Saturday, 03 September 2011 12:34

ይኢትዮጵያና የውጭ ባለሀብቶች አስገራሚ መመሳሰል

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

ዘንድሮ ታትመው ከወጡ መጻሕፍት አንዱ ነው፡፡ የ22 ስኬታማ ሰዎችን ታሪክ ይዟል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ሦስቱ ሴቶች ናቸው፡፡ ከስኬት ጋር በተያያዙ ርዕሰ ጉዳዮች የቀረቡ 23 መጣጥፎችንም ያስነብባል፡፡ በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ..ከስኬት ማማ ከወጡ አሜሪካውያን ሚሊየነሮች መካከል 95 በመቶ የሚሆኑት ሀብታቸውን ያፈሩት በውርስ ሳይሆን በጥረታቸው እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ.. የሚል ሀሳብ ሰፍሯል፡፡
የሰለጠኑት አገራት የባለሀብቶቻቸውን ቁጥር ለይተው ከማወቃቸውም ባሻገር የባለጐች የቤተሰብ፣ የትምህርት፣ የሥራ አጀማመር. . . ታሪካቸው ተጠንቶ መረጃዎችን በመተንተን፤ በጥረት፣ በትምህርት፣ በተወረሰ ሀብት፣ በሥራ ፈጠራ. . . መበልግ የቻሉት በፐርሰንት ምን ያህል እንደሆኑ በሰነድ ተዘጋጅቶ ለሕዝብ እንደሚቀርብ ያመለክታል - መጽሐፉ፡፡

ለዚህ ጽሑፍ መዘጋጀት ምክንያት የሆነኝ በኢዮብ ካሣና ሰለሞን ከበደ በተዘጋጀው ..ታላላቅ ህልሞች.. መጽሐፍ ውስጥ የተካተቱት ባለጐች የተለያዩ አገራት ዜግነት ያላቸው ናቸው፡፡ ከእነዚህ ባለታሪኮች ጥቂቶቹ ከኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ጋር ያላቸው ተመሳስሎ ግርምት ቢፈጥርብኝ ለአንባቢያን ለማስቃኘት ወይም ለማሳየት ተነሳሳሁ፡፡
ራልፍ ሎረንና ከድር ኤባ
ሎረን ያገኘውን ሥራ ሁሉ መሥራት የሚወድ ልጅ የነበረ ሲሆን የዚያኑ ያህልም በአለባበስ መሽቀርቀር ነፍሱ ነበር፡፡ ገና በታዳጊነት እድሜው ዘናጭ ሙሉ ልብሶችን በመግዛት ዘንጦ መታየት በእጅጉ ያስደስተው እንደነበር ቤተሰቦቹና የእድሜ እኩዮቹ ሁሉ ይመሰክሩለታል፡፡ ኢትዮጵያዊው ቀኛዝማች ከድር ኤባ ደግሞ ገና የ12 ዓመት ልጅ ሳሉ ጀምሮ ጥሩ ልብስ፣ ቤት፣ መኪናና ቤተሰብ እንዲኖራቸው ታላቅ ህልምና ምኞት ነበራቸው፡፡ ከሁለቱም ባለታሪክ እንደምንረዳው ሁለቱም የፈለጉትን አግኝተዋል፡፡
ሻለሞ አሻሜና ዊይን ሁይዚንጋ
ዊይን ሁይዚንጋ ለትምህርት የሚከፍሉትን በማጣታቸው ምክንያት ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዋል፡፡ የገጠማቸውን ችግር ለማሸነፍ ያገኙትን መሥራት ስለነበረባቸው ቆሻሻ በየሰፈሩ እየዞረ በሚሰበስብ ኩባንያ ተቀጥረው ለሁለት ዓመት ከሠሩ በኋላ የራሳቸውን የቆሻሻ ማንሻ መኪኖች በመግዛት የግል ኩባንያዎች ባለቤትና ውጤታማ ሆነዋል፡፡ በሚስማር ንግድ ታዋቂ የነበሩት ኢትዮጵያዊው አቶ ሻለሞ አሻሜም ተመሳሳይ ታሪክ እንደነበራቸው ይነገራል፡፡ የወዳደቁ ነገሮችን ሰብስበው ለአገልግሎት የሚያበቁ ተቋማት በወቅቱ አልነበሩም፡፡ አቶ ሻለሞ አሻሜ በመንገድ ላይ ሲሄዱ የወደቀ ሚስማር አይተው አያልፉም ነበር፡፡ በዚህ መልኩ የሚሰበስቡትን ሚስማር በመሸጥ ወደ ካፒታል ይለውጡታል፡፡ በኋላ ላይ ከመርካቶ ታዋቂ ነጋዴዎች አንዱ ሊሆኑ በቅተዋል፡፡
ራልፍ ሎረንና ሻለሞ አሻሜ
ሎረን ሀብትና ንብረቱ እያደገ በመምጣቱ ያሉትን የቡቲክ ሱቆች ብዛት ሲጠየቅ ..እኔ ምን አውቃለሁ? የእኔን ልብስ የገዙትን ሰዎች ከየትኛው ጐዳና ላይ ካለው ቡቲክ እንደገዙት እናንተው ጠይቋቸው.. ይል ነበር፡፡ አቶ ሻለሞ አሻሜም ተመሳሳይ ታሪክ አላቸው፡፡
ከትንሽ ተነስተው የሱቅና የሚከራዩ ቤቶች ባለይዞታ መሆን የቻሉት ባለታሪኩ፤ በአንድ የክረምት ወቅት በድንገት የመጣ ዝናብ ለመጠለል በቅርባቸው ወዳገኙት ቤት ይገባሉ፡፡ በዘመኑ አከራይም ተከራይም ቤት የማደስ ልምድና ፍላጐት አልነበራቸውም ይባላል፡፡ አቶ ሻለሞ ዝናብ ለመጠለል የገቡበትን ቤት ጣራ ቀና ብለው ሲያዩ በሸረሪት ድር ተሞልቶ ተመለከቱ፡፡ ከዛም ..ቤቱ ባለቤት የለውም?.. የሚል ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡
ቤት ውስጥ የነበሩት ወይዘሮ የሰጡት መልስ፤ አቶ ሻለሞ አሻሜ እንደ ራልፍ ሎረን ያላቸውን ሀብት የት የት እንዳለ እንደማያውቁ ያመላከተ ነበር፡፡ ..የቤቱ ጌታ አቶ ሻለሞ አሻሜ መባላቸውን ከመስማቴ በስተቀር አይቻቸው አላውቅም፤ ወርሃዊ ኪራዩን የወከሉት ሰው ነው የሚቀበልላቸው.. የሚል መልስ ነበር ወይዘሮዋ የሰጡት፡፡ ይህ ታሪክ መርካቶ ውስጥ ተደጋግሞ ሲነገር ይሰማል፡፡
አቶ ነጋ ቦንገርና አሊያን አብራጂሞቭ
በካዛኪስታን አቻ የሌለው ኩባንያ ለመሆን የበቃውን የብረታ ብረትና የማዕድን ማውጫ፣ አሊያን አብራጂሞቭ ከጓደኞቻቸው ጋር ያቋቋሙት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው ባለሀብት አቶ ነጋ ቦንገር ከሌሎች ጋር በጋራ በመሥራት ይታወቃሉ፡፡ በ1960ዎቹ መርካቶ ውስጥ አምባሳደር ሆቴልን በጋራ በመክፈት ጀምረው የዳማ ሆቴል፣ የሰሜን ሆቴል፣ የግሎባል ሆቴል. . . ባለድርሻ ለመሆን የቻሉት በጋራ ሠርቶ ለማደግ ፍላጐቱ ስላላቸው ነው ይባላል፡፡
አቶ በላይ ተክሉና ጆን ዊላርድ ማርዮት
እነዚህ ሁለት ባለሀብቶች መንትዮች ተብለው ሊገለ በሚችል መልኩ የሚመሳሰሉባቸው ነገሮች በርካታ ናቸው፡፡ ሁለቱም ሥራ የጀመሩት ከታች ነው፡፡ የወላጆቻቸውን ኃላፊነት ወስደው ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር ሞክረው ተሳክቶላቸዋል፡፡ ሁለቱም ከሌሎች ጋር በሽርክና ሠርተዋል፡፡ ሆቴል ቤት ከፍተዋል፡፡ በድርጅቶቻቸው ለሚሠሩ ሠራተኞች ልዩ አክብሮትና እንክብካቤ ያደርጋሉ፡፡ ሁለቱም ባለሀብቶች በተቋማቸው ውስጥ እታች ድረስ ወርደው ማንኛውንም ሥራ ይሠራሉ፡፡ አቶ በላይ ተክሉ በዘመናቸው ከሚታወቁባቸው ልዩ መለያቻው አንዱም ይህ ነበር፡፡ መርካቶ ተክለሃይማኖት አካባቢ ወደሚገኘው ኬክ ቤታቸው በማንኛውም ሰዓት ሲደርሱ ደንበኛ የተገለገለበት ጠረጴዛ ባይዳ፣ ሰሀንና ብርጭቆ ባይነሳ ሠራተኞቹን ለማዘዝ አይሞክሩም፤ መሠራት ያለበትን ራሳቸው ሠርተው ሌሎችን ለሥራ በማትጋት ይታወቃሉ፡፡ጆን ዊላርድ ማርዮትም ተመሳሳይ ታሪክ አላቸው፡፡ ..የሆቴሎቹ ሥራ አስኪያጆች ማርዮት የወጥ ቤቱ በር ላይ በስንት ሰዓት እንደሚደርስ ፈጽሞ አያውቁም፡፡ ድንገት ይደርስና. . . ወጥ ቤቱን፣ መጋዘኑን፣ ፍሪጆቹን፣ ሬስቶራንቶቹን ሁሉ ይፈትሻል፡፡ በየመደርደሪያው፣ ጠረጴዛሥር፣ በቢለዋና ሹካ መሳቢያዎች ወዘተ አቧራ መኖሩን በጣቱ እየዳበሰ ያያል፡፡..
..ታላላቅ ህልሞች.. የተሰኘው የስኬት መጽሐፍ ስለ ቀና አመለካከት፣ ሌሎችን ስለማገዝ፣ ለአገልግሎት አለመሰሰት፣ ለውጥን ለመቀበል ዝግጁ ስለመሆን፣ መሻትን ቀድሞ ስለመሳል፣ በራስ ላይ እምነት ስለማሳደር፣ ውስጥን ስለማድመጥ፣ ስለአሉታዊ አስተሳሰብና ስለመሳሰሉት አጫጭር መልዕክቶችን ..ታላላቅ ህልሞች.. ስኬታማ ታሪካቸውን ያቀረበላቸው የውጭ አገር ዜጎች ባሕርይ ኢትዮጵያውያንም የሚጋሩት መሆኑ መገረምን ሊፈጥር ይችላል፡፡ ለንግድ፣ ለስፖርት፣ ለድርሰት. . . የሚፈጠሩ ሰዎች በየትም አገርና ምድር ቢፈጠሩ የሚጋሩት ተመሳሳይ ተፈጥሯዊ ባሕርይ ሳይኖራቸው አይቀርም ያስብላል፡፡

 

Read 4904 times Last modified on Saturday, 03 September 2011 12:40