Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 27 August 2011 13:18

ራስህን ካላሸነፍክ በራስህ ትሸነፋለህ!

Written by 
Rate this item
(11 votes)

ያለምንም ጥርጥር ስኬትንየምንተነፍሰውን ያህልእንፈልገዋለን፡፡ ከተወለድንባት ቅጽበት አንስቶ የበለጠ ለማድረግ፣ የበለጠ ለማግኘት፣ የበለጠ ለመሆን እንሻለን፡፡ ስኬት ወደ ፍጽምና ለመድረስ መትጋት እንደሆነ አዕምሮአዊ ምስል ቢኖረንም እውነታው ግን የበለጠ ተፈጥሮአዊ መሆኑ ነው፡፡ ስኬት በውስጣችን ያለውን ወይም የተቀመጠውን እምቅ ህልም ወይም ሃይል የማውጣት ድፍረት ነው ተብሎ ሊገለጽ ይችላል፡፡ ትንፋሽ የመስጠት ዕድል ነው ቢባልም ያስኬዳል፡፡ አብዛኛው ሰውን ግን ይሄን ጉዳይ አይሞክረውም ምክንያቱም አደገኛ መስሎ ስለሚታየው ነው - የተለመደ የአዘቦት ቀን ተግባር አይደለምና፡፡ ከነገሩ ጋር ለተለማመዱ ሰዎች ግን የተለመደ የህይወት ጐዳናቸው ነው፡፡ እነሱ ቤተኛ ናቸው፡፡

ብዙ ወይም የበለጠ የመሻት ስሜት አንዳንድ ጊዜ በአስተዳደጋችን ወይም በባህላችን የተነሳ ከውስጣችን የሚጠፋበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ስለዚህም ከህይወት የምንጠብቀው ዝቅ ያለና ከዕፁብ ድንቅ ያነሰ ነገር ይሆናል፡፡ ሆኖም ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም፡፡ ለስኬት ያለን ፍላጐት ዳግም ሊነቃቃና ሊነሳሳ ይችላል፡፡ ዳግም ዕፁብ ድንቅ ህይወት ልንሻ እንችላለን፡፡ ከስኬት ጋርም ቤተኛ እንሆናለን፡፡
ስኬት ሁሉ ግን ስኬት እንዳልሆነ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ አንዳንዶች ህይወታቸውን ሁሉ የስኬትን መሰላል ሲወጣጡ ከርመው የማታ ማታ መሰላሉ ትክክለኛው ግድግዳ ላይ ተደግፎ እንዳልነበረ ይገነዘቡታል - እናም ስኬታቸው ትክክለኛው ወይም እነሱ የሚሹት አልነበረም ማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው ትክክለኛውን ስኬት መቀዳጀታችንን ማረጋገጥ ያለብን፡፡ የእኛን የተሟላ ሰብዕናና ችሎታ በአስደናቂ መንገድ መግለጽ የሚችል ሊሆን ይገባል ስኬታችን፡፡ ስኬት አንዲት ነጠላ ሁነት ወይም ውጤት አይደለችም - በውስጣችን ያለ ድንቅ ተሰጥኦ መገለጫ እንጂ፡፡ ዓለም ይሄንን ተሰጥኦ የበለጠ ሰዋዊና የበለጠ ውብ እንድናደርገው ህልቆ መሳፍርት ዕድሎችን ታቀርብልናለች፡፡
ተሰጥኦአችንን ወይም የነፍሳችንን ጥሪ ፈልጐ ማግኘት ግን የኛ ተግባር ነው፡፡
እውነተኛ ስኬት ለማሸነፍ ሲባል ብቻ የማሸነፍ ጉዳይ አይደለም፡፡ ቲሞቲ ጋልዌይ የተባለ የስኬት ሊቅ እንዲህ Y§L- ..ማሸነፍ አንድ የሆነ ግብ ላይ ለመድረስ መሰናክሎችን ማለፍ ነው፤ የአሸናፊነቱ ትልቅነት የሚለካው ግን በተደረሰበት ግብ ትልቅነት ነው..
ሆኖም ግን የማሸነፍ አባዜ ተጠናውቶን ብቻ የምንቀዳጀውን ጊዜያዊ ስኬት ህይወታችንንና የሌሎችን ህይወት ከሚያበለጽግልን ዘላቂ ስኬት መለየት መቻል አለብን፡፡ ትክክለኛውና ዘላቂው ስኬት የዓለምን ሃብት በከፍተኛ ሁኔታና ያለብዙ ብክነት ጥቅም ላይ ያውላል፡፡
የስኬት መርሆች ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል ተስፈኝነት (ደግ አሳቢነት) አንዱ ነው፡፡ ትላልቅ ችግርና መከራዎችን አሸንፈው ስኬትን የተቀዳጁ ሰዎች ሁሉ ምስጢር እንደሆነም ይነገራል፡፡ ኔልሰን ማንዴላ፣ ኧርነስት ሻክሌተን፣ ኢሊኖር ሩስቬልት - የመከራ ጊዜያቶችን ተቋቁመው ለማለፍ ያስቻላቸው በአዎንታዊ ነገሮች ላይ የማተኮር ችሎታቸው እንደሆነ በይፋ ይቀበላሉ፡፡ እኒህ ሰዎች ክላውዴ ብሪስቶል የተባለው ሊቅ ..የእምነት ተዓምራዊ ሃይል.. የሚለው ነገር ገብቶአቸዋል ማለት ነው፡፡
ታላላቅ መሪዎች እንዲሁ ደረቅ እውነታን ፊት ለፊት የመጋፈጥ ያልተለመደ ችሎታ እንዳላቸው ይነገራል፡፡ ለዚህ ብቸኛ ሃይላቸው አድርገው የሚቆጥሩት ደግሞ ቆራጥነት የተመላበትን ተስፈኝነታቸውን ነው፡፡ ተስፈኛ ሰዎች የሚሳካላቸው ነገሮች ጥሩ ይሆናሉ ብለው ስለሚያምኑ ብቻ አይደለም፤ ስኬትን መጠበቃቸውም ተግተው እንዲሰሩ ስለሚያደርጋቸው ጭምር ነው፡፡ ከህይወት የምንጠብቀው ትንሽ ነገር ከሆነ ትንሽ ሙከራ እንኳን ለማድረግም አንነሳሳም፡፡ ከፍ ያለ ነገር ስንጠብቅ ብቻ ነው ጥረታችንም ከፍ ያለ የሚሆነው፡፡
ስኬት የታመቀ ጥረት ይፈልጋል፡፡ አብዛኞቹ ሰዎች ጉልበታቸውን (ሃይላቸውን) በብዙ ነገሮች ላይ ይበታተኑታል፡፡ በዚህም የተነሳ በምንም ነገር የላቀ ውጤት ማስመዝገብ ይሳናቸዋል፡፡ ኦሪስን ስዌት ማርደን ይሄን በተመለከተ ሲናገር ..ዓለም ጠበቃ፣ ሚኒስትር፣ ሃኪም፣ ገበሬ፣ ሳይንቲስት ወይም ነጋዴ እንድትሆን አትጠይቅህም፤ መስራት ያለብህን አትነግርህም፤ ነገር ግን በምትሰራው ማናቸውም ሥራዎች የበቃህ እንድትሆን ትጠይቅሃለች..
ስለዚህም ስኬታማ ለመሆን የላቀ ዓላማና ግብ ሊኖርህ ይገባል፤ ያንን ለማሳካትም በቁርጠኝነት ጥረትህን መግፋት አለብህ፡፡
የዓለም ሥልጣኔ ጐህ ሲቀድ አንስቶ የነበሩ ታላላቅ መሪዎች ሁሉ የየራሳቸው ህልም የነበራቸው ናቸው፡፡ ህልም ሳይኖርህ ስኬት የሚታለም አይደለም፡፡
ሃብትና ብልጽግናን በምናብህ ሳትቀርጽ በባንክ ሂሳብህ ውስጥ ከቶውንም ልታይ አትችልም፡፡ የሚቀድመው የምትሻውን በምናብህ መሳል ነው፡፡ ከዚያም በእውንህ ታየዋለህ፡፡
ግን ህልም ከየት ይፈጠራል? Think and Grow Rich  (አስብና በልጽግ እንደማለት) የተሰኘው ድንቅ መጽሐፍ ደራሲ ናፖሊዮን ሂል፤ ህልም እንደ እሳት ከሚንቀለቀል ውስጣዊ ፍላጐት ይወለዳል ይለናል፡፡ ህልም ከችላ ባይነት፣ ከስንፍና ወይም ከፍላጐተ - ቢስነት አይፈጠርም፡፡
የስኬታማ ሰዎች ሌላው መርህ ለመሥራት ፈቃደኛ መሆን ነው - አንድ ድንቅ የሆነ ነገር ለመፍጠር ሁሌም ተግተው ይሰራሉ፡፡ ተግተን በሰራን ቁጥር ስለራሳችን አንድ ነገር እናውቃለን፡፡ የስኬት ህግ እንደሚለው አንድ ጊዜ ስኬትን ከተቀዳጀን እንዲዘልቅ የሚያደርገው ሁኔታ ራሱ ይፈጥራል፡፡
እንደ ስኬት የሚቀጥል ምንም ነገር የለም ይባላል፡፡ ዘላቂ ስኬት የሚገነባው በዲሲፕሊን ላይ እንደሆነ ማወቅ ብልህነት ነው፡፡ ለራሳችን ትዕዛዝ መስጠትና ትዕዛዙን መከተል መማር አለብን፡፡ ይሄ ጉዳይ ለጊዜው አሰልቺ ሊመስለን ይችላል፡፡ የረዥም ጊዜ ውጤቱ ግን አስደማሚ ይሆናል፡፡ ታላላቅ ስኬታማ ሰዎች ዩኒቨርስ የተገነባው በአቶሞች እንደመሆኑ ስኬት ደግሞ በእያንዳንዷ ደቂቃ እንደሚገነባ አሳምረው ÃWÝlù””በእርግጥ ለዛሬው ዘመን ህልመኞች ትዕግስትና ክፍት አዕምሮ ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው፡፡ አዳዲስ ሃሳቦችን ለመቀበል የሚፈሩና ዝግጁ ያልሆኑ ሰዎች ገና ሳይጀምሩ ያከተመላቸው ናቸው፡፡ ልትሰራ የምትፈልገው ነገር ትክክለኛና የምታምንበት ከሆነ ሳታወላውል አድርገው ይላል ናፖሊዮን ሂል፡፡ እወድቃለሁ ብለህ አትፍራ፡፡ እያንዳንዱ ውድቀት አቻውን የስኬት ዘር ይዞ ይመጣልና፡፡ የስኬትና የብልጽግና ሌላው መርህ ጥብቅ የሆነ እምነት ነው፡፡ በእርግጥ አንድን ነገር መፈለግ ወይም መመኘትና የፈለጉትን ነገር ለመቀበል ዝግጁ መሆን የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ማንም ሰው አንድን ነገር እንደሚያገኘው እስካላመነ ድረስ ለዚያ ነገር ዝግጁ ነው ማለት አይቻልም፡፡ አዕምሮው ተስፋና ምኞት ላይ ሳይሆን እምነት ላይ ማተኮር አለበት፡፡ ያውም ጥብቅና የማይናወጽ እምነት፡፡ ያኔ ነው ያሻውን በእጁ የሚያስገባው፡፡ ለእምነት ደግሞ ክፍት አዕምሮ ወሳኝ ነው፡፡ የዝግ አዕምሮ ባለቤቶች ለማመን አይነሸጡም፤ ናፖሊዮን እንደሚለው፡፡ ምናብ ዕቅዶች የሚፈጠሩበት ዎርክሾፕ ነው ይላል - ሂል፡፡ ፍላጐትህ መልክና ቅርጽ የሚይዘው እንዲሁም ወደ ተግባር የሚለወጠው በምናብህ እገዛ ነው፡፡ በምናብህ የቀረጽከውን ማናቸውንም ነገሮች መፍጠር ወይም ማድረግ ትችላለህ፡፡
ለተግባር ቸልተኛ ከሆንክ የምናብህ አቅም እየተዳከመ ሊመጣ ይችላል፡፡ ሙሉ በሙሉ ባይሞትም ለጊዜውም ቢሆን ያንቀላፋል፡፡ ሆኖም ጥቅም ላይ ስታውለው ከእንቅልፍ ሊነቃና ሊታደስ ይችላል፡፡ ራስህን ካላሸነፍክ በራስህ ትሸነፋለህ ይላል - ናፖሊዮን ሂል በመጽሐፉ፡፡ የውድቀት ዋና ሰበቡ ለውሳኔ ዳተኛ መሆን ወይም መወሰን አለመቻል ነው፡፡ የሌሎች ሃሳብ ወይም አስተያየት ተጽእኖ የሚያሳድርብህ ዓይነት ሰው ከሆንክ የራስህ ፍላጐት አይኖርህም፡፡ የራስህን ውሳኔ በመወሰንና በመከተል ለራስህ ፍላጐት ተገዢነትህን አሳይ፡፡ የራስህ ሃሳብና አዕምሮ እንዳለህ አትዘንጋ፤ ስለዚህም ተጠቀምበት፡፡
በእርግጠኝነትና በፍጥነት ውሳኔ ላይ የሚደርሱ ሰዎች የሚፈልጉትን ያውቃሉ ብቻ ሳይሆን ያገኙታልም፡፡ በየትኛውም የህይወት ዘርፍ ላይ የሚገኙ መሪዎች በፍጥነትና ፈርጠም ብለው የሚወስኑ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው መሪ የሆኑት፡፡ የሁሉም ስኬት መነሻ ፍላጐት ነው፡፡ ፍላጐታችን ደካማ ሲሆን ውጤቱ ደካማ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ሃብትና ስኬት አጥብቀው ሊፈልጉ ይችላሉ፡፡ ችግሩ ግን ጽናት ይጐድላቸዋል፡፡ የሚፈልጉትን ለማግኘት በሚያልፉት ሂደት በሚገጥማቸው ትንሽ ፈተና ወይም መሰናክል እጃቸውን ይሰጣሉ፡፡ ይሸነፋሉ፡፡ ገንዘብና ሃብት ወይም ስኬት ቶሎ የሚሳቡት አዕምሮአቸው እነዚህን ለመቀበል ዝግጁ ወደሆኑት ነው፡፡ ድህነትም የሚሳበው ድህነትን ለመቀበል ዝግጁ ወደሆነው አዕምሮ ነው፡፡ የጽናትን ልማድ ያዳበሩ ሰዎች የሽንፈት ዋስትና አላቸው፡፡ የቱንም ያህል ጊዜ ቢሸነፉ በመጨረሻ የስኬት ጣራ ላይ መውጣታቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

 

Read 15266 times Last modified on Saturday, 27 August 2011 13:28