Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 08 December 2012 11:10

አንድም ሰው በኤችአይቪ እንዳይያዝ ኃላፊነታችንን እንወጣ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ኤችአይቪ ቫይረስ እ.ኤ.አ በ1981 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በአሜሪካ አገር መኖሩ ከታወቀ ጀምሮ በዓለም ላይ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሰለባ አድርጐአል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአለማችን 34 ሚሊዮን ሰዎች ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሲሆን በሽታው እ.ኤ.አ በ2001 ዓ.ም ብቻ 1.7 ሚሊዮን ሰዎችን ለሕልፈት ዳርጓል፡፡ በሀገራችን የቫይረሱ መኖር ከታወቀበት እ.ኤ.አ 1984 ዓ.ም ጀምሮ የበሽታው ስርጭት ቀለም፣ እድሜ፣ ጾታ፣ ሃይማኖት፣ የትምህርት ደረጃ ወዘተ ልዩነት ሳያደርግ ከሕብረተሰባችን አበይት የጤና ችግሮች ወስጥ አንዱ ሊሆን በቅቷል፡፡ በዚህም ምክንየት መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶት የተለያዩ የመቆጣጠር እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ እንደነበር ይታወቃል፡፡ 

ዩኤንአይዲ 2012 ዘገባ መሠረት፤ በዓለም ላይ የፀረ ኤችአይቪ/ኤድስ መድሃኒቶች ስርጭትና ጥቅም ላይ መዋል ተጠናክሮ መቀጠሉ ከኤችአይቪ/ኤድስ ጋር በተያያዙ በሽታዎች የሚሞቱትን ሕመማን ቁጥር ለመቀነስ አስችሏል፡፡
በሪፖርቱ መሠረት በከፍተኛ ሁኔታ የሕሙማንን ሞት ቁጥር ለመቀነስ ከቻሉት ሀገራት ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ነች፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ባደረገችው ጥረት፣ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ አስችሏታል፡፡ ለምሳሌ ያህል እ.ኤ.አ 2007 ዓ.ም በሀገሪቱ የቫይረሱ ስርጭት ከአጠቃላይ የሕዝብ ብዛት 2.1%የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን ወደ 1.5% ወርዷል፡፡
እነዚህንና መሰል ተመሳሳይ አበረታች ውጤቶች በሀገራችንም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመዘገቡ ቢሆንም አሁንም ክፍተት በሚታይባቸው ቦታዎች ላይ ጠንክሮ መስራት ይገባል፡፡
ለዚህም ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በቫይረሱ መተላለፊያ መንገዶች ላይ የተደረጉ ጥናቶች (Survey) በሕብረተሰባችን ውስጥ አሁንም ቢሆን የተዛቡ አስተሳሰቦች በስፋት መኖራቸው ማረጋገጡ ነው፡፡ በዚህ ጥናት ውስጥ ከተሳተፉ ሰዎች 48% ሴቶችና 37% ወንዶች ቫይረሱ በወባ ትንኝ እንደሚተላለፍ ያምናሉ፡፡
ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ24 ጊዜ የሚከበረው የዓለም የኤድስ ቀን በሀገራችን ሕዳር 22 ቀን ይከበራል፡፡ መሪ መፈክሩም “አንድም ሰው በኤችአይቪ እንዳይያዝ ኃላፊነታችንን እንወጣ” (GETTING TO ZERO) መሆኑ ታውቋል፡፡
ኤችአይቪ የሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ችግር ሲሆን በቫይረሱ ተጠቂ ከሆኑ የሕብረተሰባችን ክፍሎች ውስጥ ሕጻናት ይገኙበታል፡፡ ሕጻናት ቫይረሱ የሚተላለፍባቸው ከወላጆቻቸው ነው፡፡ የእነዚህ ሕጻናት ወላጆች የቅድመ ወሊድ ሕክምና አገልግሎት ቢጠቀሙ ኖሮ፣ አብዛኞቹ ሕጻናት ከቫይረሱ ነጻ ሆነው በተወለዱ ነበር፡፡
ኤችአይቪ ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፈው በሶስት መንገዶች ነው፡፡ እነዚህም በእርግዝና ወቅት፣ በምጥ ወይም በወሊድ ወቅትና ጡት በማጥባት ወቅት ናቸው፡፡
በእነዚህ አጋጣሚዎች በሽታው ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ለመከላከል በጤና ተቋም የቅድመወሊድ ሕክምና ማድረግና በጤና ተቋም መውለድ ወሳኝ ነው፡፡ ወላጆች የቅድመ ወሊድ ክትትል ማድረጋቸው የእናትንና የልጃቸውን ጤንነት ለመጠበቅ ማድረግ ከሚገባቸው ነገሮች አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ይህን ሕክምና ማግኘት ለወላጆች ከሚያስገኘው ጥቅሞች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
በሽታው ካለባቸው ማድረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች እንዲያውቁ ቫይረሱ ወደ ልጁ የመተላለፍ እድሉን ለመቀነስና ጤናማ ኑሮ ለመምራት የሚያስችላቸውን እርምጃዎች እንዲወስዱ ያግዛቸዋል፡፡
የእናቲቱንና የሚወለደውን ልጅ ጤና ለመጠበቅ የሚረዱ አገልግሎቶችን በሙሉ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል፡፡ ከነዚህ አገልግሎቶች መካከል ኤችአይቪ ቫይረስን ጨምሮ ሌሎች ከእናት ወደ ልጅ ሊተላለፉ የሚችሉ የአባላዘር በሽታዎች ምርመራና ሕክምና ተጠቃሽ ነው፡፡
ወላጆች በእርግዝና፣ በወሊድና ከወሊድ በኋላ ማድረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች እንዲያውቁ ያስችላቸዋል፡፡
በጤና ተቋም መውለድ ያለውን ጥቅም አውቀው በወሊድ ጊዜ ከሚፈጠሩ ማናቸውም ችግሮች ለመከላከል የባለሙያ እገዛ እንዲያገኙ ያግዛቸዋል፡፡
ከወሊድ በኋላ መወሰድ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎችና ትክክለኛውን የሕፃናት አመጋገብ ሥርዓት እንዲያውቁ ይረዳቸዋል፡፡
በእርግዝና ወቅት ወደ ጤና ተቋም በመሄድ አጠቃላይ የቅድመውሊድ ሕክምና ክትትል ማድረግ ጤናማ ልጅ ለመውለድ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህ ረገድ አባቶችም የራሳቸው ድርሻ አላቸው፡፡ አባቶች የትዳር አጋራቸውንና የአዲሱ ልጃቸውን ጤና ለመጠበቅ፣
የትዳር አጋራቸውን በቤት ውስጥ ሥራዎች ማገዝ፣
የትዳር አጋራቸው ተገቢውን የቅድመ ወሊድ ክትትል እንድታደርግና በጤና ተቋም እንድትወልድ ማበረታታት፣ አብሮ ወደጤና ተቋም በመሄድም ተገቢውን እገዛ ማድረግ፣
ልጃቸው ከተወለደ በተወለደ በኋላ ባለቤታቸውም ሆነ ሕፃኑ ተገቢውን የድህረ ወሊድ ክትትል ማግኘታቸውንና ለሕፃኑ ትክክለኛውን የአመጋገብ ሥርዓት መከታተላቸውን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡
በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን የቅድመ ወሊድ ሕክምና ትክክል አግኝተው የሚወልዱ ሴቶች 43% ብቻ ናቸው፡፡ ይህ የጤና ሽፋን ከጥቂት ዓመታት በፊት ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲተያይ ከፍተኛ መሻሻል ታይቶበታል፡፡ ሆኖም ዛሬም በኢትዮጵያ ውስጥ ህብረተሰቡ ለቅድመ ወሊድ ሕክምና እና በጤና ተቋማት ውስጥ ለመውለድ ያለው ፍላጐት በጣም አነስተኛ ነው፡፡
ለምሳሌ በሀገራችን ከ61% በላይ የሚሆኑ ሴቶች ለሕክምና ተቋማት ውስጥ መውለድ አስፈላጊ መስሎ እንደማይታያቸው (EDHS 2011) ሪፖርት ያሳያል፡፡
አንድም ሰው በኤችአይቪ እንዳይያዝ ኃላፊነታችንን እንወጣ ስንል እንግዲህ ለመጀመሪያ ይህንን ሰፊ የግንዛቤ ጉድለት በማስተካከል መሆን አለበት ማለት ነው፡፡ ይህም የማንም ኃላፊነት አይደለም፡፡……………..የሁላችንም እንጂ፡፡


Read 4640 times