Saturday, 03 September 2011 12:58

ቅልጣን

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(1 Vote)

ምን እንደሚስበው ሳይታወቅ ሰው ሁሉ አደባባዩን ይሽከረከራል፡፡ ዑደቱን ከአራቱም አቅጣጫ የሚቀላቀለው ሰው ወዳሻው የሚሄድ ሳይሆን በእሽክርክሪቱ ተጠልፎ የቀረ ይመስላል፡፡ የአራት ኪሎ ሃውልት ቀጥ ማለቱን ትቶ የትምህርት ሚኒስቴርን ህንፃ ቢደገፍ አማስሎ - አማስሎ አረፍ ያለ የወጥ እንጨት በመሰለ ነበር፡፡ የሚያቸፈችፈው ዝናብ እሽክርክሪቱ ላይ የሚነሰነስ ብትን ሽሮ መስሏል፡፡
አፍንጫውን ወደ ቤተመንግሥቱ አቅጣጫ ተክሎ የሚያነፈንፈው ሚኒባስ ታክሲ አልሞላ ብሎ እያዛጋ ነው፡፡ እንደመሄድ እየቃጣ መለስ ይላል፡፡
ከወደ አደባባዩ እሽክርክሪቱ የተፋቸው አንዳንድ ሰዎች ቢመጡም አቅጣጫችን ከአቅጣጫቸው ስላልገጠመ ቆም እያሉ ሌላ ታክሲ ይጠብቃሉ፤ ሲመጣ ይሮጣሉ፡፡

..ካሣንችስ ሃያ ሁለት!..
አዞ አፉ ወያላ እስከመንጋጭላው ተበልቅጦ ሲጣራ ..ኑ ላንቃዬ ሥር ተጠለሉ.. የሚል ይመስላል፡፡
ሰው የማይገባው ሠፊ አፉን በመፍራት ይሆን? ስል አሰብኩ፡፡ እንደ አጠዳደፌ ቢሆን ፊት ለፊት ከተኮለኮሉት ላዳ ታክሲዎች አንዱን ኮንትራት ይዤ በተፈተለኩ፡፡ ግን የሒሳቡ ቆንጣጭነት እያስፈራራኝ አልደፈርኩም፡፡
..ካሣንችስ መናኸሪያ ሃያ ሁለት..
..ፌርማታ አፍ.. አልኩኝ፡፡
አንድ ወንድና አንዲት ሴት ተጣብቀው የተወለዱ መስለው ድንገት ዱብ አሉ፡፡ በማማሰያው ግፊት የተፈናጠሩ ጓጓላ ሽሮዎች ይሆኑ? የሚኒባሱን አለመሙላት በማየት ይመስላል በሩ ላይ ቆመው የሚያልቅ የማይመስል ወሬአቸውን መሸርከት ያዙ፡፡ ለዝናቡ ደንታ የሰጣቸው አይመስሉም፣ ለሰው ደንታ የሰጣቸው አይመስሉም፡፡ ኧረ እንደውም ለፈጣሪም፡፡  
ከሁኔታቸው ፍቅረኛሞች መሆናቸውን ተረድቻለሁ፡፡ ሴቷ ሁለት እግሯን ይዘው እንደዘቀዘቋት ሁሉ ደሟ የተከማቸው ፊቷ ላይ ነው፡፡ ወንዱ ጭልፊት ፊት ነው፡፡ ግንባሩ ጠቦ የአፍንጫዋን አቅጣጫ ይይዛል፡፡ ቅንጡና ቅንጡ ላይ ያፈጠጡ ደምስሮች ይታያሉ፡፡ ልጅቷ የነተበ ሸሚዙን እየነካካች ተለጥፋ ታወራለታለች፡፡
..ፍቅር ያዘን ብሎ የምን ደንበር ገተር
እኛም አንድ ሰሞን እንዲህ አርጐን ነበር..
አልኩ በልቤ፡፡ አሁንም ችኮላዬ ለሌላ ሳይሆን ሳልጠግበው ለተቋረጠ የጫጉላ ወግ ነው፡፡
..የሞላ ካሳንችስ ሃያ ሁለት!..
ስለምን ይሆን የሚያወሩት? ከልብ ታወራለች፣ ከልብ ያዳምጣል፡፡ እኔ ከእኔ እንደተረዳሁት የፍቅር ወግ እምኑም ውስጥ የማይገባ እንቶ ፈንቶ ነው፡፡ ግን ከየትኛውም ወሬ በላይ በስሜት የተሞላ ነው፡፡
እሱ ፀጉሯን ይነካካል፤
እሷ ሸሚዙን ትነቅሳለች
እግራቸው ስር የሚያቸፈችፈው ዝናብ ከመሬት ጋር ሲጋጭ የአሸን ክንፍ ይመስላል፡፡ የሚያወሩትን ማዳመጥ አጓጓኝ፡፡
..አንቀሳቅሰው.. ወያላው ሾፌሩን ያዝዛል፡፡ ሄደት መጠት በል ነው፡፡ የማይተዋወቅና ድንገት የተገናኘው ስለ ኑሮ ውድነት ነው የሚያወራው፡፡ ፍቅረኛሞች መረጃ አልባ ወሬ ነው የሚሸረክቱት፡፡ ፖለቲካ፣ ፍልስፍና፣ ኃይማኖት ርዕስ ቢሆኑም የሚደመጠው በወሬው መካከል የሚተላለፈው ስሜት ብቻ ነው፡፡
ሴቷ ወፍ እግር ናት፣
እሱ ድፎ ከመሰለ ጫማ ውስጥ የብልቃጥ ቂጥ የሚያክል አውራጣቱ ብቅ ብሏል፡፡
ወያላው ..ውስጥ ሁኑና አውሩ.. አላቸው፡፡ ማሟያ ሊያደርጋቸው እንደሆነ ገብቶኛል፡፡
..እሷ ናት የምትሄደው.. አለ ወንዱ፡፡
..እኮ ውስጥ ሁኑና ሲሞላ.....
ደስ ብሎኛል፡፡ የጫጉላ ወሬዬ እስኪደርስ መጥተው ከእኔ ፊት ተቀመጡ፡፡ ወንዱ እንደማኮብኮብ ብሏል፡፡
..ካሳንችስ ሃያ ሁለት.. የወያላው አፍ ማጅራቱ ላይ በነጥብ የተለያየ መሰለ፡፡ ፍቅረኛሞቹ ላይ የጣልኩት ጆሮዬ ምንም ይዞ አልተመለሰም፡፡ ማጉተምተም ብቻ፡፡ ነገር ግን እግራቸው እርጥብ ኖሮ ታክሲው ውስጥ ሰዎች ገባ ገባ ማለት ጀመሩ፡፡ እንዲህ ያለ ሁኔታ ለፍቅረኛሞች እንደ እድለቢስነት ይቆጠራል፡፡ መለያየትን ያውጃል፡፡
..ካንቺ ቀድሞ እደርሳለሁ.. ይላል ወንዱ፡፡
ለቀጣዩ ቀጠሮ መሆን አለበት፡፡ ካሁኑ ወደ ቀጠሮው ቦታ ይሄድ ይሆናል፡፡ ግንባሯን ሳማት፡፡ የረጋው ደሟ በሐፍረት ፊቷ ላይ ገነፈለ፡፡ ሰዎች ይገባሉ፡፡ ሚኒባሱ እንደመሙላት ብሏል፡፡ ከኋላ የጐደለውን ሰው ልቆጥር ዞር ስል የሰው ሁሉ ቀልብ ፍቅረኛሞቹ ላይ መሆኑን ልብ አልኩ፡፡ እነሱ እንደ አበባ ይታያሉ እንጂ አያዩም፣ ቀልብ ይስባሉ እንጂ ቀልባቸው አይሳብም፡፡
ወያላው ሚኒባሱ ላይ ወጥቶ በእግሩ ወለሉን እየደበደበ በብልቅጥ አፉ ይጮሃል፡፡ ወንዱ በወያላው ጀርባ በኩል ተሸማቆ ከታክሲው ወረደ፡፡ ቀልቡ ሁሉ ከኛ ጋር ነው፡፡ በድኑን እንደቆመ ኪሱን ፈታተሸ፡፡ የተጣጣፈ ብር አውጥቶ በመነጣጠል ሁለት መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ ወደ ወያላው ዘረጋ፡፡ ሥጋውን ቆርጦ የመስጠት ያህል ሆኖ ተሰማኝ፡፡
ወደ ፍቅረኛው ጣቱን ጠቁሞ ..መልሱን ስጣት.. አለው በኩራት
..የት ነው የምትሄደው?..
..ሃያ ሁለት..
..ታዲያ የምን መልስ ነው? እንደውም አርባ ሳንቲም ጨምር..
ልጁ ሞጠጣ ፊቱ አመድ መስሎ የሚያቸፈችፈውን ዝናብ መጠጠ፡፡
..የለኝም..
ከእኔ በቀር ልብ ያለው ያለ አልመሰለኝም ነበር፡፡ ግን ታክሲው ውስጥ ያለ ሁሉ ሳቀ፡፡ ዓለም ውርደት ለመሰላት ነገር ቸልተኛ አይደለችም፡፡ ሰማይ ጭምር ብልጭልጭ ጥርሱን አሳየ፡፡ ዷ! ዷ! ዷ! ዷ! የሰማየ ሰማይ ሳቅ፡፡
የአይን ቅብብሉ ከልጁ ወደ ፍቅረኛው፣ ከፍቅረኛው ወደኛ ተላለፈ፡፡
..ምን ያስቃል? ማጣት ያስቃል ወይ?..
ጭንቅላት ሁሉ በሐፍረት አቀረቀረ፡፡ እኔ በበኩሌ ቀና ማለት ተሳነኝ፡፡ ልጁ እንደ ጥላ የቤተመንግሥቱን አቅጣጫ ተከትሎ ውልብ ሲል ታየኝ፡፡
..በደንብ ሳቁ፤ ሌላም ልንገራችሁ፤ እኔ ስለደከመኝ ነው ያሳፈረኝ እንጂ ሁለታችንም የምንሄደው ሃያ ሁለት ነው፡፡ እሱ በእግሩ እስኪደርስ እዛ እጠብቀዋለሁ፡፡ ሳቁዋ! ምነው ዝም አላችሁ?..
መልስ የለም፡፡ ፀፀት ብቻ፡፡  
ልጅቷ ዞራ በትክክሉ ተቀመጠች፡፡ ታክሲው አንድ ሰው ብቻ ይቀረዋል፡፡ ወያላው መጥራቱን አቁሞ ያዳምጥ ኖሯል፡፡ ..ጥሪው ላድርሳችሁ.. አለ፡፡ ያም ሳይበቃው ልጁ የሰጠውን ሁለት ብር ጭኗ ላይ አስቀመጠላት፡፡
ይሄ አዞ አፍ ከኛ ተሽሎ ተገኘ፡፡ ወደድኩት፡፡ ከኔ አጠገብ ልብ ያላልኩት ባለመነጽር ብድግ ብሎ አስር ብር በትከሻዋ ላይ አሳልፎ ጭኗ ላይ አስቀመጠ፡፡ ታክሲው ውስጥ ያለው ሁሉ የፀፀቱን ዋጋ ጣለላት፡፡
አስር ብር!
ሦስት ብር!
አምስት ብር!
ሃምሳ ብር!
እኔም የፀፀቴን ያህል እጄን ዘረጋሁ፡፡
ልጅቷ እንደመባነን ብላ ወደ ኋላ አየች፡፡ ከዚያም ጭኗ ላይ ያለውን ብር እያየች ለጥቂት ጊዜ ፈዘዘች፡፡ ..ልውሰድ - ልተው.. የምትል መሰለኝ፡፡ ላደፋፍራት እጄን ሰድጄ የትከሻዋ አጥንት ላይ አኖርኩት፡፡ ከዚህ በኋላ ያሳየችው ፍጥነት ለተአምር የሚመዘገብ ነው፡፡ ብሮቹን ሰባስባ ከታክሲው ውስጥ ስትፈተለክ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ብሮች ወለሉ ላይ ወድቀው ቀሩ፡፡ ወደ ፍቅሯ በረረች፡፡
ቢጠበቁ አልመጡም፡፡ ወያላው በታማኝነት ጠበቃቸው፡፡ ቀሩ፡፡ ..የወደቀውን ሁለት ብር ወያላው ሌላ ያጣ እንዲያሳፍርበት በሙሉ ድምጽ ተወስኖ ተሰጠው፡፡ በጐደለ ሞልተን ተንቀሳቀስን፡፡ ለጥቂት ጊዜ ፀጥታ ሰፈነ፡፡ ልጆቹን ለጫጉላው ወሬዬ አሰናዳቸው ጀመር፡፡
መናኸሪያ ሆቴል እንደደረስን አንድ ላዳ ታክሲ ደጋግሞ ጡሩንባ እየነፋ ከወሰደን ሀሳብ አባነነን፡፡
ግማሹ ..ከለፍላፋ.. እያለ ይሳደብ ጀመር
..የት ለመድረስ ነው?..
በላዳው ታክሲ የኋላ መስኮት አንድ እጅ ወጥቶ ሲውለበለብ ይታያል፡፡ ሰው ሁሉ ቀልቡ ለታክሲው ተስቧል፡፡ በዚህ መካከል ወያላው አዞ አፉን በፊቴ ላይ አሳልፎ ለመሳደብ ከሞከረ በኋላ ፈዞ ቀረ፡፡ ብር የያዘበትን እጁን አወናጭፎ አፉ ላይ በመደርገም
..እንዴ፣ ልጆቹ.. አለ፡፡
ከታክሲው የሾለከው እጅ ሁለት ሆነ፡፡ ባይ ባይ እያሉን ቀደሙን፡፡ ከበስተኋላ ስንመለከት እንደተቃቀፉ ያዩናል፡፡
ሌላ የወሬ ርዕስ፡፡

 

Read 5919 times Last modified on Saturday, 03 September 2011 13:02