Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 15 December 2012 12:45

በየዓመቱ 6 ሚሊዮን ሰዎች በስትሮክ ህይወታቸው ያልፋል ስትሮክ - ድንገተኛው አደጋና ቅጽበታዊው ሞት Featured

Written by 
Rate this item
(3 votes)

የሰውነታችን አጠቃላይ አዛዥና ተቆጣጣሪ በሆነው አንጐላችን ላይ በድንገት ተከስቶ ለአካል ጉዳተኛነትና ለሞት የሚዳርገው ስትሮክ፣ ዛሬ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የዓለማችን ህዝቦች አሳሳቢ የጤና ችግር ሆኗል፡፡
የዓለማችን ታላላቅ መሪዎችን ጨምሮ በርካታ ስመጥርና ተፅእኖ ፈጣሪ የተባሉ ሰዎችን ሁሉ በድንገት ለሞት አብቅቷል - ስትሮክ፡፡
ሰውነታችን የሚያከናውናቸውን ተግባራት በበላይነት የሚቆጣጠረውና ትዕዛዝ የሚያስተላልፈው አንጐላችን ጉሉኮስና ኦክስጅን በየደቂቃው በደም አማካኝነት እንዲደርሰው ያስፈልጋል፡፡ ይህ ስርዓት ተስተጓጐለ ማለት አንጐላችን ሙሉ በሙሉ ሥራውን አቆመ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሰውነት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል አለመታዘዝ ወይም በተለምዶ ፓራላይዝድ መሆን የምንለውን የጤና ችግር ያስከትላል፡፡

ይህ ድንገተኛ የሆነ የአንጐል የደም ስርጭት መቀነስ ወይም መቋረጥ ወይንም ደግሞ አንጐል ውስጥ ደም በመፍሰሱ ምክንያት የሚከሰተው የጤና ችግር (ሴረብረል ቫስኩላር አክሲደንት) ስትሮክ በሚል መጠሪያ ይታወቃል፡፡ በዓለማችን ላይ አካል ጉዳተኛነትን ከሚያስከትሉ የጤና ችግሮች በቀዳሚነት የሚታወቀውም ይኸው ስትሮክ የተባለው በሽታ ነው፡፡
በሽታው የዓለማችን ቀዳሚ የጤና ችግሮች ከሆኑት የካንሰርና የልብ በሽታዎች ቀጥሎ በሶስተኛነት ደረጃ ላይ የሚገኝና በርካቶችን ለሕልፈተ ህይወት የዳረገ በሽታ ነው፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ባወጣው መረጃ፤ በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ስድስት ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በየዓመቱ በስትሮክ ሳቢያ ለሕልፈተ ህይወት ይዳረጋሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑት ችግሩ ካጋጠማቸው ወቅት ጀምሮ እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ ጊዜ ውስጥ ለህልፈተ ህይወት የሚዳረጉ ናቸው፡፡
የዓለማችን ታላላቅ ሰዎችም የዚህ በሽታ ሰለባ ከመሆን አላመለጡም፡፡ ከእነዚህ መካከል በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የዓለምን የፖለቲካ ምህዋር በማሽከርከሩ ቀዳሚውን ሚና እንደተጫወቱ የሚነገርላቸው የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችል፣ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ፍራንክ ሩዝቬልት እና የቀድሞው የሶቭየት መሪ ጆሴፍ እስታሊን የዚህ በሽታ ሰለባዎች እንደነበሩና የሞታቸው መንስኤም ስትሮክ የተባለው በሽታ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያወሳሉ፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ፤ በዓለም ላይ በየዓመቱ ከሃያ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በስትሮክ በሽታ እንደሚጠቁ ጠቁሞ፣ በሽታው በታዳጊ አገራት ላይ በስፋት እየታየ መሆኑን ዘግቧል፡፡
እንደ አለም ጤና ድርጅት መረጃ፤ ከሰባት ዓመታት በኋላ በ2020 ዓ.ም እ.ኤ.አ በአለም ላይ ከሚከሰተው የስትሮክ በሽታ ¾ኛ ወይንም 75 በመቶ የሚሆነው በታዳጊ አገሮች ላይ ይከሰታል፡፡
እስከአሁን የሚታወቁት የስትሮክ አይነቶች ሁለት ናቸው፡ በአንጐል ውስጥ ደም በመፍሰሱ ሳቢያ የሚከሰተው ስትሮክ አንደኛው ሲሆን ሌላው ወደ አንጐል የሚደርሰው ደም ባለመድረሱ ምክንያት የሚከሰተው ስትሮክ ነው፡
ደም ወደ አንጐላችን የሚያደርሱት የደም ሥሮች በመበጠሳቸው ምክንያት በአንጐላችን ውስጥ በሚዘዋወረው ፈሳሽ ላይ ደም ይፈሳል፡፡ ይህ ሁኔታም ስትሮክን ያስከትላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የደም መርጋት ችግር ያለባቸው ሰዎች በየቦታው ደም ይፈሳቸዋል፡፡ ይህ ሁኔታ የተከሰተው በአንጐል ውስጥ ከሆነም በተመሳሳይ መንገድ ስትሮክን ሊፈጥር ይችላል፡፡
በአደጋ ምክንያት ጭንቅላት ከተመታም በአንጐል ውስጥ ደም ሊፈስ ይችላል፡፡ የአንጐል ደም ስር መሳሳትና መለጠጥም ደም ስሩ በቀላሉ ተሰንጥቆ ደም ወደ አንጐል ውስጥ እንዲፈስ ሊያደርገውና በዚህም ስትሮክ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ለዚህ ችግር መከሰት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ የሚታወቀው በህክምና ቁጥጥር ሥር ያልዋለ የደም ግፊት በሽታ ነው፡፡
ሁለተኛው ዓይነት ደግሞ ድንገተኛ የሆነ የደም ስርጭት መቋረጥ በአንጐላችን ውስጥ በሚከሰት ጊዜ የሚፈጠረው ስትሮክ ነው፡፡ አንጐላችን በየደቂቃው በደም አማካኝነት ጉሉኮስና ኦክስጂን ሊደርሰው ያስፈልጋል፡፡ይህ ካልሆነና በተለያዩ ችግሮችና አጋጣሚዎች ደም ወደ አንጐላችን ሊደርስ ካልቻለ አንጐል ሥራውን ያቋርጣል፡፡የሰውየው ሙሉ አንጐሉ ወይም በከፊል ከሥራ ውጪ ይሆናል፡፡
በዚህ ጊዜም ሰውየው መናገር ሊሣነው፣ ሰውነቱን ማንቀሳቀስ ሊቸግረውና አልታዘዝ ሊለው ይችላል፡፡
ይህ በብዙ ሰዎች ላይ የሚከሰተው ስትሮክ አይነት ነው፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ስትሮክ መከሰት ዋንኛ መንስኤ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ከልብ ትላልቅ ደም ጋኖች የሚመነጩ የደም ቁርጥራጮች የደም ስሮችን መዝጋት፣ የልብ ህመም፣ የደም ስር መደደር፣ መቀደድና መድማትና የልብ ምት መርጋት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ስትሮክ እንዲከሰት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ የጤና ችግሮች መካከል ከፍተኛ የደም ግፊት፣ የነጭና ቀይ ደም ሴል መብዛት፣ የስኳር በሽታ፣ የልብ ህመም፣ መጠኑ ከፍ ያለ ስብ በደም ውስጥ መኖር፣ የዕጽ ሱሰኝነት፣ የእርግዝና መከላከያ መድሃኒቶች፣ HIV፣ ካንሰርና በርካታ መጠን ያለው አልኮል መጠጣት ዋንኞቹ ናቸው፡፡
አንድ ሰው በስትሮክ በሽታ ሲጠቃ የሚያሳያቸው ምልክቶች አሉ፡፡ እነዚህ ምልክቶች በሚከሰቱ ጊዜ ታማሚው በፍጥነት ወደ ህክምና ተቋማት ቢጸርስ ስትሮኩ ሊያመጣ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ ይቻላል፡፡
ዋና ዋናዎቹ የስትሮክ በሽታ ምልክቶች:- የሰውነት በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ መድከም፣ ቅጽበታዊና ኃይለኛ ራስ ምታት፣ ብዥ ማለትና ድርብ ቅርጽ ማየት፣ ትውከትና ማቅለሽለሽ፣ የሰውነት መንቀጥቀጥ፣ ህሊናን መሣት፣ ቅዠትና ድበታ፣ በሰውነት ላይ የመደንዘዝ ስሜት መኖርና የማጅራት ግትር ብሎ መቅረት ናቸው፡፡ እነዚህ ምልክቶች የስትሮክ ችግር መፈጠር ምልክቶች ሊሆኑ ስለሚችሉ፣ ታማሚው ችግሩ በተፈጠረበት ቅጽበት የህክምና እርዳታ ሊያገኝ ወደሚችልበት ቦታ ሊወሰድ ይገባል፡፡ በሽታው ድንገተኛና ቅጽበታዊ እንደመሆኑ የሚያስከትለው ጉዳትም ከፍተኛ ነው፡፡ ስትሮክ ከመከሰቱ በፊት መከላከሉ ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ ከሚደረገው ህክምና እጅግ በጣም የቀለለ ነው፡፡ ችግሩ ከመከሰቱ በፊት ለመከላከል የሚያስችለውን ህክምና ለማድረግ ከሚከናወኑ የጤና ምርመራዎች መካከል የጀርባ አከርካሪ ፈሳሽ ምርመራ፣ የአንጐል ምርመራ፣ የደም ስሮች የደም ፍሰትና ስርጭት እይታ ምርመራ፣ የደም ሴሎች ምርመራ፣ የደም ኮሌስትሮል ምርመራ ዶፕለር አልትራ ሳውንድና ማግኔቲክ ሬሰናንስ ኢሜጂንግ ምርመራ የተባሉት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ እነዚህን ምርመራዎች በማካሄድ የስትሮክ በሽታ ምልክቶች ከተገኙ ችግሩ ከመፈጠሩና ታማሚው አደጋ ላይ ከመውደቁ በፊት ህክምና በማድረግ መፍትሔ ማግኘት ይቻላል፡፡ ለስትሮክ በሽታ ከሚዳርጉ ህክምናዎች መካከልም የደም መዘዋወር ችግርን ሊያስተካክሉ የሚችሉ መድሃኒቶችን መውሰድ፣ የሳሳው ወይንም ሊበጠስ የደረሰውን የደም ስር በህክምና ዘዴ እንዳይበጠስ ማድረግ፣ የሰውነት ሙቀትን የመቀነስና የማቀዝቀዝ ህክምና፣ የረጋ ደምን የማስወገድ ህክምና እና የቀዶ ጥገና ህክምናዎች በስፋት ተግባር ላይ የሚውሉ የህክምና ዘዴዎች ናቸው፡፡ ስትሮክ በአብዛኛው ከዕድሜ መግፋትና ከሌሎች በሽታዎች ጋር ተያይዞ የሚከሰት የጤና ችግር ሲሆን በሽታው በተለይም ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ ወንዶችን የሚያጠቃና በተለይም በዘመናዊ የአኗኗር ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎችን በስፋት የሚያጠቃ በሽታ ነው፡፡
ለስትሮክ በሽታ መስፋፋት እንደ ዋንኛ ምክንያት ከሚጠቀሱ ጉዳዮች መካከል የአኗኗርና የአመጋገብ ባህል መቀየር፣ የሰውነት እንቅስቃሴን የማይጠይቁና በቀላሉ ሊሠሩ የሚችሉ ሥራዎች መበራከት፣ የዘመናዊ ትራንስፖርት አመቺ መሆንና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ ይገኙበታል፡፡
ይህንን እጅግ አደገኛና በቅጽበት ለአካል ጉዳተኝነትና ለሞት ሊዳርግ የሚችል በሽታ የአመጋገብ ሥርዓትን በማስተካከል፣ ስኳርና ደም ግፊትን በመቆጣጠር፣ የስኳር፣ የጨውና የቅባት መጠንን በመቀነስ፣ ቅጠላቅጠልና ፍራፍሬዎችን አዘውትሮ በመመገብ፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረትን በማስወገድና ቋሚ የሆነ የጤና ክትትል በማድረግ መከላከል ይቻላል፡፡ በሽታው ተከስቶ ከሚያስከትለው እጅግ የከፋ ጉዳት ቀድሞ መከላከል አማራጭ የሌለውና ቀላሉ መፍትሔ ነውና - ሊታሰብበት ይገባል፡፡

Read 11145 times Last modified on Wednesday, 19 December 2012 13:34