ ፊት ምለው ለመለያየት በቅተዋል፡፡
ከዚህ በኋላ በርካታ አመታቶች አለፉ፡፡ አቶ ትዕግስቱ ሀብታቸው እያደገ፣ በሚሊቴሪና ተራ በኮልፌ ታላላቅ ሱቆችንና ይዞታዎችን አጠናከሩ፡፡ የጫማ ሱቆች፣ ጣቃ ሱቅ፣ የወፍጮ ቋት መሸጫ ሱቆችን ከመክፈት አልፈው አስመጭና አከፋፋይ በመሆን ጫማ ፋብሪካና ዱቄት ፋብሪካዎችን አቋቋሙ፡፡ ከዚያም አልፎ በኮልፌ አካባቢ በነበራቸው ሰፊ የግል ይዞታ ላይ ፎቅ ለመገንባት እየተንቀሳቀሱ ነበር፡፡ ልጆቻቸውም ያለ ችግር እየተማሩ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እየደረሱላቸው መጡ፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸው ግን የህክምና ትምህርቱን በማጠናቀቂያው ዓመት ኢንተርንሺፕ ውስጥ እያለ በአዕምሮ ህመም ተለክፎ ትምህርቱን ከማቋረጡም በላይ በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ጤንነቱ ታውኮ ለሞት ተዳረገ፡፡
ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ሁለተኛዋ ሴት ልጃቸው ልትዳር ቀለበት ካሰረች በኋላ በድንገተኛ ህመም ህይወቷ አለፈ፡፡
እነዚህ ድንገተኛ ክስተቶች የአቶ ትዕግስቱን ባለቤትና ልጆች አንገት ሲያስደፋ፣ በአቶ ምትኩ ዘመድ ወዳጆች መካከል ግን ሌላ አሉባልታ እንዲስፋፋ መንገድ ከፈተ፡፡
አቶ ትዕግስቱ የሸሪካቸውን የአቶ ምትኩን ገንዘብ ስለካዱና በልጆቻቸው ስም ስለማሉ ..የእርግማን መቅሰፍት ደርሶባቸው ነው.. የሚለው ወሬ በከተማና በገጠር እየሰፋ መጣ፡፡ አቶ ትዕግስቱ ግን ወይ ፍንክች አሉ፡፡ ይህ ተራ አሉባልታና ግጥምጥሞሽ እንጂ እኔ ሀብት ያፈራሁት በወዜና በላቤ እንጂ በክህደት የመጣ ባለመሆኑ ማንንም ይቅርታ አልጠይቅም አሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ግን በዳንኤል ስነልቦና ላይ ከፍተኛ ችግር እያስከተለ መጣ በዚህ ሁኔታ የዳንኤል እናት ታላቅ ጭንቀት ውስጥ ሲወድቁ ዳንኤልም በደረሰበት የስነልቦና ችግር የሁለት ዓመት ተኩል የዩኒቨርስቲ ተማሪ እያለ ትምህርቱን ለማቆም ተገደደ፡፡ ዳሩ ግን የትምህርቱን ማቆም ቤተሰቦቹ አያውቁም ነበር፤ ስለሆነም ወራት አልፎ አመታት ሲተኩ የቁርጡ ቀን እየደረሰ መጣ፡፡ የምርቃቱ ቀን ሊደርስ 15 ቀን ሲቀረው አማራጭ ያልነበረው ዳንኤል መላ የማያጣውን ሞተረኛውን ጳውሎስን አወያየና ፎልደሩን አሰርቶ፣ ጋዋኑን ተከራይቶና የምረቃ መግቢያውን ካርድ ለምኖ በቤተሰብ ፊት ተመራቂ መስሎ ቀረበ፡፡
አቶ ትዕግስቱ እርግማኑ በርሳቸው ላይ እንደማይሰራ ያረጋገጡበት የዳንኤል ምርቃት፣ ታላቅ ደስታ ፈጥሮባቸው ነበር፡፡ አቶ ትዕግስቱ በታላቅ ግርማ ሞገስ ከጽዮን ሆቴል አዳራሽ ተገኝተው እንግዶችን በፈገግታ በማስተናገድ ስራ ላይ ተወጥረዋል፡፡
አዲስ በሚገነቡት ህንፃ ላይ ሱቅ ለመክፈት የሚፈልጉ የንግድ ወዳጆቻቸው ..እንኳን ደስ ያለህ.. በማለት ለዳንኤል ወርቅና የተለያዩ ውድ ጌጣጌጦችን በስጦታ አዥጐደጐዱለት፡፡
ባለሀብቱ የአቶ ትዕግስቱ ወንድም በዚህ የምረቃ ሥርዓት ላይ የመኪና ቁልፍ በስጦታ ለዳንኤል ሲያበረክቱ፣ አቶ ትዕግስቱም ቃሊቲ አዲስ የከፈቱትን የጫማ ፋብሪካ በልጃቸው ስም ስጦታ ማድረጋቸውን አበሰሩ፡፡
በዚህ መሀል ነበር ፓስተር ዴቭ በምርቃቱ ላይ ተከስቶ ያንን የማይረሳውን ንግግር በጆሮው ሹክ ያለው ..አትጨነቅ በጠንካራ እምነት ሁሉም ነገር ይሸነፋል፡፡ አንተ ግን በፀሎትህ ትጋ፤ እምነትህን አጠንክር ካሁን ሰዓት ጀምሮ ትምህርትህን ለመቀጠል ራስህን አዘጋጅ.. ያለውን ቃል አይረሳውም፡፡ ይህ የሆነው የዛሬ ሁለት ዓመት ነው፡፡ ዛሬም ፓስተር ዴቭ ከዚህች ጠባብ ቤት በትክክለኛው ምርቃት ላይ ተገኝቷል፡፡ ያኔ ..እንኳን ለዚህ ክብር አበቃህ.. አላለውም፡፡ ዛሬ ግን ..እንኳን ለዚህ ክብር በቃህ.. ብሎታል፡፡ የያኔ ምርቃት በሀሰት የተቀነባበረ እንደነበር ፓስተር ዴቭ ጠንቅቆ እንደሚያውቅ ተረዳ፡፡ አሁን ያኔ ያለው ቃል በግልጽ ገባው፡፡ የዳንኤል ጓደኞች በፓስተር ዴቭ የእጅ አዙር ግፊት በማስፈራራት በቀና መንፈስ ለዚህ ምርቃት እንዳበቁት ተገነዘበ፡፡ የሆቴል ቤት ምርቃት የሚለውን የግብዣ ካርድ አነበበ፡፡ አባቱ ለአቶ ምትኩ ኮልፌ በነበራቸው ይዞታ ላይ ሆቴል ቤቱን እንደሰጧቸው ካርዱ ላይ የሰፈረውን አድራሻ አንብቦ ተረዳ፡፡ አሁን ምንም የሚጨነቅበት ጉዳይ የለም፡፡ ሁለቱ ባንጣዎች እርቅ አድርገዋል፡፡ የመርገምት ቀምበሩም ተሰብሯል - እድሜ ለፓስተር ዴቭ! በፍቅር ስሜት እንደተሞላ እመር ብሎ ጓደኞቹን ጥብቅ አድርጐ በማቀፍ ሳማቸው፡፡ ወዲያው ደግሞ ፓስተር ዴቭ እግር ሥር ለመውደቅ ሞክሮ በርከክ አለ ፓስተሩ እጆቹን በማከላከል እንዲነሳ አደረገውና ..ይህ ሁሉ የእግዚአብሔር ድንቅ ስራ ነው፡፡.. በማለት ተናገረ፡፡

 

Read 7211 times Last modified on Saturday, 20 August 2011 11:07