Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 10 September 2011 11:34

ጉዱ ካሳ ናፈቀኝ!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ጋዜጠኛ፤ ሰዓሊና የጥበብ ታሪክ አጥኚ የነበሩት ስዪም ወልዴ ራምሴ ግለ-ታሪካቸውን በጻፉበት ..ኩረፊያ የሸፈነው ፈገግታ.. መጽሀፋቸው ላይ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ካሰፈሯቸው ትዝብቶች በአንዱ እንዲህ ..የህጉ ሰው በኢኮኖሚስቱ ሙያ ላይ ወይም ኢንጂነሩ በሕክምና ላይ ወይም ሐኪሙ በግብርና ላይ ወዘተ የመሰለወን ሀሳብ ከመስጠት የሚቆጠበውን ያህል በሌሎች መስኮች የተሰማሩ ባለሙያዎች በባህል ጥያቄ ላይ ሃሳብ ለመሰንዘር ቅንጣት ያህል አያቅማሙም፤ አሁን  በጋዜጣ፤ በመጽሔት፤ በሬድዮና ቴሌቭዥን ከዝነኛ ሰዎች አንደበት የሚባሉትን ነገሮች ላነበበና ለሰማ ስዩም ወልዴ ከአስርት አመታት በፊት የታዘቡት በባህልና ጥበብ ነክ ጉዳዮች ላይ የሚሰጡ ደፋርና ጥራዝ-ነጠቅ አስተያየቶች፣ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ህክምና ኢኮኖሚክስ ግብርና በሚል መስክ መምረጥ  እንዳቆሙ ቢሰሙ ምን ይሉ ነበር

..ረሀቡ የተከሰተው ነጋዴዎች እህሉን በየመጋዘኖቻቸው ስላከማቹት ነው..፣ ..በፊልም ሁለት ዘውጎች አሉ - ኮሜዲና ትራጄዲ..፣ ..የ1960ዎቹ አመጽ የኢትዮጵያ ወጣቶች ከአማራው ገዢ መደብ (ሕዝብ) ጋር ያደረጉት ትግል ነው..፣ የኢትዮጵያ ፊልሞች በአውሮፓ መድረክ የማይሸለሙት እነሱ የሚፈልጉትን የመጨፋጨፍ ታሪክ ስለማንሰራ ነው.. እነዚህ በአደባባይ የተነበቡ፤ የተሰሙ የታዋቂ ግለሰቦች ንግግሮች ናቸው፡፡ ብዙ አስገራሚ ንግግሮችን ማስታወስ ይቻላል፡፡ የተናገሩት ደግሞ ኢቲቪ እንደሚያደርገው ድንገት መንገድ ላይ የሚያልፉ ሰዎች ተጠይቀው ቢሆን እምብዛም ላያስገርም ይችላል፡፡ አንጻራዊ ስኬትና እውቅና ያላቸው ግለሰቦች ናቸው፡፡ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች፣ የፊልም ዳይሬክተሮች ወዘተ በአደባባይ ፍጹም የተሳሳቱና ከእውነትም ከዕውቀትም የራቁ ነገሮችን አንደዋዛ ሲናገሩ ማድመጥ የተለመደ ሆኗል፡፡
የሚከበሩ ተቋማት፤ የታፈሩ ምሁራን፤ ጠንካራ ሚዲያ ባሉበት ሀገር ሁለቴ ሳያስቡ መናገር ያስገምታል፤ ወዲያውም ያስከፍላል፡፡ ከላይ እንደተጠቀሱት ያሉ አስገራሚና ደፋር ንግግሮችን ያለምንም ሀፍረት ለመናገር እንደማጣቀሻነት የተለመዱ ሶስት ዋሻዎች አሉ፡፡ እነዚህ ዋሻዎች አንድን ነገር እውነት ይሁን ሀሰት ለማረጋገጥ ካለመመቸታቸውም በላይ አደናጋሪ ናቸው፡፡ ተናጋሪው ሃላፊነት እንዳይወስድባቸው ይመቻሉ፡፡
ዋሻ አንድ- ..በምዕራቡ ዓለም/ ባደጉት ሀገራት..
..በምዕራቡ ዓለም እንደሚታወቀው/ እንደሚደረገው.. ብሎ ንግግርንም ሆነ ጽሁፍን መጀመር ከየትኛውም ተጠያቂነት ለማምለጥ ሁነኛ ዋሻ ነው፡፡ ከግሪክ እስከ አሜሪካ፤ ከካናዳ እስከ ኒውዚላንድ የሚያካትተውን የምዕራቡ ዓለም እንደ አንድ ሰፈር ለየትኛውም ርዕሰ-ጉዳይ ማጣቀስ የደማም ንግግር መገለጫ ሆኗል፡፡
በታሪክ፤ በባህል፤ በቋንቋ ወዘተ ብዙ ገጽታ ያለው የምዕራቡን ዓለም በሁሉም ጉዳይ እንደ አንድ ቤት ለመጥቀስ ያዳግታል፡፡ በምዕራቡ ዓለም የጤና ዋስትና ማግኘት ቀላል ነው፤ በምዕራቡ ዓለም ኑሮ ውድ ነው፤ በምዕራቡ ዓለም እንግሊዝኛ ነው የሚነገረው፤ የምዕራቡ ዓለም የአምስት መቶ ዓመት እንኳን ታሪክ የለውም... ብቻ በምዕራቡ ዓለም በሚል የሚጀመር ዓረፍተ ነገር እንዴትም ሊቋጭ ይችላል፡፡
አንዳንዴ ..በምዕራቡ ዓለም ማቀዝቀዣ ርካሽ ነው.. አይነት ንግግር ሁሉ ይደመጣል፡፡ ንግግርን ለማጣፈጥ ወይም ከተጠያቂነት ለማምለጥ በምዕራቡ ዓለም የማይሆን የማይደረግ፣ የማይገኝ ነገር የለም፡፡
ዋሻ ሁለት- ..በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት..
በእንደዚህ ያሉ ንግግሮች ወይም ጽሁፎች ውስጥ ብዙ ጊዜ ባለሙያዎቹ ይስማማሉ - የስነልቦና ባለሙያዎች እንደሚስማሙበት አይነት፡፡ ባለሙያዎቹ እነማናቸው ለሚለው መልስ የለም፡፡ ስማቸው አይጠቀስም፤ ዜግነት የላቸውም፡፡ አንድም ብዙም ናቸው፡፡
በአንድ የሙያ መስክ ውስጥ የሚያስማሙ ሀሳቦች በብዛት ሊኖሩ ቢችሉም እንደየግለሰቦቹ ምንጭ፤ የዕውቀት ደረጃ፤ ርዮተ ዓለም ወዘተ የአተያይ ልዩነቶች ይኖራሉ፡፡ አንዳንዴ የሚነሱት ነገሮች ስፋት እና ጥልቀት እንኳን ሁሉም ባለሙያዎች ሊስማሙበት በአንዱ እንኳን ያልተቋጨ ሊሆን ይችላል፡፡
አንዳንዴ ደግሞ አወዛጋቢ በሆኑ ጉዳዮችም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት ሊባል ይችላል፡፡ በኛ ቸርነት መንግስቱ ለማና ጸጋዬ ገ/መድህን፤ የጥንታዊ ግሪክ ፈላስፎችና ሶፊስቶች፤ አማርትያ ሴንና ሳሙኤል ሀንቲንግተን፤ ሌንጮ ለታና ባህሩ ዘውዴ ንግግራችንን እስካሳመሩልን እናስማማቸዋለን፡፡
የፖለቲካ ተንታኞች፤ ዳይሬክተሮች፤ ኢኮኖሚስቶች ወዘተ በየመስካቸው እየተሰበሰቡ የአቋም መግለጫ የሚያወጡና ለኛ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሹክ የሚሉን ይመስላል፡፡
ዋሻ ሦስት- ..ኢዝም..
ይህቺ ዋሻ በተለይ የፊደል ቀመሶቹ መዋያ ናት፡፡ ከመደጋገም ቃላቶቹን ጓደኛ አድርገናቸዋል፡፡ በ ኢዝም ይለቁ እንጂ ምንም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ኒዮሊበራሊዝም፤ ማርክሲዝም፤ ፌሚኒዝም፤ መልቲካልቸራሊዝም፤ ናቹራሊዝም፤ ኤግዚዝቴንሻሊዝም፤ ሞደርኒዝም፤ ፖስትሞደርኒዝም... ኢዝም መች ያልቃል!
ንግግር በሆነ ኢዝም ካልተደገፈ ሞገስ ያጣል የሚል ስምምነት ያለ ይመስላል፡፡ ለዚህ ይመስላል በየትኛውም ዘርፍ በተሰማራ ባለሙያ፤ በማንኛውም ርዕሰ-ጉዳይ ላይ የሆነች ኢዝምን (ከነሙሉ ክብሯ!) ጣል ማድረግ የሚዘወተረው፡፡ በዚህ ዋሻ ውስጥ ተጠልሎ የማይባል ነገር የለም፡፡ አንዴ የሆነኛው ኢዝም ከተጠቀሰ የፈለጉትን ማውራት ተፈቅዷል፡፡  
ምንጩ ከምሁራኑ መንደር ስለሆነ እኔም እንደነሱ በሚል ቧልተኞች እየሆንን ነው፡፡ አንዳንዴ ሀሳቡን ከማጠናከር ይልቅ ያለቦታቸው የሚደነጎሩት ኢዝሞች ደግሞ ያስተዛዝባሉ፡፡
** *
የ1960ዎቹ አመጽ የኢትዮጵያ ወጣቶች (ወጣቶቹ ስለሚበዙ) መሬት ላራሹ፤ ስልጣን ለሕዝብ ብለው ዘውዳዊውን ሥርዓት ለመጣል ያስነሱት ነው፡፡ የአሁኑ ረሀብ የተከሰተው ነጋዴዎች እህሉን በመጋዘናቸው ስላከማቹት ሳይሆን ከአስተዳደር ድክመት፤ ከተፈጠሮ ልግመት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፊልሞች በዓለም-አቀፍ መድረክ የማይሸለሙት የጭፍጨፋ ታሪክ ስላልሰራን ሳይሆን ትኩስ ታሪክ (original story) ስላልጻፍን፤ ምሉዕ የፊልም ጽሁፍ (screenplay) ስለማናዘጋጅ፤ የፊልሞቻችን የምስልና የድምጽ ጥራት ደረጃ ደካማ ስለሆነ፤ ከሁሉ በላይ አዘጋጆቹ በእውቀትም በስራም ስለማንተጋ ነው፡፡
የሚከበሩ ተቋማት፤ የታፈሩ ምሁራን፤ ጠንካራ ሚዲያ ባሉበት ሀገር ሁለቴ ሳያስቡ መናገር ያስገምታል፡፡ የሐዲስ አለማየሁ ጉዱ ካሳ (ካሳ ዳምጤ) የጠንካራ ሚዲያ፤ የሀቀኛ ምሁር ተምሳሌት ነው፡፡ ሲሳሳቱ ለማረም፤ ሲዋሹ ለማጋለጥ፤ ሲያጠፉ ለመገሰጽ አያመነታም፡፡ እንደ ቄስ ሞገሴ ከመናገሩ በፊት ዓይንና ግንባር አያይም፡፡ እንዲህ እንደልብ የሚባሉት ነገሮች ጉዱ ካሳን ያስናፍቃሉ፡፡
ጉዱ ካሳ መሬት ጠብ ከማይሉ ንግግሮቹ በአንዱ እንዲህ ይላል፡-
..እንዲህ ያለ ችግር፤ እንዲህ ያለ ማጥ ውስጥ ባልገባችሁ መልካም ነበር፡፡ ከገባችሁ በኋላ ግን መውጫ መንገድ መፈለግ ነው እንጂ ማጥ ውስጥ ገብታችሁ ቆማችሁ ሰው ሁሉ እያየ እናንተ የማያያችሁ መስሏችሁ ማጥ ውስጥ አይደለንም ብትሉ ከጉዳት በቀር ምንም ጥቅም የለው..
/ዳዊት ተስፋዬ ዳይሬክተር እና ፀሐፊ ነው/

 

Read 6751 times Last modified on Saturday, 10 September 2011 11:38