Saturday, 03 September 2011 11:52

በሊቢያ ጥቃት የደረሰባት ኢትዮጵያዊት በእንግሊዝ እንድትታከም ጥረት እየተደረገ ነው

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(1 Vote)
  • መንግስት ልጃቸውን እንዳየሳክምላቸው እናት ተማፅነዋል

በሊቢያው ፕሬዚዳንት ሙአመር ጋዳፊ ልጅ ቤት ውስጥ በሞግዚትነት ስትሰራ በነበረችው ኢትዮጵያዊቷ ወጣት ሸዋዬ ሞላ ላይ የደረሰውን አስከፊ የአካል ጉዳት ይፋ ያደረጉት የሲ ኤን  ጋዜጠኞች ነበሩ፡፡  
የ30 ዓመቷ ሸዋዬ የጋዳፊ ልጅ በሆነው ሃኒባል ጋዳፊ ቤት ለአንድ ዓመት የሠራች ሲሆን ጥቃቱም የደረሰባት በልጅየው ሚስት በሚስስ አሊያን መሆኑ ተዘግቧል፡፡ አሊያን ቀደም ሲል የማቃጠል አደጋ ያደረሰችባት ሲሆን በኋላም የፈላ ውሃ በጭንቅላቷ ላይ እንዳፈሰሰችባትና ከራሷ ጀምሮ መላ ሰውነቷ ክፉኛ እንደቆሰለ ሸዋዬ ለጋዜጠኞች ተናግራለች፡፡ ይሄ ጉዳይ በዓለም አቀፍና በአገር ውስጥ የዜና ማሰራጫዎች ቢተላለፍም የልጅቷ እናት የ60 ዓመቷ ወ/ሮ ኩሪ ወልዱ ሰኞ ዕለት ደብረ ሊባኖስ ገዳም ለንግስ ሄደው ስለነበር የሰሙት ነገር የለም፡፡

ከትላንት በስቲያ ሀሙስ ከሰዓት በኋላ ቤታቸው ሲደርሱ ግን አስደንጋጭ ነገር ጠበቃቸው፡፡ ቤታቸው በዘመድና በሰፈርተኛ ተሞልቷል፡፡ ሰዎች የተሰባሰቡት ሊያናኑአቸው ቢሆንም ነገሩን የማያውቁት ወ/ሮ ኩሪ ግራ መጋባታቸው አልቀረም፡፡ በልጃቸው ላይ የደረሰው አደጋ ሲነገራቸው መንሰቅሰቅና ማንባት ጀመሩ - የልጃቸውን ስም እየጠሩ፡፡
ወላጅ አባቷን የዛሬ አስራ ሰባት ዓመት ያጣችው ሸዋዬ፤ ለቤቱ ሦስተኛ ልጅ ናት፡፡ የዘጠነኛ ክፍል ትምህርቷን ያቋረጠችው የዛሬ ስምንት ዓመት በእንጀራ ንግድ የሚተዳደሩትን እናቷን ለመርዳት አስባ ነበር፡፡ የቤተሰቡን ህይወት ለማሻሻል አጥብቃ የምትመኘው ሸዋዬ፤ ሀሳቧን ለማሳካት ስትል በቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ ወደ ቤሩት ተጓዘች፡፡ በስምንት ዓመት የቤሩት ቆይታዋም ወንድሞቿንና እህቶቿን አስተማረች፡፡ እናቷንም ከእንጀራ ጋገራ አስወጥታ ቤተሰቡን በቅጡ ማስተዳደር ያዘች፡፡
ከቤሩት ተመልሳ መጥታ በሀገሯ ለመኖር ሞክራ እንደነበር ቤተሰቡ ይናገራል፡፡ ሆኖም አሁንም የምትፈልገውን ያህል ቤተሰቧ አለመለወጡን አየች፡፡ እንደገና ለስራ ወደ ኳታር ሄደች፤ እዚያ ግን አልሆነላትም፡፡ ተመልሳ ዕድሏ የሚሰጣትን ትጠብቅ ጀመር፡፡
የሊቢያ ኤምባሲ የኢትዮጵያ ዜግነት ያላቸውን ሦስት ወጣቶች በሙአመር ጋዳፊ ልጅ ቤት በሞግዚትነት መቅጠር እንደሚፈልግ በኤጀንሲ በኩል ሰማች፡፡ ሸዋዬ አረብኛ አቀላጥፋ ስለምትናገርና በቂ የስራ ልምድ ስለነበራት፣ ለሥራው ብቁ መሆኗ ታምኖበት ወደ ሊቢያ አመራች፡፡ ሁሌም የቤተሰቧን ኑሮ ለማሻሻል የምትታትረው ሸዋዬ፤ ባገኘችው ዕድል በእጅጉ ተደስታ ወደ ሊቢያ መጓዟን እናት ያስታውሳሉ፡፡
እናቷን ..አይዞሽ ነገሮች ይለወጣሉ.. የሚል ተስፋ ሰጥታቸው ነበር የሄደችው፤ እንዳለችው ግን አልሆነላትም፡፡ የጋዳፊ ልጅ የሃኒባል ባለቤት የሆነችው አሊያን መጥፎ ሴት እንደሆነች ለጋዜጠኞች የተናገረችው ሸዋዬ፤ ከፍተኛ በደልና ስቃይ እንዳደረሰችባት ገልጻለች፡፡
ነገሩ ሲብስባትም ወደ ቤተሰቦቿ ደውላ ያለችበት ሁኔታ ጥሩ እንዳልሆነ ለእህቶቿ ነግራ ነበር - እናቷ እንዳይሰሙ በማስጠንቀቅ፡፡ ..እናቴ እንዳትሰማ፣ ጭንቅ ውስጥ ነው ያለሁት. . . አሠሪዬ ሴትዮ ጥሩ አይደለችም.. ብላ ተናግራለች፡፡ ሊቢያ ከሄደች ጊዜ ጀምሮ አንድም ጊዜ እንኳን ገንዘብ ልካላቸው እንደማታውቅ ቤተሰቦቿ ይናገራሉ፡፡ ሸዋዬ የጋዳፊ የልጅ ልጆችን ለአንድ ዓመት ሞግዚት ሆና ያገለገች ቢሆንም ምንም ክፍያ እንዳልተሰጣት ጋዜጠኞች ባገኟት ወቅት ገልጻለች፡፡
ከሸዋዬ ጋር ወደ ሊቢያ የተጓዙት ሁለት ኢትዮጵያውያን ሥራ ያገኙት የጋዳፊ ቤተሰቦች ጋ አልነበረም፡፡ ሥራውም ስላልተስማማቸው ወዲያው ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ሲሆን ሸዋዬ ያለችበትን አስከፊ ሁኔታ ለቤተሰቡ በመጠቆም ወደ ሀገሯ የምትመለስበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹም አሳስበዋቸው እንደነበር ይናገራሉ፡፡
በሊቢያ የህዝብ አመ የተነሳ ሰሞን፣ እናት የልጃቸው ነገር አሳስቦአቸው የሊቢያ ኤምባሲንና ከኤምባሲው ጋር ያገናኛትን ኤጀንሲ ማነጋገራቸውንና ልጃቸውን ወደ አገሯ እንዲመልሱላቸው መወትወታቸውን ይገልፃሉ፡፡ ከአመፁና ከግጭቱ ጋር በተገናኘ በሊቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአለማቀፍ ስደተኞች ተቋም (IOM) እና በሱዳን ኤምባሲ አማካኝነት ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ የልጃቸውን ድም ግን አለመሰማታቸውን ይናገራሉ፡፡
ከረጅም ጊዜ በኋላ የሸዋዬን ድም የሰሙት ባለፈው መጋቢት ወር እንደነበር የሚናገሩት ቤተሰቦች፤ ያን ጊዜ ከእናቷ ጋር በስልክ መነጋገሯን ያስታውሳሉ፡፡ ..እናቴ ፀልይልኝ፤ ተከበናል መፈናፈኛም የለም፤ ሴትዮዋ በጣም ትበድለኛለች፣ ራበኝ፣ ጠማኝ. . . አገሬ እንድገባ ብቻ ልይልኝ.. እንዳለቻቸውም እናት እያለቀሱ ነግረውናል፡፡ ..ከእግዚአብሔርና ከእርሷ በቀር ማንም የለኝ፤ እንደዚህ ላይደላት ሊቢያ ኤምባሲ ስትገባ 4ሺ ብር ተበድራ ነበር የከፈለችው፡፡ ልጄ ደክማ ለእኔና ለእህት ለወንድሞቿ ነው፤ ለራሷ አንዳችም ጥሪት የላትም.. ያሉት ወ/ሮ ኩሪ፤ ..ድምን ልስማው፣ ልዳብሳት፣ ህመሟን ልጋራት ልጄን አሳዩኝ፣ አሳክሙልኝ. . ... እያሉ ሲማኑ ነበር በከበቧቸው ሰዎች መሃል፡፡ የሙአመር ጋዳፊ ልጅ ሃኒባል ጋዳፊ ሚስት አሊያን ሰከፍ፤ ልጃቸው ላይ የፈላ ውሃ በማፍሰስ ከጭንቅላቷ አንስቶ መላ ሰውነቷ ላይ አስከፊ ጉዳት እንዳደረሰችባት የሰሙት እናት፤ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሊቢያ ኤምባሲ በመሄድ ልጃቸውን እንዲያሳክሙላቸው መማፀናቸውን ተናግረዋል፡፡ ..የአገር ያለህ የወላድ ያለህ፣ ድሃዋን ልጄን አሳክሙልኝ፤.. ድምዋን አሰሙኝ.. በማለት፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥትም ከጎናቸው መሆኑን እንደገለላቸው ነው ወ/ሮ  ኩሪ የተናገሩት፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት አምባሳደር ዲና መፍቲ በበኩላቸው፤ መንግስት ከዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት (IOM) ጋር በመተባበር ሸዋዬ በእንግሊዝ አገር እንድትታከም ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም የኢትዮጵያ መንግሥት ከወጣት ሸዋዬ ሞላ ጐን በመቆም እንደሚሟገትላት ተናግረዋል””ሸዋዬ ከፍተኛ ጉዳት ቢደርስባትም እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ህክምና እንዳላገኘችና የሲኤንኤን ጋዜጠኞች ሆስፒታል እንዲወስዷት እንደተማፀነች ታውቋል፡፡

 

Read 5258 times Last modified on Saturday, 03 September 2011 15:52