Saturday, 15 December 2012 12:52

“ህልም?

Written by  ኢ.ካ
Rate this item
(4 votes)

እኛ ህልም የለንም!”
ሰው ሆኖ ተፈጥሮ ህልም የሌለው የለም፡፡
የህልሙ ዓይነት ሊለያይ ይችላል እንጂ፡፡
ትናንሽ ልጆች ሳለን ህልም ነበረን፡፡ “ምን መሆን ትፈልጋላችሁ?” ስንባል ዶክተር፣ ፓይለት፣ ሳይንቲስት፣ ኢንጂነር፣ አስተማሪ፣ ሹፌር ወዘተ--- እያልን የምንመልሰው ሁሉ ህልማችን እኮ ነው፡፡ አንዳንዱ ህልም እስከ መጨረሻው አብሮ ሊዘልቅ ይችላል፣ አንዳንዱ ደግሞ በጊዜ ሂደት ሊቀር ወይም በሌላ ህልም ሊተካ ይችላል፡፡ ምንም ቢሆን ግን ህልም የሌለው ሰው የለም፡፡

ምናልባት በትክክል ሳይረዳው ቀርቶ ሊሆን ይችላል፡፡ በተረፈ ግን የትኛውም ሰው የራሱ ህልም አለው፡፡ እቺን የህልም መንደርደርያ ያስቀደምኩት “ቺክን ሱፕ ፎር ዘ ሶል” ከተሰኘው የታሪኮችና ገጠመኞች ስብስብ ውስጥ ቨርጂኒያ ሳቲር በህልም ዙሪያ ያሰፈረውን የስራ ተመክሮ ላጋራችሁ ስላሰብኩ ነው፡፡ እነሆ-
ከጥቂት ዓመታት በፊት በአሜሪካ ደቡባዊ ክፍል በማህበራዊ ደህንነት ድጋፍ ከሚኖሩ ሰዎች ጋር እንድሰራ ተመድቤ ነበር፡፡ ሁሉም ሰው ከማንም ጥገኝነት ተላቆ በሁለት እግሩ የመቆም ብቃትና አቅም እንዳለው ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው ታዲያ ሰዎች በራስ የመተማመን ስሜታቸውን አዳብረው ራሳቸውን እንዲችሉ ማነቃቃት ብቻ ነው፡፡
በዚህ እሳቤ ነው ስራዬን የጀመርኩት፡፡ እናም ወደ ስራ ስገባ፣ የአካባቢው አስተዳደር በማህበራዊ ደህንነት ድጋፍ የሚኖሩ ሰዎችን እንዲያሰባስብልኝ ጠየቅሁኝ፡፡ አንድ ቀን ተሰባስበው ጠበቁኝ፡፡
ከሁሉም ጋር ከተጨባበጥኩና ከተዋወቅሁ በኋላ ወደተለመደው ጥያቄዬ ገባሁ፡፡
“ህልማችሁ ምን እንደሆነ ማወቅ እፈልጋለሁ--እስቲ ህልማችሁን ንገሩኝ” አልኳቸው፡፡ እኒህ በተወሰነች የማህበራዊ ደህንነት ድጋፍ የሚኖሩ ሰዎች “ይሄ ሰው ጤና የለውም እንዴ!” እያሉኝ እንደነበር አልጠፋኝም፡፡ አብዛኞቹ በዝምታ ትክ ብለው እየተመለከቱኝ ሳለ ነው አንደኛው ሰውዬ በገዛ ፈቃዱ ሌሎቹን ወክሎ የተናገረው፡፡“ህልም? እኛ ህልም የለንም!” አለኝ - ሰውየው በጥያቄዬ ተገርሞ፡፡
“በልጅነታችሁም? ያኔ መሆን የምትፈልጉት ነገር አልነበራችሁም?” ስል ሁሉንም በጅምላ ጠየቅኋቸው፡፡
አንዲት ሴት መናገር ጀመረች “በህልም ምን ተዓምር ልትፈጥር እንዳሰብክ አላውቅም፡፡ እኔ ግን አይጦች ልጆቼን እየበሉብኝ ተቸግሬአለሁ” አለች - አፍጥጣ እያየችኝ፡፡
“ኦው…በጣም አሰቃቂ ነው…የአይጦቹና የልጆችሽ ነገር…ቆይ ግን እንዴት ነው ችግሩን መፍታት የምንችለው?”
መልሼ ራሷን ጠየቅኋት፡፡
“አዲስ በር ከተሰራልኝ አይጦቹ መግባት አይችሉም …የቤቴ በር ወንፊት ስለሆነ በተቀደደው በኩል እየገቡ ነው ” በማለት ችግሯን አስረዳችኝ፡፡ በእርግጥ ነገሩ አሳዛኝ ነው፡፡ ግን ደግሞ ችግሩ ያን ያህል ከባድ አይደለም፡፡ እንዴት ከዚህ ሁሉ ሰው ውስጥ ለዚህ ችግር መፍትሄ የሚዘይድ ጠፋ ስል አሰብኩ - ለራሴ፡፡ ከዛም እንዲህ ስል ጠየቅሁኝ
“ከመሃላችሁ የወንፊት በር መስራት የሚችል የለም?”
አንድ ሰው እንደሚኖር ቅንጣት ጥርጥር አልነበረኝም፡፡ አንድ ጎልማሳ ብድግ አለና መናገር ጀመረ፡፡
“ድሮ እንደዚያ ያለ ነገር እሰራ ነበር፡፡ አሁን ግን ከባድ የጀርባ ህመም አለብኝ፡፡ ቢሆንም እሞክራለሁ”
ወንፊቱን ገዝቶ የሴትየዋን በር የሚሰራላት ከሆነ ጥቂት ገንዘብ እንዳለኝ ነገርኩት፡፡
“ያንን ማድረግ የምትችል ይመስልሃል?” እርግጠኛ ለመሆን ነበር የጠየቅሁት፡፡
“አዎ…እሞክራለሁ” አለኝ፡፡
በቀጣዩ ሳምንት ከቡድኑ ጋር ዳግም ስንሰበሰብ ሴትየዋን ጠየቅኋት “እሺ --- በሩ ተሰራልሽ?”
“አዎ…ተሰራልኝ” አለች
“ስለዚህ አሁን ስለህልማችን ማውራት እንችላለና” አልኳት
ሴትየዋ ቁራጭ ፈገግታ በአየር ላይ ላከችልኝ፡፡ ፈገግታዋን ተቀብዬ በሩን ወደሰራላት ጎልማሳ ዞርኩኝና
“አንተስ እንዴት ነህ…ጀርባህን ተሻለህ?” አልኩት
“የሚገርም ነው--- በጣም እየተሻለኝ ነው” አለ - ጎልማሳው
እቺ ናት ቡድኑን ስለህልሙ ማውራት እንዲጀምር ያነሳሳችው፡፡ እቺ ትንሽዬ የምትመስል ስኬት ስለህልም ማውራት ጤና ማጣት እንዳልሆነ ለቡድኑ አስገንዝባዋለች፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ሌሎቹም በተራቸው ስለህልማቸው እንዲነግሩኝ መጠየቅ የጀመርኩት፡፡
አንዲት ሴት እጇን አወጣችና ፀሐፊ መሆን ትፈልግ እንደነበር ህልሟን አጋራችን፡፡
እኔም “ታዲያ ህልምሽን እንዳታሳኪ ምን እክል ገጠመሽ?” በማለት ጠየቅኋት፡፡
“ስድስት ትናንሽ ልጆች አሉኝ…ለማን ጥያቸው ልሂድ” አለች፡፡ በዚህ የተነሳ ነው ከህልሟ ተፋታ በቁጭት የምትኖረው፡፡
“እስቲ ቆይ” አልኩኝ “እቺ ሴት በማህበረሰቡ ኮሌጅ ውስጥ ሥልጠና እስክትወስድ ድረስ በሳምንት አንድ ወይ ሁለት ቀን ልጆቿን የሚጠብቅላት ከመሃላችሁ የለም?” ለቡድኑ ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ አንዲት ሴት ተነሳችና “እኔም ልጆች አሉኝ…ግን እንደምንም ልጠብቅላት እችላለሁ” አለች፡፡ እግዜር ይስጥሽ አልኳት - በልቤ፡፡ በቃ በዚህ መልኩ የሁሉንም ህልምና ምኞት እየጠየቅሁኝ ህልሙን እውን እንዲያደርግ ተጋሁ፡፡
ፀሃፊ የመሆን ህልም እንዳላት የተናገረችው ሴት ወዲያው ኮሌጅ ገባች- ለስልጠና፡፡ ለዛች አይጦች ልጆቿን እየነከሱባት ለተቸገረች ሴት፣ በሯን የሰራላት ጎልማሳ የተበላሹ ቁሳቁሶችን የሚያድስና የሚጠግን የእጅ ባለሙያ ሆነ፡፡ የሴትየዋን ልጆች ለመጠበቅ የፈቀደችው ሴትዮ ደግሞ ህፃናትን የመንከባከብ ህጋዊ ፈቃድ አግኝታ መስራት ጀመረች፡፡ ሁሉም እንዲህ እንዲህ እያለ ያለመው ስራ ውስጥ መግባት ቻለ፡፡
በ12 ሳምንት ውስጥም እነዚህን ሰዎች በማነቃቃት ሙሉ በሙሉ ከማህበራዊ ደህንነት ድጋፍ አስወጥቼ ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ችያለሁ፡፡እኔ ባነቃቃቸውም ቅሉ ህልም ግን አልሰጠኋቸውም፡፡ ህልሙ የየራሳቸው ነው - ለረዥም ጊዜ አብሮአቸው የኖረ፡፡ግን በጊዜ ብዛት ሊጠፋ የደረሰ ህልም፡፡ ያንን ህልም ነው ካንቀላፋበት እንዲቀሰቅሱት ያገዝኳቸው፡፡ ለነገሩ እንዲህ ሳደርግ ይሄኛው የመጀመርያዬ አልነበረም፡፡
ብዙ ጊዜ አድርጌዋለሁ፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ሰው ህልም አለው!! ህልም ብቻውን ግን ውጤት አያመጣም- በተግባር መታገዝ አለበት፡፡

Read 7697 times