Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 01 December 2012 13:47

የጠንቋዩ ትዕዛዝ

Written by 
Rate this item
(11 votes)

“ልጅ መውለዱ ባልከፋ፤ ግን በሁለት ዓመት ውስጥ ስድስት ልጅ እንዴት ነው ልወልድ የምችለው?” አለ መሀመድ ሰይድ እንባ እየተናነቀው፡፡ የቀዬው ቃልቻ ስድስት ልጅ በሁለት ዓመት ውስጥ ወልዶ በአውልያው ካላስመረቀ ከፍ ያለ እርግማን በእሱና በቤተሰቡ ላይ እንደሚወርድበት ፈርዷል፡፡ በድፍን ሀርቡ፣ በድፍን ወሎ ተሰምቶ የማይታወቅ ፍርድ ነው ጠንቋዩ የሰጠው፡፡ እንዴት በሁለት ዓመት ውስጥ ስድስት ልጅ? ያለችው አንድ ሚስት! መሀመድ ከጓደኛው እንድሪስ ጋር ከተቀመጡበት ጉብታ ስር ወደተንጣለለችው ሀርቡ ከተማ እያየ በሀሳብ ሰጠመ፡፡ በሀርቡ ሰማይ ላይ የምታቆለቁለውን ጀንበር መጥለቅ ተከትሎ ወደየማደሪያቸው የሚያመሩት የግመል ቅጥልጥሎችን የመሰለ ሀሳብ በአእምሮው ውስጥ በሰልፍ ያልፍ ጀመር፡፡

እንድሪስ የጓደኛውን በሀሳብ መባከን አይቶ ንግግር ጀመረ፡፡
“ምን አማራጭ አለህ አንተው?” የእሳቸው ከራማ ከተጣላህ ደሞ የሚመጣውን ታውቀዋለህ!” አለው የመሀመድ ጭንቀት እሱንም ያስጨነቀው መሆኑን በሚያስረዳ አኳኋን፡፡
በመንደራቸው ያለው ጠንቋይ ከተጣላ መአቱን እንደሚያመጣ ሁሉም በየቤቱ የሚያንሾካሹከው ጉዳይ ነው፡፡ ጠንቋዩ ትዕዛዙን ባልፈፀሙት ላይ የሚያመጣው ቅጣት ለሰሚ ግራ የሆነ ነው፡፡ ጠንቋዩ አያ ገብሩ ከተባሉ ሰው ጋር ተጣልቶ ያደረገባቸው ነገር ከድፍን ሀርቡ አልፎ የሚተረክ ወግ ሆኗል፡፡ ጠንቋዩ በአያ ገብሩ ላይ “ስራዬ-ፈስ” አድርጎባቸው በየሔዱበት ሲያንዛርጡ እንዲውሉ አድርጓቸዋል ተብሎ በሰፊው ይወራል፡፡ በየመንገዱ፣ በየቅሬው /እድሩ/፣ በየሰንበቴው፣ በየለቅሶ ቤቱ … የአያ ገብሩ ፈስ እንደ ጡሩንባ መሰማቱ ልማድ ሆኖ አንገታቸውን አስደፍቶ ከሰው እንደነጠላቸው በሰፊው ተነግሯል፡፡ በዚህ የተነሳ አያ ገብሩ በሀፍረት የትውልድ ቀያቸውን ጥለው እንደተሰደዱ ይታመናል - በአካባቢው ነዋሪ ዘንድ፡፡ እና የጠንቋዩን ትዕዛዝ ማን ሊገዳደር? “የአያ ገብሩን ፈስ የሰማ በጠንቋዩ ትዕዛዝ አይጫወትም” ብሒል የሰፈነ መስሏል - በሀርቡ ምድር፡፡ ምን ይኼ ብቻ! በዳውድ ሀሰን ላይ ጠንቋዩ ያመጣው መአትም በሀርቡ ምድር “እግዚኦ!” ያሰኘ ተአምር ነበር፡፡ ዳውድ ሀሰንን ያገባ ጥቁር ውሻ ይወልዳል ብሎ ፈርዷል ተብሎ ዳውድ ሀሰን በሀርቡ ምድር የሚያገባው አጥቶ ሲባክን ከርሞ በብስጭት ወደ ሌላ ሀገር ተሰዷል፡፡
“እና ምን ላድርግ?” አለ መሀመድ ሰይድ በጭንቀት ተወጥሮ፡፡
“በቃ ትዕዛዙን ፈጽም! እንዳለህ ስድስት ልጅ ወልደህ እንዲባርክልህ አድርግ!” አለው እንድሪስ፡፡
“መላው ነውይ የጠፋኝ ልጅ መውለድማ መች ጠላሁ? እንኳን ከረማው አዞኝ ይቅርና ስድስት ልጅ ቢኖረኝ ዘሬ በመብዛቱ ምን ገዶኝ? ግና … የሚስቴ ማህጸን አንድ ብቻ! በአንዱም ውስጥ ፍሬ እንዲያድር አላህ ሲፈቅድ ነው፡፡ ተሁሉ በላይ ዴሞ አንድ ፍሬ ተጽንሶ እስቲወለድ ዓመቱ መፍጀቱ ወይት ይቀራል? ወይ እንደ ማሽላ የሚያጥጥ አይዶል የሰው ልጅ!” አለ መሀመድ አንገቱን በተስፋ መቁረጥ እየደፋ፡፡
“ይቻላል! ታሰብክበት ይቻላል!” አለ እንድሪስ ፍርጥም ብሎ፡፡
“እኮ እንዴት? መላ ታለህ አቀብለኛ!”
“መላውማ … እንግዲህ መቸስ ታልተቀየምኸኝ …” አንገራገረ እንድሪስ፡፡
“ለምን እቀየምሀለው? ልስማውና ተሆነ ሆነ ታልሆነ ደሞ መቸስ ምን ይደረጋል?” አለ መሀመድ እንድሪስ ያሰበውን እንዲነግረው በሚገፋፋ አነጋገር እያበረታታው፡፡
“መቸስ ታልክማ ‘ንግዲህ … ያው ተሚሽትህ ከራማው በጠየቀህ መሰረት ልታደርስ የምትችለው ፍሬ በዛ ቢባል ሁለት ነው፡፡ አላህ አርዚቁን ሰጥቶህ መንታ መንታ ብትይዝልህ እንኳ በሁለት አመት ጊዜ ታራት በላይ ልጅ አታደርስልህም፡፡ ስለዚህ ተሚሽትህ ሌላ …” እንድሪስ ንግግሩን ሳይጨርስ መሀመድ ከተቀመጠበት እመር ብሎ ተነስቶ ከንግግሩ አቋረጠው፡፡
“አትጨርሰው እድሪስ! አትጨርሰው! ምነው ባክህ? ምነው? የባልንጀርነትህን ምኸረኝ አልሁህ እንጂ በትዳርህ ላይ ወስልት ትለኛለህ ብዬ መች ጠበኩ?” መሀመድ በንዴት ተንተከተከ፡፡ የሚወደው የልብ ጓደኛው ባይሆን ኖሮ እንዲህ ያለው፤ በያዘው ሽመል ቢነርተው በወደደ፡፡ “እና ምን ይሻል? ተዚህ የተሻለ ሀሳብ ታለህ አምጣ!...” አለ እንድሪስ በበኩሉ እንደመቆጣት ብሎ፡፡
መሀመድ የተሻለ ሀሳብ ስለልነበረው አንገቱን አቀረቀረ፡፡ ኢድሪስም የመሀመድን መለሳለስ አስተውሎ በርጋታ ይመክረው ጀመር፡፡ “እሺ እንዳው ተሌላ ሴት ጋር ተፈጣጠምኩ እንበል፡፡ ግን እንዲያው ሰሚራ ታወቀችስ?” አለው መሀመድ ምክሩን በጥሞና አዳምጦ እንደጨረሰ በስጋት በታጀለ ስሜት ውስጥ ሆኖ፡፡ ባለቤቱ ሰሚራ ታወቀችስ?
“አንድያውን ጅል ሆንክሳ ሙሄዋ! እንዴት ነው ሰሚራ የምታውቀው? ሁሉም በምስጢር ተጀምሮ በምስጢር ያልቃል!” አለው እንድሪስ የእጆቹን መዳፍ በየተራ እያጋጨ፡፡
መሀመድ ስጋት ገብቶት ለአፍታ አቀረቀረ፡፡ ሚስቱን አሰባት፡፡ በሀብሩ ምድር እንደሷ ቆንጆ አልተፈጠረም የሚባልላት ጠይም እመቤት ናት - ሰሚራ፡፡ በአይኗ ሰረቅ አድርጋ ያየችው ቀርቶ ከርቀት ከቅንጭብ ጢሻ ውስጥ ሆኖ ያያት ጎበዝ ሁሉ በፍቅሯ ሲነድላት የሚኖር ውብ፡፡ መሀመድ ከስንቱ ጋር ዱላ ገጥሞ፣ ከስንቱ ጋር ተፈናክቶ ነው በመጨረሻ ሰሚራን በእጁ ያስገባት፡፡ መሀመድ በሁሉ ነገር ተሸናፊ “እሺ” ባይ ነው - በሚስቱ ጉዳይ ካልመጡበት በስተቀር፡፡ በሚስቱ ጉዳይ ከመጡበት ግን ሽርጤን ላገልድም፣ ጊሌዬን ልታጠቅ በሚል ጊዜ አያባክንም - የለበሰውን ለብሶ የያዘውን ይዞ ከጠላቱ ጋር ይፋለማል እንጂ፡፡
በመሀመድ ፊት እንኳን ሰሚራን ቀና ብሎ የሚያይ ስለሷ ክፉም የሚያወራ ቢሆን በሀርቡ ምድር ፈልጎ ማግኘት ያስቸግራል፡፡ በዛ ላይ አንድ የአረብ ብርጭቆ የመሰለ ወንድ ልጅ ሰጥታዋለች፡፡ ባሏ በሷ ላይ ሊሸፍጥ መሆኑን ብታውቅ ግን ምን ትላለች? መሀመድ ጭንቅ - ጥብብ አለው፡፡ ለዚያውም ሀይማኖቱ ከሚፈቅደው ውጪ በስርቆሽ በር ገብቶ መውለዱን ብታውቅ ምን ትላለች?
እንድሪስ ደጋግሞ የጠንቋዩን ቁጣ እያስታወሰ አማራጭ አልባ አደረገው፡፡ አይኑን ጨፍኖ ከሌላ ሴት የመውለዱን ጉዳይ “እሺ!” ከማለት የዘለለ አማራጭ አልነበረውም፡፡
“በጄ እንግዲህ መቼስ ምን አደርጋለሁ? ሊያውስ የምትሆን ሴት ከተገኘች አይደል?” አለ መሀመድ የሚንሸራተት ልቡ በፈጠረበት ብዥታ ውስጥ ሆኖ፡፡
ምናልባት ያሰቧት አይነት ሴት በሀርቡ ምድር ባልተገኘች ብሎም እያሰበ ነበር፡፡ ካልተገኘች በሚስቱ ላይ መሸፈቱ እንደሚቀርለት ተመኘ፡፡
“ፑህ … እንደው ምናለ በለኝ! አንተ በሀሳቤ እንኳን ተስማማህ እንጂ … ታንተ ዘር መጋራቱን የምትጠላ ሴት ታገኘህ አንገቴን ለካራ!” አለ እንድሪስ በርግጠኝነት ስሜት፡፡ እውነቱን ነው! መሀመድ የዛላው ማማር ብቻ ሳይሆን ከብርቱ ዱለኝነቱ ጋር በተያያዘ የሚወራለት ጀግንነት - የሀርቡ ምድርን ሴት ለማማለል ከበቂ በላይ ነበር፡፡ እንድሪስ ጉዳዩን በምስጢር ይዞ የተባለችዋን አይነት ሴት ሊፈልግ ተስማምተው ተለያዩ፡፡ ሲለያዩ እንድሪስ አንድ ምክር ጣል አደረገ፡፡
“እንደው ሁነኛ ሴት እስክታገኝ ከሚስትህ ጋር ሙቀት መጋራቱን ብትተወው፡፡ ኋላ ተሌለኛዋ ሴት ስትሄድ ተሳንፈህ ውጥናችንን መና እንዳታስቀረው!” አለው እንድሪስ፡፡ መሀመድ ተሚስቱ ገላ ለቀናት አይደለም ለእኩለ ቀን በስስት ነፍሱን ሊነጥቅ ያደርሰዋል፡፡ ግን የጓደኛውን ምክር መስማቱ የግድ ስለሆነ አንገቱን በመነቅነቅ እሺታውን ገለጸ፡፡
መሀመድ እንደ ወትሮው በጊዜ ወደ ቤቱ ገባ፡፡ እንደ ወትሮው ግን ከሰሚራ ጋራ ወግ የመጠረቅ ልማዱ ቀርቶ አይኗን ማየት እንኳን ተሳቀቀ፡፡ በማር እና በቅቤ አርሳ ያቀረበችለትን ፈጢራ እንደነገሩ ለኮፍ አድርጎ ከመኝታው ላይ በጊዜ ሰፈረ፡፡ ሰሚራ ስራዋን ጨርሳ መጥታ ከጎኑ ስትጋደም፣ እንዳልሰማ ሆኖ የውሸት እንኩርፊያ ማሰማቱን ቀጠለ፡፡ ለወትሮው ተምኔው መሽቶ የሚስቴን ገላ በታቀፍኩ የሚለው መሀመድ፤ እንደ እሳተ ገሞራ ልውጣ እያለ ሽቅብ ቁልቁል የሚራወጥ ስሜቱን ገድቦ አደፈጠ፡፡ ሰሚራ እየተገላበጠች፤ ኩታውን በእንቅልፍ እያስመሰለች ብትገፈውም ምላሽ ሊሰጣት አልቻለም፡፡ ከአፋር እንደሚነፍስ ወበቃማ አየር የሚጋረፈው ትንፋሿ በአንገቱ በኩል እየመጣ ሁሉ ነገሩን ቢወጥረውም ስሜቱን ኮርኩዶ ጸጥ አለ፡፡
ቀናት በሳምንታት፣ ሳምንታት በወራት ተተክተው ድፍን ሁለት ወር እንደዘበት ተቆጠሩ፡፡ ከመሀመድ ጋር አንሶላ ልትጋፈፍ ፈቃደኛ የሆነችዋን ሴት ማግኘት የሀገጎትን ዳገት እንደመውጣት አስቸጋሪ ሆነ፡፡ እንድሪስ እንደው ትንሽ ቀን ሰጠኝ እያለ ሁነኛ ሴት ማማረጡን ቢቀጥልም የተባለችዋን ሴት አገኘሁ ማለቱ ከብዶት ቆየ፡፡
ሰሚራ የባሏ ድንተኛ ለውጥ ያልጠበቀችው ነበር፡፡
ያ ሁሉ መንከባከቡ ቀርቶ አይኗን ማየቱ ሲያሸብረው ስታይ ልቧ በዋግ እንደተመታ አዝመራ በጥርጣሬ ላሸቀ፡፡ ምን ሆኖ ነው? አስቸኳይ ጉዳይ እንደገጠመው ሰው በእኩለ ቀን ከመሀል ገበያ አስጠርቷት በፍቅር ጨዋታ የሚያብዱበት ጊዜ እንደዚህ በፍጥነት ታሪክ ይሆናል ብላ አስባም አታውቅ፡፡ የስሜት ትኩሳቷን እያስታመመች የባሏን ፍቅር ዳግመኛ ለማግኘት መባጀቷን ቀጠለች፡፡ ምን በድዬው ይሆን በማለት ተብሰከሰከች እንጂ ልቡ ሌላ ከጅሎ ይሆናል ብላ ለአፍታም አላሰበች፡፡
“በቃ የመጣው ይምጣ ተዛሬ በላይ አልጠብቅም፡፡ ተስሜቴ ጋር ጀርባ ተሰጣጥቼ ማደር አልችልም!” አለ መሃመድ አንድ ተሲያት ላይ እንድሪስ ላይ በቁጣ አፍጥጦ፡፡
“ታልክ እሺ!... ምን የመሰለችዋን አግኝቼልሀለው!” አለ እንድሪስ በደስታ ፊቱ በርቶ፡፡
“ምነው ስታሁን ሳትነግረኝ እያ?” አለ መሀመድ በቅሬታ ውስጥ ሆኖ፡፡
ምስጢር ጠባቂዋን እስታገኝ ነዋ! በያ ላይ ዘር መተካትህ ታልቀረ ቆንጆ ብትሆን ይበጅሃል ብዬ ነዋ!” አለ እንድሪስ ነገሩን በማስተባበል፡፡
“እንግዲያው የሆነስ ሆነና ልጅቱ የምትታወቅ ናት?”አለ መሀመድ በጉጉት
“ልጅቱማ የጋሽ ዑመር ልጅ ጠይባ ነች!” አለ እንድሪስ ታላቅ ሚስጢር እንደሚተነፍስ ሰው በለሆሳስ፡፡ መሀመድ በድንጋጤ አመዱ ቡን አለ፡፡ ጠይባ የቆየች የከንፈር ወዳጁ ነበረች፡፡ ከሰሚራ ጋር አላህ እህል ውሃችሁ ይሁን ብሎ ባያገጣጥማቸው ከጠይባ ጋር እስከ ትዳር የሚዘልቅ ቁርኝት ነበራቸው፡፡
መሀመድ ሰሚራን አይቶ ባይለከፍ…ጠይባ ሁለት ባል አግብታና ትዳሯ ፈርሶ ለብቻዋ አትኖርም ነበር፡፡ እንድሪስ ከመሀመድ ጋር የመዳራቱን ሀሳብ ሲያቀርብላት ደስታዋ ወደር አልነበረውም፡፡ ፈፅሞ ባልገባት ምክንያት እንድሪስ ቆይ ዛሬ ነገ እያለ ቀኑን ገፋው እንጂ የመጠበቁ ትዕግስት አልነበራትም፡፡
“ምነው የደነገጥክ ትመስላለህሳ?”አለው እንድሪስ መሀመድን አተኩሮ እያየው፡፡
“እንዳው ጠይባ መሆኗ ጥቂት አስደመመኝይ…” አለ መሃመድ ሀፍረት አይሉት ግርምት በገጹ ላይ እየተመላለሰ፡፡
“እልቁንስ አሁኑኑ ተዘገጃጅ፣ ታጥባ ታጥና ቤቷ ትጠብቅሃለች፡፡ በእኩል ሰዓት ውስጥ ታልደረስክ ግና ውርድ ከራሴ…”አለ እንድሪስ
“ዛሬ?” አለ መሀመድ በድንጋጤ ተሞልቶ፡፡
“አይ ሙሄዋ አሁን ብሎ ነገ አለ እንዴ?... በል ተነስ ቤቷ ባሻገር ላሳይህ እና እንደፍጥርጥርህ…” ብሎ እንድሪስ ለመሄድ ተዘጋጀ፡፡
መሃመድም ልቡ እየነጠረም ተከተለው፡፡ እንድሪስ በበዓል ቀን በአካባቢያቸው የምትዘፈነዋን ዜማ እያፏጨ ነበር፡፡
የከንፈር ወዳጄ
የከንፈር ወዳጄ
ጎጆዬን ሳልቀልስ ብቅ በይ ከደጄ
የከንፈር ወዳጄ
የከንፈር ወዳጄ ጎጆዬንን ቀልሼ ሚሽት ታጨው ኋላ፣
ውል ውል ይለኛል ሁሌ ያንቺ ገላ፡፡
***
ሰሚራ ገላዋን ታጥባ ጨርሳ አደስ እየተቀባች ሳለ የውጪው በር ሲቆፈቆፍ ሰማች፡፡ እንደነገሩ ለባብሳ በሩን ስትከፍት እንድሪስ ከውጪ ቆሟል፡፡ትንፋሹ ቁርጥ ቁርጥ እያለ ለመናገር ተቸግሮ ለአፍታ አይኑን እንደተከለባት ቆየ፡፡ ከመቼውም ጊዜ በላይ አምራና ደምቃ ታየችው፡፡
“አንተ ሰው ደጋግሜ ነገርኩህ፡፡ እኔ ከባለቤቴ ውጪ እንዲች ብዬ አልሄድም አልኩህ፡፡ ምንድነው እሱ ሳይኖር እግሩን እየጠበክ የምትመጣ?ጓደኛው ነህ ብዬ ዝም ብል ነገሬም አልል ታልከኝ ሲመጣ ጉድህን አፍረጥርጬ እነግርልሀለው፡፡” አለች ሰሚራ የእንድሪስ ሁኔታ እያብሰከሰካት፡፡
“እኔ እኮ የማይገባኝ እሱ ያንቺን ገላ ሲፀየፍ እንደው ዝም ብለሽ…” አለና አውቆ ንግግሩን አንጠልጥሎ ተወው፡፡
እንደገመተው ሰሚራ ፊቷ ልውጥውጥ አለ
“እናሳ… ይኸው ሌላ ሴት ለምዶ …ድፍን ሁለት ወር ሙሉ ከጭኗ መሽጎ…” ሲያጠና የከረማቸውን ቃላት እንደ ክላሽ ጥይት አከታትሎ ተኮሳቸው፡፡
“እኔ አላምንም” አለች እጆቿን ወደ ላይ ከፍ አድርጋ፡፡
“ሌላ ሴት መልመዱን አላምንም ያልሺኝን ዛሬ በአይንሽ አይተሸ አረጋግጪ!” አላት
ሰሚራ ንዴት በሰራ አካላቷ ሲሰራጭ አይኗ በቁጣ ፈጠጠ፡፡ እንድሪስ እየመራት ተከትላው ወደ ጠይባ ቤት አመሩ፡፡ የጠይባ ቤት በር ገርበብ ብሏል እንጂ አልተዘጋም፡፡ እንድሪስ ወደ ውስጥ እንዲገቡ ለሰሚራ በምልክት ጠቆማት፡፡ ተከተለችው፡፡ ከውስጠኛው ክፍል በሲቃ የታሸ የወንድ እና የሴት ድምፅ ተሰማ፡፡
ሰሚራ ጆሮዋን አለማመን ፈለገች፡፡ የወንዱን ለብዙ ጊዜ ስለሰማችው ታውቀዋለች፡፡ ከላይዋ ሆኖ፣ በአካላቷ ውስጥ እየሰረገ፣ ሞቃት ወዝ ከፊቱ ላይ እየፈለቀ የሚሰማው ሲቃ -መሀመድ!!! ክህደቱን ከዚህ በላይ ልትሰማ ባትፈልግም እንድሪስ ወደ ውስጠኛው ክፍል እንዲገቡ የግድ አላት፡፡
የውስጠኛውን ክፍል በር እንድሪስ ገፋ ሲያደርገው ወለል ብሎ ተከፈተ፡፡ የጠይባ ጭኖች ሽቅብ በመሃመድ ሽንጥ ዙሪያ እንደእባብ ተጠምጥመዋል፡፡ ሰሚራ ጠይባን ከወለሉ ላይ ተንጋላ ስታያት፣ መሀመድ በጭኖቿ በኩል ጠርምሶ ለማለፍ ትግል እያደረገ ስታይ ንዴቷ እንደዛር ተናነቃት፤ ማጓራት መሬት መንደባለል አሰኛት፡፡ የጠይባ አይኖች ውስጥ ያየችው እርካታ ነው? በቀል ነው? በለጥኩሽ የማለት ስሜት ነው? ምን እንደሆነ እርግጠኛ አይደለችም፡፡ ትላንት ቀምታት ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ የመቀማቱ ተራ የእሷ ነው፡፡መሀመድ በእርካታ ጣራ ላይ ደርሶ የጠይባን ገላ መጭመቅ ሲጀምር፣ እንድሪስ ሰሚራን ወደ ፊት ገፋት፡፡
ከፊት ለፊት ገጭ አለች፡፡ ድንጋጤ እና የእርካታ ጡዘት ልቡን ስውር አደረጉት፡፡ ሰሚራ ሮጣ ወጣች፤ እንድሪስ ተከተላት፡፡ ለአመታት የተመኛት በፍቅር የቃተተላትን ሴት እስከወዲያኛው እንዳገኛት እርግጠኛ ነበር፡፡ ሰሚራን በፍጥነት ሲከተል ለጠንቋዩ ወረታ ምን እንደሚከፍል እያሰበ ነበር… ይቺን የመሰለች እንቁ ለሰጠኝ ጠንቋይ ህይወቴን ብሰጥስ? እስከማለት የሚያደርስ የውለታ ጫና ውስጥ ገብቶ… ወደ ሰሚራ… ወደ ውብ ገላዋ…

 

Read 8492 times Last modified on Saturday, 01 December 2012 14:00