Saturday, 27 August 2011 13:52

የሥነ ጽሑፍመድረክ

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

ከኒቨርስቲ እስከ  ፑሽኪን
በአዲስ አበባ ከተማ ኪነ ጥበብን ማዕከልአድርገው በሣምንቱ ውስጥ ጥቂት የማይባሉ ቀናት በነፃ የመዝናኛና
የመማሪያ መድረኮች እየተፈጠሩ ነው፡፡ የመድረኮቹ ዝግጅትና አቀራረብ
አንዳንዱ ሞቅ ሌላው ዘንድ ቅዝቅዝ    ብሎም ይታያል፡፡ ሰኞ ነሐሴ 16 ቀን 2003 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ ያሳተመውን የሎሬት ጋዬ ገ/መድኅን ተውኔቶች የያዘ መጽሐፍን በብሔራዊ ቴአትር ለማስመረቅ ያዘጋጀው መድረክ ደማቅ ተብሎ በምሳሌነት ሊቀርብ የሚችል ነበር፡፡

የብሔራዊ ቴአትሩ መድረክ ከመዘጋጀቱ ከሦስት ቀን በፊት ነሐሴ 13 ቀን 2003 ዓ.ም በፑሽኪን የሳይንስና ባህል ማዕከል የቀረበው የሥነ ጽሑፍ ምሽት በተቃራኒ ቀዝቃዛ የሚባል መድረክ ነበር፡፡ በሩሲያ አገር ከሚካሄዱ የሥነ ጽሑፍ ዝግጅቶች አንዱ ነው የተባለውና በኢትዮጵያውያንም መለመድ አለበት ተብሎ በፑሽኪን አዳራሽ የቀረበው ዝግጅት ምን ይመስል እንደበር ከማስቃኘቴ በፊት ኪነ ጥበብን ማዕከል አድርገው ለመዝናኛነትና ለመማማሪያነት በነፃ የሚዘጋጁ መድረኮች ከየት ተነስቶ አሁን ላለበት ደረጃ ደረሰ? ለሚለው ጥያቄ ከሚሰጡ መልሶች ጥቂቱን ላቅርብ፡፡
የሥነ ጽሑፍ ስራዎች በተለይ ሥነ ግጥምን በአገራችን ሕዝብ በተሰበሰበበት ማቅረብ የተጀመረው ንጉሥ ኃይለሥላሴ በሚገኙበት መድረክ በ1950ዎቹ እንደነበር ይነገራል፡፡ ከዓመታት በኋላ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሚያቀርቧቸው ግጥሞች ጠንከር እያሉ በመሄዳቸው ንጉሡንና ባለስልጣናቱን ቅር አሰኝቶ በመድረኮቹ መገኘታቸውን ቢያቋርጡም ዝግጅቱ ግን እስከ 1960 ዓ.ም ድረስ ለዘጠኝ ዓመታት ያህል ዘልቆ እንደነበር የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 50ኛ የምሥረታ ዓመቱን ሲያከብር ካሳተማቸው ሁለት መፃሕፍት አንዱ የሆነው ..የኮሌጅ ቀን ግጥሞች.. ጥራዝ ይጠቁማል፡፡  
ለሥነሁፍ መድረኩ መጀመርና መድመቅ ዩኒቨርስቲውÂ ተማሪዎቹ ብቻ ሳይሆኑ የንጉሡ በመድረኮቹ መገኘት ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ በዚህ ዙሪያ ንጉሥ ኃይለሥላሴ ዛሬም ቢሆን ሊመሰገኑበት የሚችሉ ተግባራትን ይፈጽሙ ነበር፡፡ በወቅቱ የታተሙ መፃሕፍትን እየገዙ ለትምህርት ቤቶች ይሰጡ ነበር፡፡ ለደራሲያን የማሳተሚያ ገንዘብ በመለገስ ለመጽሐፍ ሕትመት መበራከት አስተዋጽኦ በማድረጋቸውም ይታወቃሉ፡፡
መሰብሰብ እንደ ወንጀል በሚታይበት በደርግ ዘመን ..ኪነት ለአብዮቱ.. በሚል ዓላማ ከሚዘጋጁ መድረኮች ውጭ በኪነ ጥበብ ሥራዎች እየተዝናኑ ለመማማር የሚዘጋጁ መድረኮች አልነበሩም፡፡ በአንድ አዳራሽ ተሰባስቦ የተለያዩ መልዕክት ያላቸውን ግጥሞች፣ ልቦለዶች፣ ወጎች፣ . . . ማንበብ ቀርቶ ደራሲያን የሚያሳትሙትንም መጽሐፍ የማስመረቅ ልማዱ አልነበረም ነው የሚባለው፡፡
ከ1983 ዓ.ም በኋላ የሥነ ጽሑፍ ምሽት፣ የመጽሐፍ ምረቃ ዝግጅት፣ በተለያዩ ክበባትና ማህበራት የሚቀርቡ የኪነ-ጥበባት ፕሮግራሞች እየተዘጋጁ በአዲስ አበባም በክልል ከተሞችም እየቀረቡ መሆኑ ይታያል፡፡ መጽሐፍ የማስመረቅ ጅማሮውም ታየ የሚባለው በዚሁ ዘመን ነው፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው መምህር ደረጀ ገብሬ በአንድ መድረክ ስለዚህ ጉዳይ ሲናገሩ ..ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ በ1995 ዓ.ም ያሳተመውን ..ጩኸት.. የሥነ ግጥም መጽሐፍ ጥቂት ወዳጆቹን ጠርቶ አነበበልን፡፡ ያ መነሻ ሆኖ ደራሲያን መጽሐፋቸው የማስመረቅ ልማድ እየዳበረ መጣ.. ብለው ነበር፡፡
መጽሐፍ ማስመረቅን ጨምሮ ባለፉን 20 ዓመታት ኪነጥበቡን ማዕከል ያደረጉ የተለያዩ ነፃ የመዝናኛና የመማማሪያ መድረኮች ተዘጋጅተዋል፡፡ ጅማሮው ወዴት ነው ማደግ ያለበት የሚያስብሉ ጥያቄዎች የሚያጭሩ ነገሮችን ማየቱም እየተለመደ መጥቷል፡፡
በአንዳንዱ ዝግጅት አንድ መጽሐፍ ወይም ሲዲ ለማስመረቅ ብሔራዊ ቴአትር የመሳሰሉ ትላልቅ አዳራሾች ሞልተው መቀመጫ የሚታጣበት አጋጣሚ ይታያል፡፡ በተቃራኒ እስከ 20 የሚደርሱ ግጥም አቅራቢያን ቢጋበዙም የሀገር ፍቅርን ትንሹን አዳራሽ የሚሞላ በመቶ የሚቆጠር ሰው ጠፍቶ ዝግጅቶቹ ብርድ ብርድ እንዳላቸው የሚጠናቀቁ መድረኮችም ጥቂት አይደሉም፡፡
ለልዩነቱ መፈጠር ምክንያቶቹ ብዙ ናቸው፡፡ ጥቅምን ወይም በቡድን ከማሰብ ጋር የሚከሰት ልዩነት እንደ አንድ ምክንያት ይጠቀሳል፡፡ የአርቱ ወይም የአርቲስቱ ደጋፊና ተቃዋሚዎች መበሻሸቃቸውን የሚገልፁበት አንዱ መንገድ ከመሆኑ ጋርም የሚያያዙት አሉ፡፡ ከዚህም በመነሳት ..ቲፎዞ ከሌላችሁ መጽሐፍ ለማስመረቅ፣ የኪነ ጥበብ ዝግጅት ለማቅረብ አትሞክሩ.. ብለው ወዳጆቻቸውን የሚመክሩ ሰዎች ያጋጥማሉ፡፡
ይህ አካሄድ ወዴት ነው የሚያድገው? ለሚለው ጥያቄ ግልጽ የሆነ መልስ ያለ በማይመስልበት ጊዜ ላይ የሩሲያዊያን አንዱ የሥነ ጽሑፍ ምሽት አዘገጃጀት በአገራችን ኢትዮጵያ ቢለመድ ጥሩ ነው በሚል ነሐሴ 13 ቀን 2003 ዓ.ም በሩሲያ ሳይንስና ባህል ማዕከል ከአሁን ቀደም ባልተለመደ አቀራረብ የኪነ ጥበብ ዝግጅት ለማቅረብ ተሞክሯል፡፡ ለፕሮግራሙ መጥሪያ በተበተነው ወረቀት ላይ መሰናዶውን የሩሲያ ሳይንስና ባህል ማዕከል ከኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ጋር በመተባበር ያዘጋጁት መሆኑን፣ በዕለቱ የተለያዩ ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡት እነማን እንደሆኑ ተመልክቷል፡፡ዕለቱ የክርስትና እምነት ተከታዮች የደብረ ታቦር (የቡሄ) በዓል የሚያከብሩበት ቀን ስለነበር የጥሪው ካርድ የደረሰው ሰው ወደ ሣይንስና ባህል ማዕከሉ ሲያቀና ከዕለቱ ጋር የተያያዘ ነገር ዝግጅቱ ላይ ሊኖር ይችላል ወይም ማዕከሉ አንድ ወቅታዊ ጉዳይን መነሻ ያደረገ ዝግጅት ሊቀርብ ይችላል የሚል ግምት ቢኖረውም በዝግጅቱ የታየው ግን ያልተለመደና አዲስ አቀራረብ ነበር፡፡
በዕለቱ 50 የሚደርሱ ታዳሚዎች ተገኝተዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ሰባት የሥራ አስፈፃሚ አባላት አራቱ ነበሩ፡፡ የሩሲያ ሣይንስና ባህል ማዕከልን ወክለው የተገኙት በሩሲያ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት የሚያገለግሉት ፕሮፌሰር ንጉሴ ካሳዬ ነበሩ፡፡ መድረኩን በመተባበር የመሩት ከደራሲያን ማህበር አቶ አበረ አዳሙና ፕሮፌሰሩ ናቸው፡፡ 15 ያህል ተጋባዦች 30 የሚደርሱ ግጥሞችን በሦስት ዙር አንብበዋል፡፡
በእያንዳንዱ ዙር በተነበቡት ግጥሞች ላይ ተሰብሳቢው የተሰማውን ስሜት እንዲገልጽ ዕድል ተሰጥቶት ነበር፡፡ ሁሉም ነገር ባልተለመደ መልኩ ነበር ሊስተናገድ የተሞከረው፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው በለጠ ንግግር እንዲያቀርቡ ሲጋበዙ ..መድረኩን ባልተለመደ መልኩ ነው የምጠቀምበት.. ብለው ሦስት ግጥሞችን አነበቡ፡፡ ሌሎች ግጥም አቅራቢዎችም በፍቅር፣ በፖለቲካ፣ በማሕበራዊ ሕይወት . . . ዙሪያ ያነበቧቸውን ግጥሞች ያቀረቡት ለዕለቱ አጀንዳንና መወያያ እንዲሆን ከተመረጠ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በቅድሚያ ተዘጋጅተውበት ሳይሆን አንባቢው በግሉ ደስ ያለውን ግጥም አንብቦ አድማጩም ደስ ያለውንና የተሰማውን እንዲገልጽ ነው መድረኩ የተዘጋጀው፡፡
..ቅጠሎች.. የሚል የአማርኛ የግጥም መጽሐፋቸውን በዕለቱ ለታዳሚዎች ያስተዋወቁት ፕሮፌሰር ንጉሴ ካሳዬ፤ በመምህርነት በሚያገለግሉበት በሩሲያ ካሉት የኪነ ጥበብ መድረኮች አንዱ ለቅርጽና ይዘት ሳይጨነቁ መደበኛ ባልሆነ መልኩ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን እያነበቡ መወያየት ነው ይላሉ፡፡ ይህ ነገር በእኛም አገር እንዲለመድ የመጀመሪያውን ሙከራ በኢትዮጵያ ሚሌኒየም በዓል ወቅት የዛሬ 3 ዓመት ለማስተዋወቅ ሞክሬያለሁ የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ ቦታው ስታዲየም ዙሪያ ካሉ ቡና ቤቶች በአንዱ ነበር በማለት ይገልፃሉ፡፡ የነሐሴ 13 መድረክንም ያሰናዱት ለዚሁ ዓላማ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ባቢሎን የጠፋችው ሕዝቦቿ ታሪካቸውን ስለረሱ ነው የሚል ምሳሌ አቅርበው GlÖÆላይz¤>N በሚል ሰበብ እኛም ታሪካችን ሲጠፋ ዝም ብለን ማየት የለብንም የሚል ንግግር ያደረጉት ፕሮፌሰሩ፤ የአማርኛን ፊደል ለቀረ አባቶች ሐውልት ሊቆምላቸው ይገባል ካሉ በኋላ በዚህ ዙሪያ ያዘጋጁትን የጽሑፍ መልዕክት ለደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት ሰጥተዋል፡፡ አቶ ጌታቸው በለጠም የሚመሩት ማህበር በቅርቡ የራሱ የሆነ የኪነ ጥበባት ማስተናገጃ እልፍኝ ባለቤት እንደሚሆን ተናግረው፣ በእልፍኙ የዕለቱን መሰል ዝግጅቶች በብዛት እንደሚቀርቡበት ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል፡፡
በ1950ዎቹ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጀምሮ ባለፉት ሃያ ዓመታት ሰፊ በሚባል መልኩ ተግባራዊ እየሆነ ያለው፤ የጥበብ መድረክ አሁን አሁን እንቅስቃሴው እየተዳከመ መምጣቱን በስጋት የሚያነሱት አሉ፡፡ መድረኮቹ እየተዘጋጁ ያሉት በአብዛኛው በግለሰቦች ይመስላል፡፡
ግለሰቦች መስኩን ለማሳደግ ያላቸው ሚና ምን ሊሆን ይችላል? ለሚለው ጥያቄ ነሐሴ 13 ቀን በፕሮፌሰር ንጉሴ ካሳዬ አነሳሽነት የቀረበው ዝግጅት አንዱ ማሳያ ሆኖ ቀርቧል፡፡ ለአጀንዳ፣ ለቅርጽ፣ ለይዘት ሳይጨነቁ የሚሰናዳ የሥነ ጽሑፍ ዝግጅት ምን ግብና ዓላማ ይኖረው ይሆን?

 

Read 3300 times Last modified on Saturday, 27 August 2011 13:55