Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 08 December 2012 13:50

ሞያን እንደ ሞያተኛ ሆነው ሲወጡት ደስ ይላል

Written by 
Rate this item
(7 votes)

የእውቅ ድምፃውያንን የሙዚቃ ቪዲዮ ክሊፖች ሰርቷል - ስንታየሁ ሲሳይ፡፡ በሚሰራቸው ስራዎች ሁሉ ኢትዮጵያዊ ባህልን ማካተትና ማንፀባረቅ ይፈልጋል፡፡ በዚህ የማይስማሙ ዘፋኞች አይስማሙኝም ይላል፡፡ አብዛኞቹ ግን የምላቸውን ስለሚሰሙኝ ምስጋና ይገባቸዋል የሚለው ዳይሬክተሩ ስንታየሁ ሲሳይ፤ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ቪዲዮ ክሊፕና ፊልሞች ዙሪያ ከጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው ጋር ያደረገውን ቃለምልልስ እንዲህ አቅርበነዋል፡፡
የሙዚቃ ቪዲዮ ክሊፕና የፊልም ዳይሬክተር ምን ማለት ነው … ሥራው ምንድነው?


ለእኔ ዳይሬክተር ማለት ልብስ ሰፊ ብለሽ አስቢው፡፡ የሙሽሮቹን ልብስ የሚሰፋ ልብስ ሰፊ፤ እጁን፣ ወገቡን… ሁሉን ነገር ለክቶ የፈለጉትን ልብስ ዲዛይን በቆንጆ ሁኔታ ያቀርብና ለሙሽሮቹ ያስጨበጭብላቸዋል፡፡ “ሙሽሮች መጡ፣ ገቡ” ያሰኛቸዋል፡፡ ከሙዚቃ ቪድዮ ክሊፕና ከፊልም ስክሪፕት ጀርባ የዳይሬክተሩ ሚና ባለ ብዙ ዓይን መሆን ነው፡፡ ስክሪፕቱ ለሰው ዓይን ምግብ ይሆን ዘንድ ስጋና ደም ማልበስና ማቅረብ በይው - የዳይሬክተሩን ሥራ፡፡
‹‹የፊልም እግዜሩ፤ ዳይሬክተሩ›› ሲባል ሰምቻለሁ…?
እውነት ነው፡፡ እንዲሁም የሙዚቃ ቪዲዮ ክሊፕ እግዜሩ ዳይሬክተሩ በይው (ሳቅ)
ብዙ ጊዜ ግን ከዳይሬክተሩ ይልቅ ተዋናዮቹ፣ ወይም በሙዚቃ ቪዲዮ ድምፃዊውና ተወዛዋዦቹ ብቻ ናቸው የሚታወቁት፡፡ ተመልካቹም ቢሆን ዳይሬክተሩን ለማወቅና ሥራውን ለማድነቅ ብዙም አይጨነቅም…
ድሮ ድሮ የዳይሬክተር ነገር ትኩረት አይሰጠውም ነበር፡፡ ያን ያህልም ማን ነው፣ ምንድነው ተብሎ አያሳስብም፡፡ አክተሩ፣ ደራሲውና ተዋንያኑን በደንብ ከታወቁ ሌላው ጥያቄ የማይሆንበት ጊዜ ነበር፡፡ ግን የዳይሬክተሩ ሥራ ወሳኝ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡
ፊልምን ብንወስድ ስክሪፕቱ ተጽፎ ይመጣል፡፡
ታሪኩ ወረቀት ላይ ነው ያለው፤ በእግሩ መሄድ አልጀመረም…ያን ነገር ተፍታቶ እንዲራመድ፤ ለእይታ አጣፍጦ እንዲላወስ የሚያደርገው ዳይሬክተሩ ነው፡፡ የእሱ ዋና ስራው ለስክሪፕቱ ህይወት መዝራት ነው፡፡ የፊልም ፅሁፉን ከብዕር ወደ ዓይን ይቀይረዋል ማለት ነው - ወደ እይታ፡፡
ለዛ ነው ፊልም ተሰርቶ አልቆ ለእይታ ሲበቃ… ዳይሬክተሩን የሚያስጨበጭብለት፡፡ የሙዚቃ ዌብ (የልብ ምት) ምልክት ታውቂያለሽ? በሰው ልብ ውስጥ ከፍ ዝቅ፣ ከፍ ዝቅ እያደረገ የሰውን ስሜት የሚቆጣጠር፤ በስክሪፕቱ ላይ ህይወት የሚዘራበት ማለት ነው - ዳይሬክተር፡፡ ከባድ የስራ ድርሻ ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ እየተሰሩ ያሉት የኢትዮጵያ ፊልሞችን እንደ ባለሙያ ስትመለከታቸው በጥሩ ዳይሬክተር የተዘጋጁ ናቸው ሊባሉ ይችላሉ?
የፊልም ኢንዱስትሪው በአንደኛው መንገድ እያደገ ነው፡፡ ፊልም ሲባል ብዙ ሞያተኞችን ያቀፈ የቡድን ስራ ነው፡፡ በአንድ ወገን እውነትም እያደገ ነው የሚያስብል ነገር አለው፡፡ በሌላ መልኩ ግን እያደጉ መስለው ቁልቁል የወረዱ አሉ፡፡ በቀረፃው፣ በምስል ግብዓቱ፣ በድምጽ ጥራት፣ ወደ ሲኒማ ደረጃ እያደጉ ያሉ ይታያሉ፡፡ በብዛት የሚሰሩት ግን ወደ ላይ እየወጡ ቢመስላቸውም ወደታች እየወረዱ ነው ያሉት፡፡
በእርግጥ ተጨንቀው የሰሩ ብዙ ባለሙያዎች አሉ፤ የተጨነቁ መስሏቸው እያጠፉም ያሉ አሉ፡፡
አንዳንዴ እንደውም የሚገርመኝ… አንዳንድ አርቲስቶች ዝም ብለው ስክሪፕት አንብበው ሊተውኑ ይችላሉ… እነሱም ታዲያ ባለሙያ ይባላሉ፡፡ ፊልም ማለት የሦስትና የአራት ወር ስራ አይደል፡፡ ጊዜ ሰጥተሽ፣ ስለ ፊልሙ ታሪክ፣ ፍሰትና ገፀባህርያት በደንብ ማወቅ አለብሽ፡፡ ዝም ብለሽ ስትገቢበት የማታውቂው አገር እንደመግባት ነው የሚቆጠረው፡፡ በፊልም ኢንዱስትሪው ከወጪ ቀሪ ብዙ አዲስ ነገሮች አሉ፡፡
እስካሁን የሰጠኸው አስተያየት ያንተን ሥራዎች ይመለከታል?
እርግጥ ነው ጉዳዩ ለእኔም ነው፡፡ የአርቲስቶችን ስራ ተቀብሎ መስራት እንደ አንድ ሃላፊነት ሆኖ፣ እንደዜጋ በእኔ በኩል የሚያልፉ ስራዎች ለአገሬ ህዝብ ምን ያህል ጣፋጭ መሆን አለባቸው የሚለው ጉዳይ እጅግ በጣም ያሳስበኛል፤ ያስጨንቀኛል፡፡ ሃላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ እና ከባህል አኳያ እጠነቀቃለሁ፡፡
ባህላችን እንዳይበረዝ እጅግ እጠነቀቃለሁ፡፡
ሙዚቃው በራሱ እንዴት እየሄደ ነው የሚለው ያስጨንቀኛል፡፡ አሬንጅመንቱ፣ ዜማው፣ ግጥሙ፣ ፍሰቱ ሁሉ እኔንም እንደ አንድ ዜጋ ይሰማኛል፤ ያመኛል፣ ያስደስተኛል፣ ያስለቅሰኛል፡፡ ከዛ አኳያ ኢትዮጵያዊ የሆነ የሙዚቃ ፕሮዳክሽን ማምጣት ነው ህልሜም፤ የጎዳናዬም መጀመሪያ፡፡
ኢትዮጵያዊ የሙዚቃ ፕሮዳክሽን ሲባል ምን ማለት ነው?
ለምሳሌ ውበት፣ ለዛ፣ አካባቢ፣ አገር እነዚህ ሲጠቀሱ በቪዲዮው ላይ በምን መልኩ መታየት አለባቸው? ኢትዮጵያዊ ማለት እርግት ያለ መንፈስ ያለው ህዝብ ነው፡፡ ለዚህ የተረጋጋ መንፈስ የተረጋጋ ምግብ ያስፈልገዋል፡፡ የምዕራባውያንን ህይወትና ባህል በኢትዮጵያዊ ሙዚቃ ውስጥ ባሳይ ተገቢ አይደለም፡፡ ከዚህ አኳያ ስሰራ እጨነቃለሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከመጨነቄ የተነሳ ስራ አዘግይቼ ነው የማደርሰው፡፡ ፈጠራው በራሱ ጊዜ ይፈልጋል፡፡
እስቲ አንተ የሰራሃቸው በቲቪ የሚቀርቡ ክሊፖችን ጥቀስልኝ...
ከድሮዎቹ ሥራዎች የጥበበ ወርቅዬ (ሊጋባ)፣ የፍቅርአዲስ ነቃጥበብ (ንዳው)የወሎ ዘፈን፣ የላፎንቴዎች(ባቡሬ)፣የትግስት አፈወርቅ (ደጉ ባላገሩ)፣ ሚሶ ነጋያ (ሐመር) ቁጥር 1 እና 2፣ የሞገስ ተካ (ማህሌታዊ ያሬድ)፣ የሄለን በርሄ (ልቤን)፣መስፍን በቀለ (ደመላሽ)፣ የሃይሉ ፈረጃ (ጉራጊኛ)፣ ኢሳን አብዱ ሰላም (አደርኛ ዘፈን)፣ ምናሉሽ ረታ፣ አሸብር በላይ (ልሻገር አለኝ ጐጃም) በቅርቡ የሃይልዬ ታደሰ (ድሬ) የሚለው እና አሁን በእጄ ያሉ አሉ - ለምሳሌ የብርሃኑ ተዘራ፡፡
የሁሉንም ቪዲዮ ክሊፕ ስሰራ ኢትዮጵያዊነት ያለው ቅርጽ ይዘው እንዲሄዱ ብዙ እጥራለሁ፡፡
ህንዶች በዚህ ጉዳይ በጣም ያስደስቱኛል፡፡ ባህላቸውን አስረግጠው ያሳያሉ፡፡
እነሱ የምዕራቡን ህይወት ከእኛ በተሻለ ሊሰሩበት ይችሉ ነበር፤ ግን አልፈለጉትም፡፡ ባህላቸውን ይዘው በዓለም ውስጥ ብዙ ስራ ይሠራሉ፡፡ እየተሳካላቸውም ነው፡፡
ይሄ ሥራ “እኔን አይመጥንም” ብለህ የምትመልስበት አጋጣሚ አለ?
አይመጥነኝም ሳይሆን ስራውን እንደሞያተኛ ካየሁ በኋላ አልሰራም ብዬ ብዙ የመለስኳቸው አሉ፡፡
አንዳንዴ ሙዚቃው፣ አሬንጅመንቱ፣ ዜማው፣ ግጥሙ እና እራሱ ድምፃዊው ሁሉም ሳይጣጣሙ ተረባብሸው ታያለሽ፡፡ ይሄን አይነቱን ለመስራት አልሞክርም፡፡ ዝም ብሎ ግድግዳ ጥግ አስጠግቶ መቅረጽ ሳይሆን የግድ መናበብ ያስፈልጋል፡፡ እና አንዳንድ ጊዜ ግጥሙ፣ ዜማው፣ አሬንጅመንቱ ከልብሽ ጠብ የማይል ሲሆን መተው ይሻላል፡፡ እንደነ ማሪያ ኬሪ ወይም ቢዮንሴ ምናምን የመሰለ ይዘው… ሲመጡ “እኔ ባህላዊ ነው የምሠራው… ወደ ባላገርኛ ነው የምመልስብሽ ይለፈኝ” እላቸዋለሁ (ሳቅ) እንግዲህ ምን ታደርጊዋለሽ? ስፈጠር ባላገር (ኢትዮጵያዊ) ሆኜ ተፈጥሬያለሁ፤ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ እኔ አገሬን በጣም እወዳለሁ፤ እንደውም ብዙ ሰዎች ቤቴን ሲያዩ በባህላዊ ነገር ያበደ ስለሆነ “ውጪ ቆይተህ ነው እንዴ የመጣኸው” ይላሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ከአዲስ አበባ ውጪ ገጠር ገጠሩን ሳካለል ነው የምከርመው፡፡ አሁንም ገና አልጠገብኩም፤ አልጠግብምም፡፡
አንድ የሙዚቃ ቪዲዮ ክሊፕ ለመስራት ምን ያህል ይፈጃል?
ከፍና ዝቅ ይላል፡፡ እንደ ስክሪፕቱ ይለያያል፡፡
ምርጥ ስራ ይሆንና ያንን ካልከፈላችሁ ብዬ አላስጨንቃቸውም፡፡ በባዶ የሰራሁት እንዳለ ሆኖ ለአንድ ክሊፕ ከ30-40ሺ ብር ይፈጃል፡፡ ወደ አራት አሪፍ ስራዎች በትብብር በነፃ የሰራሁት አለ፡፡ ስራቸው አሸንፎኛል ብዬ ራሴን መስዋዕት አድርጌያለሁ፡፡
ብዙዎቹ በቲቪ የምናያቸው የሙዚቃ ቪዲዮ ክሊፖች ያለ ልምምድ (rehearsal) የተቀረፁ ናቸው፡፡ ለምንድነው?
ከበጀት አኳያ ሊሆን ይችላል፡፡ ትክክለኛ ፕሮግራም ወጥቶለት በአንድ ወር ማለቅ አለበት ቢባልና ለአምስት ቀናት ጥናት ቢያስፈልግ የራሱ ወጪ አለበት፡፡ በደንብ አቀናጅቶ ለመስራት አቅሙ የሚመጥን አለ፣ የማይመጥን አለ፣ በአብዛኛው ችግሩ ይሄ ነው፡፡
ትልቅ ስክሪፕት ጽፌ ለአርቲስቱ ብሰጠው መክፈል ይከብደዋል፡፡ ባጀቱ ሁለት መቶ ወይም ሶስት መቶ ሺ ሊሆን ይችላል፡፡ ያንን ለአንድ ሙዚቃ ክሊፕ መክፈል ካልቻለ፣ ከስክሪፕቱ እየተመረጡ እየወጡ ባዶ ያደርጉታል፡፡ ከዚህ አንፃር መሠለኝ፡፡
እኛ አገር ሙዚቃ ሲለቀቅ ማነው ፕሮዲዩሰሩ ብትይ አይታወቅም፡፡ በሌሎች አገሮች ግን ፕሮዲዩስ የሚያደርጋቸው ኩባንያ ከአርቲስቶቹ ጋር ለአመትና ለሶስት ዓመት ኮንትራት ይፈራረማል፡፡ ከዛም ኩባንያው ለሙዚቃ ቪዲዮ ፕሮዳክሽኑ ከፍተኛ ገንዘብ ኢንቨስት ያደርጋል፤ በትልቅ በጀት ይሰራውና ኩባንያውም አርቲስቱም ይጠቀማሉ፡፡
እኛ አገር ግን ራሱ አርቲስቱ ነው የሚያሰራው፡፡ የአቅም ጉዳይ አለ፡፡ ውጭ እኮ ዘፈናቸው በየሚዲያው በተሰማ ቁጥር በፐርሰንት ይከፈላቸዋል፡፡ እኛ አገር ይሄ ነው ችግሩ የሚመስለኝ፡፡
የቴዲ አፍሮ “ጥቁር ሰው” ቪዲዮ ክሊፕ ከ400ሺ ብር በላይ ፈጅቷል ተብሏል…
ክራውዱ ሲታሰብ፣ ቁሳቁሱ ሲታሰብ፣ ፈረሶቹን፣ ሴቲንጉን ስታይው ያን ያህል ሊያስወጣ ይችላል ትያለሽ፡፡ በጥሩ ሲኒማቶግራፈር ተሰርቷል፡፡ ዳይሬክተር ግን የለውም፡፡ ያን ያህል ባጀት ወጥቶበት ዳይሬክተር አላገኘም፡፡
ከአርቲስቶች ጋር ስትሰራ የሚፈጠሩ አለመግባባቶች ይኖራሉ…
አዎ… የምጋጭበት ጊዜ አለ፡፡ ለምሳሌ አንዱ ሎቲ አድርጐ ይመጣና አውልቅ አታውልቅ ጭቅጭቅ ይኖራል፡፡ ስራው ደግሞ የእኔ እና የእሱ ብቻ አይደለም፡፡ የመላው ኢትዮጵያዊ ስራ ነው፡፡
ሙዚቃው አንድን አገር ነው የሚወክለው፡፡ ሁለታችንም የባህሉ አስተዋዋቂዎች ነን፡፡ በዛ ዘፈን ውስጥ ሆነን “ይቻት አገራችን” ነው የምንለው፡፡ ለምሳሌ አንዳንዱ አርቲስት ስራውን አይመስልም፡፡ ለምሳሌ ዘፈኑ “አገሬ እንደዚህ አድርጌልሽ እንደዚያ ፈጥሬልሽ፣ ወድጄሽ” ምናምን የሚል ይሆናል፡፡
በሙዚቃ ውስጥ የተፈጠረው ገፀ ባህሪ ታታሪ ነው፤ ደፋ ቀና የሚል ነው፡፡
አርቲስቱ ግን በሊሞዚን ፍሰስ እያለ፣ ጥሩ ኑሮ የሚኖር ይሆናል፡፡ እኔ ደግሞ አርቲስት ኑሮውን ስራው ውስጥ ሲከት አይመቸኝም፡፡ ስራውን ሲሆን ነው የሚመቸኝ፡፡
አሁን ሞገስ ተካ የሰራው “ያሬድ ማህሌት” ላይ አህያ እየነዳ ያሬድን ሲፈልገው ነው የሚታየው ከታሪኩ ጋር ይጣጣማል፡፡ አርቲስቱ ላሊበላ ላይ በእግሩ እየሄደ ይታያል፡፡ ለስራው ተገዝቷል ማለት ነው፡፡ ሌላው ያሬድን ፍለጋ በስኒከርና በመኪና ቢዳክር ፈፅሞ አያገኘውም፡፡ በዚህ ጊዜ ከአርቲስቱ ጋር እንጋጫለን፡፡ ፂሙን ፀጉሩን ማሳደግ ካለበት ያሳድጋል፡፡ በባዶ እግሩ በጭቃ ውስጥ መሄድ ካለበት ግዴታው ነው፡፡ ሞያን እንደ ሞያተኛ ሆነው ሲወጡት ደስ ይላል፡፡ ግን እግዚአብሔር ይስጣቸው ብዙዎቹ አርቲስቶች ሙዚቃቸውን ከሰማሁ በኋላ የምሰጣቸውን የዳይሬክቲንግ ሂስ ቶሎ ይሰሙኛል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡
ወደ ፊልምና የቪዲዮ ሙዚቃ ዳይሬክቲንግ የገባኸው እንዴት ነው?
አሁን እንግዲህ ዘጠኝ ዓመት ሆነኝ፡፡ ተወልጄ ያደግሁት አዲስ አበባ ልደታ ሰፈር፤ (ደሴ ሆቴል) አካባቢ ነው፡፡ ልጅ ሆኜ የህንድ ፊልም ለማየት “ሸማኔ ሰፈር” የሚባል ቦታ ከሠፈር ልጆች ጋር እንሄድ ነበር፡፡
25 እና 50 ሳንቲም ከፍለን እንገነባለን፡፡ የህንድ ፊልም አይተን ስንመለስ፣ የህንድ ዘፈን በየመንገዱ እየዘፈንኩላቸው የምመጣው እኔ ነበርኩ፡፡ ዝናብ እየደበደበን እየተሽከረከርኩ እንደ አክተሩ አክት እያደረግሁ እዘፍናለሁ፡፡ ለበርካታ ቀናቶች ፊልሙ ከውስጤ አይጠፋም፡፡ በቃ አክተሩን ሆኜ ቁጭ እላለሁ፡፡
በት/ቤት ውስጥ ደግሞ ድራማ እሰራ ነበር፡፡ የሙዚቃ አስተማሪያችን እኔን ነበር የምታዘፍነኝ፡፡ እኔ ከትምህርት ቤት ከቀረሁ ግን ሹራብ (የእጅ ስራ) ስትሰራ ክፍለጊዜው ያልቃል፡፡ እና አክተሩን ድሮ ስታር ነበር የምንለው (ሳቅ) እሱ ለእኔ ጀግናዬ ነው፡፡
ከሁሉም በላይ ግን ለዛሬ እኔነቴ የእውነት ጥበብ የሆነችኝ እናቴ ናት፡፡ ልጅ ሆኜ ንጋት ላይ ጐህ ሲቀድ ከእንቅልፌ እቀሰቀሳለሁ፡፡
ገላዬን በቀዝቃዛ ውሃ ታጥቤ፣ ነጠላ ታስሮልኝ ጠላና ድፎ ዳቦ ተሸክሜ ከእናቴ ጋር ወደ ልደታ ቤተክርስቲያን (ሰንበቴ) ቤት እንሄዳለን፡፡ በዛ ሰዓት ቤተክርስቲያኑ ግቢ ስንደርስ የሚሰማ ቅዳሴ አለ፡፡ ጽናጽሉ፣ የቄሶቹ ወረብ…ሲሰማ እናቴ በስመአብ (በመገረም) የለችም፡፡
ተሸክሜ ቆሜ እያለሁ እናቴ ከደጃፉ ላይ በግንባሯ ተደፍታ፣ የለበሰችው ነጭ ጥበብ መሬት ላይ ተንዘርፎ ተንበርክካ፣ ፀሎት አድርጋ እስክትነሳ እኔ ተሸክሜ ቆሜያለሁ፡፡ ድካሙም ትዝ አይለኝ፡፡ ወደ ሰንበቴ ቤት ገብተን ቄሱ ፀሎት አድርገው እስኪጨርሱ ዳቦው እስኪቆረስ፤ እንጀራውን፣ ምስር ወጡን እያየሁ ለራሴ “አይጀመርም እንዴ? አይጀመርም እንዴ?” የምለው… አይረሳኝም፡፡ እነዚህ እነዚህ ትልቅ ጥበቦቼ ናቸው፡፡ በኋላ ኳስ ተጫዋች ሆንኩ፡፡
ለክለብ ደረጃ ነው ወይስ…
በኦሜድላ ክለብ፣ ለቢ ቡድን ተመረጥኩ፡፡ ከዛ በኋላ ከቢ ቡድን ወደ ዋናው ቡድን ተመላላሽ አደረጉኝ፡፡ ያን ጊዜ ንጉሴ ገብሬ የሚባል አሠልጣኝ ነበር፡፡ ጐበዝ ግራኝ ተጫዋች ነበርኩኝ፡፡ ኳስ በራሱ እኮ ጥበብ ነው፡፡ በዛም አላበቃሁም፡፡
ለከፍተኛ አራት (ኮካ) ሰፈር ቡድን ተጫዋች ሆንኩ፡፡ ከዊንጌት ጋር ተጫውተን እንደውም እኔ ሁለት ጐል አግብቼ አሸንፈናል፡፡ አብደኛም ነበርኩ… ማለት አጣጥፍ ነበር፡፡ መስጠት መቀበል፣ የብራዚል ኳስ ነበር የምንጫወተው፡፡ ብዙ ልጆች ነበሩ፤ ጓደኞቼ፡፡
ከኢትዮጵያ ውጪም የሄዱ አሉ፡፡ በኳሱም ቀጥለውበት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአገር አቀፍ ደረጃ ተይዘው የሚጫወቱ ነበር፡፡
በዚህ መሃል ግን እኔ በህንድ እና በምዕራብ ፊልሞች መመሰጥ ጀመርኩ፡፡ አክተር ሳይሆን ዳይሬክተር መጥራት ጀመርኩ፡፡ የስቲቨን ስፒልበርግ፣ የጀምስ ካሜሮን ፊልም እኮ ነው፡፡ እነሱ ናቸው እኮ ዳይሬክት ያደረጉት ማለት ጀመርኩ፡፡ ዳይሬክተሮችን ማድነቅ፣ በጥበባቸው መመሰጥ ቀጠልኩ፡፡
ስለ “ሳንኮፋ” ሲወራ ሃይሌ ገሪማ ሲባል… በቃ! የምሆነው ጠፋኝ፡፡ ኢትዮጵያዊነቱን ሳውቅ ደግሞ የት ላግኘው? በጣም ህልም ሆኖብኝ ነበር… በጣም እኮራ ነበር፡፡ “ሳንኮፋ”ን ሶስት ጊዜ አይቼዋለሁ፡፡ የመጀመሪያው ጊዜ ኢትዮጵያዊ ፊልም በሚለው አየሁት፡፡
በሁለተኛው ግን እኔን ከሃይሌ ገሪማ ጋር ማስተያየት ጀመርኩ፡፡
ይሄን ነገሬን የሚያውቅ አንድ ዶ/ር ነበር፡፡ ዶ/ር ዘገብርኤል ይባላል፡፡ እሱ ነው ወደ አርት እንድገባ የገፋፋኝ፡፡
የምታደንቃቸው የፊልም ዳይሬክተሮች…
ከአፍሪካ የናይጀሪያ፣ የማሊ ዳይሬክተሮች አሉ፡፡ ከአገሬ ሃይሌ ገሪማ ትልቅ ዳይሬክተር ነው፡፡ እስከዛሬ ምን ሰራ የሚለው ጥያቄ ቢሆንብኝም፡፡ አሁን ደግሞ ብዙ ወጣቶች እየመጡ ነው፡፡ በሳል ነገር ያላቸው፣ ገና ፊልም ያልሰሩ፣ መንገድ ላይ ያሉ ድንቅ ወጣቶች አሉ፡፡ ሃላፊነት የሚገባቸው ወይም የሚሰጣቸው ብዙ አሉ፡፡
አንተስ ምን ፊልም ሰርተሃል?
አቢ ላቀው የሰራችበትን “ወደመጣሁበት” (እየሩስ) ፊልም ዳይሬክት አድርጌያለሁ፡፡ መቶ ሰማኒያ ገጽ የነበረውን የፊልም ፅሁፍ ወደ ስልሳ ገጽ ቀንሼው፣ አገራዊነቱ እንዲጐላ በጣም ተጨንቄበታለሁ፡፡ በአባይ ጐንደር አካባቢ ነው ፊልሙ የሚጀምረው፡፡
ያንን ለማሳየት ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ ግን ብዙ ፊልሞች መጥተውልኝ መልሼያለሁ፡፡ ለእኔ የሚሆኑ ባለመሆናቸው፡፡ የተጨላለፈ የተነካካ፣ ስሜት የማይሰጥ፣ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊ የማይሸቱ ሲሆኑብኝ መልሼያለሁ፡፡ አሁን የራሴን ጥሩ ስራ እየሠራሁ ነው፡፡ ሞያን ለሞያተኛ ስላልኩሽ በተቻለ መጠን በቃሌ እገኛለሁ፡፡ በተረፈ ከዱባይ ያመጣኋቸው የራሴ ካሜራና የስቱዲዮ እቃዎች አሉ፡፡
ወደ 22 ማዞሪያ አካባቢም የራሴን ስቱዲዮ እየገነባሁ ነው፡፡ ለቲቪ የሚሆኑ ተከታታይ ትምህርታዊ ድራማዎችን ጽፌያለሁ፤ አሁን ወደ ቀረፃ እንገባለን፡፡
ከዳይሬክቲንግ ጋር የተያያዘ ትምህርት ወይስ ስልጠና ወስደሃል?
እስከ 12ኛ ክፍል ተምሬ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ነጥብ ነበር ያመጣሁት፡፡ ነገር ግን ፍላጐቴ የበለጠ በአርት ስለተሳበ፣ በአፍሪካ እየተዘዋወሩ የዳይሬክቲንግ ኦፍ ፎቶግራፊ ስልጠና የሚሰጡ ጀርመኖች ጋር ባጋጣሚ ስለተገናኘሁ ለአንድ አመት ከስምንት ወር በኤዲቲንግ፣ ስክሪፕት ራይቲንግ (የፊልም ፅሁፍ አፃፃፍ) እና ተያያዥ ስልጠናዎች ወሰድኩ፡፡ ከዚህ ባለፈ ወደፊት በአገሬ ያሉትን የቅኔና የዜማ ውዳሴ ትምህርቶች በስልጠና በማዳበር ማሳደግ፣ በውስጡ ያለውን ነገር የበለጠ ለማወቅ መማር ይሆናል አላማዬ፡፡
የምታደንቀው የአገር ውስጥ ፊልም፣ ቪዲዮ ክሊፕና ዳይሬክተር?...
ከድሮዎቹ የጥላሁን ገሠሠን (ፈልጌ አስፈልጌ ያን ሰሞን የጣኋት) የመልካሙ ተበጀን (ደህና ሁኚ ፍቅሬ) የሚለውን ዘፈን ዳይሬክት ያደረጉ ባለሙያዎች ለኔ ድንቅ ነበሩ፡፡
ከዳይሬክተር ኃይሌ ገሪማና ታጠቅ ትልቅ ባለሙያዎቼ ናቸው፡፡ ከልብና በፍቅር ሙያቸውን ይሰሩታል፡፡ ካሁን ደግሞ በባህላዊ ዘፈኖች የገጠሩን ህይወት በሚያንፀባርቅ መልኩ አጉልተው የሚያሳዩ ወጣት ዳይሬክተሮች ለኔ ጀግናዎች ናቸው፡፡ ከዘመናዊ ዘፈን ዳይሬክቲንግ የዘሪቱ ከበደን ዳይሬክት ያደረገው
“ወደ መጣሁበት” የሚለው ፊልም መታየት ከጀመረ በኋላ እንደገና ወርዶ እንደተሰራና “እየሩስ” ተብሎ እንደወጣ ይታወቃል” ለምንድነው?
ፕሮዲዩሰሩ ነው ይህን ያደረገው፡፡ የተጨመሩና የተቀነሱ ነገሮች ነበሩ፡፡ እንደገና እንስራው ብሎኝ ነበር፤ ግን እኔ አልፈለግሁም፡፡

Read 6835 times Last modified on Saturday, 15 December 2012 15:38