ፈረሱ ያለቀሰው ኳንተም ለመሆን እያቀደ ሳለ የሆዱ ረሀብ ትዝ አለው፡፡ አርባ ቦታ በአንድ ቅበት መገኘት ሳይሆን የሚፈልገው፤ በኳንተም (ኳንታ) ቋንጣ ፍርፍር መመገብ ነው፡፡ ኳንተም ቋንጣ ፍርፍር የማይሰጠው ከሆነ፤ ራሱን በአርባ ኮፒ ማባዛት ምን ፋይዳ አለው አርባ ረሀብተኛ ሆድ በአንድ ቅበት አለም ላይ እንደ አንበጣ መልቀቅ መሆኑ ሲገባው፤ ስቅስቅ ብሎ ማልቀስ ጀመረ፡፡ የዶ/ር አቡሽ መጽሐፍ ነው በቅበት ከአርባ ማተሚያ ቤት አርባ ቅዠት ይዞ የሚወጣው፤... እውነተኛ መካሪ የት ጠፍቶ ነው በዚህ ሰውዬ ቋንጣ የቅዠት ፍርፍር የምጐመጀው ብሎ ማልቀሱን ቀጠለ፡፡
አጥብቆ ጠያቂው- የማነቃቂያ መጽሐፍት በብዛት መታተም አስደስቶት ነበር ፈረሱ የሳቀው፡፡ ብዙ የማነቃቂያ መጽሐፍትን ገዝቶ ራሱን ንቁ ብቻ ሳይሆን ብቁ ለማድረግ ሲጥር ሰነበተ፡፡
...ፈረሱ ያለቀሰው ከመጽሐፍቶቹ ባገኘው እውቀት ነቅቶ የሚጋልብበት ሜዳ በማጣቱ ነው፡፡ ፈረሱ ይኸው ሜዳው የታለ? ብሎ በእልህ መንሰቅሰቅ ጀመረ፡፡ ንቃት ሜዳ ይፈጃል ለካ፡፡ ተመልሶ ተኛ፡፡
የዘንድሮ ወንድ ፈረሱ በሴት እህቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ይፋ ወጥቶ ወንጀለኞች ለፍርድ እየቀረቡ መሆኑ አስደስቶት ሳቀ፡፡ ...በተለይ ከሁሉ አሰቃቂ የሆነው የአሲድ ጥቃት፤ በምን ዓይነት ጨካኝ አንጀት እንደተፈመ ማሰብ ስለሚከብደው መፍትሔ እየተፈለገ መሆኑ አስደሰተው፡፡ አሳቀው፡፡
ያለቀሰው፤ ከህሊናው ጓዳ አንድ ድም ሹክ ካለው በኋላ ነበር፡፡ ..ሴቶቹ ላይ የተደፋው አሲድ የመነጨው ከወንዶቹ ጨጓራ ነው፡፡.. ፈረሱ ማልቀስ ጀመረ፡፡ እንባው ማንንም እንዳይጐዳ፣ እንዳይልጥ ተጠንቅቆ፡፡