Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 10 September 2011 11:51

የዓመቱ ድንቅ እና ቅዥት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የዓመቱ ድንቅ - በኢትዪጵያን አይዶል፣ የታዳጊ ሃና ግርማ ድምጽ
የዓመቱ እፎይታ - መብራት ብርት ጥፍት ማለቱ (ጠፍቶ አለመቅረቱ)
የዓመቱ ቅዠት - የዋጋ ቁጥጥርና የራሽን ወረፋ (ጓድ፣ጓድ - የኮሙኒዝም ፕሪቪው)
የዓመቱ ኅብረት - ፖርላማ፣ ቢዝነስ፣ ዘፈን፣ አትሌቲክስ፣ ኑሮ ወዘተ በጋራ መፍዘዛቸው

የዘንድሮ ነገር! ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት
ድንጋይ ከመተከሉ ጋር፤ በየጊዜው እልም
የሚለው ኤሌክትሪክም ሳይጠቀስ መታለፍ
አለበት? የተለመደ ነው ትሉ ይሆናል - የቧንቧ
ውሃምኮ፤ ሲመጣ ሲሄድ ከርሟል በማለት፡፡
እያማረርኩ መስሏችኋል፡፡ GN አይደለም፡፡

ኤሌክትሪክ አልፎ  ብርት ጥፍት እያለ አመቱን ሙሉ መዝለቁን የምናገረው፤ በምስጋና ነው፡፡ የባሰም አይተናላ - ጥፍት ብሎ መቅረት፡፡ በየሳምንቱ ለሶስትና ለአራት ቀናት ያለ ኤሌክትሪክና መብራት እየዋልን ስናመሽ ትዝ አይላችሁም? ዘንድሮ ግን ተመስጌን ነው፡፡ አልፎ  ብቻ ነው መብራት የጠፋብን፡፡
በእርግጥ፤ ከግልገል ግቤ 2 በተጨማሪ፤ የተከዜና የበለስ ግድቦች ተጠናቅቀው የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት መጀመራቸውን ስታስቡት፤ ግር ሊል ይችላል፡፡ በቂ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት የሚችሉ ጣቢያዎች እስካሉ ድረስ፤ ለምንድነው መብራት በየጊዜው የሚጠፋው? ግድብና ማመንጫ ጣቢያ ብቻ ሳይሆን፤ የሃይል ማስተላለፊያ መስመሮችንም በአግባቡ ማዘጋጀትና በጠንቃቀ½ ማስተዳደር እንደሚያስፈልግ ዘንግታችኋል ማለት ነው፡፡ አለበለዚያ፤ ግድቦች የአቅማቸውን ያህል ኤሌክትሪክ እንዳያመነጩ ገደብ ይኖርባቸዋል፤ ኤሌክትሪክም በየጊዜው ብርት ጥፍት ማለቱን ይቀጥላል - በ2003 አ.ም ካየናቸው መልካም ለውጦች መካከልም አንዱ ነው፡፡
ሌላኛው የአመቱ ትልቅና መልካም ነገር... ብታምኑም ባታምኑም፤ ከኢትዮፕያን አይደል ያገኘነው እድል ነው - የታዳጊዋ ሃና ግርማ አስደናቂ የሙዚቃ ድምፅ ለመስማት መታደላችን፡፡ ዘፈንና ሙዚቃ በጠፋበት ዘመን፣ ለማመን የሚያስቸግር የድምፅ አቅምና ችሎታ ማየት፣ ለመስማት በቅተናል፡፡
ከወጣት ዘፋኞችና ከአዳዲስ የሙዚቃ አልበሞች ጋር ከተራራቅንኮ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ችግሩ፡፡ በየአጋጣሚው የሙዚቃ ኮንሰርቶች ቢዘጋጁም፤ የብዙዎችን ቀልብ መሳብና የሙዚቃ ጥማትን የሚያረኩ አልሆኑም፡፡ በቃ፤ የሚያበላሽ ነገርና የማመካኛ ሰበብ አያጡም፡፡ ዘፈንና ኮንሰርት በተበላሸ ቁጥር ...አንዴ በድምፅ መሳሪያ አለመስተካከል ይሳበባል፡፡ ሌላ ጊዜ፤ በድምፃዊያን ጉንፋን ይሳበባል፡፡ የመድረክ ቀረፃ የዘፋኞችን ድምፅ ያበላሻል ሲባልም ሰምተናል፡፡ ሊሆን ይችላል እያልን በይቅርታ ከማለፍ በስተቀር ብዙም አማራጭ አልነበረንም፡፡ ለምን?
መቼስ፤ ሙያውን ጥንቅቅ አድርጎ የሚያውቅና ስራውን ጥርት አድርጎ የሚሰራ ሰው ማግኘት፤ በጣም ብርቅ በሆነበት አገር፤ የድምፅ መሳሪያዎች ባይስተካከሉ ወይም የመድረክ ቀረፃዎች ቢዝረከረኩ አይገርምም፡፡ ታዲያ በየጊዜው ዘፈኖች ወይም ኮንሰርቶች እየተበላሹ ሰበቦች ሲቀርቡ ምን ማለት እንችላለን? የሃና ግርማ ድምፅ፤ በአይዶል ፕሮግራም ከሰማን በኋላ ግን፤ ሰበብና ማመካኛ የትም እንደማያደርስ መረዳት ይኖርብናል፡፡
mc½M\ ታዳጊዋ ሃና ስታዜም ሰምተን የተደነቅነው፤ ድንገት የመሳሪያ ጥራትና የባለሙያ እውቀት ስለጨመረ አይደለም፡፡ ለነገሩ፤ ኢትዮፕያን አይደል፤ የተራቀቁ የድምፅ መሳሪያዎችንና ቴክኖሎጂãCN በመጠቀም አይታማም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሌለ የቀረፃ መሳሪያና ቴክኖሎጂ ወይም የሙያ ደረጃና ብቃት፤ በአይዶል ፕሮግራም ላይ አታገኙም፡፡ ያው እንደአቅሚቲ የሚዘጋጅ ፕሮግራም ነው፡፡ የኮንሰርት አዘጋጆች ያህል  እንኳ አቅም የለውም፡፡ አንድ የአይዶል አዘጋጅ እንደነገረኝ ከሆነ፤ ከመድረክ የተቀረፀውን ድምፅ ለማስተካከል (ኤዲት ለማድረግ) አይሞክሩም፡፡ ከመድረክ የተቀረፀውን ድምፅ ነው የሚያስተላልፉት፡፡ የሃና ድምፅ ግን አልተበላሸም፡፡ የድምፅ ችሎታ ነው ዋናው፡፡      
ዘሪቱ ከበደንና ፀደኒያ ገ.ማርቆስንም ተመልከቱ፡፡ መድረክ ላይ፤ ድምፃቸው ያን ያህልም አይበላሽም፡፡ ሚኒልክ ወስናቸው እና ጠለላ ከበደ የመሳሰሉ ምርጥ ድምፃዊያንንም አስታውሱ፡፡ የኦፕራ ድምፃዊያን አይነት ብቃት የሚታይባቸው ድምፃዊያን ናቸው - ሚኒልክና ጠለላ፡፡ ታዳጊዋ ሃና ግርማ ደግሞ በአይዶል ፕሮግራም፤ የኦፕራ ድምፃዊያን የሚያነቅኗቸውን ዜማዎች አስደመጠችን - በሚያስደንቅ ድምፅ፡፡ ለዚያውም፤ የኦፕራ ዜማዎች አመራረጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ቢሆንም፤ አንዳንዴ የሚመርጡላት ዜማ ለሃና የሚስማማ አልነበረም - በወፍራም የወንድ ድምፅ እንድታዜም ሲያደርጓት አይተን የለ?
ነገር ግን፤ የማይስማማ ዜማም ቢሆን፤ የሃናን አስደናቂ አቅም ሸፍኖ አላጠፋውም፡፡ የሚስማማት ዜማ ሲሆንማ፤ ጥርት ብሎ እንደተቃኘ የሙዚቃ መሳሪያ፤ ድንቅ ድምጿና ዜማው አካባቢያችንንና መንፈሳችንን ይቆጣጠረዋል፡፡ የተዘጋ ወይም የተቆራረጠ፣ የሚነፋነፍ ወይም የሚንሳጠጥ ድምፅ የለም፡፡ የተለመዱ ተራ ዘፈኖችን ስትጫወት ደግሞ፤ ምን ያህል በድምጿ ለዜማዎቹ ህይወት እንደምተዘራባቸው፤ በመጨረሻው የማጣሪያ ዙር አይታችኋል፡፡
ከፍተኛ ችሎታ ያላቸው ድምፃዊያን ሲዘፍኑ ገፅታቸው ላይ፤ ምናልባት የዜማውን ስሜት ለመግለፅ ያህል ካልሆነ በቀር፤ ድምፅ የማውጣት ውጥረት ወይም  ትንቅንቅ አታዩም፡፡ መዝፈን ማለት ለነሱ እንደ መናገር ነው - ከእኩያ ጋር እንደመነጋገርና እንደመጫወት፡፡ ከምንቀርበው ሰው ጋር፤ በሚመመቸንና በሚስማማን ጉዳይ ላይ ስንነጋገር፤ ፊታችን አይገታተርም አይደል? ድምፃችንን ከፍና ዝቅ ለማድረግም፤ ማይክሮፎን ማስጠጋትና ማራቅ አያስፈልገንም፡፡ ድንቅ አቅም ያላቸው ድምፃዊያን ሲዘፍኑ፤ እንደዚያው ነው - ድምፅ ውጪ ድምፅ ግቢ ትንቅንቅ የለም፤ እንደ ጉርሻ ማይክ ማስጠጋትና ማራቅ አያስፈልግም - በስህተት አመል ካልሆነባቸው በቀር፡፡
¦Â GR¥\ ከእንደነዚህ አይነቶቹ ብርቅ ሰዎች አንዷ ነች - ድንቅ አቅም አዳብራለችና፡፡ ከሙዚቃ ፍቅሯ ጋር ጥረቷን ስትቀጥልበትና ስርአት ያለው ስልጠና ስትከታተል ደግሞ፤ በመላው አለም የሚደመጥ ድንቅ ብቃት ላይ መድረስ ትችላለች፡፡ በእርግጥ በአገራችን፤ ለሃና የሚመጥን የድምፃዊነት ስልጠና ሊሰጥ የሚችል ተቋም የለም፤ ባለሙያም የሚኖር አይመስለኝም፡፡
ደግነቱ፤ የውጭ አገር ስልጠና እንድታገኝ ጥረት ለማድረግ የፖላንድ ኤምባሲ ፈቃደኝነቱን እንደገለፀ ሰምቻለሁ፡፡ የአውሮፓ ህብረት የወቅቱ ፕሬዚዳንትነት የያዘችውና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአለማቀፍ መድረክ ጉልህ ድርሻ እያገኘች የመጣችው ፖላንድ፤ በረቂቅ ሙዚቃ ረዥም ታሪክ ካላቸው አገራት መካከል አንዷ ነች፡፡ ገንዘብ ወጪ መደረጉ ካልቀረ፤ ሃና ግርማ የስልጠና እድል እንድታገኝ ወጪ ቢሆን አይቆጭም፡፡ ድንቅ አቅም ወደ ድንቅ ብቃት እንዲደርስ ከማገዝ የበለጠ ውለታ ከየት ይገኛል? እስከዚያው ግን፤ ዘንድሮ ላየሁት ድንቅ አቅምና አስደሳች ብቃት፤ ኢትዮፕያን አይደልን አመሰግናለሁ፡፡
MNM XNµ*\ ኢትዮፕያን አይደል፤ ፕሮግራሙን ለተመልካችና ለአድማጭ ይበልጥ ማራኪ ለማድረግ፤ አዘገጃጀቱና አቀራረቡንም ይበልጥ አዝናኝ እንዲሆን፤ የቻለውን ያህል ሁሉ ባይሰራም፤ ከበፊቶቹ አመታት የተሻለ ነው፡፡ የበርካታ ወጣቶች አቅምና ብቃት በእውን እንዲታይ የሚጠቅም ስራ፤ ክብር ይገባዋል፡፡ በተለይ በተለይ፤ ዘንድሮ የሃና ግርማን ድምፅ እንድንሰማ እድል ስለፈጠረን ብናመሰግነው አይበዛበትም፡፡ የሃና ቤተሰቦችና ያበረታቷት ሁሉም፤ ምስጋና ይድረሳቸው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ፤ ሃና ትመስገን፡፡
በእርግጥ፤ ታዳጊዋ ሃና፤ እኛን ለማስደሰት ተጨንቃ ያደረገችው ነገር የለም፡፡ ሙዚቃና ዘፈን ያስደስተኛል ብላለች፡፡ ሃና ለራሷ ስለሚያስደስታት ስታዜም፤ ድምጿና ዜማዋ፤ ለኛም ደስታ ሆነ፡፡ ምስጋናችን እጥፍ ድርብ መሆን የሚገባው በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ ለናንተ ብዬ፤ ለናንተ ተጨንቄ፣ ለናንተ ተቸግሬ፣ ለናንተ ከስሬ የሚሉ እዳዎችን ተሸክሞ የሚመጣ የምፅዋት ደስታ አይደለም ከሃና ያገኘነው፡፡ ከሰው ደስታ ነው፤ ደስታ እያገኘን ያለነው - ውድና ክቡር ደስታ፡፡
አንድ ሰው፤ ለማንኛውም ሰው ሊበረክት ከሚችለው የልግስና አይነት ሁሉ የላቀ፤ ትልቁ ቅዱስ ልግስና ምን መሰላችሁ? ለማመን የሚያስቸግር ብርቅ አቅምና ድንቅ ብቃት በእውን፣ በተግባር፣ በገሃድ ማሳየት! ይሄ ነው የሰውን መንፈስ የሚያነቃቃ ትልቁ ልግስና! - ሁሉም ሰው እንደዝንባሌውና እንደሙያው፤ የቻለውን ያህል የራሱን አቅሙን እየተጠቀመ ተጨማሪ ብቃት እንዲያዳብር የሚያነሳሳ ነውና፡፡ ሰው አቅሙን ተጠቅሞ በደስታ ወደ ብርቅና ድንቅ አቅም መጓዝ እንደሚችል ላሳየችን ሃና ግርማ ምስጋና ይድረሳት፡፡
ደግሞስ፤ እንዲህ አይነት አስደሳች ነገሮች ባናገኝ ኖሮ፤ በምግብ እጥረትና በረሃብ፤ በዋጋ ንረትና በኑሮ ውድነት የጨፈገገውን የዘንድሮውን አመት እንዴት እንቋቋመው ነበር? የዛሬ አመት በታወጀው የእድገትና የትራንስፎርሜሽ እቅድኮ፤ የተረጂዎች ቁጥር በሁለት ሚሊዮን እንደሚቀንስ፣ የዋጋ ንረትም እንደሚረጋጋና ከ10 በመቶ በታች እንደሚሆን የተነግሮን ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ የዘንድሮው የምግብ እጥረት ካለፈው አመት የባሰ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡
ከብር ህትመት ጋር የብር አቅም እየረከሰ የዋጋ ንረት ከ40 በመቶ በላይ ሄዷል፡፡ አምና በአንድ ሺ ብር እንሸፍነው የነበረ ወጪ፤ አሁን 1400 ብር ይፈጅብናል፡፡ የዛሬ አመት አስር ሺ ብር የነበረ የቁጠባ ሂሳብ፤ ዛሬ ሶስት ሺ ብር ያህል ዋጋ አጥቷል፡፡ ከአምና ጋር ብቻ ሳይሆን፤ ወደ ኋላ አምስት አመት ያህል ተመልሰን ብናነፃፅረውማ፤ ራስ ያዞራል፡፡ በ99 አም በአንድ ሺ ብር የምንሸፍነው አስቤዛ፤ ዛሬ በ2500 ብር ልንሸፍነው አንችልም፡፡ ያኔ የቆጠብነው አስር ሺ ብር ደግሞ፣ ከግማሽ በላይ ዋጋውን አጥቷል፡፡ ኑሮ ምን ያህል እንደከበደና የኑ መሰረት ምን ያህል እንደተሸረሸረ አስቡት፡፡
መንገድና ግድብ መገንባቱስ? ትምህርት መስፋፋቱና ተመራቂዎች መብዛታቸውስ? የኢኮኖሚ እድገት መመዝገቡስ? ሰላም መሆኑስ? እነዚህ ሁሉ ጥሩ ናቸው - ቅዱስ ነገሮች መሆናቸው አያከራክርም፡፡ ጥሩ ነገር ማጣት፣ (ማለትም የስልጣኔ፣ የነፃነትና የብልፅግና እጦት) ነው፤ ሃጥያት ማለት፡፡ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብና መበልፀግ የመሳሰሉ ቅዱስ ነገሮች ሲበራከቱና ሲስፋፉ ማየትም ያስደስታል፡፡ ሲሸረሸሩ ማየትስ? መናገር፣ መስራትና ንብረት ማፍራት እንደወንጀል ሲቆጠሩ የነበሩበት የደርግ ኮሙኒዝም ከፈረሰ ወዲህ፤ በተለይ ደግሞ ከ1993 አ.ም በኋላ፤ የተወሰነ ያህል የመናገር፣ የመስራትና ንብረት የማፍራት ነፃነት በመገኘቱ፤ ብዙ ሰዎች የአቅማቸውን ያህል ታትረዋል፡፡ የዚያችኑ ያህል ህይወታቸውን ለማሻሻል በሚያደርጉት ጥረት ኢኮኖሚው ተነቃቅቶ፤ እድገት ተመዝግቧል፡፡ ለነገሩ አብዛኛው የህይወት መስክ፤ በጋራ ወይም አንደኛው ሌላኛውን እየተከተለ፤ የመነቃቃትና የማደግ ጉዞ ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ የአትሌቲክ ድሎች ትዝ አይሏችሁም? ያኔ ሲታተሙ የነበሩ  የወጣት ዘፋኞች አዳዲስ አልበሞች ጥቂት አልነበሩም፡፡ የሰከኑ የነፃ ፕሬስ ውጤቶች ሲበራከቱ ያየነውም ያኔ ነው፡፡ ታሪክ ነክ፣ ሙያዊ እና የፈጠራ መፃህፍትም እንዲሁ፡፡ ፖለቲካውም ሳይቀር፤ የመነቃቃትና የመሰልጠን አዝማሚያ እየያዘ አልነበር? አሳዛኙ ነገር፤ የአትሌቲክስ ውጤትና የሙዚቃ አልበም ቀስ በቀስ እየተዳከመ እንደመጣው ሁሉ፤ ቢዝነስና ንግድ፣ ኢኮኖሚና ኑሮም ቀስ በቀስ እየተዳከመ ወይም እየተናጋ ሲመጣ አይተናል፡፡ የተወሰነ የነፃነት ጭላንጭል በተፈጠረበት በኢህአዴግ ዘመን፤ ብቅ ብቅ ማለት የጀመረው የኢኮኖሚ፣ የፈጠራና የፖለቲካ መነቃቃት፣ አጀማመሩን እያፋጠነ ከመሄድ ይልቅ፤ ባለበት መርገጥና የኋሊት መንሸራተት ሲጀምር ማየት አያሳዝንም? 2003 ደግሞ፤ ጭራሽ የኮሙኒዝም ዘመንን የሚያስታውስ እስከመሆን ደርሶ ነበር፡፡ እስቲ በዚህ ዘመን፤ የፓርቲ ጉባኤ ላይ በይፋ፤ ጓድ-ጓድ መባባል የጤና ነው? በፌደራል፣ በክልል፣ በወረዳና በቀበሌ ደረጃ፤ ኢህአዴግና አጋሮቹ፤ ከ99.5 በመቶ በላይ የምክርቤት ወንበሮችን ካሸነፉ ወዲህም፤ ፖለቲካው መደንዘዙና ፓርላማው ጭር ማለቱን ስናይ ከርመናል - የገናና ፓርቲ ወይም የአውራ ፓርቲ ስርአት ይሉታል፡፡ ዘንድሮ ኮሙኒዝምን እንድናስታውስ የተደረግነው ግን፤ በዚህ በዚህ ብቻ አይደለም፡፡ እንደ ደርግ ዘመን፤ መንግስት የንግድ ኮርፖሬሽኖችን ሲያቋቁም እንዲሁም ገበያ ውስጥ ገብቶ የሸቀጦችን የዋጋ ተመን ሲያውጅ አይተናል - ለዚያውም ነጋዴዎችን የሚያሸማቅቁ ስድቦችን እያዥጎደጎደ፡፡ የዋጋ ቁጥጥሩ ብቻ ሳይሆን፣ ውጤቱም የድሮውን የሚያስታውሰን ከመሆን አላለፈም፡፡ የገበያ ግርግር፣ የሸቀጦች እጥረት፤ ድብቅ የአየር ባየር ንግድ፣ ራሽን፣ ወረፋ፣ የሸማቾች ማህበር... ልክ እንደድሮው በአምስት ወራት ውስጥ፤ አብዛኞቹን የዋጋ ቁጥጥር መዘዞች ለማየት ችለናል፡፡ የኋላ ኋላ የዋጋ ቁጥጥሩ ጋብ በማለቱ ነው፤ ትንሽ እፎይ ያልነው፡፡ ሌሎቹ ተመሳሳይ ስህተቶችም፤ እንደዚህኛው የኮሙኒዝም ፕሪቪው፤ በአጭሩ ተቀጭተው ዳግም ላይመለሱ ቢቀሩልን፤ በተቃራኒው ደግሞ የስልጣኔ፣ የብልፅግና የነፃነት ጉዳናዎች በርከትከት አድርገን ብንሞክር... ሳይታወቀኝ የአዲስ አመት መልካም ምኞት መዘርዘር ጀመርኩ፡፡

 

Read 4950 times Last modified on Saturday, 10 September 2011 11:58