Saturday, 08 December 2012 11:04

የጃፓን በጐ ፈቃደኞች 40ኛ ዓመታቸውን አከበሩ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

ኢትዮጵያና ጃፓን የበጐ ፈቃደኞች አገልግሎት (የጃፓን የባህር ማዶ በጐ ፈቃደኞች ትብብር) የተጀመረበት 40ኛ ዓመት ትናንት ተከበረ፡፡ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር፣ ሂሮዩኪ ኪሺኖ ባደረጉት ንግግር በ1964 ዓ.ም በሁለቱ አገሮች መካከል በተደረገው የትብብር ስምምነት መሠረት 25 ጃፓናውያን በጐ ፈቃደኞች የኢትዮጵያን ምድር መርገጣቸውን ጠቅሰው እስካሁን ድረስ 600 በጐ ፈቃደኞች በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በልማት ሥራ በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት 47 በጐ ፈቃደኞች በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች እየሠሩ መሆናቸውን የጠቀሱት አምባሳደሩ በሳይንስና በሂሳብ ትምህርቶች፣ በሰውነት ማጐልመሻ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በንፁህ ውሃ አያያዝ፣ በእርሻና በሌሎች ዘርፎችም ከአገሬው ሕዝብ ጋር ተቀራረብው እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በጐ ፈቃደኞቹ የተመደቡበትን አካባቢ ቋንቋ እየተናገሩ ከሕዝቡ ጋር ተመሳስለውና ሕዝቡ የሚበላውን እየበሉ ባህሉን እየኖሩ እውቀትና ልምዳቸውን እያካፈሉ 40 ዓመት መቆየታቸው የትብብሩን ስኬታማነት ያመለክታል ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት 50 በጐ ፈቃደኞች በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የሳይንስና ሂሳብ ትምህርቶች በማስተማር ህዝቡን በማገልገል ላይ መሆናቸውን የገለፁት የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፉአድ ኢብራሂም የሳይንስና የሂሳብ ትምህርቶችን ጥራት ለመሻሻል 13 በጐ ፈቃደኞች በአማራ፣ በኦሮሚያና በአዲስ አበባ ካሉ የ1ኛ ደረጃ መምህራን ጋር እየሠሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
የልብስ ስፌት ቱሪዝም፣ የገጠር ልማት በጐ ፈቃደኞቹ ከሚያስተምህረት በርካታ ትምህርቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው ያሉት አቶ ፉአድ፤ በየት/ቤቱ የቤተ ሙከራ ማዕከል እንደሚያቋቁሙ፣ በአካባቢው ከሚገኙ ቁሶች የቤተ - ሙከራ መሳሪያዎች እንደሚሠሩ፣ ንድፈ ሐሳብን በተግባር እንደሚሞክሩና ለመምህራንና ተማሪዎች በሰሚናር ትምህርት እንደሚሰጡ ገልፀዋል፡፡

Read 2472 times