Saturday, 08 December 2012 14:31

‹‹...እውቀት በገንዘብ አይገዛም...››

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(2 votes)

‹‹ኤችአይቪ ሀብታሙንም ደሃውንም ይይዛል ... ደሀውን ግን ይገድላል፡፡›› ዶ/ር ይፍሩ ብርሀን
ባለፈው ሳምንት እትም በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዘንድ ያለውን ለኤችአይቪ መጋለጥ ሁኔታ መሰረት በማድረግ እውነታውን ለማወቅና ለንጽጽርም እንዲረዳ በሀገሪቱ በሚገኙ አምስት ዩኒቨርሲቲዎች ጥናት መደረጉን እና የተገኘው ውጤትም ተመሳሳይ እንደነበር ዶ/ር ይፍሩ ብርሀን የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና የጥናቱ ተሳታፊ አብራርተዋል፡፡ ጥናት የተደረገባቸው ዩኒቨርሲቲዎችም መቀሌ ፣ጎንደር፣ ጅማ ፣ሐሮማያ እና ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ካምፓሶች እንደነበሩ ተጠቅሶአል፡፡ ለማስታወስ ያህልም በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በመማር ላይ የሚገኙ ተማሪዎች የግብረስጋ ግንኙነት መፈጸም የሚጀምሩት አንዳንዶቹ ገና በአንደኛ ደረጃ ተማሪነት እያሉ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከገቡ በሁዋላ ነው፡፡ በእርግጥ ወደዩኒቨርሲቲ ከገቡ በሁዋላ ለወሲብ ድርጊት የተገፋፉ መኖራቸውም አይካድም፡፡

ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ከገቡ በሁዋላ ለምን ወደ ወሲብ ድርጊት ይገፋፋሉ የሚል ጥያቄ ሲነሳ የብዙዎች መልስ ተማሪዎቹ ባላሰቡት ሁኔታ ከቤተሰብ ቁጥጥር ነጻ ስለሚሆኑ ነው የሚል ይሆናል፡፡ በእርግጥ የተወሰነ እውነታ ቢኖረውም እንደጥናት አቅራቢዎቹ ከሆነ በአብዛኛው ችግሩ የሚከሰተው ተማሪዎቹ ከሚገባቸው በላይ ገንዘብ እጃቸው ላይ የሚገላበጥ ከሆነ ነው የሚል ይሆናል፡፡
በአለማችን ከኤችአይቪ ኤይድስ ጋር ይኖራሉ ተብለው ከሚገመቱት ሰዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሴቶችና ልጃገረዶች ወይንም ሴት ሕጻናት መሆናቸውን ጥናቶች ይፋ አድርገዋል፡፡ (ሕጻን ማለት እንደአለም አቀፍ ትርጉዋሜው ከአስራ ስምንት አመት በታች ማለት ነው፡፡) ለኤችአይቪ ኤይድስ በከፍተኛ ሁኔታ የሚጋለጡ ሴቶችን በሚመለከት አፍሪካን ጨምሮ በ28 ባላደጉ ሀገራት የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ከሰሃራ በታች ባሉት የአፍሪካ ሀገራት በተገኘው ውጤት ከወንዶች ይልቅ ሴቶቹ በቫይረሱ የሚያዙ ሲሆን ለዚህም ልቅ የሆነ የግብረስጋ ግንኙነትን መፈጸም እንደዋና ምክንያት የተቀመጠ ነው፡፡ ጥናቱ በተደረገባቸው ሀገራት በቫይረሱ ከሚያዙ ሴቶች 3/4ኛዎቹ የሚሆኑት ጥንቃቄ የጎደለው ወሲብ የሚፈጽሙ ሲሆን የስራ ማጥት ትምህርትን አለመማር ከዚህም ጋር ተያይዞ የሚከሰተው ድህነት ለቫይረሱ እንዲጋለጡ ተጽእኖ እንደሚያደርግ የጥናቱ ውጤት ያሳያል፡፡
በኢትዮጵያ ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር ተያይዞ ከተደረጉ ጥናቶች በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የተደረገው ጥናት አንዱ ነው፡፡ የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ከአባላዘር በሽታዎች መተላለፍ (ኤችአይቪን ይጨምራል) ጋር በተያያዘ በጥናቱ የተካተቱት ተማሪዎች በሰጡት መልስ ፡-
* ወሲብ የሚፈጽሙት ጥንቃቄ በጎደለው መልኩ መሆኑን እና ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል ምንም መከላከያ እንደማይወስዱ ያመለክታል፡፡
* በእርግጥ ይላል ጥናቱ...ወንድና ሴት ወጣቱ መወዳጀታቸው በሌላ በኩል የሚደገፍ ነው፡፡ የዚህም ምክንያቱ፡-
* ፍቅርን በተግባር መተርጎምን እና መቀራረብን ፣አንዳቸው የሌላኛውን ፍላጎት መረዳትን ፣ቅርበትን መፍጠርን ይማሩበታል፡፡
* ስለወደፊቱ ሕይወታቸው ማቀድ የሚጀምሩበት እድሜ ስለሆነ እንደጥሩ አጋጣሚ ይጠቀሙበታል፡፡
* አብሮ በመኖር ረገድ በጎና ክፉውን የሚለዩበት እድሜያቸው ላይ በመሆናቸው ጊዜውን ሳያባክኑ መጠቀማቸውን ያሳያል ፡፡
ከላይ የተጠቀሰው በጎ ነገር እንዳለ ሆኖ ነገር ግን ወሲብን ካለጊዜው ጥንቃቄ በጎደለው እና ልቅ በሆነ መንገድ መፈጸማቸው ኤችአይቪን ጨምሮ ለተለያዩ የአባላዘር በሽታዎች ሊያጋልጣቸው ከመቻሉም በተጨማሪ ላልተፈለገ እርግዝናና ለተለያዩ የማህጸን በሽታዎች ሊያጋልጣቸው እንደሚችል መጠንቀቅ ይባቸዋል ፡፡
እንደውጭው አቆጣጠር በ2005 በኢትዮጵያ ተካሂዶ የነበረው ጥናት እንደሚያመለክተው በጥናቱ ከተካተቱት 9.9ኀ ያህሉ በእድሜያቸው ከ15-19 አመት የሚደርሱ መላሾች ..14.6ኀ ከወንዶቹ እና 5.3ኀ ከሴቶቹ.. የወሲብ ድርጊትን እንደጀመሩ ገልጸዋል፡፡ ከነዚህ መላሾች ውስጥ 31.2ኀ ከወንዶች እና 2.7ኀ ከሴቶቹ ወሲብን ከተለያዩ ሰዎች ጋር እንደሚፈጽሙና 38.5ኀ ያህል ደግሞ ካለ ኮንዶም ወሲብ እንደሚፈጽሙ መስክረዋል፡፡
በኢትዮጵያ በሐዋሳ ፣በጅማ፣ በሓሮማያ፣ በጎንደር እና በመቀሌ ዩኒቨርሲቲዎች በተደረገው ጥናት የኮንዶምን አጠቃቀም በሚመለከት የተገኘው ምላሽ እንደሚያሳየው...በጥናቱ ከተካተቱት 3/4ኛ ያህሉ 74.7ኀ የወሲብ ግንኙነትን እንደሚፈጽሙና ኮንዶምንም እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህ መላሾች ውስጥ 38.2ኀ ያህል ወንድና ሴት ልጆች ኮንዶምን የተጠቀሙት ወሲብን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲፈጽሙ ሲሆን ቀሪዎቹ 56.6ኀ የሚሆኑት ደግሞ ኮንዶም ሁልጊዜ እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል፡፡ የተቀሩት ማለትም 43.4ኀ የሚሆኑት ደግሞ አልፎ አልፎ እንደሁኔታው መመቻቸት ወይንም አንድ ጊዜ ብቻ እንደተጠቀሙ መልስ ሰጠተዋል፡፡ ከመላሾቹ ወደ 22.6ኀ የሚሆኑት ደግሞ ወሲብን ከኮንዶም ውጭ እንደሚፈጽሙ ገልጸዋል፡፡ ኮንዶምን ላለመጠቀም ምክንያት ብለው ተማሪዎቹ ከዘረዘሩዋቸው ውስጥ ጉዋደኛን ማመን ፣ኮንዶምን በመጠቀም ምክንያት ምቾት አለማግኘት ፣ኮንዶምን በቀላሉ አለማግኘት የሚሉ የሚገኙበት ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ አስፈላጊ መሆኑን እንደማያምኑበት እና ለዚህም ምክንያታቸው ወሲብን ለመፈጸም በአጣዳፊ ሁኔታ ላይ እንደነበሩ ይገልጻሉ፡፡ ሌሎቹ ምክንያቶች ደግሞ ጉዋደኛዬ ኮንዶም መጠቀምን አይፈልግም ወይም አትፈልግም የሚል እና ሁለታችንም ጉዋደኛሞቹ ከኤችአይቪ ቫይረስ ነጻ ስለሆንን ኮንዶም መጠቀም አያስፈልገንም ወይንም ኮንዶም የወሲብ ስሜትን ይቀንሳል ፣ኮንዶምን እራሱን አላምነውም የሚል እና ኮንዶም መጠቀም ያሳፍረኛል የሚሉ ምላሾች ከብዙ በጥቂቱ ተሰጥተዋል ፡፡ ኮንዶምን በመ ጠቀም ረገድ ባለው የተሳሳተ ግንዘቤ ስለሚያስወግዱና ጥንቃቄ የጎደለው ወሲብ ስለሚፈጽሙ ተማሪዎቹ ለተለያዩ የአባላዘር በሽታዎች ..ኤችአይቪን ጨምሮ .. እና ላልተፈለገ እርግዝና በመጋለጥ በሚከተለው ውጤት ትምህርታቸውን የሚያቋ ርጡ እና ለተለያዩ የስነተዋልዶ ጤና ችግር እንደሚጋለጡ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡
ዶ/ር ይፍሩ ብርሀን የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት እንደሚገልጹት በተለይም ጥሩ ገንዘብ ከሚያገኙ ቤተሰቦች ማለትም የወር ገቢያቸው ከሶስት ሺህ ብር በላይ የሆነና ተማሪዎቹም በወር ከሶስት መቶ ብር በላይ የሚላክላቸው ከሆነ ይበልጡኑ ለኤችአይቪ ቫይረስ እንደሚጋለጡ በአምስቱ ዩኒቨርሲቲዎች ..በሐዋሳ ፣በጅማ፣ በሓሮማያ፣ በጎንደር እና በመቀሌ.. የተደረገው ጥናት ያሳያል፡፡ ቀደም ሲል እንደሚገመተው ለቫይረሱ የሚጋለጡት በኑሮአቸው አነስተኛ ደረጃ ላይ ያሉ እና ያልተማሩ ናቸው የሚል ሲሆን የዚህ ግምት መነሻም በኑሮ አነስተኛ የሆኑት ሰዎች ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ከሚከሰትባቸው ሕመም ለማገገም አቅም ስለማይኖራቸው እና ስለሚሞቱ ነው፡፡ ነገር ግን በኑሮአቸው በጥሩ ሁኔታ ላይ ያሉ እና የተማሩ ሰዎች ቫይረሱ ቢኖርባቸውም ለራሳቸው አስፈላጊውን ጥንቃቄ ስለሚያደርጉ በጤንነት ይቆያሉ ፡፡ በአጭሩ ..ኤችአይቪ ሀብታንም ይይዛል ነገር ግን ደሃውን ይገድላል.. ብሎ መደምደም ይቻላል... ብለዋል ዶ/ር ይፍሩ፡፡ ማወቅና መተግበር የተለያዩ ነገሮች እንደመሆናቸው በተለይም በቫይረሱ የመተላለፊያ ዘዴዎች ላይም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ በቂ እውቀት ያላቸው ሰዎች የባህርይ ለውጥ ለማምጣት ይቸገራሉ፡፡
በአምስቱም.. መቀሌ ጎንደር ሐዋሳ ሐሮማያ ጅማ.. ዩኒቨርሲቲዎች በጥናት የተካተቱት ተማሪዎች ወሲብን እና ሱስ አስያዥ እጾችን አጠቃቀማቸው አንድ አይነት መሆኑ በጥናት የተረጋገጠ ሲሆን የተማሪዎቹም አቅምና ልምድ ተመሳሳይ ነበር፡፡ ከተማረ ቤተሰብ የወጡ፣ በትምህርት ላይ እያሉ ጠቀም ያለገንዘብ የሚላክላቸው፣ ወሲብን ገና ዩኒቨርሲቲ ሳይገቡ የጀመሩ ፣ሱስ አስያዥ እጾችን ..ጫት እና ሲጋራ.. ቀደም ሲል የጀመሩና ዩኒቨርሲቲ ከገቡ በሁዋላ በዋጋው ከበድ ወዳለው ሺሻ ወደተባለው ያሳደጉ ፣በየምሽት ቤቱ የሚሄዱ እና ፖርኖግናፊ ፊልም የሚመለከቱ ፣ጥሩ ገቢ ካላቸው እና ከተማሩ ቤተሰቦች የወጡ ናቸው፡፡ በኑሮአቸው ዝቅተኛ ደረጃ ከሆኑ ቤተሰቦች የተገኙትእና እጃቸው ላይ በቂ ገንዘብ የሌላቸው ተማሪዎች ግን በዩኒቨርሲቲው የሚዘጋጀውን ምግብ በመመገብ እና በትምህርት ተቋሙ ተወስነው የሚጠበቅባቸውን የትምህርት ክትትል ከማድረግ በስተቀር አጉዋጉል ባህርይ አይስተዋልባቸውም ማለት ይቻላል፡፡ በእርግጥ በባህሪያቸው የታነጹ ጥሩ ገንዘብና እውቀት ያላቸው ልጆች እንደማይታጡ ሁሉ በኑሮአቸው ዝቅተኛ ሆነውም የሚማግጡ አልፎ አልፎ እንደሚኖሩ አይካድም፡፡እንደ ዶ/ር ይፍሩ ብርሀን ማጠቃለያ .. እውቀት በገንዘብ አይገዛም.. ፡፡ ወላጆች ልብ ሊሉት የሚገባ ነገር አለ፡፡ ልጆቻቸው ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡላቸው በርከት ያለ ብር እየመደቡላቸው ከሆነ ልጆቻቸውን ወደየት አቅጣጫ ሊመሩዋቸው እንደሚችሉ አስቀድመው መገመት እና ማስተዋል ይጠበቅባቸዋል፡፡ አንድ/ዲት ተማሪ በትክክለኛው መንገድ ሊጠቀምበት/ልትጠቀምበት ከሚገባው/ት በላይ ገንዘብ በእጁ/ዋ ካለ አላስፈላጊ መዝናናትን ከመሰሎቹ/ዋ ጋር በመፈጸም ወደተሳሳተ አቅጣጫ ሊጉዋዝ/ልትጉዋዝ ይችላል/ትችላለች፡፡ ለዚህ ቤተሰብ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡
ተማሪዎች ለትምህርት በሚሄዱባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ውጤታማ ሆነው እንዲመለሱ ቤተሰብ ሊያደርግ የሚገባውን እገዛ ከልክ በላይ ሳይሆን በተገቢው መንገድ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ እንደዚሁም ተማሪዎቹ ወደ ዩኒቨርሲቲ ከመግባታቸው አስቀድሞ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በሚኖሩበት ጊዜ ልጆች ናቸው በሚል እሳቤ ብቻ ከምንም ነገር ነጻ ናቸው ብሎ መደምደም የዋህነት መሆኑንና ወላጅ አስቀድሞውኑ በቂ ክትትል በማድረግ የልጆቹን ማንነት ማረጋገጥ አለበት ብለዋል ዶ/ር ይፍሩ ብርሀን በሀዋሳ ሆስፒታል የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት፡፡

Read 5036 times