Print this page
Saturday, 15 December 2012 12:43

‘እረፍት’ የሚያሳጡ ነገሮች…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(10 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ይቺን አንድ ቦታ ላይ ያነበብኳትን ስሙኝማ…
እግዜሐር በመጀመሪያ መሬትን ፈጠረና እረፍት አደረገ፡፡
ከዚያም እግዜሐር ወንድን ፈጠረና እረፍት አደረገ፡፡
ቀጥሎ እግዜሐር ሴትን ፈጠረ፡፡ ከዛ ጊዜ ጀምሮም እሱም ሆነ ወንድ እረፍት አግኝተው አያውቁም፡፡
ይህች የምድረ ‘ሾቭኒስት’ ተረት መሆን አለባት፡፡ እርግጥ ‘እረፍት ማጣቱ’ ያለ ቢሆንም ይህን ያህል አይጋነንማ! ቂ…ቂ…ቂ…የምር ግን የሚያሳዝነው ምን መሰላችሁ…አሁን፣ አሁን ይህን ተረት እውነት የሚያስመስሉ እንትናዬዎች መብዛታቸው፡፡ እንደው እንግዲህ ጨዋታም አይደል… የሆኑ ታሪኮችን ስትሰሙ ወይም ራሳቸሁ በዓይናችሁ በብረቱ ስታዩ (‘ይሉኝታ’ በስህተት ከአበባ ኤክስፖርት ጋር ካርቶን ውስጥ ተከትቶ ተልኮ እንደሆነ ይታይልንማ!)

የሆነ ውሉን የለቀቀ ነገር ያለ አይመስላችሁም! ለምንድነው በጣም ውድ የሆኑ ማህበራዊ እሴቶች ሲፈራረሱ ግድ የሚሰጠን ሰዎች የማንታየው! “እሷ እኮ የወለደች የከበደች ሴት ወይዘሮ ነች…” መባል ክብርና ጌጥ የሆነበት ዘመን እየሳሳ ሲሄድ የምር አስቸጋሪ ነው፡፡
“እሱ እኮ አራት ልጆች ያሉት አባወራ ነው…” አይነት የአከብሮት አባባል “እና ምን ይጠበስ!” አይነት መልስ የሚያሰጥበት ዘመን መድረስ የምር አሳሳቢ ነው፡፡
‘ናይት ላይፍ’ የሚወዱ ወዳጆቼ “ሰዶምና ገሞራ ማለት ይቺዋ የእኛ ከተማ ነች” ይሉኛል፡፡ የምር ግን ‘ይሉኝታ’ እኮ…አለ አይደል…የሚጎዳ ገጽታ እንዳለው ሁሉ አሪፍ ነገርም ነው፡፡ በአደባባይ የህብረተሰቡን ልማድና ባህል ችላ እያልን ‘እንደፈለግን ከመሆን’ የሚያድነን እኮ ‘ይሉኝታ’ ነበር፡፡ (‘ነበር’ የምትለዋ ቃል በሰዋስው ‘ሀላፊ ጊዜ’ ነች፣ አይደል!)
የሰዉን ሁኔታ ታዩና…አንዳንዴ ስታስቡት…አለ አይደል… “እነኚህ ሰዎች የእውነት ስምንተኛው ሺህ መድረሱን ሹክ ያላቸው ነገር አለ እንዴ!” ያሰኛችኋል፡፡ አሀ…ልክ ነዋ ምን ተገኘና ነው በሌላ ነገር የማንሞክረውን በእንትንና እንትን ነገሮች ‘የጋራ ተጠቃሚነት’ የበዛው፡፡
ስሙኝማ…
አትመልከች ሱፍ አትዪ መኪና
እኔም እገዛለሁ ዕድሌ ሲቃና
አይነት ዘፈን ከጥቂት ዓመታት በፊት ያለፈበት ምናምን ተብሎ ይታሰብ ነበር፡፡ አሁን ይኸው ነገርዬው ሁሉ ተለወጠና… አለ አይደል… ‘ዘሎ መኪና ላይ ጉብ’ አይነት ነገር እየሆነ ነው፡፡ አንድ ወዳጄ ምን አለኝ መሰላችሁ…መኪና በራሱ የማግኔትነት ሀይል አለው፡፡ ቀና ስትል አጠገብህ ከየት መጣች ከየት ሳታውቅ ምን የመሰለችው ቺክ ጉብ ብላ ታገኛለህ፡፡”
እናላችሁ…ዘመኑ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ሚስትና ልጆቹ ማታ እያዛጉ ሲጠብቁት ከቤድ ቤድ ሲዘል ግማሹን ሌሊት የሚጨርስ መአት አባወራ የበዛበት ዘመን ነው፡፡ የምትሰሟቸው ታሪኮች በእርግጥም ‘ፋክት ኢዝ ስትሬንጀር ዛን ፊክሽን’ የሚለውን ነገር የሚያረጋግጥላችሁ ነው፡፡ አለ አይደል…ሚስት “አንዴ ቤት ከገባች በኋላ…የት አባቷ ትሄዳለች…” በሚል አይነት ‘አዲስ ጉርምስና’ የሚጀምረው ወንድ በጸጉር ልክ ሊሆን ምንም አልቀረው፡፡
እናማ…“ቀጥሎ እግዜሐር ወንድን ፈጠረ፡፡ ከዛ ጊዜ ጀምሮም እሱም ሆነ ሴት እረፍት አግኝተው አያውቁም፣” ማለትም ያስኬዳል፡፡ ልክ ነዋ…አምደኚስቱ፣ ቦተሊካ ተንታኙ (ቂ…ቂ…ቂ… ያውም በኢትዮዽያ!) ቶክ ሾው አዘጋጁ ምኑም ምናምኑም በወንዶቹ ተሞላና የዛኛውን ወገን ድምጽ መስማት አልተቻለም፡፡
እኔ የምለው…ሚዲያው በእንደዚህ አይነት… አለ አይደል… ህብረተሰብን የሚያስተሳስሩ መሰረቶች ሲናጉ ምነው ‘አልኮነስረው’ አለ! የሩኒ ቁርጭምጭሚት ዘላለም ‘ሰበር ዜና’ ሆኖ መኖር አለበት እንዴ!
እናላችሁ…አስቸጋሪ ነገሮች እየበዙ እንዲሁም ዝምታችን በዛው ልክ እየበዛ ነው፡፡
ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው የለየለት ቁማርተኛ ነው፡፡
እናላችሁ… አንድ ምሽት እንዲሁ ሲጫወት ያነጋና ያለውን ቤሳ ቤስቲኒ በሙሉ ሙልጭ አድርገው ይበሉታል፡፡ እናላችሁ…ቤት ሲሄድ ለሚስቱ እንዲህ ይላታል፡፡ “ያለኝን ገንዘብ በሙሉ ስለተበላሁ ወጪያችንን ለመቀነስ የኑሮ ዘዴያችንን መለወጥ ይኖርብናል…” ይላታል፡፡ እሷም ምን ሊያመጣ ነው በሚል ዝም ብላ ታዳምጠዋለች፡፡
ታዲያማ ለወጪ ቁጠባ በሚል ምን ይላታል መሰላችሁ… “አንቺ ምግብ መሥራት በደንብ ብትለምጂ ወጥ ቤቱን ማባረር እንችላለን” ይላታል፡፡
እሷ ምን ብትለው ጥሩ ነው…“አንተ ደግሞ ፍቅር መሥራት በደንብ ብትለምድ አትክልተኛውን ማባረር እንችላለን፡፡” እንዲህ ናት ጨዋታ! አትክልት ኮትኩት ተብሎ ተቀጠረ እንጂ እንትን…ብቻ ተዉትማ! እንኳንም እኛ አገር አትክልተኛ መቅጠር ለሀብታም ብቻ ሆነ፡፡
እናማ…የዝምታው መብዛት አስገራሚ ደረጃ ላይ ደርሷል፡ የእንትን ቀን፣ የእንትን ቀን እየተባለ ባንዲራ መድረክ ላይ ከመስቀልና በክት ልብስ ምናምን አሸብርቆ… “የዛሬውን ቀን ልዩ የሚያደርገው…” እያሉ ለቴሊቪዥን ካሜራ በሚመች መልኩ ከመደስኮር በላይ ዓይናችን ስር ብዙ ነገሮች እየተበላሹ እያለ ዝምታው የምር የሚገርም ነው፡፡
እናላችሁ…ማን ከማን ያንሳል በሚል አይነት ‘ዘ ባትል ኦፍ ዘ ሴክስስ’ ቅልጥ ያለ ነው የሚመስለው፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ይቺን አውርተናት ከሆነም እንድገማትማ… ሰውየው ሁልጊዜ ሲጠጣ አምሽቶ ጥምብዝ ብሎ ነው የሚገባው፡፡ ሚስቱ ግራ ይገባትና አንድ ዘዴ ትዘይዳለች፡፡ አንድ ቀን እንዲሁ ጥምብዝ በሎ ሲመጣ ልታስደነግጠው ሰይጣን የሚያስመስላት አለባበስ ለብሳ ተደብቃ ልትጠበቀው ወሰነች፡፡
እሱም እንደለመደው በመጠጥ ጧ ብሎ ሲመጣ ከተደበቀችበት ጨለማ ውስጥ ድንገት ዘላ ትወጣበታለች፡፡
እሱ ሆዬ እንኳን ሊደነግጥ ምን አላት መሰላችሁ…“እባክህ አታስፈራኝም፣ እህትህ እኮ ሚስቴ ነች!” አለላችሁና ቁጭ፡፡
ታዲያላችሁ…በዛ ሰሞን ወዳጆቼ ጣጥ ብለው የሚገቡ ሚስቶች ቁጥር እየበዛ ነው ሲሉ ነበር፡፡ እዚህ አገር በእነኚህ አይነት ነገሮች ላይ ጥናት ማድረግ አልተለመደም እንጂ… ጥናት ቢደረግ ኖሮ ጉድ ነበር የሚወጣው፡፡
እኔ የምለው…የ‘ቦተሊከኞች’ ሥራ መግለጫ ማውጣትና ሪባን መበጠስ ብቻ ነው እንዴ! ልክ ነዋ…የህብረተሰቡን መሰረት የሚያናጉና ለመጪው ትውልድ እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮች እየበዙ ስለሆነ የሆነ ነገር እንዘይድ…” ምናምን አይባልም! በሆነው ባልሆነው ቁጥር መጥራት ብቻ እኮ ምንም ማለት አይደለም! (“ምነው ሸዋ!” ይሉ ነበር እናቶቻችን፡፡)
የ‘ቦተሊካ’ ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ትንሹ ልጅ አባቱን “አባዬ፣ ፖለቲካ ማለት ምን ማለት ነው?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ አባትዬውም እንዲህ ሲል ይመልስለታል፡፡
“የእኔ ልጅ፣ ይህንን ለማስረዳት አስቸጋሪ ነው፡፡ ግን እስቲ ልሞክር፡፡ ለምሳሌ ሠርቼ ገንዘብ የማመጣው እኔ ስለሆንኩ ካፒታሊዝም ነኝ እንበል፣ እናትህ የገንዘቡን ወጪ ስለምትቆጣጣር መንግሥት ነች እንበል፣ የእኛ ሀላፊነት ያንተን ፍላጎት መጠበቅ ስለሆነ አንተን ደግሞ ህዝብ ነህ እንበል፣ ሞግዚቷ የሠራተኛው መደብ ነች እንበል፣ ትንሹ ወንድምህን ደግሞ መጪው ጊዜ እንበለው፡፡ እስቲ ይሄን አስብና ስሜት ይሰጥ እንደሁ ተመልከት…” ይለዋል፡፡ ልጁ አባቱ ስለነገረው ነገር እያሰበ ሄደ፡፡ ያን ዕለት ሌሊት ትንሽ ወንድሙ ሲያለቅስ ሰማና ተነስቶ ወደ ክፍሉ ሄደ፡፡ ትንሹ ልጅ ሽንቱን ሸንቶ ስለነበር ዳይፐሩ በጣም እርሶ ያያል፡፡ ወደ ወላጆቹ ክፍል ሲሄድ እናቱ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወስዷታል፡፡
እሷን ላለመቀስቀስ ብሎም ወደ ሞግዚቷ ክፍል ይሄዳል፡፡ በሯ ተቆልፎ ስለነበር በቁልፍ ቀዳዳ አጮልቆ ሲያይ አባቱ ሆዬ ከሞግዚቷ ጋር ተኝቶ ፍቅር ሲሠራ ያያል፡፡ ተስፋ ይቆርጥና ወደ ክፍሉ ተመልሶ ይተኛል፡፡
በማግስቱ ልጅየው ለአባቱ “አባዬ፣ አሁን ፖለቲካ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ገብቶኛል፣” ይለዋል፡፡ አባትየው ደስ ይለውና “ጎሽ የእኔ ልጅ፣ እስቲ ፖለቲካ ምን እንደሆነ ንገረኝ” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ልጁ ምን አለው መሰላችሁ…“ፖለቲካ ማለት ካፒታሊዝም ከሠራተኛው መደብ ጋር ተኝቶ ፍቅር ሲሠራ፣ መንግሥት ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወስዶታል፣ ህዝቡ ተረስቷል፣ መጪው ጊዜ ደግሞ በሽንት እርሷል” አለውና ቁጭ አለላችሁ፡፡
እኔ የምለው… እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ…ይሄ የኳስ ነገር፣ በዛ ሰሞን “ከሠላሳ ምናምን ዓመት በኋላ…” ምናምን እያልን ስንፈነጥዝ ልከ ከአዲስ አበባ እስከ ሞያሌ የሚደርስ ስፋት ያለው የዘይት ጉድጓድ ያገኘን አስመስለነው ነበር፡፡ ከዛ ትንሽ ቆየና ደግሞ “ዝግጅቱ የታለ የተጀመረው?” “ምነው ዝምታ በዛ…” ምናምን መባል ተጀመረ፡፡ አሁን ‘ዝግጅቱ ሲጀመር’ ደግሞ ልክ እንደ ዘይት መገኘት አይነት ነገር እንደገና ብቅ፣ ብቅ እያለ ነው፡፡ ቀዝቀዝ ማለት ያስፈልጋል…አለ አይደለ፣ ‘ቅጽሎቹ’ ትንሸ ቀነስ ቢሉ አሪፍ አይመስላችሁም!
እናላችሁ…በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡ እንዲሁ እንደ ቀልድ እያወራናቸው እየባሰባቸው ያሉ ነገሮች በዝተዋል፡፡ ‘ካፒታሊዝም’ም ሆነ ምንም የሚከተለው ነቃ ይበልልንማ፡፡እግዜሐር በመጀመሪያ መሬትን ፈጠረና እረፍት አደረገ፡፡ቀጥሎ እግዜሐር ሴትንና ወንድን ፈጠረ፡፡ ከዛ ጊዜ ጀምሮም እነሱም ሆኑ እግዜሐር እረፍት አግኝተው አያውቁም፡፡
እረፍት ከሚያሳጡ ነገሮች ይጠብቀንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 6824 times