Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 01 December 2012 13:04

የጐጆ ባለሙያው!

Written by 
Rate this item
(3 votes)

“የሚያምር እንጨት ካየሁ አላልፍም”
ከሙያህ እንጀምራ… እስቲ የምትሰራቸውን በዝርዝር ንገረኝ…
የሀገር ባህል ቤቶች የእንጨት ስራና የኮንስትራክሽን ሰራተኛ ነኝ፡፡ የሀገር ባህል ስራ ስልሽ ጐጆ ቤቶች ሳር የሚለብሱ፣ በሳር ብቻ አይደለም በፊላ፣ በቀርከሃ እሠራለሁ፡፡ የእንጨት ስራ ስልሽ ከተለመደው ውጪ በተለይም ከባህር ዛፍ፣ ከግራር እንጨት፣ ከዋንዛና ከዝግባ የተለያየ እና ማራኪ በተለይም እስከ እነ ተፈጥሮዋቸው ሳይፈለጡ፣ ሳይጋጋጡ፣ ሳይነካኩ ቅርፃቸውን በጠበቀ መልኩ እስከ እነ ውበታቸው ዕይታ ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ ነው የእኔ ሞያ፡፡ የራሳቸውን የተፈጥሮ ውበት በጠበቀ መልኩ ስልሽ እንጨቶቹ ለምሳሌ የሰው፣ እንስሳ፣ ዋርካ የመሳሰሉ የእንጨቶች በሃሪ የየራሳቸውን ውበትና ዲዛይን ይዘው ነው፡፡

የተፈጥሮ ውበታቸውን በጠበቀ መልኩ ስራ ላይ የምታውላቸው የዛፍ አይነቶችን ከየት ታገኛለህ?
ሰዎች ዛፎችን ከመኖሪያ ቤትና ከመስሪያ ቤቶች ቆርጠው ይጥሏቸዋል፡፡ ያጫርቱታል፡፡ የእንጨቶችን ባህሪና ውበት ለይቼ ስለማውቅ በየመንገዱና በየአካባቢው አይኔ እንጨቶችን ፍለጋ ይባዝናል፡፡ የተጣሉ የእንጨት ዝርያዎችን የመበስበስና ያለ አግባብ ወድቀው ከመቅረት የማዳን ስራ ነው የምሰራው፡፡
በእግሬ ስጓዝ እንኳን የወደቀና የሚያምር እንጨት ካየሁ አነሳለሁ፡፡ በተፈጥሮዋቸው ውስጥ የራሳቸውን ባህሪ እፈልጋለሁ፡፡ ሶፋ፣ የመስታወት ፍሬም፣ የወንበር እግሮች፣ ጠረጴዛ የመሳሰሉትን ይገኝበታል፡፡
እንዴት ነው ወደዚህ ሙያ የገባኸው?
ውስጤ ያለውን ሞያ አውጥቼ እንድጠቀም የረዳኝ እግዚአብሔር ነው፡፡ ከዚህ ስራ ጋር የምተዋወቅበት ምክንያት አልነበረም፡፡ በችግር ምክንያት ቤተሰቦቼን ለመርዳት ብዬ የቀን ስራ ተቀጥሬ በመስራት ነው ነገሮች እዚህ ደረጃ የደረሱት፡፡
ለቤተሰቤ ሁለተኛ ልጅ ነኝ፡፡ ገና 8ኛ ክፍል እያለሁ በ14 ዓመቴ ነው እየተማርኩ ቤተሰቤን ለመርዳት ወደ ቀን ስራ ገባሁት፡፡ በቀን 3 ብር ከ50 ሳንቲም አገኝ ነበረ፡፡
እኔ እና የአሁን ሞያዬ በዚህ ሁኔታ ተጣጥመን እዚህ ደረሰን እንጂ የእኔ ፍላጐት ቦክሰኛ መሆን ነበር፡፡ ኑሮው ግን አልተመቸም… እንኳን ተደባድቤበት… እናም ኑሮ ግራ ሲያጋባኝ ከጓደኞቼ ተደብቄ የ3 ብር ከ50 ሳንቲም ስራዬን ጀመርኩ፡፡ መቼም ይደርስብኝ የነበረው ጫና የሚገርም ነው፡፡ ጓደኞቼ “አንተ ኩሊ፣ ከእኛ ጋር እየተማርክ እንዴት የቀን ስራ ትሠራለህ” እያሉ ያሸማቅቁኝ ነበር፡፡ ግን ለዛሬ ስኬት ያበቃኝ ትናንት ያገኘሁትን ሥራ መስራቴ ነው፡፡
የቀን ስራ ስትል… ምን አይነት ነው?
የሰው ቤት አጥር እሰራ ነበር - በቆርቆሮ በእንጨት፡፡
ሲሚንቶ እሸከም ነበር፡፡ ድንጋይ ከመኪና አወርዳለሁ፡፡ ይህን እየሠራሁ ትምህርቴን ጨረስኩ፡፡ ከዛም ተግባረድ ገባሁ፡፡
ከተግባረዕድ በኋላ ነው ወደ እንጨት ስራ የገባኸው?
አዎ! ለእንጨት ውበት ያለኝ ፍቅርና አድናቆት የተለየ ነው፡፡ እንጨት ሲማገድ፣ ያለ አግባብ ሲጐሳቆል ደስ አይለኝም፡፡ በጣም አዝናለሁ፡፡ የማይረሳኝ ገጠመኝ አለ፡፡
አንዲት እናት እንጀራ ይጋግራሉ፤ በእንጨት፡፡ ቆሜ ስመለከታቸው በጣም የሚያምረውን እንጨት አንስተው ይማግዱታል፡፡ የእንጨቱ ቅርጽ አፉን ይከፍትና መንታ ምላስ ያለው እባብ ይመስል ነበር፡፡ ስጡኝ ብላቸው ‹‹እየጋገርኩት ያለው ሊጥ ይበላሽ? እንጀራ እየጋገርኩ መሰለኝ›› ብለው ተቆጡ፡፡ ልክፈል ብላቸውም እንኳን እምቢ አሉኝ፡፡ ‹‹ምን ትፈላሰፍብኛለህ!›› ሲሉኝ ዞር አልኩ፡፡ ያንን የመሰለ የእንጨት ውበት ከየትም ላመጣ እንደማልችል ስለማውቅ እንባ ነው የተናነቀኝ፡፡
ውበት ያላቸው የእንጨት ዝርያዎች በተለይ ከየት ታገኛለህ? ከአዲስ አበባ ነው ወይስ…
አዲስ አበባ አዲስ አበባ ደግሞ ምን የሚታይ እንጨት አለ፡፡ አርሲ ነገሌ ብትሄጂ የዛፎቹ ተፈጥሮ ያስደንቅሻል፡፡
ጉብጥብጥ ያሉና የተለያዩ አይነት ቅርፆች ያላቸው ዛፎች አሉ፡፡ የሰው ቅርጽ የሚመስሉ አሉ፡፡ ወንድና ሴት፣ ትናንሽ ልጆች፣ የወንድና የሴት ብልት የሚመሳስሉ ሁሉ አሉ፡፡ እዛ አካባቢ ዝግባ፣ ቀረሮ፣ ባህር ዛፍ፣ ግራር የመሳሰሉ ዛፎች አሉ፡፡ አቤት ሲያሳዝንሽ… ደን ልማት ብትይ የአካባቢው ማህበረሰብ እንደ ጉድ ነው አልኩሽ የሚጨፈጭፋቸው፡፡ እንጨቶቹ እንዲሁ ወድቀው ስታያቸው እምባሽ ይመጣል፡፡ ባክነው እንዳይቀሩ እኔ ወደ ህዝብ እይታ አመጣቸዋለሁ፡፡ ደብረብርሃን፣ አክሱም፣ ዝዋይ፣ ጅማ፣ አካባቢ ያሉ እንጨቶችም ድንቅ ጥበብና አፈጣጠር ያላቸው ናቸው፡፡ እኔ በእንጨት ፍቅር ወድቄያለሁ፡፡
የአገር ባህል ቤቶችንም ትሰራለህ?
ሌላው ህይወቴ የተመሠረተው በጐጆ ቤቶች ጥበብና ውበት ነው፡፡ በሳር፣ በፊላ፣ በቀርከሃ ጐጆ ቤቶች እሰራለሁ፡፡ በመዝናኛ ቦታዎችና በተለይ በአዲስ አበባ ጥሩ ገቢና መኖሪያ ያላቸው ሰዎች ግቢ ውስጥ ምርጥ ጐጆዎችን ሰርቻለሁ፡፡
እስቲ ከሰራሃቸው መዝናኛ ስፍራዎች ጥቀስልኝ? ያንተ ጐጆዎች የት የት ይገኛሉ?
የአፍሪካ ቫኬሽን ክለብ፣ ቦራቲ ሎጂ፣ የሳቫና ሎጅ፣ በአዋሳ የሌዊ ሪዞርት የሚጠቀሱ ሲሆን በላንጋኖ ዙሪያ የሚገኙ ባለሀብቶች ገዝተው የሚያከራይዋቸውና ከነቤተሰቦቻቸው የሚዝናኑበትን ጐጆዎች ዲዛይኑን ከማውጣት ጀምሮ እስከመገንባት ድረስ ሰርቻለሁ፡፡ በአዲስ አበባ ሃያት፣ ሲኤምሲ፣ ቦሌ፣ ፒያሳ እና ሌሎች አካባቢዎች በግለሰቦች መኖሪያ ቤት ውስጥ ጐጆዎችን እንዲሁም ባንኮኒና ባንኮኒ ዙሪያ የሚቀመጡ ወንበሮችን በእንጨት አሳምሬ ሰርቻለሁ፡፡ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ጊቢያቸው ውስጥ ወይንም በሳሎናቸው ውስጥ ጐጆ ቤት እንዲሰራላቸው ይፈልጋሉ፡፡
ለምን መሰለሽ ጐጆ ቤት ሙቀት ሆነ ቅዝቃዜ የአየር ንብረቱን ከመቆጣጠሩ በተጨማሪ የአገር ቤት ስሜት ይፈጥራል፡፡
ከሚያብረቀርቅርና ከተፈጥሮ ውጭ ከሆነ ጌጣጌጥ የበለጠ ያምራል፡፡ ብቻ ደስታ ይሰጥሻል፡፡ የገጠር ድባብ ይፈጥርልሻል፡፡ ይሄው እንግዲህ 18 ዓመት ሙሉ ህይወቴ ሆኗል፡፡
ጐጆ ቤት ለመስራት ወጪው ውድ ነው ይባላል?
ተመጣጣኝ ነው፡፡ ውድም ቢሆን እኮ እድሜ ይቀጥላል፡፡ እንዴት መሰለሽ… ጐጆ ቤት ውስጥ ዘና ብሎ መጽሐፉ ማንበብ፣ እረፍት ማድረግ፣ ቡና መጠጣት… በጐጆ ቤቶች ውስጥ የምትተነፍሽው አየር ሁሉ ደስ የሚልና የሚያነቃቃ ነው… የተረጋጋ መንፈስ ይሰጥሻል፡፡
አይንሽን አይሰለቸውም፡፡ በእርግጥ ሳሩና ቀርከሃው ውድ ነው፡፡ እኔ የማስበው እንዴት ተውቦ ይሰራል የሚለውን እንጂ የሚያስወጣኝንና የማተርፈውን አይደለም፡፡ ደግሞ ከየት ነው የምታመጣው ብለሽ ገበያዬን እንዳትዘጊብኝ… ከሩቅ አካባቢ ነው (ሳቅ)
አንዱ ጎጆ በምን ያህል ብር ይሠራል?
በርግጥ እንደ ሁኔታው ቢለያይም በአማካይ ልነግርሽ እችላለሁ፡፡ ሶስት በአራት የሆነ ጎጆ ስልሳ ሺህ ብር ይሠራል፡፡
የጐጆ ቤት ዲዛይኑ የራስህ ነው ወይስ ሰዎች እንዲህ ሥራልን ይሉሃል?
ሰዎች ፍላጐታቸውን ይነግሩኛል፡፡ እኔ ደግሞ የዲዛይኑን ውበት በአዕምሮዬ ስዬ እንደዚህ ይሁን እላቸዋለሁ፡፡ እነሱም ይሰሙኛል፡፡ ቦታውን አያለሁ… የሚያመቸውን ዲዛይን መርጬ በሚያምር መልኩ አስውበዋለሁ፡፡
እንዴት ነው… ሰው ጐጆ ቤት ይፈልጋል?
ዛሬ ዛሬ በጣም ብዙ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ሰው መኖሪያ ቤቱን በጐጆዎችና በተፈጥሮ እንጨቶች ማስጌጥ ይፈልጋል፡፡ ግን ያን ያህል ጥቅሙ የገባው አለ ማለቱም ይቸግራል፡፡
ባለሃብቶች አካባቢ ግን ፍላጐት አለ፡፡ ከውጭ የሚመጡ ሰዎች መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ጐጆ ቤትና የእንጨት ስራ ውጤቶች እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ፤ ያሠራሉም፡፡ የውጭ ዜጐችም የመኖርያ ቤታቸውን በር፣ መቀመጫ፣ ጠረጴዛ… የተለያዩ የቤት ቁሳቁሶችን ወዘተ… በእንጨት ውጤቶች ያሰራሉ፡፡
ጎጆዎች ስያሜ አላቸው?
አዎ! የሲዳሞ ባህላዊ ጐጆ የሚሰራው በቀርከሃ ሲሆን ውስጣዊ ክፍሉ ግርግዳው ዙሪያውን በወፊጮ (በሰኔል) ይሠራል፡፡
የወላይታና የጎጃም በሳር ይሠራል፡፡ የኦሮሚያ አካባቢ በፊላ ይሠራል፡፡
በስርህ ስንት ሰራተኞች ይተዳደራሉ?
እንደ ስራው ሁኔታ በየጊዜው ቢለያይም እስከ 50 ጊዜያዊ ሠራተኞችን እቀጥራለሁ፡፡ በስሬ እስከ 15 ባለሞያዎች አሉኝ፡፡
የአንተ መኖሪያ ቤትስ… በዚህ መልኩ የተሰራ ነው?
ቤቴን በዚህ መልኩ ለመስራት ዲዛይኑን ነድፌ አስቀምጫለሁ፡፡ ግን ሃዘን ላይ ስለነበርኩ እስካሁን አልተሰራም፡፡ አሁን ተረጋግቻለሁ፡፡ በቅርቡ ቤቴን በጐጆና በእንጨት ስራ ውጤቶች አስውቤ በአጭር ጊዜ ውስጥ እጋብዝሻለሁ፡፡
ቤተሰብ መስርተሃል?
አዎ ሁለት ልጆች አሉኝ፡፡ የ6ኛ እና የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው፡፡ ባለቤቴ የዛሬ ሦስት ዓመት አካባቢ በካንሰር በሽታ አርፋለች፡፡ ራሴ ያስተማርኳቸው እህትና ወንድሞቼ ከእኔ ጋር ይኖራሉ፡፡ በባለቤቴ ሀዘን ምክንያት አንዳንድ ያሰብኳቸውንም ስራዎች አጓትቻቸው ነበር፡፡ እንግዲህ በቅርቡ የራሴን ቤት በባህላዊ መልኩ ከመገንባት በተጨማሪ በዝዋይ የራሴን የእንጨት ቤት እየከፈትኩ ነው፡፡ ስራዬ ተንቀሳቃሽ በመሆኑ እዚህ አዲስ አበባም የእንጨት ቤት አለኝ፡፡ በዚህ ሁኔታ ነው ያለሁት፡፡
ገቢህ ምን ያህል ነው?
ገንዘቡን ተይው ግን እግዚአብሔር ይመስገን ገቢዬ ከፍተኛ ነው፡፡ ጥሩ ገንዘብ ሰርቻለሁ፤ የተሻለ ጊዜ ላይ ነኝ ብልሽ ይበቃል፡፡ ዛሬም እንግዲህ ቀን ከሌሊት እየሰራሁ ነው፡፡ በኮንስትራክሽን ስራም እድገት እያሳየሁ ነው፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን ሁሉም መልካም ነው፡፡

Read 7118 times Last modified on Saturday, 22 December 2012 11:54