Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 08 December 2012 11:09

የፖለቲካ ነገር፤ መጀመሪያ ዘርዛራ ወንፊት፤ ቀጥሎ ጠቅጣቃ ወንፊት በፍፃሜው መሹለኪያ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

የሌለው ድፍን ወንፊት ነው፡፡ ” ያገሬ ባላገር
ከሮበርት ዶድስሌይ ተረቶች አንዱ ይህን ይላል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን፤ አንድ ባህር-ዛፍና የወይን-ዛፍ ጎን ለጐን ይኖሩ ነበር ይባላል፡፡
ወይኑ፤ “የማንም ጥገኛ ሳልሆን ራሴን ችዬ በነፃነት እኖራለሁ፡፡ ስለዚህም አንተ ኖርክም አልኖርክም ምንም አትሠራልኝም” አለው ባህር ዛፉን፡፡
ባህር ዛፍም፤
“የወይን ተክል ሆይ! አንተ በተፈጥሮህ ቀጥ ያለና ወደሰማይ የማደግ ባህሪ የለህም፡፡ ዞሮ ዞሮ እንደማንኛውም የሐረግ ዘር በሌላ ጠንካራ ግንድ መደገፍ አለብህ” ሲል ነገረው፡፡

የወይን ዛፍ ግን፤ 
“አሳይሃለሁ እንዴት እንደማድግ!” ብሎ በመፎከር ያለ አንዳች ድጋፍ ከመሬት ጥቂት ከፍ ሲል ታየ፡፡ አንድ ሰሞን ጉድ! ተባለ፡፡ ቅርንጫፎቹ በዙ፡፡ ግራና ቀኝ ተንሰራፉ፡፡ ሰፋፊ ቅጠሎቹ በዙሪያው ተንዠረገጉ፡፡
“እህስ አያ ባህር ዛፍ! አስተዳደጌን አየህ?! ማንም ሳይደግፈኝ ራሴን ችዬ የማደግ ችሎታ እንዳለኝ አስተዋልክ?” ሲል በኩራት ጠየቀው፡፡
“ምስኪን የወይን - ዛፍ - ቁጥቋጦ ሆይ! እንደ ኔ ሸበላ ለመሆን ምን ያህል ዓመታት እንደሚያስፈልግህ ሳስብ ታሳዝነኛለህ፡፡ ዛሬ ቆመ ሲሉህ ነገ የምትሽመደመድ ጉንድሽ ፍጥረት ያለህ ፍጡር መሆንህን አትርሳ! ባህሪህ ዘላቂ አይደለም፡፡ በዕውነት ራስህን ችለህ ትቆማለህ? አይምሰልህ! ይልቁንም የጣፋጭ ፍሬዎችህን ጭማቂ በጥንቃቄ ግንድህን ለማወፈሪያ እና ለማጠንከሪያ ብትጠቀምበት መልካም ነበር፡፡ ነገ የሚረግፍ ቅርንጫፍና ቅጠል ከማብዛት ነዋሪ ግንድህን ብታጠነክር ይሻልሃል! ተራ ሜዳ ላይ በሚስፋፉ ቅጠሎች ተከበህ ባትኩራራ መልካም ነው! ከጥቂት ጊዜ በኋላ መሬት ላይ ስትንከባለልና ስትሳብ እንደማይህ እርግጠኛ ነኝ፡፡ አንተ፤ ልክ ባዶ ኪሱን ሆኖ በከንቱ ጉራ እንደሰከረና የሌሎቹን ኢኮኖሚ እንደሚንቅ፤ ራሱን ችሎ እንደሚኖር ያወራውን የጉራ ወሬ ያረጋገጠ እየመሰለው፤ ያለችውን ቅሪት ሜዳ ላይ እንደሚዘራ ሰው ነህ” አለው ይባላል፡፡
***
እንደ ወይኑ-ዛፍ ከመፎከር እንደ ባህር ዛፍ ረጅም መቆሚያን ማበጀት ይጠበቅብናል፡፡ የአዕምሮ ነፃነት፤ የተቋም ነፃነትም ሆነ ድርጅታዊ ነፃነት መላ ይፈልጋል፡፡ መላ የሌለው፣ ዕድሜ የለውም እንዲሉ! ባንድ ወገን ያለ ባህሪያችን ራሳችንን ችለን በነፃነት እንቆማለን ማለት ከንቱ ውዳሴ የሆነውን ያህል፤ በሌላ ወገን አበው እንደሚሉት “በአፍላ ጉልበታቸው ደብሩን ተክለው፣ ካህናትን ደልድለው፤ ሥራቱን አስተካክለው ያደራጁትን ሰዎች በአንድ ጀንበር ወግዱ ማለት እንዳይቻል እያወቃችሁ ስለምን ብልሃቱ ይጠፋችኋል?” ብሎ መጠያየቅ ዋና ነገር ነው፡፡
ጥያቄው፤ እንደማይክል አንጀሎ ጥበበኛ በመሆን ፍፁም ውስጣዊ ኃይል ቢኖረን ይሻላል (Intensive) ወይስ እንደ ኪሲንጀር ሁሉም ቦታ እጅን በማስገባትና አማካሪ በመሆን (Extensive እንዲሉ) ተፈላጊነት ማረጋገጥ (Indespensible) የሚለው ነው እንደየአገሩና እንደየዘመኑ አንዱ ወይም ሁለቱም ሊሠራ ይችላል፡፡
ማኪያ ቬሊ፤ ከመወደድ መፈራት ይሻላል ይላል፡፡ ፍርሃትን መቆጣጠር ይቻላል፤ ፍቅርን ግን በፍፁም! (Fear you can Control. Love, never.) ሌሎች እናጣሃለን ብለው በመፍራት ባንተ ቢመኩ እንጂ ወደውህ ወዳጅ ማድረጋቸውን/አጋርህ መሆናቸውን/አታፍቅር ነው ነገሩ! ዞሮ ዞሮ ምርጫው የራሳችን ነው - ወፍ እንደ አገሩ ይዘፍናል ነውና፡፡ አንድም፤ አገሬን በጣም እወዳታለሁ ማለትን በማብዛት እናቅፋታለን ብለን እንዳናንቃት እንጠንቀቅ እንደማለትም ነው፡፡
አገራችን የተያያዘችው ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ውጣ-ውረድ ውስጥ፤ የፖለቲካ ሥልጣኑ ማህፈድ (Political Tower) አናት ላይ መገኘት ወይስ ግንድን ማጠንከር? ብሎ ራስን መጠየቅ ደግ ነው፡፡ “ቁልቋል የወደቀው ቅርንጫፍ ካበዛ በኋላ ነው” የሚለውን የትግሪኛ ተረት አንርሳ!
እንደዕለት ፀሎት የማንዘነጋውን የሙስና ጉዳይ እናውጋ፡፡ “አታላይ ሰው አያሌ የሚያታልላቸው ሰዎች የሚያገኘው የሰው ልጅ በጊዜያዊ ጥቅሙ ተገዢ ስለሆነና አዕምሮውም የተወሳሰበ ስላልሆነ ነው” (ማክያቬሊ)፡፡ የሰው ልጅ ለሙስናና በሥልጣን ለመባለግ ቅርብ መሆኑን ሲነግረን ነው! በየዓይነቱ ሌብነትና ዘረፋ እንዳለ ቢታወቅም የሙስና ዶቃ የለውም፡፡ አዘለም አንጠለጠለም ያው ተሸከመ ነው - ቀልቀሎ ስልቻ፣ ስልቻ ቀልቀሎ፤ ነው!
“በሉ እኔ ልሰናበት ምቀኛዬ መጣ!” ይላል የባህር ዳር አዝማሪ፤ ሌላ አዝማሪ ሲተካው፡፡ ቃሉን በቁሙ ከወሰድነው መተካካት አሉታዊ ጎንም አለው እንደማለት ነው፡፡ ቀና ቀናውን ያሳየንና ሂያጁም መጪውም በፍቅርና በዕድገት አኳያ ይተያዩ ዘንድ ተግተን እንፀልይ፡፡ ራዕይ ቅን ልቡና ይፈልጋልና “ልብና ልቦና ይስጠን” ብለን እናሳርግ እንደሰባኪው ካህን!
አገራችን “ልጓም የሚጠብቀውን፣ ሜዳ የማይበቃውን ጮሌ ሠንጋ ፈረስ እንደ እንዝርት የሚያሾር ምርጥ ፈረሰኛ - መሪ፣ ምርጥ ኃላፊ፣ ምርጥ ባለሙያ፣ ምርጥ ካህን ወዘተ ትሻለች፡፡ አዲሱ አሮጌውን በሚተካበት ሂደት፤ ጉዳይ የሥልጣን - ሽግሽግ - ተኮር ሳይሆን ምርጥ አመራር የመፍጠር መሆን ይኖርበታል፡፡ አህያይቱን የመከራት ውሻ “ተይ ወይዘሮ አህያ አታናፊ:- የፊተኛው መቀስቀሺያ፣ ሁለተኛው መቅረቢያ፣ ይሄኛው መበያ ነው” እንዳለው ቀና አመራር ከዚህ ነፃ መሆን ይገባዋል፡፡ አለበለዚያ የዲሞክራሲም፣ የፍትሕም፣ የልማትም፣ የመልካም አስተዳደርም ተስፋ ያገሬ ባላገር አለ እንደሚባለው፡- “የፖለቲካ ነገር፣ መጀመሪያ ዘርዛራ ወንፊት፣ ቀጥሎ ጠቅጣቃ ወንፊት፣ በፍፃሜው መሹለኪያ የሌለው ድፍን ወንፊት” እንዳይሆን መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡

Read 5812 times