Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 15 December 2012 12:30

የተጠማ ከፈሳሽ - የተበደለ ከነጋሽ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ሉ ሱን የተባለው የቻይና ገጣሚ የፃፈውን ግጥም ፀሐፌ-ተውኔት ገጣሚ መንግሥቱ ለማ ወደ አማርኛ መልሰውታል - “ሐሳብን ለመግለፅ” በሚል ርእስ፡፡ ይህን ግጥም በስድ ስናስበው የሚከተለውን አይነት ጭብጥ ይዞ እናገኘዋለን፡፡ ስለዚህም እንዲህ እንተርተዋለን፡፡
ተማሪ አስተማሪውን ይጠይቃል፡፡
“መምህር ሆይ! አንድ የቸገረኝ ነገር ገጥሞኛል”
“ምን ገጠመህ የኔ ልጅ?”
“ላስረዳዎት” ይልና ሁኔታውን እንደሚከተለው ያስረዳል፡-

ከእለታት አንድ ቀን አንድ የንጉሥ ልጅ ይወለዳል፡፡ ትላልቅ መኳንንትና መሳፍንት፣ ጨዋ ጨዋ ባላባቶች እንዲሁም ያገር ሽማግሌዎች ንጉሡን “እንኳን ደስ አለዎ!” ለማለት ወደ ቤተመንግሥት ይመጣሉ፡፡ ከዚያም እያንዳንዳቸው እየተነሱ ለልጁ ያላቸውን የመልካም እድል መግለጫ ይናገራሉ፡፡ በመጀመሪያ አንድ መኳንንት ይነሱና፡-
“ንጉሥ ሆይ! ይሄ ልጅ ጄኔራል ይሆናል! ይደግ ይመንደግ!” ይላሉ
ቀጥሎ ሌላ አዛውንት ይነሳሉ፡፡
“ንጉሥ ሆይ! ይህ ልጅ ሊቅ አዋቂ ነው የሚሆን! አምላክ አዕምሮውን ብሩህ ያድርግለት! ይደግ ይመንደግ!” ብለው ይቀመጣሉ፡፡
ሌላው ያገር ሽማግሌ ይነሱና፤
“ንጉሥ ሆይ! ይህ ልጅ ይቺን አገር ሚዛናዊ አስተዳደር ሰጥቶ፣ ፍትሐዊ መንገድ ተጠቅሞ፣ የህዝቡን ችግር ባግባቡ እየፈታ ወደፊት አገራችን የምድር ገነት ትሆን ዘንድ በትክክል የሚመራ ታላቅ ንጉሥ ይሆናል!” አሉ፡፡ በዚህ አይነት ብዙዎች ደስታቸውን ይገልጣሉ፡፡ ንጉሡም አፀፋውን በፈገግታ ይመልሳሉ፡፡
በመጨረሻ፤ አንድ የአገር ፈላስፋ ነው የሚባል ሊቅ ይነሳል፡፡
“ንጉሥ ሆይ! እንኳን ደስ አለዎ፡፡ ሺ ዓመት ያንግሥዎ! ብሩህ ህሊና ይስጥዎ! ህዝብ ልቡን አይንፈግዎ! እኔም እንደሌሎቹ ከኔ በፊት እንደተናገሩ አባቶቼ አስተያየቴን እንድሰጥ፣ ሃሳቤን እንድገልጥ እድል ስለተሰጠኝ አመሰግናለሁ፡፡
እርግጥ ነው ሌሎቹ ተናጋሪዎች እንዳሉት ይህ ልጅ ጄኔራል፣ ሊቅ፣ ታላቅ ንጉሥ ወዘተ. ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም፤ የንጉሥ ልጅም ቢሆን፣ ዞሮ ዞሮ ያው ሰው ነውና አንድ ቀን ይሞታል!” አለ፡፡
የተሰበሰበው ሰው ሁሉ በተናገረው ተናደደ፡-
አንዱ - “ሟርተኛ! ሟርተኛ ነው ይሄ!” አሉ
ሌላው - “ጥቁር ምላስ! ይሄ አርባ መገረፍ ነው ያለበት!” አሉ፡፡
ደሞ ሌላው - “በጅራፍ መቆንደድ አለበት! ቀላማጅ! ጋጠ-ወጥ! ክብረ-ነክ ንግግር ማስቀጣት አለበት!” አሉ
በተራ በተራ እየተነሱ እርግማን አወረዱበት!
ተማሪው ይህንን ታሪክ ለአስተማሪው ከተረከ በኋላ ተማሪው እንዲህ ሲል ጠየቀ፡፡
“መምህር ሆይ! ራሴን በፈላስፋው ቦታ አስቀምጬ ሳየው - ውሸት ተናግሬ ህሊናዬን ማሰቃየት አልፈልግም፡፡ እውነት ተናግሬ ደግሞ እርግማንና ጅራፍ እንዲወርድብኝ አልፈልግም፡፡ ምን ማድረግ ነው ያለብኝ?”
መምህሩም፤
“አየህ ልጄ እንዲህ ያለ ነገር ሲያጋጥምህ፤ እንዲያው በደፈናው
‘ኦሆሆ አሃሃ!
አሃሃ ኦሆሆ!’
እያልክ እየሳቅህ መውጣት ብቻ ነው የሚያዋጣህ!” አሉት
***
ሃሳብን ለመግለፅ መቻል መታደል ነው፡፡ የመናገር ነፃነት፣ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት፣ የመሰብሰብና የመደራጀት ጉዳዮች ሁሉም የዲሞክራሲ ልጅ-ልጆች ናቸው፡፡ የከፋው ኢ- ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት “ኦሆሆ አሃሃ!” ማለትንም እንደማይፈቅድ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ አንዳንዴ የተከለከለውን በማየት የተፈቀደውን የማየት እድል ይገኛል፡፡ በ125ኛ አመቷ የአዲስ አበባ ሽንት ቤት መቆሸሽ እጃችንን እንድንታጠብ አረገን - ይመስገነው! (ፈረንጆች A Blessing in disguise የሚሉት አይነት ነው)
ተበታትኖ ማሰብ የሃሳብ ልዩነትን ለማየት የሚያግዘንን ያህል፤ አንድ ላይ ሆነን ማሰብ የአንድነትን ጉልበት ያሳውቀናል፡፡ ዞሮ ዞሮ አንድነትም ልዩነትም በህብር መያዝ ያለባቸው የዲሞክራሲ ገፅታዎች ናቸው፡፡ ፈረሱን በትክክል መጋለብ የምንችለው ልጓሙን ለሌሎች ካልለቀቅን ነው - ይላሉ አበው፡፡ ሃያላን መንግሥታት ወይም በዱሮ ስማቸው “የውጪ ሃይሎች” ከአፍሪካ ቅርጫ ዘመን (Scramble for Africa) ጀምሮ፣ አገር አጥኚዎቹም፣ አገር “አቅኚዎቹም”፤ ቅኝ-ገዢዎቹም፣ የእጅ አዙር ገዢዎቹም - “ዛሬም እኛን?!” አሉ እንደሚባሉት አርበኛ፣ ‘ዛሬም አፍሪካን?’ መባል ያለባቸው ጊዜ ነው፡፡ ቱሪስትና ፒስኮር መለየት አለብን፡፡
ዱሮ ዱሮ ሽማግሌው ማርክስ From Potato Sacks to smashed potato የሚለው ነገር ነበረው፡፡ ከድንች ከረጢት አንድ ላይ ወደተፈጨ ወይም ወደተደቆሰ ድንች መሸጋገር እንደማለት ነው፡፡ ገልብጠንም ብናየው ከተፈጨ ድንች ወደ ከረጢት መክተትም ቢሆን፤ ዞሮ ዞሮ ሃያላን አገሮች ለአገዛዝ እንዲመቻቸው አንዴ በከረጢት አስረው፣ አንዴ ሁላችንንም አንድ ላይ ፈጭተው እንደሚያበጃጁን ነው ፅንሰ-ሃሳቡ እሚነግረን፡፡ የዱሮ ፈሊጥ ነው፡፡ የዱሮ ስሙ The New Regional Order ነው፡፡ አዲሱ አህጉራዊ አበጃጀት የሚባለው ይሄው ነው!
የመስፋት ወይም የመሸንሸን ጉዳይ ነው - ዞሮ ዞሮ ለመግዛት ወይ ለመሸጥ ነው - ይሏል፡፡ የአፍሪካ አገሮች በባኮ በባኮ ይቀመጡ ወይስ በችርቻሮ ለመሸጥ እንዲመቹ ነጠላ ነጠላ ሆነው ይቀመጡ? አይነት ጥያቄ ነው፡፡ “እንዲህ እያልሽ ውቴልሽን ሽጪ” ይላል ወሎ ያልሆነ ብልጥ ነገር ሲገጥመው፡፡
የምሁራን ሚና በተለይ ዛሬ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ለውጥ ይመጣ ዘንድ ለዋጭ አዕምሮ ያስፈልገናል፡፡ ጉዳዩን የሚያውቅ ምሁር ካልተሾመ ስንደናቆር መኖራችን ነው፡፡ አበው ገጣሚያን፤
“ድንጋይ በድንጋይ ላይ የነበረ ሹመት
ሊቅ ፈልጐ መጣ ገባ ‘ተማሪ ቤት”
አሉ ይባላል አዋቂ ሰው በተሾመ ሰአት፡”
አርበኝነት ወይም ሽፍትነት እንደሙያና እንደመፍትሄ ይቆጠር በነበረበት ዘመን፤ ሁሉም ትምህርቱን እየተወ ወደ ጦርነት ይሄድ ነበረና አበው ገጣሚያን፤
“ግቢ ተማሪ ቤት ተመለሺ ቅኔ
ወንዶች እዋሉበት እውላለሁ እኔ!”
አሉ ይባላል፡፡
ወደ እውቀትም ወደ ሽፍትነትም የሚኬደው ወይም የተኬደው፤ የአገርን ችግር ለመፍታት ነው፡፡ መሪዎች፣ ኃላፊዎች፣ አለቆች፣ ፖለቲከኞች ይሰሙ ዘንድ ጆሮ፣ ያዩ ዘንድ ዐይን ተሰጥቷቸዋል፡፡ ካልተጠቀሙበት አባክነውታል፡፡ ህዝቦች ሃሳባቸውን ይገልፁ ዘንድ ቅን ልቦና አላቸው - የተጠማ ከፈሳሽ፣ የተበደለ ከነጋሽ - ፈውሱን ማግኘት ይሻል፡፡ የህዝብን ችግር እናዳምጥ - የፖለቲካም ይሁን፣ የኢኮኖሚም ይሁን፣ የሃይማኖትም ይሁን የባህል፤ እናዳምጠው!!

Read 6581 times