Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 01 December 2012 12:57

“የስደተኛ እናት ታጠቂ በገመድ፤ልጅሽን አሸዋ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ” Featured

Written by 
Rate this item
(12 votes)

ጅቡቲ ድንበር ልንደርስ ስንል በውሃ ጥም ምላሴ ተጣብቆ፣ እኔም እንዳልሞት ብዬ የሚቀመስ ጠብታ ውሃ ስናጣ ግዜ ሁለት ቀን ሙሉ የገዛ ሽንቴን ጠጥቻለሁ፡፡ ይሄውልህ በእጄ እንዲህ እያደረኩ! ሌሎቹም ወንዶቹም ሴቶቹም እኮ የገዛ ሽንታቸውን እንደኔው ጠጥተዋል!----
የየመን የገሃነም ጉዞ
የእኛ ሰዎች ተሰደው የሚኖሩባቸውን የተለያዩ የአለማችንን ሀገራት አንድ ሁለት እያልን ብንቆጥር የተሳካና የከሸፈ የስደኝነት ህይወት መሳ ለመሳ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ስኬትና ሽንፈት መሳ ለመሳ ሆነው የማይገኙባት ብቸኛይቱ ሀገር ብትኖር የመን ናት፡፡ በድሮዋ የመን የተሳካ የስደተኝነት ህይወት የመሰረቱ ኢትዮጵያውያን ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የአሁኗ የመን ግን ከቀድሞዋ የመን በእጅጉ የተለየች ናት፡፡ የአሁኗ የመን ለስደተኞች የሚራራ አንጀት የላትም፡፡ የምድር ላይ ገሃነመ እሳት ናት፡፡

ነገር ግን የሞትም አይነት አለው እንደሚባለው ሁሉ የስደትም ስደት አለው፡፡ የየመንን ስደት ከአሜሪካና አውሮፓ ስደት ጋር ለማነፃፀር መሞከር እንደ ትልቅ ስህተት ሳይሆን እንደ ትልቅ ሀጢአት ሊቆጠርብን ይችላል፡፡ የየመንን ስደት ሌላው ቢቀር ከጅቡቲ ስደት ጋር እንኳ ለማወዳደር እጅግ በጣም ያስቸግራል፡፡
በጦርነት ጊዜ ገዳይና ተገዳይ፣ቆሳይና አቁሳይ የመኖራቸው ነገር ጥያቄ የማይቀርብበት ገሃድ እውነት ነው፡፡ በመሆኑና በግራም ሆነ በቀኝ በጦርነቱ የሚወድቁት ተዋጊዎች፣ አብዛኛውን ጊዜ ወግ ላለው ቀብር አይበቁም ስለሚባል፣ ልጇ ጦር ሜዳ ለዘመተባት እናት “የወንድ ልጅ እናት ታጠቂ በገመድ፤ ልጅሽን አሞራ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ” ተብሎ የተገጠመላትን ግጥም ለዘመናት እየሰማነው ኖረናል፡፡
አሁን ይሄ ግጥም ጥቂት ማሻሻያ ተደርጐለት፣ልጇ ወደ የመን ስደት ለሄደባት እናት ተገጥሞላታል - “የስደተኛ እናት ታጠቂ በገመድ፤ ልጅሽን አሳ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ፡፡” “የስደተኛ እናት ታጠቂ በገመድ ልጅሽን አሸዋ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ” በሚል፡፡ ወደ የመን የተሰደዱ የእኛን ሰዎች በተመለከተ በየእለቱ ከወደ የመን የሚወጡ ዜናዎችን በሙሉ ሳይሆን አንድ ሁለቱን ብቻ መመልከት፣ ወደየመን የተሰደደ ልጅ ላላት እናት የተገጠመው አዲስ ግጥም ምን ያህል እውነትና ትክክለኛ እንደሆነ ከሚገባው በላይ ያስረዳል፡፡
ሀራዳና ካራዝ በተባሉት የየመን ከተሞች በአስር ሺዎች ከሚቆጠሩት ስደተኛ ኢትዮጵያውያን መካከል አይሻ ኑር ሁሴንና (የአባቷ ስም የተቀየረ) ሃፍቶም ግደይ (የአባቱ ስም የተቀየረ) ያንን የየመን የገሃነም ጉዞ ከተጓዙትና ነፍሳቸው በአንዳች ተአምር ከተረፈችላቸው መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
አይሻንም ሆነ ሃፍቶምን በዚያ የገሃነም የስደት ጉዞ ወቅት የባህሩ ውሃና አሳው፣ አሸዋና ንዳዱ ስንቶቹን የእኛ ሰዎች በልቶ እንዳስቀረ ብትጠይቋቸው፣ በወሬ የሰሙትን ሳይሆን በአይናቸው በብረቱ ያዩትን እንዲሁም ራሳቸው ከጨካኙ መልአከ ሞት ጋር ስንት ጊዜ ፊትለፊት እንደተፋጠጡ ይነግሯችኋል፡-
የሀራድህ ከተማን እምብርት ወደ ግራ ትታችሁ አንድ ሁለት ኪሎ ሜትር ያህል ወደ ከተማዋ ጠርዝ ከተጓዛችሁ፣የአለም አቀፉን የስደተኞች ድርጅት (lom) የመስክ ቢሮ ታገኙታላችሁ፡፡ ከዚህ ቢሮ ደጃፍ ላይ ቆማችሁ ፊታችሁን ወደ ግራ ካዞራችሁ ደግሞ አይናችሁ ከሁሉም ቀድሞ መመልከት የሚችለው ይሄው ድርጅት ያቋቋመውን የስደተኞች ጊዜያዊ መጠለያ ካምፕን ነው፡፡ በዚህ ትልቅ የስደተኞች ጊዜያዊ መጠለያ ካምፕ ውስጥ ኢትዮጵያ ያላችሁ እስኪመስላችሁ ድረስ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኛ የእኛን ሰዎች ታገኛላችሁ፡፡ እዚህ ካምፕ ውስጥ ልታገኟት የማትችሉት አይሻ ኑርሁሴንን ብቻ ነው፡፡ እሷ የምትገኘው በሀራድህ ከተማ እምብርት፣ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ ከሚገኝ አንድ አውራ ጐዳና ዳር ነው፡፡
በዚያ አውራ ጐዳና ዳርቻ ላይ ከወገቧ በታች በእርጥበት የወረዛ ሰማያዊ አበባ ያለው ነጭ የሆስፒታል ፒጃማ የለበሰችና አንገቷ ላይ የበፊት ቀለሙ ነጭ ይሁን ቡናማ በውል የማይታወቅ ጉፍታ ጠምጥማ፣ በእርጥበት የራሰ ካርቶን ላይ ተኝታ የምትለምን ጠይም ቀጫጫ ልጅ እግር ኢትዮጵያዊ ሴት ካያችሁ፣ አይሻ ኑር ሁሴን ማለት እሷ ናት፡፡
አይሻ ኑር ሁሴንን ብታገኟትም በቀላሉ ልታነጋግራችሁ አትችሉም፡፡ ከሰዎች ጋር መነጋገሩን ጠልታው ሳይሆን የሰውነቷ ጠረን እጅጉን ስለሚያሸማቅቃት ብቻ ነው፡፡ አይሻ ሽንቷን መቆጣጠር አትችልም፡፡ የለበሰችው ፒጃማ ከወገቧ በታች የወረዛውና የምትተኛበትን ካርቶን በእርጥበት የራሰው በዚሁ መቆጣጠር በማትችለው የራሷ ሽንት የተነሳ ነው፡፡ ለአይሻ ከሁሉም የባሰ ቅጣት የሆነባት በሽንቷ እርጥበት የሚፈጠረው መጥፎ ጠረን ነው፡፡ ይሄ ጠረን ፈፅሞ ሰው አያስቀርብም፡፡ አይሻን ለማነጋገር የሚፈልግ ሰው ሁለት ፈተናዎችን መቋቋም ግዴታው ነው፡፡ የቻለውን ያህል ዘዴ ተጠቅሞ ፈቃደኝነቷን ማግኘትና አፍንጫንና አይንን የሚቆጠቁጠውን መጥፎ ጠረን እንደምንም ብሎ መቋቋም፡፡
የአይሻ ኑር ሁሴንን ፊት በጥሞና ያስተዋለ ሰው፣ የየመን የስደት ህይወት ይህችን አንድ ፍሬ ልጅ ምን እንዳደረጋት በከፊል ማወቅ ይችላል፡፡ የተቀበለችው ግፍና መከራ የፈፀመው ጀብዱ በትላልቅ ፊደላትና በሰፋፊ መስመሮች ፊቷና አይኗ ላይ በጉልህ ተቸክችኮባታል፡፡ የአሳዛኙን ታሪኳን ግማሽ ክፍል ደግሞ እንዲህ ትነግራችኋለች-፡
“ተወልጄ ያደኩት ወሎ ባቲ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ እስከ ሠባተኛ ክፍል ድረስ እዚያው ባቲ ከተማ ተምሬአለሁ፡፡ ትምህርቴን ያቋረጥኩት አባቴ ሊድሩኝ ሲሉ ጠፍቼ ባቲ ገጠር አጐቴ ጋር በመሄዴ ነው፡፡ ባል ይሁንሽ ያሉኝ አቅሜና እኩያዬ ቢሆን ኖሮ በጀኝ ባልኩኝ ነበር፡፡
ጓደኞቼ ሙላቸው እኮ አግብተዋል፡፡ ያመጡልኝ ባል ግን እንዲያው እግርና እጁን ማንሳት የማይችል አጁዛ ነው፡፡ ዛደያንስ እኔ የሬሳ መድፊያ ነኝን ብዬ አጐቴ ጋር ገጠር ጠፋሁ፡፡ ከዛን ጊዜ በኋላም ትምህርት አልተማርኩም፡፡ መማር ግን እፈልግ ነበር፡፡
“አጐቴ ጋር እየኖርኩ ብዙ አመት ባጀሁ፡፡ የአጐቴ ሶስቱ ሴት ልጆች አረብ አገር ነው ያሉት፡፡ ቤይሩት አሉ የሚባሉት ሁለቱ ነውይ ወሬአቸው የሌለ--- ሳኡዲ አለች የምትባለዋ አንዲቱ ካለፍ አገደም ስልክ ደውላ ተናቷና ታባቷ ጋር ትገናኛለች፣አምሳም መቶም ዶላር ትልካለች ይላሉ፡፡ አጐቴና ሚስቱ ታታ መሪማ፣ የሚወስድ ሰው ተፈላልጐ እኔም አረብ አገር ህጄ እናትና አባቴን ሳይሞቱ እንዳሳልፍላቸውና አለም እንዳሳያቸው ነጋ ጠባ ነው ሚነግሩኝ፡፡
“አንድ ጊዜ ግን ደሴ ነው ኮምቦልቻ እኔ እንጃ ብቻ-- ካላሙዲን እሚባለው ፋፍሪካ ስራ ይዟል የሚባለው ያጐቴ ትልቁ ልጁ ሽፋ አብዱልቃድር፣ አረብ አገር ወሳጅ ሰው አግኝቻለሁ ልሄድ ነው ብሎ ሲል እሷንም ይዘሃት ህድ ተባለና አብሬው መጣሁ ልሄድ፡፡ እናንተዬ እንዲያው እናትና አባቴንም እኮ አልተሠናበትኳቸው፣ እንሂድ ተነሽ ሲለኝ ጊዜ ዝም ብዬ ብድግ--- ከዚያም እኔና ያጐቴ ልጅ ሽፋ፣ ታማራም፣ ተትግሬም ተወሮሞ አገር ከመጡ ሌሎች አስራ አንድ ሰዎች ጋር አስራ ሶስት ራሳችን ሆነን ባቲን ላዩን አድርገን፣ በአፋር በረሃ በእግራችን ወደ ጅቡቲ መንገድ ጀመርን፡፡ መንገድ የጀመርነው በ2003 ዓ.ም ሮመዳን ኢድ ባለፈ ልክ በሁለት ወሩ ግድም ነው፡፡
“ታፋር የመጣው መንገድ የሚመራን ሰውዬ ዝም ብሎ ቀልበ ቢስ ጀብራራ ሆኖ እንዲያው መአት ጊዜ መንገዱ ጠፋብኝ እያለ፣ በዚያ በረሃ አስራ ሶስት ቀን ሙሉ በንዳድ በውሃ ጥምና በረሃብ ሲያንከራትተን ባጅቶ ጅቡቲ ጠረፍ አደረሰንና ሄደ፡፡
ያነግዜ ውሃ ጥም ሰውን ይፈግማል ሲሉ ስሰማ የውነት አይመስለኝም ነበር፡፡ እናንተው እዚያ የአፋር በረሃ ላይ አየሁት እንጂ! እመጫት ነኝ አራስ ልጅ ቤት ትቸ ነው የመጣሁት ያለች አንዲት የትግሬ አገር ሰውና ከማልቀስ በቀር እንዲያው አንዲት ክፉ በጐ የማትናገር፣ ፀጉሯን የተቆነደለች ልጅ እግር ሴት-- እሷም የትግራይ አገር ሰው ናት መሰል--- ለጥቆ ደግሞ አንድ ሲሄድ እግሩ ትንሽ ሸፈፍ ሸፈፍ የሚልና ሹፌር ነኝ እያለ ለነሽፋ ሲነግራቸው የነበረ ሽበታም ጥቁር ሰውዬ፣ በንዳዱ በረሃ አናታቸው ከስሎና ምላሳቸው ተጣብቆ ደርቀው የሞቱት ገና ጅቡቲ ድንበር ሳንደርስ ባስር ቀናችን ነበር፡፡ አሸዋውን ማስ ማስ አድርገው እንደነገሩ የቀበሯቸው ወንዶቹ ናቸው፡፡ “ጅቡቲ ድንበር ልንደርስ ስንል በውሃ ጥም ምላሴ ተጣብቆ፣ እኔም እንዳልሞት ብዬ የሚቀመስ ጠብታ ውሃ ስናጣ ግዜ ሁለት ቀን ሙሉ የገዛ ሽንቴን ጠጥቻለሁ፡፡ ይሄውልህ በእጄ እንዲህ እያደረኩ! ሌሎቹም ወንዶቹም ሴቶቹም እኮ የገዛ ሽንታቸውን እንደኔው ጠጥተዋል!
እናተየ መቸስ ከመሞት መሠንበት ይበጃል ተብሎ እኮ ነው! አንድ ቀን ግን ይሄውልህ የበረሃው ንዳድ ራሴን አክስሎኝ ሌሊት ላይ ውሃ ጥሙ ሊገድለኝ አንገበገበኝ፡፡ ታዲያ እንኳን ውሃ ሽንቴን እንኳን እንዳልቀምስ ከየት አባቴ ላምጣው- -- ከጐኔ ተኝታ የነበረችውና ሁልጊዜ ሌሊት ሌሊት የምታንኮራፋው ወፍራሟ ልጅ በላስቲክ ውሃ ይዛ አይቻት ነበር፡፡ ከዚያ መቸም አይኔ እያየ በንዳድ ከስየ፣አፌ ተጣብቆ ከምሞት የያዘችውን ውሃ ሰርቄ ብጠጣ አላህም አይቆጥርብኝም ብዬ፣ ቀስ ብዬ ሳትሠማኝ አነሳሁና የጥማቴን ያህል አንዴ ብለው ሽቅብ ሊለኝ ተናነቀኝ፡፡ የጐማው ውሃ ለካንስ ውሃ ሳይሆን የልጅቷ ሽንት ኑሯል፡፡ ሽንቷን በጐማው አቁታ ይዛው ኑሯል፡፡
“የጅቡቲን ኬላ በጨለማ ተሻግረን አለፍንና ጅቡቲ ገባን፡፡ እዚያም ወንዶቹ ወደ የመን የሚያሻግሩ ሰዎችን እየፈለጉ፣ አንዴ ተገኝቷል አንዴ ቀርቷል ሲሉ አንድ ወር ከሶስት ሳምንት ከረምን፡፡ ከዚያ ቦሳሶ ነው እንጂ እዚህ የሚወስዳችሁ ሠው አታገኙም ሲባል ጊዜ ወደ ቦሳሶ ቁልቁል ጉዞ ጀመርን፡፡ ባቲ ላይ ከተነሳነው መንገደኞች አንድ አራት የሚሆኑት ግን እድላችንን እዚያው ጅቡቲ ሆነን እናየዋለን እንጂ ወደ ቦሶሳ አንሄድም ብለው ሲቀሩ እኛ ግን ሄድን፡፡ ሶስት ቀን በእግራችን ከተጓዝን በኋላ ፑንትላንድ ከሚባለው ቦሳሶ አገር ደረስን፡፡ በምንገድ ግን ውሀ ጥሙ ሊገድለኝ ሲሆን ጊዜ የባህሩን ውሀ እንዳገኘኝ ጠጥቼ ተቅማጥ አንጀቴን አልቦ ሊገድለኝ መቸም አላህ አተረፈኝ፡፡
“ቦሳሶ እንደልብ ይገኛል ያሉት ወደ የመን የሚወስደን ጀልባ ቢጠበቅ ቢጠበቅ ጨርሶ ብቅ አልል ብሎ ሁለት ወር ሙሉ አከረመን፡፡ እዚያ ሁለት ወር ሙሉ ስንከርም የረሀቡ ነገር አልሆን ሲለን ጊዜ ለመርከብ መሳፈሪያ ብለን የያዝናትን ጥሪት እየቆረጠምን ልናዋግዳት ሲሆን ጊዜ ይዞኝ የመጣው ያጐቴ ልጅ ሽፋ አብዱልቃድር፣ እኛ ሌሊት ሌሊት ከምናድርበት ወና መስክ አካባቢ ከመርከብ አንድ ማት እቃ እያወረዱ እንደገና ደግም ከሚጭኑት ሶማሌዎች፣ ሱዳኖች፣ ኡጋንዳዎችና ሩዋንዳዎች ሰዎች ጋር አንዳንድ ጊዜ ዋዛ ፈዛዛ ብታቃለጅ እኮ ትንሽ ገንዘብ ይሰጡሻል ብሎኝ ነበር፡፡ እኔ ግን ልጅ ነኝ፣ በዚያ ላይ ደግሞ እንዲህ ያለ ነገር ሀራም ነው፣ አይሆንም ብዬ ቀረሁ፡፡ እሱኮ እንዲህ ያለኝ አንዳንዶቹ በዚያ በቋንቋቸው ቆንጆ ልጅ እያሉ የሚበሉትን ዳቦም ሩዝም ቂጣም ደግሞ እንደ ድንጋይ የደረቀ የኮቸረ ነገር ብይ እያሉ የሚሰጡኝን አይቶ እኮ ነው!
“እንዲህ እያልን እንደ ከረምን ልክ በሁለት ወራችን የሶማሌዎች ጀልባ መጣለች ተባለና ተነሳን፡፡ በዛች ጀልባ ተሳፍሮ ወደ የመን ለመሄድ አንደኛው ሲጠብቅ የባጀው ሰው ሁሉ ባንዴ ሲሠበሰብ ጊዜ ገበያ መስሎ ቁጭ አለ፡፡ ብቻ ሸፋ እንደምንም ብሎ የያዝናትን ብር በሙሉ በሙሉ ለሶማሌዎች ከፈለና ከጀልባዋ ላይ ለመሳፈር ቻልን፡፡ እዚያ ጅቡቲና ቦሳሶ ሳለን ጀልባዋን የሚነዷት ሶማሌዎች የባህሩ ማዕበል ከተነሳ የተሳፈረውን ሰው በተለይ ሰውነቱ መንዲስ የሆነውን እየመረጡ ባህር ውስጥ ይከቱታል ሲሉ ሰምቼ ስለነበር፣ ሲጀመር ጀምሮ የእናት አባቴ ውቃቤ አንደዜ ታረቀኝና እግሬን መሬት ለመርገጥ ካበቃኸኝ፣ ቡናህንና ጣንህን ከድሜ፣ ጀባ ጀባ እልሀለሁ እያልኩ ስሳል፣ መለስ እልና ደሞ አላህን መንገዴን አንተ አብጅልኝ እያልኩ ስማፀን፣ የመን የባህር ጠረፍ ሁዳይዳ ከተማ ገባን፡፡
ያቺ ውሀ ነው ብዬ በጐማ ያቋተችውን ሽንቷን ሰርቄ የጠጣሁባት ወፍራሟ ልጅማ ሁዳይዳ ጠረፍ እስክንደርስ ድረስ እንዲችው ስታነበንብና አሁንም አሁንም ፊቷን ስታማትብ ነበር፡፡
“የመን ሁዳይዳ የባህር ጠረፍ ላይ የደፋችን የሶማሌዎች ጀልባ ተመልሳ ሄደች፡፡ ጠቅላላችን አንድ አርባ ወይም አንድ ሀምሳ መቸም እንሆናለን፡፡ (ይህ የእነአይሻ ጉዞ በግንቦት 2003 ዓ.ም አርባ ስድስት ኢትዮጵያውንና አስራ ሁለት ኤርትራውያን ስደተኞች በአንዲት ጀልባ ተሳፍረው ያደረጉትና አንድም ስደተኛ አደጋ ሳያጋጥመው በህይወት የመን ሁዳይዳ የጠረፍ ከተማ መግባት የቻሉበት ህገወጥ የባህር ጉዞ ነው)
“ታዲያ ምን ማድረግና ወዴት እንደምንሄድ አላውቅበት ብለን እንዲሁ በመንጋ እየተንጋጋን ድንገት ሁለት ትላልቅ ጩቤ ያገለደሙ የመኒዎች በፈረስ እየነዱ (እየጋለቡ ለማለት ነው) መጡና በአረብኛ የሆነ ነገር ተናገሩን፡፡ ከእኛ ጋር ከነበሩት ሰዎች አንዲት ሴት አረብኛ መናገር ታውቅ ኑራ አናገረችው፡፡ ከዚያም ሁላችሁም ወደ የመን እንኳን በደህና መጣችሁ! እዚያ ማዶ በምታዩት መንደር ሸክ አብዱልቃዊ፣ ይጠብቋችኋል፡፡ ወደምትሄዱበት እስክትሄዱ ድረስ እዚያ እርሳቸው ጋር ታርፋላችሁ፣ እህል ውሀም ታገኛላችሁ ስለዚህ ኑ በሉ፣ ወደ እርሳቸው እንሂድ” ይላችኋል ብላ ነገረችን፡፡ ድካሙ ረሀቡና ውሀ ጥሙ ገድሎን ስለነበር በጣም ደስ አለንና የሠዎቹን ፈረስ ተከትለን ማዶ ወዳለው መንደር ሄድን፡፡
“በመንደሩ ያለው ቤት በጠቅላላው ቢቆጠር አንድ አስር እንኳ አይሞላም፡፡ ብዙ ሰውም የለውም፡፡ ግና እዚያ ደርሰን አንድ ሰፊ ግቢ ውስጥ እንደገባን በእስልምና ወንድና ሴት አንድ ላይ አብሮ አይሆንም አሉና፣ ወንዶችንና ሴቶቹን ለይተው በተለያየ ክፍል ውስጥ ከተቱንና ቶሎ ብለው በሩን ከኋላ ቆለፉብን፡፡ በኋላ ላይ ብዙ ቆይተው በሩን ከፈቱንል፡፡ በሩ ላይ ቆመው ያየናቸው ብዙ ወንዶች የመኖች ናቸው፡፡ ከዚያ የያዛችሁትን ገንዘብም ሆነ ሌላ ነገር አምጡ እያሉ በያዙት የፈረስ መግረፊያ የጠፍር አለንጋ አይን ጥርስ ሳይሉ ይደበድቡን ጀመር፡፡
“ድብደባው ሲጠነክርብን ሁሉም የያዘውን ገንዘብም ሆነ ሌላ ነገር ሁሉ ሰጣቸው፡፡ እኔ ምን ምንም አልሰጠሁዋቸውም፡፡ የአጐቴ ሚስት ታታ፣ ለክፉም ለደጉም ብላ በጨርቅ ቋጥራ የሠጠችኝና ሳኡዲ ያለችው ልጇ አንደዜ የላከችልኝ ነው ያለችው ሀምሳ ዶላር በብልቴ መሀል ደብቄ ይዣት ነበረ፡፡ በተለይ አንዱ የመን ሰውየ፣ አንቺ የያዝሽው ገንዘብ የለም ወይ እያለ በዚያ አለንጋው መአቱን ቢያወርድብኝም፣ ወላሂ አልያዝኩም እያልኩ እግሩ ላይ ተንበርክኬ ለመንኩት፡፡ ሰውነቴ እሳት እንደፈጀው እስኪቃጠል ድረስ ሞሽልቆ ሞሽልቆ ለቀቀኝ፡፡ ያን ያህል ባልተወለደ አንጀታቸው የግርፊያ መአቱን ካወረዱብን በኋላ በሩን ከሁዋላ ዘግተውብን ሄዱ፡፡ ምን መአት ወረደብን ብለን ተላቀስን፡፡ ደንገዝገዝ ሲል እንደገና መጡና በሩን ከፍተው ገቡ፡፡ ሁለት ናቸው፡፡ በወገባቸው አንድ አይት ጩቤ ታጥቀዋል፡፡ ወዲያው አይናቸው የፈቀዳትን ሴት ነይ አንቺ! ተነሽ አንቺ እያሉ እያስነሱ እዚያው ወለሉ ላይ እፊታችን አይናችን እያየ መገናኘት (ወሲብ መፈፀም) ጀመሩ፡፡ መንጋ ሴት ሁላ ቢጮህ፣ ቢያለቅስ ማን ይድረስለት! በግምት እኩለ ሌሊት እስከሚሆን ድረስ እየወጡ እየገቡ ያሻቸውን ሴት ተነሽ እያሉ ሲገናኙ አምሽተው በሩን ቆልፈውብን ሄዱ፡፡“መቸም ያደረብን ረሀብና የወረደብን መአት ለብቻው ነበር፡፡ ገና ሠማይና መሬቱ ተላቆ ከመንጋቱ አምስት ስድስት ሆነው መጡና ልክ እንደማታው ሴቱን ሁሉ ነይ አንቺ! አንቺኛይቱ ተነሽ! እያሉ ተራ በተራ ሲገናኙን አረፈዱብን፡፡ በጥግ በኩል በዚያች ወፍራም ሴት ልጅ ጀርባ አንገቴን ቀብሬ ኑሬ ነይ ብሎ ያስነሳኝ አልነበረም፡፡ ከመካከላቸው እንደ ሱማሌዎች የሚመስለው ትንሽ ሸምገል ያለ የመን፣ ይቺን ወፍራሟን ልጅ የታጠቀውን ጩቤ መዞ ነይ ብሎ ሊገናኛት ሲያስነሳት ወየት አባቴ ልግባ፡፡ ከሷ ጋር ተገናኝቶ እንደለቀቃት እንዲያው አንድ አፍታም እንኳ አልቆየ፣ ነይ አንቺ ብሎ ሲጠራኝ፣ድንጋጤው አድርቆኝ ከተቀመጥኩበት ሳልነሳ እሪ እያልኩ ሳለቅስ ሴቶችን ሁሉ እመር ብሎ ተራምዶ መጣና፣ ያን የሚያብረቀርቅ ጩቤውን መዞ እያስፈራራ፣ የቀኝ ክንዴን ጨምድዶ ይዞ አንጠልጥሎ አስነሳኝና ወለሉ ላይ አፈረጠኝ፡፡ ከወዲያና ወዲህ እየተፈራገጥኩ፣እያለቀስኩ ብለምነውም በጀ አላለኝም፡፡ ያን የበለዘና የተሸራረፈ ጥርሱን ግጥጥ አድርጐ እየሳቀ ላየ ላይ ተጫነኝ፡፡
“ከስር ሆኘ የሞት ሞቴን እየዳጨርኩ ኧረ ልጅ ነኝ ተወኝ! እያልኩ ለመንኩት፡፡ ጨርሶ አልሰማኝም፡፡ ወዲያው ሁለት እጄን በአንድ እጁ ጥርቅም አድርጐ ከወለሉ ጋር ሰፍቶ ያዘና በአንድ እጁ ቀሚሴን ዘንጥሎ ከገለበኝ በኋላ ሙታንታየን ለማውለቅ ወደታች ሲስበው ያችን በጨርቅ ጠቅልየ ደብቄ ይዣት የነበርኳትን ሀምሳ ዶላር አገኛት፡፡ እኔም ግዴለህም ውሰዳት ብቻ እኔን ተወኝ፣ ልጅ ነኝ እያልኩ ለመንኩት፡፡ ብሯን እንዳገኘና እጄን ለቆኝ ከላዬ ላይ ሲነሳ የለመንኩትን ሰምቶኝ ሊተወኝ መስሎኝ ነበር፣ እሱ ግን ከት ብሎ እየሳቀና በአረብኛ አል ሀበሻ! አል ሀበሻ! እያለ እየለፈለፈ ወጥቶ ሄደ፡፡ እኔም ከወደኩበት እያለቀስኩ ተነሳሁና ተቀምጬበት ከነበርኩበት ጥግ ሄጄ ተቀምጬ ማልቀሴን ቀጠልኩ፡፡ ሴቶቹ አይዞሽ! አይዞሽ! ቢሉኝም ሆድ አልሆነኝም፡፡ ንፍጤና እንባየ ተደባልቆ ፊቴ እስኪዝረከረክ ድረስ ፍጥርቅ ብዬ አለቀስኩ፡፡
“ወዲያው ግን ያው ሰውየ ሌሎች አራት የመኖችን አስከትሎ መጣና ከተቀመጥኩበት በጣቱ እያመለከተና ጮህ ብሎ በአረብኛ እየለፈለፈ መሳቅ ጀመረ፡፡ የወሰዳትን አምሳ ዶላር አሁንም ጫፏን አንጠልጥሎ እንደያዛት ነው፡፡ በፍርሀት እየተንዘፈዘፍኩ ሳለቅስ ሁለቱ መጡና ግራና ቀኝ እጅና እጄን አንጠልጥለው በማንሳት ወለሉ ላይ ወስደው አፈረጡኝ፡፡ ስወድቅ ወለሉ ራሴን በሀይል ስለመታኝና ሁሉም ነገር ስለዞረብኝ መፈራገጥና መለመን ጨርሶ አቃተኝ፡፡ ወዲያውኑም ሁለቱ የመኖች ግራና ቀኝ በመቆም፣ በሁለቱ እግራቸው አንድ እጄንና እግሬን ከመሬቱ ጋር ረግጠው ሲይዙኝ፣ ያ ሰውየ እላየ ላይ በመውጣት የለበስኩትን ያደፈ ቀሚስ እስከአፍንጫዬ ድረስ ወደ ላይ ገልቦ ተገናኘኝ፡፡ ይሄኛው ልክ ጨርሶ ሲነሳልኝ በሩ አጠገብ ቆመው ከነበሩት አንደኛው ወዲያውኑ ተተካና ተገናኘኝ፡፡ ይህኛው ሲጨርስ ደግሞ ሌላኛው እያሉ ተፈራረቁብኝ፡፡ “እስከ ቀትር ድረስ እየተፈራረቁ ሲሉኝ ቆይተው፣ ወለሉ ላይ በደም እንደተለወስኩ ትተውኝ በሩን ከኋላ ቆልፈውት ሄዱ፡፡ ከህመሙ የተነሳ ሩሄን ልስት ስል ሴቶቹ አፋፍሰው አንስተው በምናምኑ ደሜን ጠራረጉኝና ጥግ ላይ ወስደው አጋደሙኝ፡፡ ሁሉም እኔን እኔን እያዩ ምርር እያሉ ያለቅሱ ነበር፡፡ ረሀቡ ብሎኝ ብሎኝ ወስፋቴ ስለተዘጋ መራቡን ትቶኛል፡፡ ውሀ ጥሙ ግን መላ አካሌን ከእግር ጥፍሬ እስከ ራስ ፀጉሬ ድረስ አንሰፈሰፈኝ፡፡ በተለይ እየተፈራረቁ ሲገናኙኝ የፈሰሰኝ ደም አለቅጥ ውሀ ውሀ አሰኘኝ፡፡ እኩለ ሌሊት ሲሆን መላ ሰውነቴ ላብ እየደፈቀኝ ያንቀጠቅጠኝ ጀመር፡፡ ወዲያው ደግም ቅዠት ጀመረኝና መለፍለፍ ብቻ ሆነ፡፡ ሴቱ ሁሉ ከቦኝ እያለቀሱ ሳለ፣ አንዷ አረብኛ መነጋገር የምትችለው ሴት በሩን እየደበደበች በአረብኛ ስትጮህ አንድ ጐባጦ ሽማግሌ የመን እየተነጫነጩ ከፈቱላት፡፡
በጣቷ ወደ እኔ እያመለከተች በአረብኛ የሆነ ነገር ተናገረቻቸው፡፡ ከትንሽ ቆይታ በኋላ በትንሽ የብረት ቶፋ የተሞላ ውሀ አቀበሏትና በሩን በላያችን ላይ መልሰው ዘጉት፡፡”
(ይቀጥላል)

Read 22576 times Last modified on Saturday, 01 December 2012 15:24