Saturday, 27 August 2011 13:50

የጥበብ ፍርድ ቤት

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(1 Vote)

ፍርዱ ይቀጥላል፡፡ ወንጀለኛው ወንጀለኛ የተባለው በጥበብ መለኪያ እንጂ በፍትሐ ብሔር ስላልሆነ ቅጣቱም ፍርዱም ይለያያል፡፡ ተከሳሽ ታስሮ አይቀርብም፡፡ ዘና ብለው ተቀምጠው እንደ ማሕበር ጠበል ፀዲቅ እየቀመሱ ሊሆን ይችላል ፍርዱ የሚካሄደው፡፡. . . ላዳብረው ወይንስ እንደ አመጣጡ በፍጥነት ላፍርጠው? የሚያስብሉ አንዳንድ ሐሳቦች አሉ፡፡ ይህ አሁን የምፈው ሐሳብ ብልጭ ካለ ሰላሳ ደቂቃ አይሞላውም፡፡ አንባቢው እና እኔ ለመጀመሪያ ጊዜ በላይቭ ትራንስሚሽን ግንኙነት እያደረግን ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ሲሰረዝ እና ሲደለዝ ባልቆየ ሁፍ . . . እንደወረደ አሰፍረዋለሁ፤ እንደሰፈረ ታነቡታላችሁ፡፡ አንዳንዴ ብልጭ እንዳለ እሳቱን አያይዞ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ብልጭ ማለቱ ድንገተኛ እና ፈጣን አጋጣሚ ይመስላል እንጂ . . . ሳይፈተግማ ያልከረመ ነገር ብልጭ አይልም፡፡

ሀሳቡ የሚከተለው ነው:- ፍትህ ለሰው ልጅ መሰረታዊ ነገር ነው፡፡ የፌደራል ፍርድ ቤቶች አሉን፡፡ የሀይማኖት ፍርድ ቤት እነ እንቶኔ አላቸው፡፡ . . . ለእኛስ ለምን የጥበብ ፍርድ ቤት አልተቋቋመልንም . . . ወይም አይቋቋምልንም?  
ሀሳቤ በአጭሩ፤ የጥበብ ፍርድ (ፍትህ) ያስፈልገናል፤ የሚል ነው፡፡ ወንጀሉን እና ወንጀለኛውን ከሶ ችሎት የሚያስችል አቃቤ - ጥበብ ያስፈልገናል፡፡ . . . የአእምሮ ንብረትን ከዘራፊ የሚከላከል ዘብ ብቻ ሳይሆን፤ የአእምሮ ንብረትን ዋጋ የሚተምን፤ እና ከንብረቱ መሀል፤ ..ዋጋ.. የሚመስለውን ..እዳ.. ነቅሶ የሚከስስ ፍርድ ቤት . . . ፡፡
ምናልባት፤ በዚህ ፍርድ ቤት መጀመሪያ የምከሠሠው እኔ ራሴ መሆን እችላለሁ፡፡ እንደ መለማመጃ፡፡ ክሱም ደግሞ ቀልድ መሆን የለበትም፤ ቅጣት ያስፈልገዋል፡፡ . . . ግን ከሳሹ ተከሳሹን ለተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኛ መሆኑን አሳይቶ ማሳመን መቻል አለበት፡፡ . . . ማሳመን ካልቻለ ወንጀለኛው እሱ ራሱ ነው፡፡
. . . ከፍርድ ቤት በፊት ህግ ያስፈልጋል፡፡ እስካሁን ስለ ጥበብ በሁሉም ሁሌ ይወራል፤ ግን ስለ ጥበብ ትርጉም በእርግጠኝነት መናገር የሚደፍር ማንም ሰው የለም፡፡ ..ጥበብ ትርጉም አልባ መሆኗ ነው ትርጉሟ.. የሚል የሚመስል መግባባት በሚመለከታቸው ዘንድ ሁሉ ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡ . . . ትርጉም የሌለውን ነገር ለመዳኘት ትርጉም የሌለው ፍትህ ጥበብ ሊኖር ነው ማለት ነው፡፡
ታዲያ ግን፤ ጥበብ ትርጉምም ህግም አለው፤ በእውቀትም ይጠቀለላል፡፡ ይጠቃለላል፡፡ ህግ እና ትርጉም ያለው ነገር ሁሉ ..ጥሩ.. አሊያም ..መጥፎ.. ተብሎ ሊበየን ይችላል፡፡ መበየን ብቻ ሳይሆን ጥሩ አሊያም መጥፎ የሆነበትንም ምክንያት በጥሩ አመክኒዮ ቁልጭ አድርጐ ማሳየት ይቻላል፡፡ ፍትሐ - ጥበብ አመክኒዮ ነው፡፡
ለምሳሌ፤ የጥበብ አቃቤ ህጉ፤ አንዱን ሠዓሊ ክስ መስርቶ ፍርድ ቤት ገተረው እንበል፡፡ ..ክሱ.. ስዕልህ ምንም ትርጉም የለውም.. የሚል ነው፡፡
..ትርጉም ለኔ ወይንስ ለእናንተ?.. ብሎ ተከሳሽ መለሰ፡፡
..አንተ ሠዓሊውንና እኛ ተመልካቾቹን የሚያገናኝ ነገር ስላለ ነው ፈጠራህን ..ገለፃ.. ብለህ የጠራኸው፡፡ ለራስህ የምትገል ከሆነ እዛው ራስህ ውስጥ ብታስቀረው አይሻልም?..
..ሽንቴ ሲወጥረኝ መሽናት ያለብኝ በመጀመሪያ ደረጃ ለራሴ ነው፤ ስሜትም ለኔ ካልተገለፀ እንደ ሽንት ፊኛ ፈንድቶ እኔን ይጐዳኛል..
..ጥበብን ከሽንት ጋር አቆራኝቶ መግለፁ ለጥበብ ያለውን ንቀት ያሳያል ክቡር ፍርድ ቤት፤ ቅጣቱ ላይ አንድ አመት ከስዕል ተገልሎ እንዲቆይ ተጨማሪ ቅጣት ይመዝገብልኝ.. አቃቤ ህግ፡፡ ľ:- ..ፀጥታ.. በመዶሻ ጠረጴዛውን እየቀጠቀጡ ለጥበብ ታዳሚው፡፡
ፍርዱ ይቀጥላል፡፡ ወንጀለኛው ወንጀለኛ የተባለው በጥበብ መለኪያ እንጂ በፍትሐ ብሔር ስላልሆነ ቅጣቱም ፍርዱም ይለያያል፡፡ ተከሳሽ ታስሮ አይቀርብም፡፡ ዘና ብለው ተቀምጠው እንደ ማሕበር ጠበል ፀዲቅ እየቀመሱ ሊሆን ይችላል ፍርዱ የሚካሄደው፡፡ ምክንያቱም ሀያሲውም፣ አርቲስቱም የአርት አፍቃሪውም የፈጠራ ግዛት ሰዎች ናቸው፤ ጭንቅ አይችሉም፡፡ . . . እርግጥ ይህ የኔ ሐሳብ ነው፡፡ ሀሳብን በሐሳብ ማሻሻል ይቻላል፡፡ . . . ሳሻሽለው ደግሞ እንደሚከተለው ይሆናል፡፡
ተከሳሹ ታስሮ ይቀርባል፤ ክሱን ተከራክሮ መርታት ካልቻለ ዘብጥያ ይወርዳል፡፡ ለምሳሌ ..የቡርቃ ዝምታ.. ደራሲ በጥበብ ፍርድ ቤት ተከሶ ከቀረበ፤ እና ጥበቡ ዘርን ከዘር ጋር ለማጋጨት ተጠቅሞበታል የሚል ወንጀል ከተመሰረተበት፣ እና  ራሱን በማስረዳት ነፃ ማውጣት ካልቻለ፤ ዘብጥያ ሳይሆን የሞት ፍርድም ሊጠብቀው ይችላል፡፡ ...ግን አይ ይቅር ጥበብ ሰውን ከቻለ ማዳን እንጂ ማጥፋት በባህርይው አይደለም፡፡ ሰውን ለማጥፋት ጥበባቸውን የተጠቀሙ አርቲስቶች ካሉም ማጥፋት የሚያስፈልገው ጥበባቸውን እንጂ እነሱን አይደለም፡፡ ጥበባቸውን በመንጠቅ ሰውን ከሞት ማትረፍ ይቻላል፡፡ ግን ይሄንንም ለማድረግ የጥበብ ፍርድ ቤት ያስፈልጋል፡፡
በጥበባቸው ሰውን ማጥፋት ሳይሆን ኋላ ያስቀሩም አሉ፤ ጥበብን እንደ ሀይማኖት በቀኖና ሸብበው፤ እንዳይለወጥ ፈጣኑን የጥበብ ፈረስ ዛፍ አድርገው በአንድ ስፍራ የተከሉ፡፡ ዛፉን እየላጡ ያደረቁ፣ ከደረቀ በኋላ ጉቶው ላይ ቁጭ ብለው ተመሳሳይ ታሪክ እና ይዘት በተመሳሳይ ቅርጽ የሚያወሩ የጥበብ አጽም ሰብሳቢዎች እነዚህም ከጥበብ ፍርድ ክሱ አያመልጡም፡፡ በተለይ ፍርድ ቤቱ ከጠነከረ የጥበብ ህግን የተማሩ በብዛት ተመርቀው ይወጣሉ እና ስራ ይጀምራሉ፡፡ ነገር ግን ያስፈራል ዳኛ እና ጠበቃ ከበዛ ደግሞ ክስ ይበዛል፡፡ መከሰስ የሌለበትንም ህጉ ላይ አንቀጽ እየጨመሩ እና ነገር እያወሳሰቡ ጥበበኛውን እንዳይጨርሱት ያሰጋል፡፡ አይ አይ ይቅር! በጣም ጥቂት ዳኛ እና ጠበቃ ብቻ ነው ሚያስፈልገው፡፡ ጠበቃ የጥበብ ተቆርቋሪ ነው ዳኛ ሀያሲ መሆኑ ነው፡፡ እዚህ ሀገር እስካሁን ሃያሲ እንደ ጥቁር አበባ ሲበቅል አልታየም፡፡ የጥበብ እውቀት ሳይኖር ዳኝነት፣ ዳኝነት ሳይኖር የጥበብ ፍርድ አይታሰብም፡፡
ህልም አለኝ አንድ ቀን የሀገሬ ጥበብ ከሽማግሌ ዳኝነት እና ከቡድን ወይንም የጐጥ ባህላዊ ደንብ ወጥታ በሰለጠነ ፍርድ ቤት ፍትሕ ታገኛለች፡፡ ወንጀል የመክበሪያ ዘዴ በሆነበት ለጥበብ ዘራፊ፣ ወንበዴ... እንደ ጀግና ግጥም የሚገጠምበት ሀገር ላይ ፍትሕ የበላይ መሆኗ አይቀርም፡፡ ግን መጀመሪያ፤ ከጥበብ ህግ የበላይነት በፊት፤ የጥበብ ህጉ ምን እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
..አብስትራክት የአንጐል ቋንቋ ነው በስሜት ህዋሳቶቻችን (በአይናችን ተመልክተን መረዳት ያለብንን የስዕል ሸራ፣ በአንጐል ቋንቋ (አብስትራክት) ሳልኩ የምትለኝ ለምንድነው?.. ብሎ አቃቤ ጥበብ ለአርቲስቱ በሚጠይቅበት ጊዜ፤ ሰአሊ ማስረዳት መቻል አለበት፡፡ ስዕል ላይ ያሉ መሰረታዊ ህጐችን በተከተለ መንገድ መስራቱን ማሳየት አለበት፡፡ የስዕል ሸራ ላይ የጋዜጣ ጽሑፍ ቆራርጦ ለጥፎ ..ስዕል ነው.. ያለበትን ምክንያት መግለጽ መቻል ይጠበቅበታል፡፡ በስዕል እና በጋዜጣ መሀል ተደባልቆ የተፈጠረው ሚዲየም፤ ሁለቱንም በመደባለቁ በመግለጽ ረገድ የበለጠ ማሻሻል መቻሉን ማስረዳት ካቃተው ድሮ የነበረውን የቀየረው ለመፍጠር ሳይሆን ለማጥፋት ነው ተብሎ ፍርድ ቤት መቅረቡ አይቀርም፡፡...
ግን ጥበብ ፍርድ ቤቱ ላይ ሙሰኛ ዳኞች እና ..የማያውቁ ታዋቂዎች.. እንዳይኖሩ የጥበብ ፀረ ሙስና ከፍትሕ ሂደቱ ጋር እጅና ጓንት ወይንም ጥበብ እና እውነትን ሆነው አንድ ላይ መስራት ይችላሉ፡፡ ሙሰኛ ሐያሲዎች ጉቦ ተቀብለው፤ መጥፎውን ጥበብ ጥሩ እንደሆነ አድርገው ማሞካሸት አይችሉም፡፡ በወዳጅነት እና ሽርክነት ወንጀለኛን ማስመለጥ ወይንም ሳይከሱ መተው አይችሉም፡፡ ከቻሉ ወንጀለኛ ዳኛ ሆነዋል፡፡ ወንጀለኛ ዳኛ ራሱ መከሰስ አለበት፡፡ የጥበብ ፍርድ ቤት፤ ለመወንጀል ብቻ ሳይሆን ለመሸለም/ለመሾም ጥበበኛን ይጠራል፡፡ ይህም ከሌላው ፍርድ ቤት ልዩ የሚያደርገው ዋና ባህርይው ነው፡፡ የአመቱን ምርጥ ጥበብ ይሸልማል፤ የአመቱን ምርጥ ወንጀል ይቀጣል፡፡ በመሐል ያሉትን በመሀከለኛ ማስጠንቀቂያ እና ማሸማቀቂያ ያልፋቸዋል፡፡ የጥበብ ጀግኖች በጥበብ ካላንደር አቆጣጠር ላይ መጠሪያ ይሰየምላቸዋል፡፡ ጀግና በጥበብ እንደ ሌላው የጦር ሜዳ ገዳይ አይደለም፡፡ ገዳይ አይደለም እንጂ ማራኪ ግን ነው፡፡ የጥበብ ጀግና ህዝብን ያረካ ሳይሆን ጥበብን ያረካ ነው፡፡ ጥበብ ከሰው ቀደም ብላ መንገድ የምትጠርግ ስለሆነች፤ ህዝብን አትመስልም፡፡ ህዝብን ያስደሰተ ጠቢብ፤ ከጥበብ ፍርድ ቤት (ወንጀለኛ ተብሎ) ክስ ሊቀርብበት ይችላል፡፡ በህዝብ ተወዳጅ የሆኑ የጥበብ ወንጀለኞች አሉ፡፡ ምርጥ የጥበብ ስራ ሰርቶ ከተሸለመ በኋላ፤ በተከታታይ ባወጣው ስራው ጥበብን ያስቀየመ ጠቢብ ..ጠባብ.. ተብሎ ይወነጀላል፡፡ ጥሩ የጥበብ ስራ ባንክ ውስጥ እንደተቀመጠ በጣም ትልቅ የሆነ አክብሮት ወይንም ስም አሊያም ዝና ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ባንክ ውስጥ የተቀመጠ ብርም ከስር ከስር እየተቀነሰ እየተመነዘረ ከሄደ ማለቁ አይቀርም፡፡
እንደ ጥሪት ስም አክብሮትም ይሁን ምስጋና ይጠራቀማል፣ የተጠራቀመው ከተሸነቆረ ይንቆረቆራል፡፡ ከዛ ባዶ ይቀራል፡፡ ከዛ ከድሮው አክብሮት ምስጋና እና ዝና ላይ (ወይ ስም) መበደር ይመጣል፤ ከብድር በኋላ ክስረት ይከተላል፡፡ ፍርድ ቤቱ የአክብሮት ባንክ አካውንቱን ከፍቶ የወሰደውን የብድር አክብሮት መጠን ከሶ ማስመለስ መቻል አለበት፡፡ ተከሳሹ መመለስ ካልቻለ፤ አስይዞ የተበደረበት የድሮ ስሙ ይወረሳል፡፡ ...አቤት! በጣም ጭካኔ ነው ያሰብኩት...፡፡ ግን ለማሰብ ያክል እንጂ፤ በተግባር ይሆናል ብዬ አይደለም፡፡ ጥበብን እንደቁም ነገር የሚወስድ የሰው ልጅ እና የጥበብን እድገት እፈልጋለሁ፡፡ ጥበብን እንደ እረፍት ሰአት ጊዜ መግደያ ለሚያይ የአእምሮ ንቃት ህግ ያለው ጥበብ አያስፈልግም፡፡ ትርጉም ያለው ኪነት፤ እና ኪነት ያለውን ትርጉም መረዳት አያሻውም፡፡ ጠቢቡም፤ የጥበብ አቋም መግለጫ xÃSfLgWM፡፡ ሲያደርጉ ያየውን ማድረግ ብቻ ነው ያለበት፡፡ የሚፈጥረው ፍጥረት እሱን ሊገልፀው ያልቻለውን ያህል እሱም መግለጽ በማቃት አፉን ከፍቶ መቅረት፡፡ የኮምፓስ አቅጣጫ ጠቋሚ ወደ ሰሜን ..እኔ ነኝ የጠቆምኩህ.. ሲለው ..እንዴት  የት እንዳለ የማያውቅ ሰው እኔን እዚህ ነው ያለኸው ብሎ ይጠቁመኛል?.. ብሎ መልሶ ያፈጥበታል፡፡ ሁለቱንም የሚዳኝ ፍርድ ያስፈልጋል፡፡ ህጉ እና ፍትሑ ያስፈለገው ወንጀለኛን ከመቅጣት ጀግናውን ከመሸለም ባሻገር የት እንዳለን ለማወቅ ነው፡፡ ጥበብ የሰው ልጅን አቅጣጫ የሚጠቁም ኮምፓስ ነው፡፡

 

Read 3212 times Last modified on Saturday, 17 September 2011 10:48