Print this page
Saturday, 15 December 2012 13:37

የሕይወት ታሪክ መፃህፍት ቅኝት

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(10 votes)

“ደማሙ ብዕረኛ” በሚል ርዕስ የደራሲ፣ ባለቅኔና ፀሐፌ ተውኔት መንግሥቱ ለማን ግለ ታሪክ ይዞ በ1988 ዓ.ም በታተመው መጽሐፍ ውስጥ “መንደርደሪያ” በሚለው ክፍል “በኢትዮጵያ ስነ ጽሑፍ የሕይወት ታሪክ (Biography) የግል ማስታወሻ (Diary) ስነ ጽሑፍ እምብዛም አልተለመደም፡፡ ያሉት ጥቂቶች ናቸው፡፡ “ኃተታ ዘርአ ያዕቆብ” ፣ “መጽሐፈ ትዝታ”፣ “የታሪክ ማስታወሻ”፣ “ህይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ” ናቸው፤ እኔ የማውቃቸው” ይላሉ - ፀሃፊው፡፡


ግለ ታሪካቸውን መፃፍ በጀመሩበት በነሐሴ ወር 1972 ዓ.ም ካሰፈሩት ከዚህ ሃሳብ ጐን ለጐን ተዘጋጅተው የተቀመጡ፤ግን ያልታተሙ የሕይወት ታሪክ መፃሕፍት ስለመኖራቸው መስማታቸውን ይጠቁማሉ፡፡ የዛሬ 30 ዓመት ቁጥራቸው አነስተኛ የነበረው ግለ ታሪክና የህይወት ታሪክ መፃሕፍት አሁን በርከትከት እያሉ ናቸው፡፡
ግለ ታሪኩን የሚያዘጋጅ ሰው ጽሑፉን በምን መልኩ ማስኬድ እንደሚኖርበት ባለቅኔ መንግሥቱ ለማ ከራሳቸው ጋር ያደረጉትን ጥያቄና መልስ በ”መንደርደሪያ” በማስፈር ሌሎችን የሚያግዝ ልምድ አካፍለዋል፡፡ በጉልምስና የግል አስተያየትና አመለካከቱን ብቻ ነው ማስፈር ያለበት ወይስ የድርሰት ተሰጥኦው መቼና እንዴት በውስጡ ሊገኝ እንደቻለ በሳይኮሎጂ መፃሕፍት እየታገዘ ማብራራት ይኖርበታል? በማለት ይጠይቃሉ፡፡
የታሪኩን ቅደም ተከተል ሥራውን ከመጀመሩ በፊት የሚነድፍ ግለ ታሪክ ፀሐፊ ምዕራፎቹን “ልጅነት፣ ጋብቻ፣ እርጅና…” ከሚሉት ይልቅ ሰፋ ባለ መልኩ “የፍቅር ሕይወት፣ ሥነ ጥበብ፣ ሥራ፣ ፖለቲካ…” እያሉ መመደብ ተመራጭ ስለመሆኑም ያመለክታሉ፡፡ ይህንንም ቢሆን ከዚህ በተሻለ መመደብ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡ ለምሳሌ “ፖለቲካ” የሚለውን ምዕራፍ ባለታሪኩ እንደኖረበት ዘመን “የኢጣሊያ ወረራና የቅኝ አገዛዝ፤ የነፃነት መመለስ፤ የመንግስቱ ንዋይ መፈንቅለ መንግስት፤ የ66ቱ አብዮት” በማለት መንደፍ እንደሚቻልም ገልፀዋል፡፡
በእኔ ግለ ታሪክ ከሥራው ይልቅ የስነ ጥበብና የፖለቲካው ምዕራፎች ናቸው ሰፋ ያለ ገጽ የሚይዙት ያሉት ባለቅኔ መንግሥቱ ለማ፣ “ከምር የያዝኩት ስራ፣ የመንግስት ስራ የለም፡፡ የእለት እንጀራዬን ለመብያ፣ ጊዜያዊ ሰላም ለማግኛ ነው ስራ የያዝኩት፡፡ ስራ “የመታሻ” መድረክ ነበር ለኔ” ብለዋል፡፡ ይህ አባባል የህይወቴን ሰፊውን ምዕራፍ ይይዛል ያሉትን ሙያ እንደ ስራ አላዩትም ወይ? ያስብላል፡፡ ምክንያቱም በእነዚህ ሙያዎች የደመቀው ስብዕናቸው ነው ግለ ታሪካቸውን ለመፃፍ ያነሳሳቸው፡፡ አንባቢያንም ለ”ደማሙ ብዕረኛ” መጽሐፍ የሚኖራቸው አድናቆት ከዚሁ ነውና የሚመነጨው፡፡
ሥራቸው መበልፀጊያ ወይም መታወቂያ ሆኖላቸዋል ተብሎ ከልምድና ተሞክሯቸው ሌሎች እንዲማሩበት የህይወት ታሪካቸው በመጽሐፍ ከቀረበላቸው ሰዎች ጥቂት የማይባሉት የተሰማሩበት ሙያ በአገር አቀፍ፣ አንዳንዶቹም በዓለም አቀፍ ደረጃ ምን ታሪክ እንዳለው ለማስቃኘት ሲሞከር ይታያል፡፡
“በቀለ ሞላ የትጋት አርአያ” በሚል ርዕስ በሺበሺ ለማ ተዘጋጅቶ፣ በ2002 ዓ.ም የታተመውን መጽሐፍ ብንመለከት ባለታሪኩ አቶ በቀለ ሞላ በሆቴል ዘርፍ በመሰማራት ስምጥ ሸለቆን በመከተል ከሞጆ እስከ ኬኒያ ድንበር ድረስ 14 ያህል ሆቴሎችን መክፈት ችለዋል፡፡
የሕይወት ታሪካቸውን ያዘጋጀው ደራሲ፣ የሆቴል ዘርፍ በአገራችንም በዓለምም ምን ታሪክ እንዳለው በማመልከት ወይም በማነፃፀሪያነት በማቅረብ፣ የአቶ በቀለ ሞላን ጥረትና ትጋት እንዲሁም ውጤታማነት ለአንባቢያን ማስቃኘት ችሏል፡፡
“በፈተናና በጥረት የታጀበ ስኬት” በሚል ርዕስ በገብረክርስቶስ ኃይለሥላሴና በአፈወርቅ በቀለ ተዘጋጅቶ በ2003 ዓ.ም በታተመውና የአቶ ይጋ አሳመሪን የሕይወትና የሥራ ታሪክ በሚያስቃኘው መጽሐፍ፣ ባለታሪኩ ስኬታማ የሆኑበት የፔትሮሊየም ዘርፍ በአገራችን ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ ታሪካዊ ፍተሻ በማድረግ የባለታሪኩን ስኬት ለማጉላት ከመሞከሩም ባሻገር ስለዘርፉ አነሳስና ዕድገት ለአንባቢያን መረጃ አቅርቧል፡፡
“ያልተነገረለት የሀገር ባለውለታ” በሚል ርዕስ በይድነቃቸው አሰፋ (ወ/ሮ) ተዘጋጅቶ በ2004 ዓ.ም የታተመው መጽሐፍ፣በ1950ዎቹ በቦክሰኝነቱ ይታወቅ የነበረውና በኦሎምፒክ የተሳተፈው በቀለ ዓለሙ (ጋንች) ሲተርክ፣ እግረ መንገዱን የኦሎምፒክ ታሪክ በዓለምና በአገራችን ምን እንደሚመስል፤ስለቦክስ ስፖርትም በተመሳሳይ መልኩ በስፋት አብራርቷል፡፡
አቶ በላይ ተክሉ በሕይወት እያሉ “ሀገር መውደድ” የሚል በአማርኛ እና “Love of mother land” በሚል በእንግሊዝኛ አዘጋጅተው ለወዳጆቻቸው በነፃ ያሰራጩት መጽሐፍ፣በኋለኛው ዘመን ኢትዮጵያዊያን እየተካኑበት የመጣው ኬክ ጋገራና ሽያጭ ከየት ተነስቶና በምን ሂደቶች አልፎ ለዛሬ እንደደረሰ መረጃ የምናገኝበት ታሪካዊ ሰነድ ነው፡፡ “የሕይወት ታሪኬ” በሚል ርዕስ ታትሞ ለአንባቢያን በቀረበውና የፊታውራሪ አመዴ ለማን የሥራና የሕይወት ታሪክ የሚያስቃኘው መጽሐፍ ደግሞ በንጉሡ ዘመን የፓርላማ አባል ለመሆን ውድድሩና ምርጫው ምን ይመስል እንደነበር እንዲሁም ስለ አገራችን የቀድሞ ፖለቲካ ያስቃኘናል፡፡
በወሰን ደበበ ማንደፍሮ ተዘጋጅቶ “ዘመን ተሻጋሪ ባለውለታ” በሚል ርዕስ የተስፋ ገብረሥላሴን የሕይወትና የሥራ ታሪክ በሚያስቃኘው መፅሃፍ ውስጥ የሕትመት ኢንዱስትሪው በዓለም አቀፍ ደረጃና በአገራችንም ምን ታሪክ እንዳለው የሚያመለክቱ ብዙ መረጃዎች ተካትቷል፡፡
በማህበራዊ ጥናት መድረክ ተዘጋጅቶ በ1999 ዓ.ም የታተመው “ተካ ኤገኖ - አንጋፋው የኢንቨስትመንትና የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ተዋናይ” የሚል አነስተኛ መፅሃፍ (ባለሀብቱ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ለሽልማት ስለበቁበት የእርሻ ዘርፍ ሰፋ ያለ ትንታኔ ባያቀርብም) አቶ ተካ ኤገኖና መሰል ባለሀብቶችን ያፈራው የአገራችን ንግድ፣ ከየት ተነስቶ ወዴት እያደገ እንዳለ ሊያመለክት ሞክሯል፡፡
ባለቅኔ መንግሥቱ ለማ፣ ከሌላው ይልቅ ለስነ ጥበቡ ሕይወታቸው ቅድሚያ ለመስጠት እንደፈለጉት ሁሉ፣ በአብዛኛው የሕይወት ታሪክ መፃሕፍትም አንድን ርዕሰ ነገር አጉልቶ ለማሳየት ጥረት ሲደረግ ይታያል፡፡ በበለጠ አበበ ተዘጋጅቶ “ድሮና ዘንድሮ” በሚል ርዕስ ለአንባቢያን የቀረበው የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት የግርማ ወልደጊዮርጊስን መጽሐፍ በተጨማሪ ምሳሌነት ማቅረብ ይቻላል፡፡ ሰፊ የሕይወትና የሥራ ታሪክ ያላቸው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ፣ አሁን ላሉበት ደረጃ ለመድረስ ምክንያት ነው የሚሉትን ሲገልጹ “ለአገሪቱ ፕሬዚዳንትነት ሊያስመርጡኝ ከቻሉት ነገሮች መካከል አንዱ ለአካባቢ ደህንነትና ጥበቃ ተቆርቋሪ መሆኔ ይመስለኛል” ይላሉ፡፡
ከላይ ካየናቸው የተለያዩ መፃሕፍት አቀራረብ አንፃር፣ይህንን የፕሬዚዳንቱን ጥቆማ ስንመለከተው፤ ስለ አካባቢ ደህንነትና ተቆርቋሪነት በዓለም አቀፍና በአገራችንም ያለው ታሪክ ምን ይመስላል የሚል ጥያቄ በማንሳት፣ የመጽሐፉን ርዕሰ ጉዳዮች ማስፋት ይቻል ነበር፡፡
ከዚህ በተቃራኒ ስለ ሕይወትና የሥራ ታሪካቸው ሲተርኩ ሙያቸው፣ ገጠመኛቸው…ቀደም ብሎ በዓለምና በአገራችን ምን ይመስል እንደነበር ፍተሻ ማድረጉ ግድ ሳይሰጣቸው የግላቸውን መውደቅና መነሳት፣ ጥረትና ስኬት እንደወረደ ያቀረቡ የሕይወት ታሪክ መፃሕፍትም አሉ፡፡ “ፈተና” በሚል ርዕስ በአስቴር ሰይፉ ተዘጋጅቶ የታተመው መጽሐፍ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ በመንፈሳዊ ዓለም ያለውን መጠላለፍ ዋነኛው ርዕሰ ጉዳይ አድርጐ በቀረበው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በዓለምና በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የታዩ ሌሎች ክስተቶች ምን ይመስላሉ? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ አላኖረም፡፡
መነሻዬ ላይ ባለቅኔ መንግሥቱ ለማ፣ ግለ ሕይወት ታሪካቸውን ለመፃፍ ሲነሱ የሕይወት ታሪክ እንዴት ነው መፃፍ ያለበት ብለው ለግላቸው ያቀረቡት ጥያቄና በመጽሐፋቸው “መንደርደሪያ” ያስቀመጡትን መልስ ማዕከል አድርገው “ደማሙ ብዕረኛ” መጽሐፍን በአስተማሪነት እንዳቀረቡት ሁሉ፤ በተመሳሳይ መልክ ተዘጋጅተው እየታተሙ ያሉት የሕይወት ታሪክ መፃህፍትም በዘርፉ ለተጀመረው ሥራ ድንቅ ማሳያ ሆነው መቅረባቸውን ማመልከት የመነሻዬ መድረሻ ሆኖ አበቃሁ፡፡ 


Read 9257 times