Saturday, 08 December 2012 13:16

የኬፕታውን የባቡርካፌ

Written by  ኤልሣቤት እቁባይ
Rate this item
(1 Vote)

የደቡብ አፍሪካ መንግስት የአገሬው ነዋሪ ካልሆኑ ሰዎች ታክስ በግድ አይወስድም፡፡ ደቡብ አፍሪካ ገብተው ዕቃ ገዝተው ደረሰኝ መሰብሰብ እና ወደ አገርዎ ሲመለሱ ደረሰኙን፣ የገዙትን እቃ እና ፓስፖርትዋን በማሳየት ታክስ ተብሎ እቃ ሲገዙ የተወሰደበትን ገንዘብ ማስመለስ ይችላሉ፡፡ ኬፕታውን የጆሀንስበርግን ያህል ባይሆኑም ኢትዮጵያውያኖች ይኖሩባታል፡፡ በከተማዋ እምብርትም ኪንግስ ኢን ኬፕ እና አዲስ ኢን ኬፕ የተባሉ የኢትዮጵያ ሆቴሎች ይገኛሉ፡፡ ኬፕታውን የሸንቃጦች ከተማ ናት፡፡ ወፍራሞች አይመቿትም፡፡

አብዛኛው ነዋሪዋ ሸንቃጣ ነው፡፡ ለሰውነታቸው ውበት የሚጨነቁ የሰውነታቸው ቅርፅ ዝንፍ እንዲል የማይፈልጉ አይነቶች የተሰባሰቡባት ከተማ ናት፡፡ ብዙው ሰው በቁምጣና በቲሸርት ውር ውር የሚልባት ኬፕታውን፣ለአካል ብቃት ትልቅ ትኩረት ትሰጣለች፡፡ ክረምት መጥቶ እንዴት እንደሚለብሱ ሳላይ ብመለስም፣ኬፕታውነኞች የፀሐዩን ወቅት እጅግ እንደሚናፍቁት መገመት አያስቸግርም፡፡ ሌላው ያንገበገበኝ ጉዳይ ደግሞ ከአዲስ አበባ ህንፃዎችና የብሎኬት ድርድሮች፣ ወይም ደግሞ ተመሳሳይ አብረቅራቂ መስታወቶች ዞር ማለት ቢፈለግ የትም የምንሄድበት አለመኖሩ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህፃናትና አረጋውያን እንዲሁም በመካከለኛ እድሜ ላይ ያሉ ሰዎች የት ይሆን  የሚንሸራሸሩት? የኬፕታውን ፓርኮች እጅግ ያስቀናሉ፡፡ አጥር የላቸው፣ እንደኛ አገር ማለፍ ክልክል ነው አይሉም፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምን ይል ይሆን? ኬፕታውን  ውስጥ ካየኋቸው እና እጅግ ከቀናሁባቸው ነገሮች አንዱ የባቡሩ ካፌ ነው፡፡ አፄ ምኒሊክ ያስገቡት የመጀመሪያው ባቡር የት ይሆን? ከኦሎምፒያ ወደ መስቀል ፍላወር በሚወስደው መንገድ ላይ አንዳንድ የባቡሩ ፉርጐዎች ወደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያነት ተለውጠዋል፡፡ አሮጌዋ የኬፕታውን ባቡር ግን ካፌ ሆና ታዝናናለች፡፡ ለነገሩ ዋናው ማሰብ ነው እንጂ አሁንም ቢሆን ገና አልረፈደም፡፡ Atlantic Express Cake and Coffee Train  በኬፕታውን ሲፖይንት ተብሎ በሚጠራ  አካባቢ የሚገኝ የባቡር ካፌ ሲሆን ቀላል ምግቦች እና ትኩስ መጠጦች ይሸጡበታል፡፡ ይሄ የድሮ ባቡር የትራንስፖርት አገልግሎቱን ጨርሶ ጡረታ ሲወጣ ወደ ካፌነት ተለውጧል፡፡ በእግርም ሆነ በመኪና ሲጓዙ ቆይተው ባቡር ውስጥ ገብተው ቡና መጠጣት እንዴት እንደሚያዝናና አልነግራችሁም፡፡የሮቢን አይላንድን ለመጐብኘት ያደረግሁት ሙከራ ሁለት ጊዜ በመጥፎ አየር ምክንያት ቢስተጓጐልም ከሩቁ አይቼዋለሁ፡፡ በነገራችን ላይ እኔ ደቡብ አፍሪካ በገባሁ ማግስት የሮቢን አይላንድ ግዞተኛ የነበረው ማንዴላ ምስል በአገሪቱ የመቶ ብር ኖት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ታትሞ በስርጭት ላይ ውሏል፡፡ በነገራችን ላይ ስለቤት አሰራር እና አኗኗር የተፃፈበት ቦታ ላይ አሠራሩም ሆነ አገልግሎቱ ከኛዎቹ አፋሮች ጋር ምንም አይነት ልዩነት የሌለው ተንቀሳቃሽ ቤት አሠራር እንደነበራቸው ያስረዳል፡፡ እኛ አገር እዚሁ አፋር ክልል ላይ የተንሰራፋው ፕሮሰፒስ የተባለውን አይነት ዛፍም አስመልክቶ፣ ከአገር በቀሎቹ ዝርያዎች ጐን ለጐን ስለዛፉ አይነት፣ ስለ ጥቅሙ እና ስለጉዳቱ በመተንተን እንዴት ጥቅም ላይ እየዋለ እንደሆነ ያስረዳል፡፡  በስፖርት የዳበረ እና እጅግ የሚያምር ሰውነት ያላቸው ሰዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች መስሪያ ማሽን ላይ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ፣ ለህፃናት በተሠሩ መጫወቻዎች  ላይ ህፃናት ሲጫወቱ እንዲሁም ጎልማሶች ሲያነቡ ይታያል፡፡ የውቅያኖሱን የእንቅስቃሴ ትርኢት እየኮመኮሙ ዘና ብሎ መመለስ የኬፕታውያኖች የዕለት ተዕለት የሚያስቀና የህወት ዘይቤ ነው፡፡ በአቅራቢያው ባለ ትምህርት ቤት በኩል ደግሞ ሠፊ ፓርክ አለ፡፡ ፓርኩ የተለያዩ የህፃናት መጫወቻዎችን፣ ለአዋቂዎች የሚሆን የስፖርት እንቅስቃሴ መሳሪያዎች እና በአገሪቱ ስለሚገኙ የዛፍ አይነቶች የሚያስረዱ አጫጭር ጽሑፎች ያገኛሉ፡፡ የአትላንቲክ ውቅያኖስ የኬፕታውን አይን ሲሆን ከጠዋት እስከ ማታ በእንቅስቃሴ የተሞላ ነው፡፡ ኬፕታውን እጅግ ውብ ከተማ ናት፡፡ የአትላንቲክ ውቅያኖስ እና ሜዲትራኒያን የሚገናኙበት ኬፕ ፖይንት፣ እንዲሁም የነፃነት ታጋዩ ማንዴላ የታሠሩባት ሮቢን አይላንድ ዋና ዋና ፈርጦቿ ሲሆኑ የአገሪቱ የቱሪስት መዳረሻ የሆነው ቴብል ማውንቴን ከኢትዮጵያ የሰሜን ተራሮች ብዙም ባይለይም ስሙ ግን እጅግ የገዘፈ ነው፡፡ አንድ ነጭ ፈጠን ፈጠን እያለ ከሄደ ሶምሶማ ነው፡፡ ክልስ ሮጥሮጥ እያለ ከሄደ ባቡር እንዳያመልጠው ነው፡፡ አንድ ጥቁር ራመድ ራመድ ካለ ወይ ሰርቆ ነው ወይ ከፖሊስ እያመለጠ ነው ይላሉ፡፡ በአገሪቱ በዋናነነት እንደየ ኑሮ ደረጃቸው የተቀመጡት የቆዳ ቀለሞች ነጭ፣ ክልስ እና ጥቁር ናቸው፡፡ በቆይታዬ የሰማሁት በአገሪቱ የሚነገር ቀልድ የቀለም ልዩነቱን አስከፊነት ብቻ ሳይሆን በህብረተሰቡ ውስጥ የተለመደውና ቅቡል የሆነውን አመለካከትም ያሳያል፡፡ ደቡብ አፍሪካ አስራ አንድ የስራ ቋንቋ ያላት፣በኢኮኖሚዋ ያደገች፣በመሠረተ ልማት አውታሮቿ የመጠቀች፣የምዕራቡን አለም ከተማ ቅጂ የምትመስል አፍሪካዊ አገር ናት፡፡ “The Rainbow Nation” እያሉ የሚጠሯት ደቡብ አፍሪካ፣ በማንነት ፍለጋ ላይ ያለች አገር ትመስላለች፡፡ አብዛኞቹ የአገሪቱ መሠረተ ልማቶች የተዘረጉት የነጮችን አኗኗር እና ጥቅም በሚያስከብር አኳሃን ነው፡፡ የቱሪዝም ዘርፉ የሚንቀሳቀሰው በነጮቹ በመሆኑ፣የጥቁሮቹን አኗኗር እና ባህል ለማወቅ ከባድ ጥረት ይጠይቃል፡፡ አፓርታይድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተቀብሯል ቢባልም ጥሎት ያለፈው አሻራ አሁንም በተለያዩ መንገዶች ይንፀባረቃል፡፡ አብዛኛው ጥቁር ተስፋ የቆረጠ እና ደሀ ሲሆን መኖሪያውም ከዋናው ከተማ እጅግ የራቀ ነው፡፡ የጥቁሮች መኖሪያ ቤቶች ጣሪያቸውን ነፋስ እንዳይወስደው በድንጋይ የተደገፉ ናቸው፡፡ በጥቁሮች እና በነጮቹ መካከል ያለው ልዩነት እጅግ የሰፋ ነው፡፡ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሄድ ሳር ቤት የሚገኘውን የአገሪቱ ኤምባሲ ውጣ ውረድ ማለፍ የግድ ይላል፡፡ ኤምባሲው በቀን ከ35 በላይ ቪዛ ጠያቂዎችን አያስተናግድም፡፡ ከሌሊቱ አስር ሰአት ሄዳችሁም ሰላሳ አምስት ቪዛ አመልካቾች ስማቸው ቀድሞ ከተመዘገበ፣በሚቀጥለው ቀን ሰላሳ አምስቱ ውስጥ ለመግባት ጥረት ከማድረግ ውጭ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ ኤምባሲው ለአገልግሎት ፈላጊዎች ብዙም የሚጨነቅ አይመስልም፡፡ ባለጉዳይ ተራ ደርሶት ውስጥ እስኪገባ ድረስ ለፀሐይ ወይም ለዝናብ መጋለጡ የግድ ነው፡፡ ቪዛውን ለማግኘት ጠያቂው ያስገባው  ማስረጃ በቂ ቢሆንም ቪዛው ሲመታም “ትክክለኛ የመመለሻ ትኬት መያዝ ግዴታ ነው” የሚል ማሳሰቢያ አይቀሬ ነው፡፡

Read 4165 times