Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 01 December 2012 12:36

አሣሣቢው የቲቢ በሽታ

Written by 
Rate this item
(11 votes)

በ2003 ዓ.ም ብቻ 154ሺ አዳዲስ የቲቢ ህሙማን ተመዝግበዋል
መድሃኒቱን የተለመደ ቲቢ ስርጭት አሣሣቢ ደረጃ ላይ ደርሷል
በዓለም እጅግ ከፍተኛ የቲቢ በሽታ ስርጭት ካለባቸው 22 አገራት ኢትዮጵያ አንዷ ስትሆን በዘጠነኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
የቲቢ በሽታ በዓለማችን ከተከሰተ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ምርመራውም ሆነ ህክምናው የተጀመረው ብዙዎችን ለህልፈተ ህይወት ከዳረገና በዓለም ዙሪያ ስርጭቱ ከተስፋፋ በኋላ እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ነው፡፡ በሽታው ማይክሮ ባክቴሪየም ቲዩበርክሎስስ በሚባል ባክቴሪያ አማካኝነት የሚከሰት ሲሆን ይህ ባክቴሪያ በጋራ የምንጠቀመውን አየር መድረክ አድርጐ ወደሰው አካል ውስጥ ከገባ በኋላ ራሱን ያራባል፡፡

የ ቲቢ ባክቴሪያ በሰውነታችን ውስጥ ከገባ በኋላ ለመራባት ረዘም ያለ ጊዜን ይወስድበታል፡፡ ቀስ እያለ በመራባትና በሰውነታችን ውስጥ በመሰራጨት የTB በሽታን ያስከትላል፡፡ 
የTB በሽታ ሁሉንም የሰውነታችንን ክፍሎች የሚያጠቃ ሲሆን በስፋት የሚታወቀውና ብዙዎችን ለህመምና ለሞት እየዳረገ ያለው በሣንባ ላይ የሚከሰተው የቲቢ በሽታ ነው፡፡ በሽታው ፆታ፣ ዕድሜ፣ ዘርና ቀለም ሣይመርጥ በሁሉም ሰው ላይ የሚከሰት በሽታ ሲሆን በይበልጥ የሚያጠቃው ግን በድህነት ውስጥ የሚኖሩ፣ በተጠጋጋና በተፋፈገ ሁኔታ የሚኖሩ፣ በHIV ቫይረስ የተያዙና የዲያቤቲክስ ህመም ያለባቸውን ሰዎች ነው፡፡
TB አምጪው ባክቴሪያ በትንፋሽና ሌሎች መንገዶች ወደ ሰውነታችን ውስጥ ገብቶ መራባትና መሰራጨቱን ይቀጥላል፡፡ ይህንን አጠናቆ ህመም ለመፍጠር ሰፋ ያለ ጊዜን ይወስዳል፡፡ ይህም በሰውየው በሽታን የመቋቋም አቅምና በተወሰደው የባክቴሪያ መጠን የሚወሰን ይሆናል፡፡
በድህነትና በምግብ እጦት መጐዳት፣ ዕድሜና በተጓዳኝ ህመሞች መጠቃት በበሽታው በፍጥነት መጐዳትና አለመጐዳት ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
የሣንባ TB በሽታ የተለያዩ ደረጃዎች ሲኖሩት እነዚህም በአግባቡ ህክምናን ካለማድረግና መድሃኒቶችን ከማቋረጥ የሚከሰቱ ናቸው፡፡ ተገቢ ጥንቃቄና ህክምና ያልተደረገለት የTB በሽታ ወደ MDR TB (Multi Drug Resistant TB) ወይንም መድሃኒቶችን የተለማመደ ቲቢ የሚቀየር ሲሆን፤ የዚህ ህክምና ደግሞ እጅግ ከፍተኛ ጥንቃቄንና ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ ነው፡፡ የ MDR ቲቢ ህክምና በአገራችን እ.ኤ.አ በ2009 ዓ.ም በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ውስጥ የተጀመረ ሲሆን እስከአሁን 600 የሚሆኑ የ MDR ቲቢ ህሙማን ህክምና እየተደረገላቸው ነው፡፡ በርካታ ህክምናውን በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ ህሙማንም አሉ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ፣ አለርትና ሆስፒታሎች የ MDR ቲቢ ህክምና የሚሰጉባቸው ቦታዎች ሲሆኑ የ MDR ቲቢ ምርመራ ላብራቶሪ በኢትዮጵያ ጤናና ሥነ ምግብ ምርምር ተቋም (ፓስተር)፣ ቅዱስ ጴጥሮስ፣ አዳማ ባህርዳርና ጅማ ይገኛል፡፡ በቅርቡ 800 የሚሆኑ ለ MDR ቲቢ ህሙማን ህክምና ለመስጠት የሚያስችሉ መድሃኒቶች ወደ አገራችን ገብተዋል፡፡ ህክምናው ከ18-24 ወራትን የሚወስድ ሲሆን ከ3500 ዶላር በላይ ወጪን ይጠይቃል፡፡
ለቲቢ በሽታ ስርጭት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ ተብለው የሚጠቀሱት በርካታ ህዝብ ተፋፍጐና ተጠጋግቶ የሚኖርባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡ ለምሣሌ የስደተኞች መኖሪያ ካምፖች፣ ማረሚያ ቤቶች፣ የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርቶች፣ ሲኒማና ቲያትር ቤቶች፣ የእምነት ቦታዎች፣ ትምህርት ቤቶችና ሆስፒታሎች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ እነዚህ በርካታ ህዝብ በአንድ ሥፍራ የሚሰባሰብባቸው ቦታዎች አየር እንደልብ የሚያስተላልፉ መስኮቶችና በሮች ከሌሏቸውና በተዘጋና አየር በማይገባበት ሁኔታ የተሰሩ ከሆነ በሽታው ከአንድ ሰው ወደሌላው ሰው በቀላሉ ሊዛመት ይችላል፡፡ የቲቢ በሽታ በወቅቱና በአግባቡ ህክምና ከተደረገለት በቀላሉ ሊድን የሚችል በሽታ ነው፡፡ የቲቢ በሽታ መድሃኒትን ጀምሮ ማቋረጥ መድሃኒቱን ለተላመደ ቲቢ ወይም MDR ቲቢ ያጋልጣል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ግሎባል ቲቢ ሪፖርት በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ ላይ እንዳመለከተው በዓለማችን ከፍተኛ ቲቢ በሽታ ስርጭት ካለባቸው 22 አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን በከፍተኛ ሁኔታ ቲቢ ካጠቃቸው አገራት ውስጥም በዘጠነኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
ይኸው መረጃ አገሪቱ ከአፍሪካ በTop Five ውስጥ ከተካተቱ አገራት አንዷ እንደሆነችም ያመለክታል፡፡
ከቅርብ አመታት ወዲህ መንግስት በቲቢ በሽታ ስርጭት ላይ ትኩረት አድርጐ መንቀሣቀስ የጀመረ ቢሆንም አሁንም ድረስ በየዓመቱ ከ100ሺ በላይ አዳዲስ የ ቲቢ ኬዞች ይመዘገባሉ፡፡ ከ1991-2003 ዓ.ም ድረስ ባሉት 13 ዓመታት ብቻ 1,539,568 የቲቢ ህሙማን ተመዝግበዋል፡፡ መረጃው በ2003 ዓ.ም ብቻ 159,017 የቲቢ ህሙማን ለህክምና መመዝገባቸውን ያመለከተ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 153,194 የሚሆኑት አዳዲስ እንደሆኑም አመልክቷል፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከ TB Care እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ሰሞኑን በአዳማ ከተማ በ TB, MDR TB እና TB/HIV በሽታዎችን መከላከልና መቆጣጠር ዙሪያ ለጋዜጠኞች አዘጋጅቶት በነበረው ስልጠና ላይ የTB Care አስተባባሪ ዶ/ር ብርሃነ መስቀል እንደተናገሩት የ TB በሽታ ጊዜና ሁኔታዎችን ጠብቆ የሚያጠቃና ባክቴሪያው በሰውነታችን ውስጥ ከገባ በኋላ ለውጥ ሣያሣይ ረዘም ላለ ጊዜ መቆየት የሚችል መሆኑንና ህክምናው ሰፋ ያለ ጊዜያትን የሚወስደውም በባክቴሪያው ባህርይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የቲቢ ታማሚው በሽታው እንደያዘው ወደ ጤና ተቋማት ከሄደና በወቅቱ ህክምናውን ከጀመረ በቀላሉ ሊድን የሚችል እንደሆነ የተናገሩት ዶክተሩ፤ ይህ ሣይሆን ቀርቶ ህክምናውን ጀምሮ ማቋረጥ፣ መድሃኒቶችን እየተዋዋሱ መውሰድ እጅግ አደገኛ ለሆነውና በቀላሉ ሊድን ለማይችለው MDR ቲቢ (መድሃኒቶችን የተላመደ ቲቢ) ያጋልጣል ብለዋል፡፡ “ቲቢን ሣይነካኩ ዝም ብሎ መተው ይሻላል፡፡
ተነካክቶ በአግባቡ ካልታከመ ወደ MDR ቲቢነት ይለወጣል፡፡ ይህ ደግሞ የቆስለ አንበሣ ሆነ ማለት ነው፡፡ የቆሰለ አንበሣ ደግም ሣያጠቃ በፍፁም አይተውም፤ ቲቢን ከነካኩ በአግባቡ ጨርሶ መግደል፣ አለበለዚያ ደግም ፈፅሞ አለመነካካት ነው” በማለት በአግባቡ ያልታከመ የቲቢ በሽታን አደገኛነት ዶ/ር ብርሃነ መስቀል ገልፀዋል፡፡
የMDR ቲቢ ህክምና እንደመደበኛው ቲቢ በየጤና ተቋማቱ እንደልብ የሚሰጥ አይደለም፤ ህክምናው የተለየ ጥንቃቄንና ከፍተኛ ቁጥርን የሚጠይቅ ነው፡፡
ለ MDR ቲቢ ታማሚ ተገቢና ጥንቃቄ የተሞላበት ህክምና ካልተደረገለት በሽታው ወደ DR ቲቢ ሊቀየር ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ እጅግ አደገኛና የመዳን እድሉም የመነመነ ነው፡፡ ምክንያቱም በሽታው ለቲቢ በሽታ ተብሎ የተሰሩ መድሃኒቶች በመላመዱ ምክንያት ሊድን አይችልም፡፡ የ MDR ቲቢ ህሙማን በተለየ ሥፍራና ከሌሎች ህሙማን ተለይተው ህክምና የሚደረግላቸው ሲሆን በዚህ ህክምናውን በመስጠት ሂደት ውስጥም በበሽታው የተያዙ የጤና ባለሙያዎች አሉ፡፡ የMDR ቲቢ ህመምተኛ በሽተኛውን ወደ ሌሎች ሰዎች በሚያስተላልፉበት ወቅት በቀጥታ የሚያስተላልፉት ያንኑ MDR ቲቢ ነው እንጂ መደበኛውን የ ቲቢ በሽታ አይደለም፡፡ በበሽታው የተያዙ ሰዎችን አይቶ በቀላሉ መለየት የማይቻል ቢሆንም የቲቢ ህሙማን የሚያሳዩዋቸው አንዳንዱ ምልክቶች ይኖራሉ፡፡ ከእነዚህ የበሽታው ምልክቶች መካከል ዋንኞቹና በአብዛኛው የ ቲቢ ህሙማን ላይ የሚታዩት ከሁለት ሣምንታት በላይ የቆየ ሣል፣ አክታ፣ ውጋት፣ የትንፋሽ ማጠር፣ ከሁለት ሣምንታት በላይ የቆየ ትኩሣት፣ የሰውነት መቀነስና ከፍተኛ ላብ ናቸው፡፡ በሽታውን ለመከላከል ቀላሉ መንገድ መስኮቶችን በመክፈት አየር በቀላሉ እንዲዘዋወር ማድረግ ዋነኛው ሲሆን ብዙ ሰዎች በአንድነት በሚኖሩበት አካባቢና በህዝብ ትራንስፖርት ውስጥ (ታክሲ አውቶቡሶች) ይህንን ተግባር እንደመሠረታዊ ልማድ አድርጐ መያዝ ይገባል፡፡ የቲቢ ስርጭት ያለበት ሁኔታ እጅግ አሣሣቢና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት በማድረግ ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር ተባብሮ የሚያከናውናቸው ተግባራት ቢኖሩም እነዚህ ብቻ በሽታውን ለመቆጣጠርና ሥርጭቱን ለማስቀረት አልቻሉም፡፡
ህብረተሰቡ በቲቢ በሽታ ላይ በቂ ዕውቀትና ግንዛቤ ኖሮት ህሙማኑን ከማግለል ይልቅ ጥንቃቄ በማድረግ ህሙማኑ ወደ ህክምና ተቋማት እንዲሄዱና ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ ይገባዋል፡፡ የቲቢ ህክምና በሁሉም የጤና ተቋማት በነፃ ይሰጣል፡፡

Read 16971 times Last modified on Saturday, 22 December 2012 14:07