Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 08 December 2012 11:06

በ5 እጥፍ ይጨምራል የተባለው የስኳር ምርት አልቀመስ ብሏል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ዘንድሮ ወደ 2 ቢሊዮን ብር የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገኝ ታቅዶ ነበር
ግን በተቃራኒው ያንን በሚያክል የውጭ ምንዛሬ ከውጭ ማስመጣት የግድ ነው
መንግስት ቢዝነስ ውስጥ ገብቶ አገሪቱን ልማት በልማት ሲያደርጋት ለማየት የሚፈልጉ ሰዎች ጥቂት አይደሉም። ደግሞም ፍላጎታቸውን ለማሟላት ቃል የሚገባ መንግስት አያጡም። በእውን፣ በተጨባጭ ወይም በተግባር ፍላጎታቸውን የሚያረካ ነገር ለማየት ባይታደሉም፤ ቢያንስ ቢያንስ በምኞት ደረጃ የልብ የሚያደርስ እቅድ በሽ በሽ ነው። ልማታዊ መንግስት እቅዶች ያንሱታል ተብሎ አይታማም። በየአቅጣጫው የሚፈበረኩ እቅዶችን ትተን፤ የስኳርን ምርት በብዙ እጥፍ ለማሳደግ የወጡ እቅዶች ብቻ ብናይ እንኳ ያስጎመጃሉ።

ለምሳሌ በ1997 የወጣው የአምስት አመት እቅድ፤ የአገሪቱ የስኳር ምርት በአምስት እጥፍ እንደሚጨምር የሚገልፅ ነው። በወቅቱ ሶስት ሚሊዮን ኩንታል የነበረው አመታዊ የስኳር ምርት በፈጣን እድገት በ2002 ዓ.ም ወደ 15 ሚሊዮን ኩንታል እንደሚደርስ የያኔው እቅድ ያብራራል። ያጓጓል አይደል? መቼም መንግስት ቢዝነስ ውስጥ ሲገባ፣ እቅዶች አይሳኩም። የመንግስት ጉድለት፣ የፓርቲ ድክመት ወይም የባለስልጣናት ስንፍና አይደለም ችግሩ። በቃ፤ የትም አገር የትኛውም ፓርቲ ስልጣን ቢይዝ፣ ማናቸውም ባለስልጣን ቢሾም አልያም አንዱ ተሽሮ በሌላው ቢተካ ለውጥ የለውም። የመንግስት ቢዝነስ ውሎ አድሮ ከትርፉ ይልቅ ኪሳራው ይበዛል፤ እቅዶቹ ሃብት እያባከኑ ይጓተታሉ፤ ምኞት ብቻ ሆነው ይቀራሉ። 
የስኳር ምርት በአምስት እጥፍ ለማሳደግ የወጣው እቅድ ግን ምኞት ብቻ ሆኖ እንደማይቀር፣ ከአመት በኋላ በ1998 ዓ.ም የወጣው የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ያበስራል። በፊንጫ፣ በወንጂና በመተሃራ የስኳር ፋብሪካዎች ላይ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆናቸውን ይጠቅሳል፤ በተንዳሆም አዲስ የስኳር ፕሮጀክት እየተፋጠነ እንደሆነ ያወሳል። የገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ባሳተመው ባለ 108 ገፅ አመታዊ የአፈፃፀም ሪፖርት ገፅ 79-81 ይመልከቱ (PASDEP Annual progress report 2005-2006)።
በወንጂ፣ ነባሩን መሬት የማሻሻልና አዲስ ከ3ሺ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ስራ እንደተጀመረ የሚያበስረው ይሄው ሪፖርት፤ አሮጌውን ፋብሪካ በአዲስ ተተክቶ አመታዊ ምርቱን ከሰባት መቶ ሺ ኩንታል ወደ 2.8 ሚሊዮን ኩንታል እንደሚደርስ ይገልፃል።
በፊንጫ 800ሺ ኩንታል አመታዊ ምርቱን ወደ 2.7 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ መታቀዱንና የፋብሪካ ተከላ ጨረታ መዘጋጀቱን ሪፖርቱ ጠቅሶ ከ12ሺ ሄክታር በላይ የመሬት ልማት እንደሚካሄድ ይዘረዝራል።
በመተሃራም እንዲሁ፣ የከሰም ግድብ ሲጠናቀቅ ከ12 ሺ በላይ ሄክታር በማልማት፤ እንዲሁም የፋብሪካው አቅም ላይ ሁለት እጥፍ በመጨመር ምርቱን ከ1.2 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 3.75 ሚሊዮን ኩንታል ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ሪፖርቱ ያወሳል።
በ1999 ዓ.ም አንድ ሚሊዮን ኩንታል ስኳር በማምረት ስራ እንዲጀምር በታሰበው አዲሱ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ፣ የ22ሺ ሄክታር ልማት እንደተጀመረና በ2002 ዓ.ም የፋብሪካው አመታዊ ምርት 6 ሚሊዮን ኩንታል እንደሚደርስ ይጠቁማል።

እንግዲህ በእነዚህ የማስፋፊያ እና የአዲስ ፋብሪካ ፕሮጀክቶች ነው የአገሪቱ የስኳር ምርት ከሶስት ሚሊዮን ኩንታል ተነስቶ በ2002 ዓ.ም ወደ 15 ሚሊዮን ኩንታል ይደርሳል ተብሎ በ1997 ዓ.ም እቅድ የወጣው። በ1998 ዓ.ም የአፈፃፀም ሪፖርትም፣ እቅዱ በትክክል እየተተገበረ እንደሆነ ያብራራል።

በ1999 ዓ.ም የወጣው የአፈፃፀም ሪፖርት ላይ የምናገኘው ጠቅላላ ገለፃ ተመሳሳይ ነው፣ ግን ትንሽ የቁጥር ለውጥ ተደርጓል። በ2002 ዓ.ም የአገሪቱ የስኳር ምርት 15 ሚሊዮን ሳይሆን፣ 12 ሚሊዮን ኩንታል ይደርሳል ሲል የቀድሞውን እቅድ በመቀለስ አቅርቦታል (PASDEP Annual progress report 2006-2007 ገፅ 91)። እቅዱ ለምን ተከለሰ ቢባል፣ በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። ለምሳሌ፤ የተንዳሆ እና የከሰም ግድቦች እንደታሰበው ሳይጠናቀቁ ቀሩ (በነገራችን ላይ አሁንም ድረስ ሙሉ ለሙሉ አልተጠናቀቁም)። የሽንጎራ አገዳ ልማቱም ያለ ውኃ ሊከናወን አይችልም። ለነገሩ የፋብሪካ ግንባታውም ሳይጀመር ቀርቷል። ስለዚህ ቀደም ብሎ የወጣውን እቅድ መከለስና በአንድ አመት ማሸጋሸግ አስፈለገ።
ቢሆንም ስራዎቹ በሙሉ ስለተጀመሩ፣ እቅዱ ከአንድ አመት በላይ እንደማይጓተት የ1999 ዓ.ም የአፈፃፀም ሪፖርቱ ያስረዳል። በ2002 ዓ.ም የአገሪቱ ምርት 12 ሚሊዮን ኩንታል ይደርሳል የተባለውም በዚህ ምክንያት ነው። ይሄ እንግዲህ የመጀመሪያው ክለሳ ነው። ግን ይህም የሚሳካ አልሆነም። ግድቦቹ፣ የሽንኮራ አገዳ ተከላው፣ የፋብሪካ ግንባታው በሙሉ እንደታሰበው በጊዜ አልተጠናቀቁም። አንዱም አልተሳካም። ስለዚህ እንደገና እቅዱ ተከለሰና በአንድ ተጨማሪ አመት ተሸጋሸገ። የስኳር ልማት ኤጀንሲ የ2000 ዓ.ም ሪፖርት መመልከት ይቻላል። የአገሪቱ የስኳር ምርት 12 ሚሊዮን ኩንታል የሚደርሰው በ2004 ዓ.ም ነው ተባለ።
እንዲህ ሁለቴ የተከለሰው የ2000 ዓ.ም እቅድም ቢሆን እንደታሰበው እንደማይሳካ ወዲያውኑ ግልፅ እየሆነ መጣ። የተንዳሆ ግድብና የሽንኮራ አገዳ ልማት “በዚህ አመት ይጠናቀቃል” እየተባለ 2002 ዓ.ም አለፈ። ለመተሃራ ስኳር ፋብሪካ ማስፋፊያ ታስቦ የነበረው የከሰም ግድብና የአገዳ ልማት ደግሞ የባሰ ነው። ድምፁ ጠፋ ማለት ይቻላል።
እቅዱ እንደገና ለሶስተኛ ጊዜ ተከለሰ። በ2002 ዓ.ም የወጣው የአምስት አመት እድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ፤ ያልተጠናቀቁትን ጅምር ፕሮጀክቶች በመከለስና ተጨማሪ ፕሮጀክቶችን በማካተት አዲስ እቅድ አቀረበ። በዚሁ እቅድ መሰረት፤ የአገሪቱ የስኳር ምርት 12 ሚሊዮን የሚደርሰው በ2006 ዓ.ም ነው ተብሎ ለተጨማሪ ሁለት አመታት እንዲሸጋሸግ አደረገ። ግን ክለሻ የተደራረበት የስኳር ምርት እቅድ አሁንም አልተሳካም።
“2006 ዓ.ም ገና ሳይደርስ እንዴት እቅዱ አልተሳካም ትላለህ?” የሚል ጥያቄ ልታነሱ እንደምትችሉ ይገባኛል። ለነገሩ፤ እቅዱ በተያዘለት ጊዜ ለማስኬድ ጥረት እየተደረገ ነው እየተባለ ሲነገር በተደጋጋሚ እንሰማለን።
ለምሳሌ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል “ኮርፖሬሽኑ የስኳር ልማቱን ለማፋጠን የሚያስችሉ ስራዎች ማከናወኑን ገለጸ” በሚል ርዕስ በጥቅምት 12 ቀን ያሰራጨው ዜና መጥቀስ ይቻላል። የስኳር ኮርፖሬሽን አንድ የስራ ሃላፊ፣ “በአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ የተካተቱት የነባር ስኳር ፋብሪካዎች ማስፋፊያና የአዳዲስ ፋብሪካዎች ግንባታ በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል” በማለት አስፍሯል። እስቲ የጊዜ ሰሌዳዎቹን እንያቸው።
በ97 ዓ.ም በወጣው እቅድ መሰረት
የአገሪቱ አመታዊ የስኳር ምርት በ2000 ዓ.ም ከሰባት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ይሆናል፤ በ2002 ደግሞ አመታዊው ምርት 15 ሚሊዮን ኩንታል ይደርሳል ተባለ።
በ1999 ዓ.ም በተከለሰው እቅድ መሰረት
የአገሪቱ አመታዊ የስኳር ምርት በ2001 ዓ.ም ከሰባት ሚሊዮን በላይ እንደሚሆን፤ በ2002 ዓ.ም ደግሞ 12 ሚሊዮን ኩንታል ገደማ ምርት እንደሚገኝ ተገለፀ።
በ2000 ዓ.ም በተከለሰው እቅድ መሰረት
የአገሪቱ አመታዊ የስኳር ምርት በ2002 ዓ.ም ሰባት ሚሊዮን እንደሚሆን እና በ2004 ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚገኝ ተነገረ።
በ2002 ዓ.ም በወጣው የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ መሰረት
የአገሪቱ አመታዊ የስኳር ምርት በ2004 ዓ.ም ሰባት ሚሊየን ኩንታል እንደሚደርስ፣ ከዚያም በ2006 ዓ.ም ከ12 ሚ. ኩንታል በላይ ስኳር እንደሚመረት ተበሰረ።
እንግዲህ አስቡት፤ እስካሁን የአገሪቱ አመታዊ የስኳር ምርት ከተለመደው 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ብዙም ፈቅ አላለም። ይልቅስ ወደ ላይ ሳይሆን ወደ ታች ሲወርድ፣ ከአመት አመት ምርት ሲቀንስ ነው የምናየው። በእድገትና በትራንስፎርሜሽን እቅድ መሰረት፤ በ2004 ዓ.ም የአገሪቱ የስኳር ምርት ሰባት ሚሊዮን ኩንታል ሊደርስ ይቅርና እንደወትሮው ሶስት ሚሊዮን አጠገብ ለመቆየትም አልቻለም። የአምናው ምርት ካለፉት አመታት በእጅጉ ያንሳል። 2.6 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ ነው የተመረተው (የስኳር ልማት ኮርፖሬሽን ዌብሳይት www.ethsugar.gov.et)።
የዘንድሮው ምርት ደግሞ ካለፈው አመትም የባሰ እንዳይሆን ያሰጋል። በ97 ዓ.ም የወጣው እቅድ እውን ለመሆን ቢበቃ ኖሮማ የዘንድሮው ምርት ከ15 ሚሊዮን በላይ ይሆን ነበር። ያ ሳይሳካ አልፏል። ቢያንስ ቢያንስ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የጊዜ ሰሌዳው ጠብቆ ቢከናወን ኖሮ፤ የዘንድሮው ምርት 10 ሚሊዮን ኩንታል ገደማ ይሆን ነበር። ግን ጨርሶ ሊሳካ አይችልም። የዘንድሮ ምርት ከአምናውም ያነሰ ሊሆን እንደሚችል ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት። ለምን ቢባል...
ከስድስት አመታት በፊት ሥራ ይጀምራሉ ተብለው የነበሩ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶችና አዳዲስ ፋብሪካዎች፤ እንደተለመደው ዘንድሮም በአብዛኛው ወደ ሥራ መግባት አይችሉም። ከአመት አመት እየተጓተተ፣ ሁሌም “አሁን ማምረት ይጀምራል” እየተባለ አመታትን ያስቆጠረው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ፤ ዘንድሮም ሥራ አይጀምርም።
የመተሃራ ማስፋፊያ ተብሎ እቅድ ወጥቶለት የነበረው የከሠም ግድብ ገና አልተጠናቀቀም፤ ፋብሪካውም ገና አልተጀመረም።
በእርግጥ፣ የፊንጫና የወንጂ የማስፋፊያ እቅዶች ለአመታት ቢጓተቱም ከሌሎቹ ፕሮጀክቶች ጋር ሲነፃፀሩ ሻል ይላሉ። ለዚህም ነው አምና በጥቅምት እና በመጋቢት ወር ላይ ምርት እንደሚጀምሩ በስፋት ሲነገርላቸው የነበረው። ግን እንደገና ግንባታቸው ስለተጓተተ፣ እቅዳቸው እንደገና ወደ ዘንድሮ ተሸጋግሮ፤ ዘንድሮ ጥቅምት ወር ላይ ወደ ምርት እንደሚሸጋገሩ በተደጋጋሚ ተነግሮላቸው ነበር። እንዲያውም፤ ከነባሮቹ የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ሁለት ክፍሎች መካከል አንደኛው ከወዲሁ ስራ እንዲያቆም ተደርጓል - በአዲሱ ፋብሪካ ይተካል ተብሎ።
አዲሱ የወንጂ ፋብሪካ ግን እንደታሰበው በጥቅምት ስራ አልጀመረም። ወደ ጥር ወር ተራዝሟል ተባለ። ግን ምን ዋጋ አለው? ለጥር የተያዘው እቅድም እንደማይሳካ ምንጮች ጠቁመዋል። አሳዛኙ ነገር፤ የነባሩ ፋብሪካ አንድ ክፍል ተዘግቷል። ገና ያልተዘጋው የነባሩ ፋብሪካ ሁለተኛ ክፍል ደግሞ፤ አንድ ቀን ዝናብ ከዘነበ ምርቱ ይስተጓጎላል - አካባቢው በቀላሉ ስለሚጨቀይ። በሌላ አነጋገር፤ ዘንድሮ የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ምርት ካለፉት አመታትም በእጅጉ ያነሰ ይሆናል።
ትንሽ ተስፋ ያለው የፊንጫ ነው። ነገር ግን እሱም የሌሎቹን ጉድለት ይሸፍናል ተብሎ አይገመትም። በአጠቃላይ ሲታይ፤ አስር ሚሊዮን ኩንታል ይመረትበታል በተብሎ እቅድ በወጣለት 2005 ዓ.ም፤ የአገሪቱ የስኳር ምርት ካለፉት አመታት በታችና ከ3 ሚሊዮን ኩንታል በጣም ያነሰ ሊሆን ይችላል።

Read 5461 times