Saturday, 15 December 2012 13:34

‹‹ያልተዘመረላቸው›› በእኔ ዕይታ

Written by  ኃይለገብርኤል እንደሻው gizaw.haile@yahoo.com
Rate this item
(4 votes)

*በአርታኢነት ስማቸው የተጠቀሰው ሰዎች
ሃላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም
*አንባቢ ገንዘቡን ከፍሎ ጥራት የጎደለው
መጽሐፍ እንዲያነብ ተደርጓል
‹‹‹ያልተዘመረላቸው›› በሚል ርዕስ ለንባብ የቀረበው መፅሐፍ (ቅጽ-1)የህትመት ዘመን ይህ የያዝነው ዓመት (2005 ዓ.ም.) ሲሆን፣ አዘጋጁ ፍፁም ወልደማርያም ይባላል፡፡ አዲሱ መጽሐፍ የሃያ-አንድ እውቅ ኢትዮጵያውያንን አጫጭር የህይወት ታሪኮች በ273 ገፆች አካቶ ይዟል፡፡ መጽሐፉን ካነበብኩ በኋላ፣ ያስተዋልኳቸውን አንዳንድ የቋንቋ ግድፈቶች በማስመልከት የተሰማኝን ለማለት ፈለግሁ፡፡

ቀላል በማይባል ዋጋ ለአንባቢያን የሚቀርቡ መጽሐፍት ከይዘትና ቅርፅ አኳያ ጥራታቸው የተጠበቀ ሊሆን ይገባል፡፡ በተለይም በቋንቋ አጠቃቀም ረገድ ትኩረት ያገኙ የማይመስሉ መጽሐፍት በቁጥር አናሳ አይደሉም፡፡ 
ከፍ ብሎ እንደተጠቀሰው የዚህ ጽሁፍ ዓላማ የቋንቋ አጠቃቀም ችግር ከታየባቸው መጽሐፍት መካከል ከላይ በስም የተጠቀሰውን መሰረት በማድረግ አስተያየት መስጠት ይሆናል፡፡
ዕድሜና ጤናው ካለ በቀጣይ ሌሎች የሕትመት ውጤቶችን እያነሳሁ ከአንባቢዎቼ ጋር እወያያለሁ፡፡
‹‹ያልተዘመረላቸው›› በሁለት ጋዜጠኞችና በአንድ የፒ.ኤች.ዲ. ተማሪ የጀርባ ሽፋን አስተያየት (blurb) የተፃፈለት፣ በሁለት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራን የአርትኦት ስራ የተሰራለት መጽሐፍ ነው፡፡
በአርታኢያኑ፣ በአስተያየት ሰጪዎቹና በራሱ በአዘጋጁ እንደተገለፀው፣ መጽሐፉ በአንድ የሃገር ውስጥ ኤፍ.ኤም ሬዲዮ ጣቢያ ተላልፈው የነበሩትን ጽሁፎች አሰባስቦ በማሳተም የተዘጋጀ ነው፡፡ አዘጋጁ በዚህ ዓይነት አቀናብሮ ለሰራው ስራ አድናቆት ሊቸረው ይገባል፡፡ እግረ-መንገዴንም በዚህ ዓይነት እየተስፋፋ የመጣው ባንድ ወቅት በጋዜጣና በመፅሔት ቀርበው የነበሩ ፅሁፎችን አሰባስቦ በመጽሐፍ መልክ የማሳተሙ ጅምር እንቅስቃሴ ሊበረታታ የሚገባው መሆኑን ሳልገልፅ አላልፍም፡፡
በጋዜጣና በመፅሔት የተነበቡ መጣጥፎችን በቀጥታ ወደመጽሐፍ የመቀየሩ ስራ ብዙም ችግር ላይኖረው ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ፣ በኤሌክትሮኒክ የመገናኛ ዘዴዎች የተላለፉትን ጽሁፎች ምንም ሳይለወጡ፣ እንዳሉ በመጽሐፍ መልክ አዘጋጅቶ ለንባብ ማቅረብ ስህተት ነው፡፡ ይህን አስመልክቼ በጣም በጥቂቱ አንዳንድ ነገሮችን ባነሳ እወዳለሁ፡፡
በሬዲዮ የሚቀርብ የጽሁፍ መልዕክት ለአድማጮች ሲሰራጭ መስማትን ብቻ ታሳቢ አድርጎ ስለሆነ፣ ከህትመት ጽሁፍ ይልቅ ለየት ያለ ስራ በይዘቱና በቅርፁ ላይ ሊሰራ ይገባል፡፡ በንባብ ላይ ዓይን ወደኋላ ሊመለስ ይችላል፡፡ ሬዲዮ በሚደመጥበት ጊዜ ግን ጆሮ ወደፊት ብቻ ነው የሚያተኩረው፡፡ በሬዲዮ የተላለፈን ጉዳይ መለስ ብሎ የመመርመር ዕድሉ ለጆሮ ያስቸግረዋል ለማለት ነው፡፡ ለሬዲዮ የሚዘጋጅ ፅሁፍ በንግግር ዓይነት ዘይቤ ሊጠናቀር ይችላል፡፡ እንዲህ ከሆነ ደሞ በቋንቋው ላይ ብዙም የአርትኦት ስራ መስራት ላያስፈልግ ይችላል፡፡ በጥቅሉ በሬዲዮ የሚተላለፍ የጽሁፍ ስራ፣ ‹‹understanding is more important than grammar…›› በሚል የተለመደ አሰራር ሊከናወን ቢችል እንደስህተት አይቆጠርም፡፡ከዚህም በተጨማሪ ያለችግር ከአንድ ርዕሰ-ጉዳይ ወደ ሌላ የመዝለል ዕድሉ ይኖራል፡፡
አድማጩን ይዞ ለማቆየት ሲባል የሬዲዮ ጽሁፍ አጠር አጠር ተደርጎ ሊቀርብ ይገባል፡፡ ተደራሲው መልዕክቱን በሁሉም የስሜት ህዋሳቱ ይገነዘብለት ዘንድ የሬዲዮ ፅሁፍ አዘጋጁ ይሆነኛል ያለውን የአፃፃፍ ቴክኒክ ሊጠቀም ይችላል፡፡ እንዲሁም ቃላት ተንቀሳቃሽ ስዕሎችን ፈጥረው እንዲታዩ ማድረግ የአድማጩን አቅል ለመሳብ የሚጠቅም ሌላው ዘዴ ነው፡፡ የተለያዩ የሙዚቃ ግብዓቶችንም በመጠቀም በጽሁፉ ላይ ሕይወት መዝራት ይቻላል፡፡ የአነባቡ ሁኔታም ወሳኝነት ይኖረዋል፡፡ የቱ ጋ ትንፋሽ መያዝ እንዳለበት፤ የቱ ጋ ድምፁን ከፍና ዝቅ ማድረግ እንዳለበት የሚያውቀው አንባቢው ወይም ተራኪው ስለሆነ፣ የራሱን ምልክቶች ወይም ስርዓተ-ነጥቦች ጥቅም ላይ በማዋል መጠቀም ይችላል፡፡ ባጠቃላይ በሬዲዮ የሚደመጥ ዝግጅት ለአፍታ ተደምጦ የመረሳት ዕድሉ ላቅ ያለ ስለሆነ፣በተደራሲው በኩል ብዙም ጠልቆ የመመርመር አጋጣሚው አይኖርም፡፡ ስለዚህ ከህትመት ጽሁፍ በተለየ መልኩ የሬዲዮ ጽሁፍ የራሱ የሆነ ልዩ የአፃፃፍ ቴክኒኮች መጠቀምን ይጠይቃል፡፡
በመጽሐፍ መልክ ተዘጋጅቶ ለአንባቢ የሚቀርብ ጽሁፍ፣ ለሬዲዮ ከሚቀርበው በተለየና ጠንከር ባለ ጥንቃቄ ሊሰራ የሚገባው ነው፡፡ ጽሁፉ የቋንቋውን የሰዋሰው ሕግ ተከትሎ ተደራሲውንና ፀሐፊውን በሚያግባባ መልኩ ታሽቶ መሰራት አለበት፡፡ ቋንቋ ስርአት አለው፡፡ ስርአቱን ተከትሎ መስራት ደሞ ከፀሃፊው ይጠበቃል፡፡ አንባቢ ጊዜ ወስዶ በጥልቀትና በድግግሞሽ ሊያነባቸው ስለሚችል፣ በርግጥም በህትመት ለሚወጡ የጽሁፍ ስራዎች ላቅ ያለ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡
በ‹‹ያልተዘመረላቸው›› መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት ፅሁፎች፣ በዚህ ዓይነት ትኩረት ተሰጥቷቸው ከሬዲዮ ጽሁፍነት ወደ ህትመት ስራዎች ሊቀየሩ ይገባቸው ነበር፡፡ በአርታኢነት ስማቸው የተጠቀሰው ሰዎች የተሰጣቸውን ሃላፊነት ባግባቡ ስላልተወጡ፣ መጽሐፉ ያለተገቢ የአርትኦት ስራ ገበያ ላይ ውሎ ለንባብ በቅቷል፡፡ በዚህም ምክንያት የሚከተሉት ያልተጠበቁ ውጤቶች ተከስተዋል፡፡
አንባቢው ገንዘቡን ከፍሎ ተገቢውን ግልጋሎት አላገኘም፤የመጽሐፉን በጉጉት የመነበብ ሁኔታን የማደብዘዝ አጋጣሚ ተከስቷል፤ የአዘጋጁ የወደፊት ስራ ላይ የተአማኒነት ጥያቄ ሊያንዣብብ ችሏል፡፡…
በአርትኦት ጉድለት ምክንያት የታዩትን ሕፀፆች ከመፃሕፉ እየነቀስን በማውጣት እንመልከት፡፡ በገፅ 13 ላይ የሚከተለውን እናነባለን፡፡ ‹‹…ታዲያ ከእነዚህ የታሪክ ባለውለታዎቻችን መካከል የህይወት ታሪካቸውንና ስራዎቻቸውን ለተተኪው ትውልድ የሚያስተላልፉልን የታሪክ ድርሳናት ቁጥር አናሳ ናቸው፡፡›› ይህንን ጨምሮ ከዚህ በታች ለውይይት በሚቀርቡት ጥቅሶች ላይ የሚቀመጠው ሰረዝ የኔ መሆኑን አንባቢዎቼ እንዲያውቁልኝ ይሁን፡፡ ከላይ ከመጽሐፉ ከተወሰደው ጥቅስ ውስጥ የተሰመረባቸው ቃላት ለቋንቋው ስርዓት አልተገዙም፡፡ የነጠላ ቁጥር ስም በብዙ ቁጥር ረዳት ግስ ታስሯል፡፡ በሬዲዮ ቢሆን ችግር ላይኖረው ይችላል፡፡ በህትመት ላይ ግን ስህተቱ በቀላሉ ጎልቶ ሊወጣ ችሏል፡፡
‹‹…እነዚህ መጽሐፍት ግማሹ በእንግሊዝኛ ለውጪ አንባቢያንና ለምሁራን የተዘጋጁ መሆናቸው፤ በአማርኛ የተፃፉትም ቢሆኑ…›› (ገፅ 13) በዚህ ጥቅስ ላይ የተሰመረባቸውን ሁለት ቃላት ብንመለከት፣ የቁጥር ያለመጣጣም (ሰዋሰዋዊ) ግድፈት እንደተከሰተባቸው እንረዳለን፡፡
‹‹…የጠቀስኳችሁ ደራሲያንና ፀሐፊያን በሙሉ ለተዋስኳቸው ጽሑፎቻቸው ምስጋና ይገባቸዋል፡፡
…››(ገፅ 14)የዚህ ዓ. ነገር የቋንቋ ስርዓት መፋለስ በቀላሉ ይታያል፡፡
በተለይም የተሰመረባቸውን ሁለት ቃላት አፅንኦት ሰጥተን ስናነብ፣ ችግሩ ይታወቀናል፡፡‹‹የጠቀስኳችሁ›› የሚለው ቃል ‹‹ይገባቸዋል›› ከሚለው ቃል ጋር ባለመጣጣሙ ችግሩ ተከስቷል፡፡
በገጽ 17 ላይ ደሞ የሚከተለውን ዓ. ነገር እናነባለን፡፡ ‹‹…‹ገብረሃና ይህን ቀልድህን ተው፣ አንተ በቀልድህ ተጠራ›….››ይሄ አደናጋሪ አባባል መሆኑን ለመለየት አያስቸግርም፡፡
በተመሳሳይ ገፅ ላይ፣‹‹…አለቃ ገብረሐና በጎንደር ቤተ መንግስት ከታወቁ ምሁራን ሁሉ የበለጠ ስማቸውን በመልካም ነገር ያስነሳላቸው የነበረው አለማዊና ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን አንድነት አጣምሮ የያዘውን ፍትሐ ነገስት የተባለውን መጽሐፍ በመተርጎም ጥረታቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡…››
የሚል የተሳሳተ ዓ. ነገር ሰፍሯል፡፡ የተሰመረበት ቃል በዓ. ነገሩ ላይ ለተከሰተው የቋንቋ ስህተት በመንስኤነት ሊወሰድ ይችላል፡፡
‹‹…በቤተመንግስቱም በሚደረገው ግብዣ መኳንንቱን ሁሉ ቀልድ በተሞላበት ህብር ንግግራቸው ሁሉንም በማሸነፍ ስለማይረቱ ይሸለሙ ነበር፡፡…›› (ገጽ 20) የቃላት ድግግሞሽና አላስፈላጊ የድህረ-ቅጥያ አጠቃቀም ዓ. ነገሩን ጣዕም የለሽ አድርጎታል፡፡
‹‹…እኛ ባንደበተ ስልነታቸው ይታወቁ የነበሩት አለቃ ገብረሃና በእድሜያቸው መጨረሻ ላይ ዝምተኛ ሆነው ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ ከአለማዊ ኑሯቸው ገለል ብለው ወደ መንፈሳዊ ህይወታቸው ተመልሰው ቤተክርስቲያንን ማገልገል ጀምረው ነበር፡፡ አለቃ ገብረሐና አንደበታቸው ቢቆጠብም የአእምሮቸው ስልነት አልተለያቸውም፡፡ ለዚህም ነበር ወደ እርጅናው ሲሸጋገሩ ከፈጣሪ ጋር ክርክር ያስገባ ቅኔ የተቀኙት…›› (ገጽ 22)በጥቅሶቹ ላይ ሰረዞቹን የማኖረውና ቃላቱን እንደወረዱ የምጠቅሰው፣ታዛቢ በቃላቱ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንዲያነበው በሚል ነው፡፡ በዚህ ከላይ በተጠቀሰው ዓ. ነገር ውስጥ የቃላት ድግግሞሽ፣ የባለቤትና የግስ ያለመስማማትና ሌሎችም የቋንቋ ግድፈቶች ይስተዋላሉ፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ የቃላት ድግግሞሽ ከሚታይባቸው ዓ. ነገሮች መካከል በገጽ 80 ላይየሚገኘው አንደኛው ነው፡፡ እንዲህ ይነበባል፡፡
‹‹…ብላቴናውም በነበረው ወግና ስርአት መሠረት ያባቱን ጋሻ ያነሣ ዘንድ፣ የቆየውን የቤተሰቡን ታሪክ እንዲቀጥል ያደርግ ዘንድ፣ ክብሩንም ይወርስ ዘንድ ተማሪ ቤት ተላከ፡፡…››
በሬዲዮ የሚቀርብ ፅሁፍ ካንዱ ርዕስ ወደሌላው ቢዘል እንደችግር ሊቆጠር አይችልም ብለናል፡፡ በዚህም ምክንያት ለመሸጋገሪያነት የሚያገለግሉ ቃላት ወይንም ሐረጎችን መጠቀም ላያስፈልግ ይችላል፡፡
በህትመት ጽሁፍ ላይ ግን ይሄ ዓይነቱ አካሄድ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ለምሳሌ በገጽ 27 ላይ የመጨረሻዎቹ ሁለት አንቀጾች ተያያዥነት ወይም ዝምድና እንዲኖራቸው አልተደረገም፡፡ በዚሁ ገጽ ላይ የሶስተኛው አንቀጽ የመጀመሪያው ዓ.ነገር ባለቤት ወይም ድርጊት ፈፃሚ ስለሌለው፣ ጉዳዩ እየተወራ ያለው ስለማን እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በገጽ 28 ላይ የሚገኘው ሦስተኛው አንቀጽ ከሌላ ቦታ ተቆርጦ የተወሰደ ዓይነት ሆኖ ነው የሚነበበው፡፡
ችግሩ የተከሰተው አያያዥ ቃላትን ወይም ሐረጎችን በመጠቀም ከአንቀጽ ወደ አንቀጽ የሚደረገውን ሽግግር ለማዋዛት የተደረገ ጥረት ባለመኖሩ ነው፡፡ አማረ ማሞ ይህን አስመልክተው ‹‹የቀለም ጠብታ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው የሚከተለውን ይጠቅሳሉ፡፡
‹‹በተገቢው የመሸጋገሪያ ቃላትና ሐረጎች የተዋቀሩ አንቀጾች ከአንዱ ፍሬ-ሐሳብ መዳረሻ ወደሚቀጥለው ፍሬ-ሐሳብ መነሻ አንባቢን ያለምንም ግራ መጋባት ሰተት አድርገው ያስተላልፋሉ፡፡›› (ገጽ 124)
በተመሳሳይ ሁኔታ በገጽ 133፣ 152፣ 153፣ 157፣ 160፣ 177፣ 197 እና በሌሎችም ገጾች ላይ የሚታዩትን ዋና ዋና የቋንቋ አጠቃቀም ግድፈቶች ማንሳት ይቻል ነበር፡፡ ሆኖም አንባቢ እንዳይሰለችብኝ ስለምሰጋ፣ ለጊዜው እዚህ ላይ በማቆም ወደሌላው ጉዳዬ አመራለሁ፡፡ አነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ማስረጃዎች ከሬዲዮ የተወሰዱ ጽሁፎች ምንም መሻሻል ሳይደረግባቸው በመጽሐፍ መልክ ለማዘጋጀት የተደረገን ሙከራ ከነስህተታቸው ለማሳየት የሚረዱ ናቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡
በሌላም በኩል የተሟላ መረጃ ባለመስጠት የተከሰቱ ስህተቶችን ለማሳየት የሚከተለውን እንመልከት፡፡ ‹‹…ይህን ምስክርነት በመጽሐፉ ላይ ያሰፈረው አንድ ታዋቂ አውሮፓዊ ጋዜጠኛና ደራሲ ነው፣…›› የሚል ዓ. ነገር በገጽ 68 ላይ ተጽፎ ይነበባል፡፡ ይሄ ዓ.ነገር የሚናገረው በገጹ የመጀመሪያው አንቀጽ ላይ ስለተመለከተው አንድ ጥቅስ ነው፡፡ በዓ.ነገሩ ላይ ስለተባለው መጽሐፍና ፀሐፊ በስም የተገለፀ ነገር ባለመኖሩ፣ አንባቢ ጥቅሱ ከየት እንደተወሰደ የሚያሳይ መረጃ ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ ይሄ ጥቅስ በቀጥታ ‹‹አጤ ምኒሊክ›› በሚል ርዕስ በጳውሎስ ኞኞ ከተጻፈው መጽሐፍ ገጽ 159 የተወሰደ ነው፡፡ ወጣት ፍፁም ጥቅሱን የተዋሰበትን የመጽሐፍ ስምና ፀሐፊውን ላለመጥቀስ የፈለገው ለምን እንደሆነ ሊገባኝ አይችልም፡፡ ለንፅፅር እንዲመቸን ሁለቱንም ጥቅሶች እንመልከት፡፡
‹‹ ሃያ ሺህ ያህል ወታደሮች ያሉበት የአውሮፓ ጦር በአፍሪካ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተሸነፈ፡፡ በእኔ እምነት መሰረት በዘመናችን ታሪክ ውስጥ እንደዚህ ያለ ጦርነት አልታየም፡፡ በእልቂቱ 25000 ሺህ ሰዎች በአንድ ቀን ጀምበር የሞቱበትና የቆሰሉበት ነው፡፡…ፖለቲካና ታሪክ አበቃ፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ታላቅ ሃይል መነሳቱ ታወቀ፡፡ የአፍሪካ ተወላጆች ታሪክ ተለወጠ፡፡ ጥቁሩ አለም በአውሮፓውያን ላይ ሲያምፅና ሲያሸንፍ የመጀመሪያው መሆኑ ነው፡፡ አበሾች አደገኞች ሕዝቦች ስለመሆናቸው ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ተፅፎላቸዋል፡፡ የኛ አለም ገና ቶርና ኦዲዮን በሚባሉ አማልክት ሲያምን በነበረበት ጊዜ አበሾች ክርስትና ሃይማኖትን የተቀበሉ ናቸው፡፡ አሁን የሁሉንም ፍላጎት ዐድዋ ዘጋው፡፡›› (ያልተዘመረላቸው ገጽ 68)
‹‹…ሃያ ሺህ ያህል ወታደሮች ያሉበት የኤሮፓ ጦር በአፍሪካ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተሸነፈ፡፡ በኔ እምነት መሠረት በዘመናችን ታሪክ ውስጥ እንደ አድዋው ያለ ጦርነት የለም፡፡ በእልቂቱ 25፣000 ሰዎች በአንድ ቀን ጀምበር የሞቱበትና የቆሰሉበት ነው፡፡ ፖለቲካና ታሪክ አበቃ፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ታላቅ የተወላጆች ኃይል መነሳቱ ታወቀ፡፡ የአፍሪካ ተወላጆች ታሪክ ተለወጠ፡፡
ጥቁሩ አለም በኤሮፓውያን ላይ ሲያምፅና ሲያሸንፍ የመጀመሪያው መሆኑ ነው፡፡ አበሾች አደገኛ ሕዝቦች መሆናቸው ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ተጽፎላቸዋል፡፡
የኛ ዓለም ገና ቶር እና ኦዲዮን በሚባሉ አማልክት ሲያመልክ በነበረበት ጊዜ አበሾች የክርስትናን ሃይማኖት የተቀበሉ ናቸው፡፡ አሁን የሁሉንም ፍላጎት አድዋ ዘጋው፡፡›› በርክሌይ (አጤ ምኒሊክ ገጽ 159)
በተጨማሪም አንድ ጽሁፍ ከሌላ መጽሐፍ ተወስዶ ሲጠቀስ፣ ስርዓቱ በሚፈቅደው መሰረት የተወሰደበት የመጽሐፍ ርዕስና የደራሲው ስም፤ ገጹን ጨምሮ ባመልካች ቁጥሮች፣ በአስተሪስክስ (asterisks)፣ በዳገርስ (daggers)፣ በግርጌማ (በግርጌ ማስታወሻ foot notes)ወይንም በማጣቀሻ (reference) መልክ ሊጠቆም ይገባል፡፡ ይሄ በመጽሐፉ በገጽ 68 መጀመሪያ ላይ የተመለከተው ጥቅስ በጽሁፉ በስተመጨረሻ ከተጠቀሱት አምስት ዋቢ የጽሁፍ ምንጮች መካከል ከየትኛው እንደተገኘ የሚያሳይ መረጃ የለም፡፡
ሌላው ልነካካው የምወደው ጉዳይ፣ ‹‹መልእክተ-ኤዞፕ›› በሚል ርዕስ አስተያየት የተሰጠበት የመጽሐፉ ክፍል ነው፡፡ በሁለት ገጾች የተሰጠው አስተያየት በቋንቋ አጠቃቀም ረገድ ግድፈት የሚታይበት ነው፡፡ አንዳንዶቹ ከዚህ በታች ተጠቅሰዋል፡፡
‹‹ወጣቱ ፍፁም ወልደማርያም ለበርካታ ጊዜያት መጻሐፍትን ያነብ ነበር፡፡…›› (ገጽ 6) ይሄ ዓ.ነገር የተፃፈበት የሰዋሰው ስርዓት የሃላፊ ጊዜ የሚባለው ነው፡፡ በዚህ ዓይነት የሚፃፍ ዓ.ነገር የሚያስገነዝበው ድርጊቱ ባንድ ወቅት የተደረገና ባሁኑ ጊዜ ግን ያበቃለት መሆኑን ነው፡፡
በዚህም መሰረት ከላይ የምናነበው ዓ.ነገር የሚያስገነዝበው፣የመጽሐፉ አዘጋጅ የተባለውን የንባብ ልምዱን በአሁኑ ሰዓት ስለመተዉ ነው፡፡
ለማለት የተፈለገው ግን ይሄ እንዳልሆነ ይገባኛል፡፡ ይሁን እንጂ ፀሐፊዎቹ ትክክለኛውን የቋንቋ ስርዓት ባለመከተላቸው አንባቢው ያልተፈለገውን ግንዛቤ እንዲጨብጥ አድርገዋል፡፡
ከላይ በተጠቀሰው ገጽ ላይ፣ ‹‹…ፍፁም በሚያነብበት ወቅት ማለፊያ ማስታወሻ የመያዝ ጥንቅቅ ያለ ባህሪ አለው፣›› የሚል ዓ.ነገር ተፅፎ ይነበባል፡፡ ይህ ዓ.ነገር ባላስፈላጊ ቅፅሎች የተጀቦነ ግራ አጋቢ ሙገሳ ነው፡፡
‹‹ማለፊያ›› የሚለው ቅፅል ለማን የቆመ ነው? በመሰረቱ ቅፅል የሚያገለግለው ስምን ለመግለፅ ነው፡፡
‹‹ማስታወሻ›› የሚለው ስም ‹‹ማለፊያ›› በሚለው ቅፅል ሊገለፅ የተፈለገ ይመስላል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ‹‹ማለፊያ ማስታወሻ›› ማለት ምን ማለት እንደሆነ ግልፅ አይደለም፡፡ ‹‹ጥንቅቅ ያለ ባህሪ›› ሲባልስ ምን ማለት ነው? በደንብ ታስቦበት የተጻፈ አይመስልም፡፡
አስተያየት ሰጪዎቹ በገጽ 6 ላይ የሚከተለውን አስፍረዋል፡፡
‹‹…ይህንን ፈለግ መከተሉ ነው ፍፁም ይህንን መጽሐፍ እውን ያደረገው፡፡…›› ይሄ ቀሽም ዓ.ነገር ነው፡፡ በነገራችን ላይ አስተያየት ሰጪዎቹ በገጽ 6 እና 7 ላይ ‹‹ይህንን›› እና ‹‹ሆነ››የተባሉትን ቃላት ከ15 ጊዜያት በላይ ተጠቅመዋል፡፡ በሃምሳ-ስምንት ቃላት በተመሰረተው በሶስተኛው አንቀፅ ውስጥ ብቻ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ቃላት አራት ጊዜያት ተጠቅሰዋል፡፡
‹‹…ዘለአለማዊ ድል የምናስፅፍበት ማንበብ አሁንም ማንበብ ነው፡፡…›› (ገጽ 7) ይሄም የደከመ አባባል ነው፡፡ ባጠቃላይ በገጽ 6 እና 7 ላይ የሚነበበው አስተያየት የአርትኦት ስራ ሊቸረው የሚገባ ውልግድግድ ጽሁፍ ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡
በመቀጠል ሳላነሳ የማላልፈው ጉዳይ በገጽ 39 ላይ ሐኪም ወርቅነህን አስመልክቶ የተፃፈው ያልተለመደና ግርታን የሚፈጥር አባባል ነው፡፡ ‹‹…‹የመጀመሪያው ባለ አንጎል ጥቁር ሐኪም› የሚል የምስክር ወረቀትና መቀስ ተሸለሙ፡፡…›› በዚህ ጥቅስ ላይ፣ ‹‹ባለ አንጎል›› የሚለው አባባል ምን ለማለት ተፈልጎ የተጠቀሰ እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ምናልባት brainy ለሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የተሰጠ አቻ ትርጉም ይሆን? ምናልባት በእንግሊዝኛው የጽሁፍ ምንጭ ላይ brainy የሚል ቃል ተጠቅሶ ከሆነ፣ ‹‹ባለ አንጎል›› የሚለው የአማርኛ ትርጉም በጭራሽ ሊተካው አይችልም፡፡ግምቴ ትክክል ከሆነ፣ለዚህ brainy ለሚለው የእንግሊዝኛ ቃል፣‹‹ብልህ፣ ንቁ፣ ፈጣን፣ አዋቂ፣ ምሁር…›› የሚሉት ቃላት በአቻነት ቢተኩት የተሻለ ይሆን ነበር፡፡
በተጨማሪም ልተችበት የምፈልገው ነጥብ የመጠሪያ ስምን አስመልክቶ በ‹‹ያልተዘመረላቸው›› መጽሐፍ ላይ የተጠቀሰውንይሆናል፡፡ ደራሲ ወይም author የሚለው መጠሪያ ስም የሚሰጠው አንድን የጽሁፍ ሥራ ለፈጠረ ፀሐፊ ነው፡፡ ይሄ እንግዲህ በግርድፉ በእኔ ሲበየን ነው፡፡ Merriam-Webster መዝገበ-ቃላት author የሚለውን ቃል ሲተረጉም፣ ‹‹ያገኘ›› ወይም ‹‹የፈጠረ›› በሚሉ ቃላት አፍታቶ ነው፡፡ author የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል አመጣጡ ከላቲኑ auctor ሲሆን፣ ትርጉሙም ‹‹አግኚ››ወይም‹‹ያገኘ፣›› የሚል ነው፡፡
በዚህ ብይን የምንስማማ ከሆነ፣ የ‹‹ያልተዘመረላቸው›› መጽሐፍ ድርሰት ወይንም የፈጠራ ስራ ስለመሆኑ ልንጠይቅ እንገደዳለን፡፡
በርግጥም የመጽሐፉ አስተያየት ሰጪዎች በገጽ 6 ላይ፣ ‹‹በዚህም ሐሳብ ወጣቱ አንባቢ ፍፁም ወልደማርያም እራሱን ደራሲ ሆኖ አገኘው፡፡…፣›› በማለት አዘጋጁን የደራሲነት ካባ አከናንበውታል፡፡
አዘጋጁ ፍፁም እንደሚነግረን ከሆነ ደሞ ያዘጋጃቸው ጽሁፎች የተገኙት ከተለያዩ መጽሐፍት፣ ጋዜጦች፣ መጽሄቶችና ሌሎች ምንጮች ነው፡፡ እሱ ያደረገው ነገር ቢኖር፣ እነዚህን ጽሁፎች አሰባስቦ ለህትመት ማብቃት ብቻ ነው፡፡ ራሱ አዘጋጁ እንዳለውም፣ መጽሐፉ ‹‹…የበርካታ መጽሐፎች፣ ጋዜጦች፣ መፅሄቶችና የመመረቂያ ጽሁፎች ጥንቅር ውጤት ነው፡፡…›› (ገጽ 14) ታዲያ በዚህ ዓይነት የተጠናቀረን የታሪኮች ስብስብ ያዘጋጀ ሰው ደራሲ ተብሎ ሲጠራ ስህተት አይሆንም ወይ! በመጽሐፉ ውስጥ የተፈጠረ አንዳችም አዲስ ነገር ስላላየን ለፍፁም ይህንን ስም ልንሸልመው ከቶም አይገባን!
ሌላው የአፃፃፍ ስርዓትን አስመልክቶ ሊጠቀስ የሚገባው የስርዓተ-ነጥብን ባግባቡ ያለመጠቀም ጉዳይ ነው፡፡በዚህ መጽሐፍ አዘጋጅ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ፀሐፍት በተደጋጋሚ የሚታይ ችግር ነው ማለት እችላለሁ፡፡
በአራት ነጥብ ቦታ ድርብ ሰረዝ፤ በድርብ ሰረዝ ምትክ ነጠላ ሰረዝ የመጠቀሙ አባዜ አሁን አሁን እየተስፋፋ የመጣ ክፉ ልማድ ይመስላል፡፡
ሳይጠቀሱ የሚታለፉ የፅሁፍ ክፍሎችን ለማመልከት ሦስት ነጠብጣቦችን እንጠቀማለን፡፡ እዚህ እየተወያየንበት ባለው መጽሐፍ ላይ ግን ከሦስት ያነሱና የበለጡ ነጠብጣቦች በግዴለሽነት በግልጋሎት ላይ ውለው ይታያሉ፡፡ በመጽሐፉ በገጽ 49 ላይ ያሉት አንቀፆች በማስረጃነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡
ባጠቃላይ በእኔ ዕይታ ‹‹ያልተዘመረላቸው›› መጽሐፍ በደረሰበት የአርትኦት ችግር ምክንያት ትንሽ በማይባሉ የቋንቋ ህፀፆች ተጀቡኖ ለንባብ ቀርቧል፡፡
አንባቢ ገንዘቡን ከፍሎ ጥራት የጎደለው መጽሐፍ እንዲወስድ ተደርጓል፡፡ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው ማን ነው? ይሄ የሁላችንም ጥያቄ ሊሆን ይገባል፡፡

Read 3776 times