Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 08 December 2012 13:36

በኢትዮጵያውያን ላይ ሊሳለቅ ሞክሯል የተባለው መፅሐፍ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

በሚያዝያ ወር 1934 ዓ.ም በደብረ ብርሃን ከተማ መግቢያ ጠባሴ በሚባል መንደር በእረኝነት ላይ ተሰማርቶ የነበረ አንድ የስምንት ዓመት ልጅ በቅርብ ርቀት በአስፋልቱ ላይ ባለፈው ሮልስ ሮይስ መኪና መስኮት ውስጥ ያየው ሰው ምስል በቀላሉ ከህሊናው የሚጠፋ አይነት አልሆነበትም፡፡ ማታ ከብቶቹን ሰብስቦ ቤቱ ሲገባ ቀን ስላየው መኪና፣ ስለ አጀቡና በመኪናው መስኮት ውስጥ ስላየው ሰው ለአባቱ ሲነግራቸው፣ ባለ ሮልስ ሮይሱ መኪና አፄ ኃይለሥላሴ መሆናቸው አልጠፋቸውም፡፡ ልጅ አበበ ቢቂላና ጃንሆይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተያዩት ያን እለት ነበር፡፡

በ1941 ዓ.ም የ16 አመት ወጣት ሆኖ፤ የክቡር ዘበኛ አባል መሆንን ተመኝቶ ከደብረ ብርሃን ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ካራ አካባቢ እናቱ ዘንድ ነበር ያረፈው፡፡ በዘመኑ ወላጅ እናቱ ከባለቤታቸው ጋር ተለያይተው፣ አዲስ አበባ መጥተው መኖር ከጀመሩ ሦስት አመት አስቆጥረዋል፡፡ ወጣቱ የክቡር ዘበኛ አባል መሆን ባይሳካለትም፣ በ6 ኪሎ አካባቢ ንጉሠ ነገሥቱን የማየት ሁለተኛ እድል አገኘ፡፡
በ1943 ዓ.ም በተመሳሳይ መልኩ ለክቡር ዘበኛ አባልነት ለመወዳደር ከደብረ ብርሃን ወደ አዲስ አበባ መጣ፡፡ በዚህም አልተሳካለትም፡፡ በሚያዝያ ወር 1945 ዓ.ም ግን የክቡር ዘበኛ አባል መሆን የሚያስችለውን ውድድር ማለፍ ቻለ፡፡ ስልጠናቸውን አጠናቀው የተመረቁ እለት የክብር እንግዳ ሆነው የመጡትን ንጉሠ ነገሥት ለሦስተኛ ጊዜ ማየት ቻለ፡፡
በ1949 ዓ.ም በሚልቦርን ኦሎምፒክ ተሳትፈው ለተመለሱ የልዑካን ቡድን አባላት በጃን ሜዳ የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ሲደረግ፣ ከክቡር ዘበኛ ወታደሮች አንዱ የነበረው አበበ ቢቂላ፤ ጃንሆይን ለአራተኛ ጊዜ በማየቱ ብቻ ተደስቶ አልቀረም፡፡
ከአራት ዓመት በኋላ በሚካሄደው የኦሎምፒክ ውድድር ተሳትፎ አሸንፈው ከሚመጡት አንዱ እንደሚሆን ሲናገር የሰሙት ቢኖሩም የሚያምነው አላገኘም፡፡ ይህ መረጃ “ብሔራዊ ጀግኖች” በሚል ርእስ በኢብራሂም አህመድ ተዘጋጅቶ በ1967 ዓ.ም በታተመው መፅሐፍ ውስጥ ሰፍሯል፡፡
በዚያው ዓመት በጦር ኃይሎች የስፖርት ውድድር ላይ በማራቶን ሩጫ የተወዳደረው አበበ ቢቂላ፤ በድል በማጠናቀቁ ብቻ ሳይሆን ርቀቱን 2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ በመጨረሱ ከሁሉም በላይ ንጉሠ ነገሥቱን አስደነቀ፡፡ ያን እለት ጃንሆይን ያየበትን ቁጥር በአንድ ከማሳደጉም ባሻገር ከንጉሠ ነገሥቱ እጅ ለመሸለም በቃ፡፡
ጃንሆይ ለክቡር ዘበኛው ወታደር ድል ልዩ አክብሮት እንዲሰጡ ግድ የሚላቸው አሳዛኝ ታሪካዊ ክስተት ከዓመታት በፊት ገጥሟቸዋል፡፡ በ1924 ዓ.ም በፈረንሳይ የተካሄውን 8ተኛ የኦሎምፒክ ውድድር ባዩበት አጋጣሚ፣ አገራቸውን ተሳታፊ ለማድረግ ጥያቄ ሲያቀርቡ “ስፖርታችሁ ስላላደገ በኦሎምፒክ መወዳደር አትችሉም” ተብለዋል፡፡ እንደዚያም ሆኖ ኢትዮጵያዊያን በሜልቦርን ኦሎምፒክ ለመሳተፍ በቅተዋል፡፡ ጅምሩን ሊያሳድግ የሚችል አትሌት በአገር ውስጥ በማየታቸው ነበር አክብሮታቸውን በሽልማት የገለፁት፡፡ አበበ ቢቂላ በአገር ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ባስመዘገበው ድል፣ ከጃንሆይ ሽልማት በተሰጠው በ15ኛ ቀኑ አባቱን በሞት አጥቶ ጥልቅ ሀዘን ተሰማው፡፡ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ መሳተፍ እንድትችል ካፒቴን ሆኔል ስካን፣ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡
ካፒቴኑ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የመጣበት ዋናው ምክንያትም ለስፖርት አሰልጣኝነት ነበር፡፡ አወዛጋቢ የሕይወትና የሥራ ታሪክ የነበረው ካፔቴን ሆኔል ስካን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን ወደ አውስትራሊያ (ሜልቦርን) ከመሄዱ ሁለት ዓመት በፊት በ1947 ዓ.ም ከንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የሻምበልነት ማዕረግ ተሰጥቶታል፡፡ ኢትዮጵያዊ ዜግነትም ነበረው፡፡አበበ ቢቂላ በጦር ኃይሎች ስፖርታዊ ውድድር አስደናቂ ውጤት ካስመዘገበ በኋላ መቶ አለቃ (በኋላ ኮ/ል) መለሰ አበበ ተመድበውለት፣ የስፖርት ስልጠናውን መከታተል ቀጠለ፡፡ በ1952 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቡድን ለሮም ኦሎምፒክ ጉዞ ተዘጋጅቶ ባለበት የመጨረሻ ሰዓት ላይ ከልኡካን ቡድኑ አንድ የነበረው ዋሚ ቢራቱ፤ እግር ኳስ ሲጫወት ቁርጭምጭሚቱ ላይ ጉዳት ሰለደረሰበትና ጉዳቱ ቶሎ አይድንም ስለተባለ፣ አበበ ቢቂላ የእሱን ቦታ ተክቶ ወደ ሮም እንዲሄድ ተወሰነ፡፡ በዘመኑ የስፖርት ፌዴሬሽን ወይም የኦሎምፒክ ኮሚቴው አመራሮች አቶ ይድነቃቸው ተሰማ፣ አቶ ፍቅሩ ኪዳኔና ሻምበል ሆኔል ስካን ነበሩ፡፡
በሮም ሁለት ትላልቅ ችግሮች ገጠሙት፡፡ እንግሊዝኛ ቋንቋ ባለማወቁ ምክንያት ከሌሎች ጋር በቀላሉ መግባባት አለመቻሉ አንዱ ሲሆን ለእግሩ 48 ቁጥር ጫማ መታጣቱም ሌላው ነበር፡፡ በዚህ ሊሳለቁበት የሞከሩ ነበሩ - በተለይ አሜሪካዊያን አትሌቶች፡፡ በተቃራኒው የደገፉትና ያበረታቱም ነበሩ፡፡ በሜልቦርን ኦሎምፒክ በማራቶን የተያዘው ሰዓት 2፡22፡23 ነበር፡፡ በሮም ኦሎምፒክ አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ሮጦ ከማሸነፉም ባሻገር 2፡15፡27 በመግባት አዲስ ሪከርድ አስመዘገበ፡፡
የልዑካን ቡድኑ ወደ አገሩ ሲመለስ ጃንሆይ ለሆኔል ስካን የሳባ ኮርዶን ኒሻን ሰጡት፡፡ ይህ ኒሻን ከዚያ በፊት ለደጐል፣ ለማርሻል ቲቶና ለተለያዩ አገራት ጳጳሳት የተሰጠ ታላቅ ሽልማት ነበር፡፡ ለአበበ ቢቂላ ደግሞ የ10 አለቃ ማዕረግ፣ የፈረሰኛ ኮርዶን 5ኛ ደረጃ ኒሻንና “አገርህንና አፍሪካን አኩርተሀል” ብለው የአልማዝ ቀለበት ሸለሙት፡፡ በገነተ ልዑል ቤተመንግሥት በተከናወነው በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ 10 አለቃ አበበ ቢቂላ ጃንሆይን ያየበት እለት ቁጥር ወደ አምስት አሳደገ፡፡በ1956 ዓ.ም በቶኪዮ ኦሎምፒክ ለሁለተኛ ጊዜ ስናሸንፍ የመቶ አለቃ ማዕረግ የተሰጠው አበበ ቢቂላ፤ ድሉ ንጉሠ ነገሥቱን እንደቀድሞ አላስደሰተም ወይም ጮቤ አላስረገጠም፡፡ ምክንያቱም በ1953 ዓ.ም መፈንቅለ መንግሥት ተጠርጥረው ከታሰሩትና በብዙ እንግልት ውስጥ ካለፉት የክቡር ዘበኛ ወታደሮች አንዱ አትሌቱ ነበርና፡፡ ከእስር የተፈታውና በቶኪዮ ኦሎምፒክ መወዳደር የቻለውም የተለያዩ አገራት መንግሥታትና ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ባቀረቡት ጥያቄና ጉትጐታ ነበር፡፡
በዚህም የተነሳ የደረሰበት የመኪና አደጋና ህልፈቱ የጃንሆይ እጅ አለበት ተብሎ እንዲወራ ምክንያት ሆኗል፡፡ አሉባልታው እውነታ አለው እንዴ? የሚያስብሉ ነገሮችም ተከስተዋል፡፡ ለምሳሌ አበበ ቢቂላ ላይ የመኪና አደጋ የደረሰው መጋቢት 14 ቀን ሆኖ ሳለ፣ ጋዜጦች ዜናውን የዘገቡት ከ10 ቀን በኋላ መጋቢት 24 ነው፡፡ የመኪና አደጋ የደረሰበትን ቦታ በተመለከተ የተለያዩ ጋዜጦች የተለያዩ መረጃዎች ነው የሚሰጡት፡፡በተቃራኒው ይህ አሉባልታ እውነታ እንደሌለው የሚያመለክቱ መረጃዎችም አሉ፡፡ በ1962 ዓ.ም በሜክሲኮ ኦሎምፒክ ተሳትፎ ሲመለስ፣ እንደቀድሞው ድል ባይቀናውም ንጉሠ ነገሥቱ የሻምበልነት ማዕረግ ሰጥተውታል፡፡ “ብሔራዊ ጀግኖች” በሚል ርእስ ኢብራሂም አህመድ ባሳተመው መፅሐፍ ውስጥ፣ ለሻምበል አበበ ቢቂላ በዚህ ዙሪያ ለቀረበለት ጥያቄ “ከግብርና አንስቶ ለዚህ ያበቃኝ ንጉሠ ነገሥት ላይ እንዴት አምፃለሁ?” የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡
***
ከላይ የቀረበው ታሪክ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህሩ ሰለሞን ተሰማ፤ እሁድ ህዳር 23 ቀን 2005 ዓ.ም በሚዩዚክ ሜይዴይ መድረክ ተጋብዘው ካቀረቡት ሰፊ ጥናታዊ ፅሁፍ ተቀንጭቦ የተወሰደ ነው፡፡ በእለቱ ለውይይት የተመረጠው በፖል ራምፓኒ ተፅፎ “ሮማን የወረረ ጀግና” በሚል ርእስ በትዕኩ ባህታ ተተርጉሞ የቀረበው መፅሐፍ ነበር፡፡ ጥናታዊ ፅሁፍ አቅራቢው ገለፃቸውን በሦስት የተለያዩ ርእሶች ከፍለው ነበር ያብራሩት፡፡ የአበበ ቢቂላና የጃንሆይ ትውውቅ ምን እንደሚመስልና ለአበበ መንፈስ መነሳሳትና ባለድል መሆን የጃንሆይ አስተዋፅኦ እንዳለበት ከላይ የቀረበው ታሪክ ተጠቃሽ ነው፡፡ በስፖርት ፌዴሬሽን አካባቢ ከቀድሞ ዘመን እስካሁን ድረስ ያሉ ጥሩና መጥፎ አሰራሮችን ያመለከቱበት ንዑስ ርእስ ሁለተኛው ሲሆን ለዕለቱ ለውይይት በተመረጠው መፅሐፍ ላይ ያቀረቡት ግምገማ ሦስተኛው ነው፡፡
“ሮማን የወረረ ጀግና” በሚል ርእስ ተተርጉሞ የቀረበው መፅሐፍ ብዙ ችግሮች አሉበት ያሉት መምህር ሰለሞን ተሰማ፤ የመፅሐፉ ደራሲ ፖል ራምፓኒ መፅሐፉን ለማዘጋጀት ጥልቅ ምርመራ አለማድረጉን በመጥቀስ በተለይ ሻምበል አበበ ቢቂላን አለማነጋገሩ ለተፈጠሩት ችግሮች ምክንያት ሆኗል ብለዋል፡፡ “አበበ ቢቂላ በ1953 ዓ.ምቱ መፈንቅለ መንግሥት ከመሳተፉም ውጭ ተኩሷል ይላል፡፡ ይህ ውሸት ነው፡፡ አበበ ቢቂላና መንግስቱ ንዋይ በአንድ ቦታ ስለመታሰራቸው ፅፏል፡፡ ይህም እውነት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ጀነራል መንግሥቱ ንዋይ በገነተ ልዑል፤ አትሌት አበበ ቢቂላ ንግሥት ዘውዲቱ ባሰሩትና ቄራ ተብሎ በሚጠራው እስር ቤቶች ነበር የታሰሩት፡፡
“ፖል ራምፓኒ ሆላንዳዊ ነው፡፡ ታዋቂ የስፖርት ዘጋቢና ብዙ አድናቂ ያለው ጋዜጠኛ ነው፡፡ ሌሎች መፃሕፍትም አሉት፡፡ “ሮማን የወረረ ጀግና” ተብሎ በተተረጐመለት መፅሐፉ በኢትዮጵያዊያን ላይ ሊሳለቅብን መሞከሩ ይታያል፡፡
በ1908 ዓ.ም በአዋጅ የተከለከለውን የሌባ ሻይ ጉዳይ የቅርብ ታሪክ አድርጐ ያሰፈረው ለዚህ ነው፡፡ የሌባ ሻይ ብቻ ሳይሆን አውጫጭኝም በ1957 ዓ.ም በአዋጅ እንዲቀር ተደርጓል፡፡”
በመፅሃፉ ውስጥ አሉ ያሉትን ሌሎች ተመሳሳይ ግድፈቶች ያመለከቱት መምህር ሰለሞን ተሰማ፤ ተርጓሚው “ቢያደርጉት ኖሮ” በሚል አስተያየታቸውን አቅርበዋል፡፡ ትርጉሙ በአዛማጅ ትርጉም ቀርቦ የባለታሪኩ ቤተሰቦች ልጆችና ጓደኞች ቢጠየቁ፤ ታሪኩን የሚያሳዩ ፎቶግራፎች እንዲይዝ ቢደረግና ስለ ስፖርት የሚያውቅ ኤዲተር ቢመለከተው መልካም ነበር ብለዋል፡፡
በእለቱ መምህር ሰለሞን ተሰማ የውይይቱን ርእሰ ጉዳይ ማዕከል አድርገው በጣም ሰፊና ጥልቅ ገለፃዎችን ያቀረቡ ሲሆን፡፡ በንግግራቸው የተደመመ አንድ ተሳታፊ “የአበበ ቢቂላን ታሪክ እርሶ ለምን አይፅፉልንም” ብሏቸዋል፡፡

Read 4244 times