Saturday, 03 September 2011 13:03

ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውድቀት ማን ይጠየቅ?

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)
  • ፌደሬሽኑ፤ አትሌቶች ወይንስ መንግስት?

በደቡብ ኮሪያዋ ከተማ ዳጉ  ሲካሄድ በቆየው 13ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በነበራት ተሳትፎ እስከ ትናንት በአንድ ወርቅና በሁለት ነሐስ ሜዳሊያዎች መወሰኗ እያነጋገረ ነው፡፡ ባለፉት 4 ዓመታት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ እያጋጠመ ላለው ድክመትና የሜዳሊያ ድርቅ ተጠያቂ መኖር አለበት በሚል አስተያየቶች እየተሰጡ ነው፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት በታላላቅ የአትሌቲክስ የውድድር መድረኮች የኢትዮጵያ አትሌቶች ባስመዘገቡት ታሪክና የውጤት ገድል ስንኮራ ኖረናል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን አንገት እየደፋን ነው፡፡ የባንዲራችን ምልክትና መታወቂያችን የሆነው የአትሌቲክስ ስፖርት ከእጃችን እያመለጠ እንደሆነ ይስተዋላል፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በፍፁም የበላይነት በሜዳሊያ እያሸበረቅን ውጤት ባስመዘገብንባቸው የአትሌቲክስ ውድድሮች የጠበቅነውን እያገኘን አይደለም፡፡ ታድያ ለዚህ ውድቀት ማን YºyQ? ፌደሬሽኑ፤ አትሌቶች ወይንስ መንግስት?
በ13ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የመክፈቻ ቀን በሴቶች ማራቶን ትልቁ ውጤት ከሜዳሊያ ውጪ በዲፕሎማ በግል 4ኛ ደረጃ በቡድን 3ኛ ደረጃ የተመዘገበ ሆነ፡፡ ኬንያ ከ1-3 ወጥተው ሶስቱንም ሜዳልያዎች ወሰዱ፡፡ በ10ሺ ሜትር የሴቶች ውድድርም ለ2ኛ ተከታታይ የዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያው ከኢትዮጵያ አመለጠ፡፡ ትልቁ ውጤት በብዙነሽ በቀለ 4ኛ እና በመሰለች መልካሙ 5ኛ ደረጃ ማግኘት ተወሰነ፡፡ ኬንያውያን በአንፃሩ ከ1-3 በመውጣት የሜዳልያ ሽልማቶቹን በድጋሚ ጠራረጉ፡፡ በሴቶች 5ሺ ሜትርም የ10ሺን ድል ከኢትዮጵያ ላይ የነጠቁት ኬንያውን በድጋሚ የበላይነታቸውን በማሳየት ወርቅና ብሩን ወሰዱ፡፡ ይህን የኢትዮጵያና የኬንያ ልዩነት ለመላው ኢትዮጵያዊ እንደ መርዶ ወረደ እንጂ የተጠበቀው አይደለም፡፡
በዓለም ሻምፒዮናና በኦሎምፒክ መድረኮች አስቀድሞ በ3ሺ መሰናክል ብቻ ተቀናቃኝ ያልነበራቸው ኬንያውያን አሁን በረጅም ርቀት ውድድሮች ኢትዮጵያውያን የነበራቸውን የበላይነት በመንጠቅ ቀድመው መሄድ ጀምረዋል፡፡ በእነዚህ የረጅም ርቀት የአትሌቲክስ ውድድሮች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የበላይነቱን እያጠናከረ መቀጠል ይገባው ነበር፡፡ ሁኔታው የተገላቢጦሽ ሆኖ ውጤቱ እያሽቆለቆለ መጥቷል፡፡
ሳይንሳዊና ዘመናዊ የሥልጠና መዋቅር አለመኖር
በባህርማዶ ባለሙያዎች አንዳንድ ሳይንሳዊ ጥናቶች ተሰርተው የኢትዮጵያ ምርጥ የረጅም ርቀትና ማራቶን አትሌቶች በ2 የአገሪቱ ክልሎች በሚገኙ ህዝቦች እንደሚመጡ ያረጋግጣሉ፡፡ 73 በመቶ የሚሆኑት እነዚህ ምርጥ አትሌቶች ከሁለቱ ከተሞች አሰላና በቆጂ የሚገኙ ናቸው፡፡ 43 ከመቶ የሚሆኑት በአስተዳደጋቸው እና በተማሪ ቤት ቆይታቸው በቀን ከ5-10 ኪ.ሚ በመሮጣቸው ከብቃታቸው ጋር የተገናኙ እንጂ መደበኛ ልምምድ የሚያደርጉ አይደሉም፡፡ 29 በመቶ የሚሆኑ አትሌቶች በመደበኛነት በትራክ በሜዳ ልምምድ የሚሠሩ ቢሆንም በአገሪቱ ብሔራዊ ስታዲየም ብቸኛ የመሮጫ ትራክ ልምምድ የሚሰሩ በመሆናቸው ደረጃቸውን ዝቅተኛ አድርጓል፡፡ 15 ከመቶ የሚሆኑ አትሌቶች ብቻ የወቅቱ የዓለም አትሌቲክስ የሚጠይቀውን የልምምድ ደረጃ የብቃት ማሟያ ዝግጅት የሚያደርጉ ናቸው፡፡ እነዚህ የምርምርና የጥናት ግኝቶች ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ምን ያህል ግብዓት ሆነዋል ከተባለ ተወቃሹ በኢትዮጵያ አትሌቲክስን በበላይነት የሚመራው ፌዴሬሽን ነው፡፡ ይህን መሰል ሳይንሳዊ ጥናትና ዘመናዊ የልምምድ መዋቅር በአግባቡ ተዘርግቶ በእኛ አገር እየተሠራበት አይደለም፡፡
ተጠብቀው ያልሆነላቸው የኦሎምፒክ ፈርጦች
በዘንድሮው የዓለም ሻምፒዮና  በቤጂንግ ኦሎምፒክ ላይ የወርቅ ሜዳልያ የነበራቸውና በየውድድር መደባቸው ታላላቅ የሚባሉ አትሌቶች ክብራቸውን ለማስጠበቅ ሳይሆንላቸው መቅረቱም ኢትዮጵያን ያካተተ ነው፡፡ ታላላቆቹ አትሌቶች በዓለም ሻምፒዮናው bgùÄT\ውድድር በማቋረጥ፣ በቴክኒክ ስህተትና በብቃት መጓደል አልሆነላቸውም፡፡ ታዋቂው አውስትራሊያዊ የምርኩዝ ዝላይ ተወዳደሪ ስቲቭ ሁከር ማጣርያ ማለፍ ሳይችል ቀርቷል፡፡ በ100 ሜትር የማጣርያ ውድድር የሪኮርዱ ባለቤቱ ዩሴያን ቦልት በአነሳሱ ሁለቴ በፈፀመው ስህተት በቀይ ካርድ ተሰናብቷል፡፡ ራሽያዊቷ የምርኩዝ ዝላይ ተወዳዳሪ ዬሌና ኢዝንባዬቫም በውድድር ዓይነቱ የዓለም ሪኮርድን እንደመያዟና በኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ብትወስድም በዳጉ ካልሆነላቸው የዓለም ምርጥ አትሌቶች ተርታ መሰለፍ ግድ ሆኖባታል፡፡ ፈጣኖቹ የአጭር ርቀት አትሌቶች ጃማይካዊው አሰፋ ፓውልና አሜሪካዊው ታይሴን ጌይ ዳጉ ደርሰው ሲያበቁ ከነበረባቸው ጉዳት ሳያገግሙ በመቅረታቸው ተሳትፏቸውን ሰርዘዋል፡፡ ሁለቱ ኢትዮጵያውያኖች መሰረት ደፋርና አትሌት ቀነኒሳ በቀለም ያልሆነላቸው የኦሎምፒክ ፈርጦች ናቸው፡፡ በ10ሺሜ ውድድር እንደሚያሸንፉ ግምት ተሰጥቷቸው የነበሩት መሠረትና ቀነኒሳ ውድድራቸውን በተለያዩ ምክንያቶች አቋርጠው ወጥተዋል፡፡ በአጠቃላይ ከ3 ዓመት በፊት በቤጂንግ በተደረገው ኦሎምፒክ ሻምፒዮን ሆነው የወርቅ ሜዳልያ ከወሰዱ 17 አትሌቶች መካከል በዳጉ የዓለም ሻምፒዮና ክብራቸውን በማስጠበቅ የወርቅ ሜዳልያ የወሰዱት 3 ብቻ ናቸው፡፡ ይህ ሁኔታም የኦሎምፐ የወርቅ ሜዳልያ የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን በቂ የብቃት ማረጋገጫ እንዳልሆነ አመልክቷል፡፡
በወንዶች 10ሺ ሜትር ላይ ለ2 ዓመታት በጉዳት ሳቢያ ከውድድር ርቆ የቆየው አትሌት ቀነኒሣ በቀለ ክብሩን እንደሚያስጠብቅ ተገምቶ ቢገባም ሩጫውን ከ6 ኪ.ሜ በኋላ አቋረጠ፡፡ የ29 ዓመቱ አትሌት ቀነኒሣ በቀለ በ10ሺ ሜትር ውድድር አቋርጦ መውጣት ይቅርና ሽንፈት ሲያጋጥመው በሩጫ ዘመኑ ለመጀመርያ ጊዜ ነበር፡፡ ከ11 ወራት በኋላ በሚደረገው የለንደን ኦሎምፒክ ካለበት ጉዳት በብቃት አገገግሞ የኦሎምፒክ ክብሩን ለማስጠበቅ ከባድ ፈተና እንደሚሆንበት የተለያዩ ዘገባዎች ተንትነዋል፡፡በሴቶች 10ሺ ሜትር ውድድር ጥሩነሽ በጉዳት ከተሳትፎዋ ከቀረች በኋላ እሷን ለመሸፈን የገባችውና ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷት የነበረችው አትሌት መሠረት ደፋርም ከ6 ኪ.ሜ በኋላ  ውድድሩን አቋርጣ ወጣች፡፡ ምክንያቷም ዳጉ ከገባች በኋላ በፍሉ ቫይረስ በመጠቃቷ እንደሆነ ዘገባዎች ገለፁ፡፡ ውጤታማ ትሆንበታለች ተብሎ በተገመተው የሴቶች 5ሺ ሜትር ውድድርም የመሠረት ስኬት በነሐስ ሜዳልያ ተወሰነ፡፡ በሁለቱ አትሌቶች ድክመት ማንን መወንጀል YÒ§L? በግል የሚስተዋለው ለእነሱ ተተኪ የሚሆኑ አትሌቶች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አለማፍራቱ ነው፡፡ ይህን ጉልህ ድክመት ለመሸፈን በእግር ኳስ ስፖርት የለመድናቸው የሽንፈት ሰበቦችና ምክንያቶች ወደ አትሌቲክሱ መዛመታቸውም እጅግ ያሳስባል፡፡ ፌዴሬሽኑ የአትሌቶቹን ወቅታዊ የጉዳት ሁኔታና የብቃት ደረጃ በአግባቡ ሳያገናዝብ በዓለም ሻምፒዮናው መሳተፉም የሚያስተዛዝብ ነው፡፡
የኬንያ አትሌቲክስ ከኢትዮጵያ ለምን ላቀ?
አንዳንድ የኬንያ ሚዲያዎች እንደዘገቡት በዳጉ እየተደረገ በሚገኘው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የኬንያ አትሌቲክስ ቡድን ለኢትዮጵያ ከተፎካካሪነትም በላይ ልቆ ሄዷል፡፡ ኬንያውያን ከአጭር ርቀት እስከ ማራቶን በሜዳልያ የተንበሻበሹት በተደራጀ የአስተዳደር እንቅስቃሴና የመንግስት ድጋፍ በመታገዝ በከፍተኛ ልምምድና የላቀ ትጋት ለፉክክር በመግባታቸው ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ በኬንያና በኢትዮጵያ የአትሌቲክስ እንቅስቃሴ ሰፊ ልዩነት ይስተዋላል፡፡ የኢትዮጵያ ጥቂት አትሌቶች በርካታ የኬንያ አትሌቶችን በመብለጥ በታላላቅ የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ውድድሮች ያስመዘገቡት የውጤት ታሪክ እየተፋቀ ካለፉት 4 ዓመታት ወዲህ ልዩነቱ እየጠበበ ነው፡፡ የኬንያ አትሌቶች ብዛት በተለይ በረጅም ርቀት ውድድሮች ከኢትዮጵያ በ10 እጥፍ ብልጫ እያሳየ መምጣቱ ለልዩነቱ መጥበብ አበይት መንስኤ ነው፡፡ ምክንያቱም ተተኪና ወጣት አትሌቶች በኬንያ በዝተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ደግሞ የሉም ወይም የተሳትፎ ዕድል አጥተዋል፡፡ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውጤታማ እና ተቀናቃኝ የሌላቸው ጥቂት ምርጥ አትሌቶች በ10 ዓመት አንዴ ሲከሰቱ በኬንያ ግን ተተኪ አትሌቶች በየዓመቱ እንደ አሸን መፍላታቸው ልዩነቱን ፈጥሯል፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ ውድድር ኢትዮጵያውያን ይታወቁበት የነበረው የቡድን ሥራ ካለፉት 4 ዓመታት ወዲህ እየቀረ ሲመጣ ኬንያውያን ይህን ኮርጀው የራሳቸው አድርገውታል፡፡ ይህ የቡድን ሥራ ችግር በኢትዮጵያ አትሌቲክስ መታየቱ ፌዴሬሽኑን፣ አትሌቶቹንና አሰልጣኞቹን በእኩል ተጠያቂ የሚያደርግ ነው፡፡
የኬንያ አትሌቲክስን በበላይነት የሚመራው ኬንያ አትሌቲክስ በ2006 እኤአ ላይ የራሱን ሙዚዬም ከመክፈቱም በላይ የተደራጀና ዘመናዊ የአስተዳደር መዋቅርና በስፖንሰርሺፕ የደመቁ ብሄራዊ ውድድሮችን በማከናወን ተደንቆም ለ3 ጊዜያት የኬንያ ምርጥ የስፖርት ፌደሬሽን ተብሎ በመንግስት ሊሸለም በቅቷል፡፡ የኬንያ አትሌቲክስ ከ4 ዓመት በፊት በቤጂንግ ኦሎምፒክ 14 ሜዳልያዎች ሲያገኝ አምስቱ የወርቅ ሜዳልያ የነበሩ ሲሆን በአጭር፤ በመካከለኛና በረጅም ርቀት የአትሌቲክስ ውድድሮች በርካታ ምርጥ አትሌቶቹን የማፍራት ሂደትን ባለፉት ሁለት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች አረጋግጧል፡፡ ባለው ራዕይም ለሚቀጥሉት 5 እና 6 የዓለም ሻምፒዮናና የኦሎምፒክ ውድድሮች አትሌቲክሱን በከፍተኛ ስኬት ለማሳደግ እየሰራ ነው፡፡ በአንፃሩ በቤጂንግ ኦሎምፒክና ከዚያም b|§ በተደረጉ የዓለም ሻምፒዮናዎች ከእነድክመቱ የዘለቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን የራሱን ቢሮ ህንፃ በመገንባትና ሌላ በሃራጅ የተገዛ ሆቴል በባለቤትነት ከመያዝ ውጪ ለስፖርቱ የረጅም ጊዜ እቅድ እንኳን ሳይኖረው እየሰራ ይገኛል፡፡
በኬንያ አትሌቲክስ ዘመናዊ አደረጃጀት ተጠናክሯል የክለቦችና የአገር አቀፍ ውድድሮች እንቅስቃሴ፣ የመንግስት ሁለገብ ድጋፍ፤ የአንጋፋና ምርጥ አትሌቶች ኢንቨስትመንትና የውጪ ኩባንያዎች የስፖንሰርሺፕና የልማት ድጋፍ በኬንያ የላቀ ለውጥ እየፈጠረ ይገኛል፡፡ በአንጻሩ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ክለቦች እንቅስቃሴ አበረታች ሊባል ቢችልም በዘመናዊ አደረጃጀት አለመዋቀሩ፣ በመንግሥት ድጋፍ በቂ አለመሆን፤ የአንጋፋና ምርጥ አትሌቶች በስፖርቱ ላይ ያላቸው ኢንቨስትመንት መዳከሙ ለስፖርቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ተዕኖ ፈጥሮ ይስተዋላል፡፡ በኬንያ አትሌቲክስ በመንግስት፤ በግል ተቋማትና በአትሌቶች ኢንቨስትመንት ደረጃ እስከ 10 የማሰልጠኛ አካዳሚዎች እና ትራክ ያላቸው ከ8 በላይ የመለማመጃ ስፍራዎች ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ በቅርቡ ከተሰራው የጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ከ2 የትራክ መለማመጃ በአገሪቱ ብሔራዊ ስታድየም የሚገኘው ብቻ ነው፡፡  
በኬንያ ያሉ የአትሌቲክስ ክለቦች ምንም እንኳን ደረጃውን የጠበቀ የመለማመጃ ትራክና ሌሎች አስፈጊ መሠረተ ልማቶች በበቂ ሁኔታ ያልተሟሉላቸው ቢሆኑም ያላቸው የአደረጃጀት ዘመናዊነት እድገት ፈጥሮላቸዋል፡፡ ክለቦቹ በየጊዜው የዓለም አቀፍ ስኬትን ሊያስመዘግቡ የሚችሉ ወጣትና ተተኪ አትሌቶችን በብዛት የሚያፈሩባቸው ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ የአትሌቲክስ ክለቦች በየዓመቱ በሚደረጉ ብሔራዊ ሻምፒዮናዎች እና ሌሎች ውድድሮች ለመሳተፍ ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር በዘመናዊ አደረጃጀት የሚሠሩ ካለመሆናቸውም ሌላ የተሟላ መሠረት ልማት አለመያዛቸው ተተኪዎችን የማፍራት ተስፋቸውን አሟጥጦታል፡፡ በኬንያ አትሌቲክስ ክለቦች ያላቸውን አደረጃጀት በፋይናንስ ለማጠናከር ከተለያዩ የአገሪቱ ኩባንያዎችና ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ፈጥረው በመሥራታቸው አቅማቸውን አሳድገዋል፡፡ በዚህም የፋይናንስ አቅም መጠናከር በስፖርቱ በሚያደርጉት የዕድገት እንቅስቃሴ የረጅም ጊዜ ዕቅድ በማውጣት እንደሠሩ አግዟቸዋል፡፡ በአንጻሩ በኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ምንም እየተሠራ አይደለም ለማለት ይቻላል፡፡
ኢብራሂም ጄይላን ከየት mÈ? ከጃፓን
በ13ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዳጉ ላይ ኢትዮጵያ 42 አትሌቶች ብታሳትፍም  የሜዳሊያ ድሎችን  እስከ ትናንት ያስመዘገቡት ሦስት አትሌቶች ብቻ ናቸው፡፡ በሻምፒዮናው በሁለተኛው ቀን በወንዶች 10ሺ ሜትር 1ኛ እና 3ኛ ደረጃ ባገኙት ኢብራሂም ጄይላንና ኢማና መርጋ እንዲሁም ትናንት በሴቶች 5ሺ መሠረት ደፋር 3ኛ ሆኖ በጨረሰችበት ውድድሮች የተገኙ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት 10 የዓለም ሻምፒዮናዎች በ10ሺ ሜትር ወንዶች የወርቅ ሜዳልያ ድሏን ጠብቃ እንድትሄድ መታደግ የቻለው ኢብራሂም ጄይላን ክስተት ነው፡፡ የ22 ዓመቱ አትሌት ኢብራሂም ጄይላን ያስመዘገበው የወርቅ ሜዳልያ ድል ሃይሌ ገብረስላሴ በሲድኒ ኦሎምፒክ ያስመዘገበውን ድል ያስታወሰ  ነው፡፡ የሚገርመው ኢብራሂም ጄይላን ወደ አትሌቲስ ስፖርት የገባው ሃይሌ በሲዲኒ ኦሎምፒክ ከፖል ቴርጋት ጋር እስከመጨረሻው መስመር ተናንቆ በ9 ማይክሮ ሰከንድ ልዩነት በመቅደም የወሰደውን የወርቅ ሜዳልያ ተመልክቶ ነበር፡፡ ዳጉ ላይ ኢብራሂም የእንግሊዙን አትሌት ሞ ፋራህ ቢያንስ 300 ሜትር ርቀት በማሳደድ በመጨረሻዎቹ 12 ሜትሮች ቀድሞ ገብቶ የሃይሌን ታሪካዊ ድል ደግሞታል፡፡ ኢብራሂም ጄይላን ወደዚህ የወርቅ ሜዳሊያ ድል ከመምጣቱ በፊት በኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን  በቤጂንግ ኦሎምፒክና በበርሊን የዓለም ሻምፒዮና ይገባው የነበረውን የተሳትፎ ዕድል አላገኘም ነበር፡፡ በዳጉ የወርቅ ሜዳሊያ ድሉ ካስመዘገበ በኋላ አትሌት ኢብራሂም ጄይላን ከአይኤ.ኤ.ኤፍ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ሁኔታው ያበሳጨው እንደነበር ተናግሯል፡፡ የደረሰበትን በደል ለመቋቋም አትሌቱ ማናጀሩ ከሆነው ብሩክ በቀለ ጋር በመነጋገር በጃፓን በሚገኝ አትሌቲክስ ክለብ ለመስራት ወሰነ፡፡  ቋሚ ገቢና የውድድር ዕድል በሚያገኝበት የአትሌቲክስ አስተዳደር ለመሥራት እንደሚያመች ገብቶታል፡፡ ከ2010 እ.አ.አ. ጀምሮ ከቶክዮ ከተማ አቅራቢያ ወደምትገኘው ሳያተማ የተባለች ከተማ ተቀማጭ ሆኖ በሆንዳ ሞተርስ የአትሌቲክስ ክለብ አባልነት ሲሰራ ቆየ በዳጉ የዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያውን ሊጎናፀፍም በቃ፡፡

 

Read 2909 times Last modified on Saturday, 03 September 2011 13:07