Saturday, 15 December 2012 13:59

‹‹ቅድመ ወሊድ፣ ወሊድና ድህረ ወሊድ አገልግሎት በነጻ››

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(3 votes)

እናቶችና አዲስ የተወለዱ ሕጻናት በምን ምክንያት ይሞታሉ? የዚህን ችግር ምንጭ ለማግኘትና የተሸሻለ እርምጃ በመውሰድ ሕይወትን የማዳን ቀጣይ ስራ ለመዘርጋት ሲባል የአለም አቀፉ የጽስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር (FIGO) ከኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር (ESOG) ጋር በመተባበር በሀገራችን በተለያዩ ክልል ለመስተዳድሮች ከሚገኙ ዘጠኝ ሆስፒታሎችና አርባ አምስት የጤና ጣቢያዎች ጋር የየእለት ሁነቶችን በመመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡ ክልላዊ መስተዳድሮቹም ኦሮሚያ፣ አምሀራ እና ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልላዊ መስተዳድሮች እና በአዲስ አበባ የካቲት 12 እና ቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የተሰኙት መንግስታዊ ሆስፒታሎች ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር የእናቶችና ጨቅላ ሕጻናት ጤንነትን በሚመለከት ለሚሰራው ስራ የፕሮጀክቱ ማናጀር አቶ ብሩክ ተ/ስላሴ ሲሆኑ በየወሩ በየሆስፒታሎቹ በመገኘት የተሰሩ ስራዎችን በሪፖርት በመሰብሰብ
* እናቶችና ጨቅላ ሕጻናት በምን ምክንያት ለሞት ይዳረጋሉ
* እናቶች በምን ያህል ደረጃ ወደጤና ተቋማት በመሄድ የእርግዝና ክትትል ያደርጋሉ
የእርግዝና ክትትል ናደረጉት መንከልስ ምን ያህሎቹ በሰለጠነ ባለሙያ እገዛ ይወልዳሉ
* ወደየጤና ተቋማቱ ሲሄዱ ምን ያህሎቹ የህክምና እርዳታ ያገኛሉ
የሚሉትንና ተያያዥ ጥያቄዎችን ማእከል ባደረገ መልኩ ውይይቶች ይካሄዳሉ፡፡ እንደውጭው አቆጣጠር በ October /2012 የተሰራውን ስራ ከ November 16/2012 ጀምሮ በዘጠኙም ሆስፒታ ሎች በመዘዋወር ስራውን የዚህ አምድ አዘጋጅ ቃኝታለች፡፡ በዚህ እትም ከአማራ ክልል በደ ብረብርሀን አካባቢ ያለውን ሁኔታ በሆስፒታሉ ስራውን በመስራት ላይ የሚገኙት ባለሙያ ዎች ያብራሩልናል፡፡
--------------////----------------
‹‹ ...ስሜ ዶ/ር ሜላት ሰብስቤ ይባላል፡፡ በአሁኑ ወር በደብረብርሀን ሶስት የእናቶች ሞት ተመዝግቦአል፡፡
ለዚህም ምክንያቱ ከእርግዝና ጋር ተያይዞ የሚመጣ የደም ግፊት(Eclampsia,preclampsia) ሲሆን በዚህ ችግር ሁለት እናቶሰስን አጥተናል፡፡ ሌላው ምክንያት የወባ ሲሆን ከዚህም ጋር ተያይዞ በተከሰተ የደም ማነስ ምክንያት አንዲት እናት ለህልፈት ተዳርጋለች፡፡ በእርግጥ በእርግዝና ጊዜ ለሚከሰት የደም ገፊት የሚሰጥ መድሀኒት ማግኔዥየም ሰልፌት እና ሌላም ግፊትን ማውረድ የሚችል መድሀኒት ቢኖርም እናቶቹ ለረጅም ጊዜ እስከ አራት እና ከዚያም በላይ ለሆነ ቀን በሽታው እያሰቃያቸው በቤታቸወ ቆይተው የመጡ ስለነበሩ ሆስፒታል ከደረሱ በሁዋላ በጣም ቢዘገይ ለሰላሳ ደቂቃ ያህል ብቻ በሕይወት የቆዩ ነበሩ፡፡
ስለዚህ አብዛኛው ነገር ከተዳከመ በሁዋላ ሆስፒታል በመድረሳቸው ሕይወታቸውን ማትረፍ አልተቻለም፡፡ ወባ የነበረባትና የደም ማነስ የገጠማት እናትም የመጣችው ከሸዋ ሮቢት ሲሆን ሆስፒታል ስትደርስ ሄሞግሎቢንዋ 2.2 የደረሰና በከፍተኛ ደረጃ የታመመች ስትሆን ታሪኩዋንም ስናጣራ ወባ ባለበት አካባቢ የምትኖር እና ከስድስት ወር በላይ በወባ ሕመም ትሰቃይ የነበረች ችግሩን በሙሉ በቤቷ ይዛ የቆየች ነበረች፡፡
እነዚህ እንግዲህ ወደሆስፒታል ደርሰው ሕይወታቸው ያለፉት ሲሆኑ በቤታቸው እንዳሉ የሚሞቱትን ግን ለጊዜው ባናውቅም ከጤና ጣቢያዎች ጋር ባለን የስራ ግንኙነት ወደፊት በሚሰጡን ሪፖርትም ሆነ እኛም ሄደን መረጃውን ለመሰብሰብ እቅድ አለን፡፡››
----------------///--------------------
‹‹..ዶ/ር አዲሱ ግርማ እባላለሁ፡፡ ከእኛ ጋር ከሚሰሩ አምስት ጤና ጣብያዎች ጋር ባለን የስራ ግንኙነት እንደምናውቀው ሁለት ጤና ጣቢያዎች ማለትም ደብረብርሀንና ጫጫ ጤና ጣቢያዎች ከጤና ኤክስ..ንሽን ሰራተኞቹ ጋር በየሳምንት እየተገናኙ በእናቶች ዙሪያ ያሉ መረጃዎችን ይቀባበላሉ፡፡ በየትኛው ቀበሌ እርጉዝ ሴት እንዳለች በመመዝገብ የእርግዝና ክትትል እንዲያደርጉም በመምከር ጤናቸውን እንዲከታተሉ ይደረጋል፡፡ በእነዚህ ጤና ጣብያዎች ዙሪያ በሚሰሩ የጤና ኤክስ..ንሽን ሰራተኞች አማካኝነት እናቶች ቢሞቱ እንኩዋን ስለሚታወቅ ይመዘገባል፡፡ አንኮበር ጤና ጣቢያ ላይ ግን ትስስሩ የላላ በመሆኑ እናቶች ቢሞቱ እንኩዋን ሪፖርት አያደርጉም ፡፡
ቀይት እና ጎሽይድ ጤና ጣቢያ ላይም እርጉዞች የእርግዝና ክትትል ቢያደርጉም በወሊድ ጊዜ ግን ወደሐኪም ቤት ሄዶ መውለዱ የሳሳ እና ቢሞቱም ሪፖርት ስለማይደረግ ክፍተት አለ፡፡ ››
------------------------////--------------------
‹‹...ዶ/ር ፍሰሐ ታደሰ እባላለሁ፡፡ በደብረብርሀን ሆስፒታል የጽንስና ማህጸን ሐኪምና የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ነኝ፡፡ በአካባቢያችን ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች ብዙውን ጊዜ ወላዶች ወደሕክምና ተቋም ሄደው አለመውለዳቸው አንዱ ችግር ሲሆን ሌላው ደግሞ ከሄዱም በአቅራቢያቸው ወደሚገኘው ወደጤና ጣቢ ያዎች ሳይሆን መውለድ የሚፈልጉት ወደትልቅ ሆስፒታል በመሄድ ነው፡፡ የዚህም አንዱ ምክንያት ብዙው ሕዝብ የሚኖረው በገጠር አካባቢ መሆኑና በአቅራቢያቸው ጤና ጣቢያዎች አለመገኘታቸው ሲሆን ወደትልቅ ሆስፒታል ለመምጣት ደግሞ የትራንስፖ ርትና የተለያዩ ችግሮች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ይህንን ችግር ግን በየወረዳው የተመደቡ አምቡላንሶች እየፈቱት ይገኛሉ፡፡ ሌላው የክፍያ ጉዳይ ሲሆን ይህም በክልሉ መንግስት በነጻ ሕክምናው እንዲሰጥ በመወሰኑ ትልቅ ችግር ተቃልሎአል ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እናቶች በቤታቸው የሚወልዱት በባህላዊ ወይንም በልማዳዊው አኑዋኑ ዋር በምጥ ሰአት ቤተሰብ ስለሚያጅብና ሲወልዱም አብረው እፍን እፍን በማድረግ ስለ ሚያስተናግዱዋቸው ሲሆን ይህ ሁኔታ በሆስፒታል ወይንም በጤና ጣብያ ለመውለድ በሚመጡበት ጊዜ የማያገኙት በመሆኑ መውለድን በቤታቸው ቢያደርጉት ይመርጡ ነበር፡፡
በአሁኑ ወቅት ግን ጤና ተቋማቱ ለቤተሰብ በአቅራቢያ መሆናቸው እና መደጋገፍ መቻላቸው ሁኔታዎችን እያመቻቸ ስለሆነ ችግሩ በመቃለል ላይ ይገኛል፡፡ ስለዚህም በሂ ደት በህክምና ተቋማት የመውለድ ነገር እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው፡፡ በደብረብርሀን ሆስፒታል ከአስር አመት በፊት በአመት እስከ ሁለት መቶ ድረስ ይወለድ የነበረ ሲሆን በአሁን ጊዜ ግን በአመት ከሁለት ሺህ በላይ እናቶች በሆስፒታል በሰለጠነ ባለሙያ ይወ ልዳሉ፡፡
እንደምናገኘው ሪፖርት ከሆነ ጤና ጣቢያዎቹም ከአሁን ቀደም ምንም የማያዋ ልዱ ሲሆን አሁን ግን የወሊድ መጠኑ እየጨመረ ያለበት ሁኔታ እየተመዘገበ ነው፡፡
ከአሁን ቀደም ከተመዘገቡ ችግሮች አንዱ የባለሙያ እጥረት ሲሆን በአሁን ወቅት ግን አዋላጅ ነርሶች በየጤና ተቋሙ እየተመደቡ ስለሆነ ችግሩ በመቃለል ላይ ይገኛል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በወሊድ ጊዜ ለሚያጋጥም አፋጣኝ አገልግሎት ብቁ የሆኑ ባለሙያ ዎች እጥረት የነበረ በመሆኑ የማህጸን መተርተር የመሳሰሉት ችግሮች ሲከሰቱ አገልግ ሎቱ የሚሰጠው በደብረብርሀን ሆስፒታል ብቻ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን ጠቅላላ ሐኪሞች በመሰልጠናቸው በመሀል ሜዳ ሆስፒታል እና በአለም ከተማ ሕክምናውን በመስጠት ላይ በመሆናቸው እናቶች ካለችግር በአካባቢያቸው ባሉ የሕክምና ተቋማት መውለድ ችለዋል፡፡ ስለዚህ ሁኔታዎች በመሻሻል ላይ በመሆናቸው የእናቶችን ሞት ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት እየዋለ እያደረ ስኬታማ እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡››
-----------------------///-------------------------
‹‹ ... አቶ ጌታቸው እባላለሁ፡፡ የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ ነኝ፡፡ በወደፊቱ አካሄድ እንደ ተስፋ ሊቆጠር የሚችለው በአሁኑ ወቅት ጥሩ ልምድ ያላቸው የህክምና ተቋማት ለሌሎቹ ልምዳቸውን በማካፈል ላይ በመሆናቸው እንደ ጥሩ ነገር ልንወስደው የምን ችለው ነው፡፡ በዚህም መሰረት የደብረብርሀን ሆስፒታል በምስራቅ አማራ አካባቢ ካሉ ሆስፒታሎች ለጥናት በመመረጥ እና በሌሎችም አሰራሮቹ እንደ መሪ ሆስፒታል የሚቆጠር ሆኖአል ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የእናቶችና ጨቅላ ሕጻናት ሞት መንስኤን ለማወቅ የሚረዳው ይህ አሰራር በሌሎች ሆስፒታሎች ዘንድ ተነሳሽነትን የፈጠረበት ሁኔታ ተስተውሎአል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የክልሉ መንግስት ምክር ቤት የእናቶችን የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ቅድመ ወሊድ ፣የወሊድና እና ድህረ ወሊድ አገልግሎት በየሆስፒታሉ በነጻ እንዲሰጥ አውጆአል፡፡ ይህ ህብረተሰቡን በጣም አበረታትቶአል፡፡ በክልሉ በተለያዩ ቀበሌ ገበሬ ማህበራት የሚሰሩ የጤና ኤክስ..ንሽን ሰራተኞች በየቤቱ በመዞር የልደትና የሞት መጠንን በመመዝገብ ላይ በመሆናቸው የእናቶችና የጨቅላ ሕጻናት ሞት ምክንያትን ለማወቅ አመቺ አሰራር ተዘርግቶአል ማለት ይቻላል፡፡ ››

Read 9753 times