Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 15 December 2012 14:04

ዋልያዎቹ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ከ31 ዓመታት መራቅ በኋላ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሚካፈለው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን መደበኛ ልምምዱን ከጀመረ አንድ ሳምንት ሲያልፈው በደቡብ አፍሪካ የሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ አንድ ወር ቀርቶታል ፡፡ብሄራዊ ቡድኑ ካሳንችስ በሚገኘው ኢንተር ኮንትኔንታል ሆቴል በማረፍ በቀን ሁለት ጊዜ ልምምዱን እየሰራ ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሐረር ቢራና በደሌ ቢራ ፋብሪካዎችን ከገዛው ሄኒከን ኢንተርናሽናል ጋር የ24 ሚሊዮን ብር የስፖንሰር ሺፕ ስምምት ተፈራረመ፡፡ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በሂልተን ሆቴል በተደረገ ስነስርዓት ስምምነቱን የተፈራረሙት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በኩል ፕሬዝዳንቱ አቶ ሳህሉ ገብረወልድ እና በሄኒከን ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ተወካይ ሚስተር ጆሃን ዶየር ናቸው፡፡ በሄኒከን ኢንተርናሽናል ባለቤትነት የተያዘው በደሌ ቢራ ‹በአፍሪካ ዋንጫው ጉዞ አብረን እንደሰት፤ ገስግሱ ዋልያዎች› በሚሉ መርሆች የስፖንሰርሺፕ ድጋፉን ሊሰጥ አቅዷል፡፡ የሄኒከን ኢንተርናሽናል ተወካይ የሆኑትና የበደሌ ቢራ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ ሚስተር ጆሃን ዶዬር ኩባንያቸው ዋልያዎቹን በአብይ ስፖንሰርነት በመደገፉ ኩራት እንደሚሰማው ተናግረዋል፡፡ በስምምነቱ መሰረት በዋልያዎቹ ስፖንሰርሺፕ ከሄኒከን ኢንተርናሽናል በዓመቱ የ12 ሚሊዮን ብር ክፍያ እንደሚፈፀም ሲገለፅ በመጀመሪያው ዙር ክፍያም 6 ሚሊዮን ብር ከፊርማ ስምምነቱ በኋላ እንደተሰጠ ታውቋል፡፡ 
ይህ በእንዲህ እንዳለ የ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ ደቡብ አፍሪካ ያደረገችውን ዝግጅት ለመታዘብ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ከሳምንት በፊት ወደዚያው አገር ተጉዞ መመለሱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኮሚዩኒኬሽን ክፍል ገለፀ፡፡ ለመስክ ጉብኝቱ ወደ ደቡብ አፍሪካ ያቀኑት የእግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ሳህሉ ገ/ወልድና የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ናቸው፡፡ ልዑካኑ በደቡብ አፍሪካ ቆይታው ብሄራዊ ቡድኑ የሚያርፍበትን ሆቴል በመምረጥ እና የመስተንግዶ ሁኔታውን በመፈተሽ፤ ልምምድ የሚሰራበትን ቦታ በስፍራው ተገኝቶ በመገምገምና የምድብ ጨዋታዎቹን የሚያደርግበትን ስታድዬም በመጎብኘት እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት እያደረጉ ያሉትን እንቅስቃሴ በመታዘብ ሰፊ ተግባራትን አከናውኗል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከጆሀንስበርግ ኤርፓርት የ8 ደቂቃ መንገድ ርቀት በሚገኘው ባለ አምስት ኮከብ ፕሪቶኣ ሆቴል እንዲያርፍ መወሰኑን የጠቀሰው የኮምኒኬሽን ክፍሉ መግለጫ ልምምዱንም ከ10-15 ደቂቃ ጉዞ በማድረግ በአካባቢው በሚገኘውና የተፈጥሮ ሳር በተነጠፈለት ስታዲየም እንደሚያከናውን አመልክቶ ልዑካኑ በልምምድ ሜዳው ላይ የተወሰኑ ማሻሻያዎች እንዲደረጉለት አስተያየት በመስጠት ከመግባባት ላይ መደረሱን ጠቁሟል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሚያርፍበት ሆቴል ማናጀርና ዋና ሼፍ ጋር ልዑካኑ እንረተናጋገረና በተጨዋቾች አመጋገብ ላይ ሊኖር የሚችለውን መስተንግዶ የሚያሳይ መረጃ መቀበሉንም ለማወቅ ተችሏል፡
የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት እና ዋና አሰልጣኙ በምድብ 3 ዋልያዎቹ ግጥሚያዎችን የሚያከናውኑበትን የኔልስፕሪት ክፍለሀገር ውስጥ የሚገኘውን የሞምቤላ ስታድዬምም ጎብኝተዋል፡፡ ዋልያዎቹ የምድብ ጨዋታቸውን የሚያደርጉበት ስታድዬሙ ከጆሀንስበርግ በ55 ደቂቃ የአውሮፕላን በረራ ወይም በምድር ትራንስፖርት ከ2-3 ሰዓት በሚወስድ ጉዞ እንደሚደረስ በኮምኔክሽን ክፍሉ በተላከው መረጃ ተገልጿል፡፡ አቶ ሳህሉ ገብረወልድ እና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ከደቡብ አፍሪካ እግር ኳስ ማህበር (ሳፋ) የውድድር አዘጋጅ ዋና ሃላፊ ጋር በመነጋገርም በቲኬት፣በቪዛ ፕሮሰስ፣ስለትጥቅ አጠቃቀምና በአጠቃላይ ስለውድድሩ በመረጃ የተደገፈ ሰነድ ይዘው መምጣታቸውን አመልክቷል፡፡የልዑካን ቡድኑ በተጨማሪም ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከኢትዮጵያውያን ኮሚዩኒቲ ተወካዮች ጋር በመቀናጀት ብሔራዊ ቡድኑን ለመደገፍ ጠንካራ ኮሚቴ አዋቅረው ስለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ክትትል በማድረግም ውጤታማ ስራዎችን ለማከናወን ማቀዱ ታውቋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የቅዱስ ጊዮርጊስንና የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ታዋቂ አስጨፋሪዎች የሆኑት አቼኖና አዳነ ደቡብ አፍሪካ ድረስ በመጓዝ ከኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ አባላት ጋር በመሆን የእግር ኳስ ውድድሮችንና የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ የፌዴሬሽኑ የኮሚዩኒኬሽን ክፍል የላከው ዘገባ ያስረዳል፡፡
ከ50 በፊት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ብድን ‹ጥቁር አናብስት› ተብሎ ብቸኛ የአፍሪካ ዋንጫ ድሉን በእነቫሳሎ፤ በእነ መንግስቱ ትውልድ ማስመዝገቡ ይታወሳል፡፡ የያኔው ብሄራዊ ቡድን የአፍሪካ ብራዚል ተብሎ በበርካታ የአፍሪካ መገናኛ ብዙሃናት ሊደነቅ የበቃ ነበር፡፡ ዛሬ ‹ዋልያዎቹ› ተብሎ የሚጠራው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በእነ አዳነ፤ ሳላዲንና በደጉ ትውልድ ከ31 ዓመታት በኋላ በታሪኩ ለ10ኛ ጊዜ ወደ የሚሳተፍበት የአፍሪካ ዋንጫ በማለፍ ታሪክ መስራቱን ጀምሯል፡፡በቅርቡ ለንባብ የበቃው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ላይ እትም ሰላምታ መፅሄት በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ ከምድብ ማጣሪያው እንደማታልፍ ሲገምት የቡድኑ ቁልፍ ተጨዋች ኡመድ ኡክሪ መሆኑንም ገልጿል፡፡ አፍሪካ ዋንጫው ሊጀመር አንድ ወር እስኪቀረው እየወጡ ባሉ ቅድመ ግምቶች ኢትዮጵያ ከምድቡ የማለፍ እድሏ የተመናመነ መሆኑን የሚገልፁ ጥቂት አይደሉም፡፡ አንዳንድ መረጃዎች ግን ዋልያዎቹ ያልተጠበቀ ውጤት በማስመዝገብ መላው አህጉሪቱን እንደሚያስደንቁ ይገልፃሉ፡፡ ሳላዲን ሰኢድ፤ አዳነ ግርማ እና ደጉ ደበበ በበርካታ ዘገባዎች ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫው ወሳኝ እና ቁልፍ ሚና እንደሚኖራቸው ተመስክሯል፡፡
በዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ዘገባዎቹ የሚታወቀው ጐል የተባለው ድረገፅ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ላይ ሙሉ መግለጫ ከመስጠቱም በላይ አንባቢዎቹን ባሳተፈ የውጤት ትንበያ ያገኛቸውን መረጃዎችንም በስፋት አቅርቧል፡፡ከ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በፊት ኢትዮጵያ ከ31 ዓመት በፊት በተካፈለችባቸው 9 የአፍሪካ ዋንጫዎች 24 ግጥሚያዎች አድርጋ 7 ድል፣ 2 አቻ፣ 15 ሽንፈት ስታስመዘግብ በተጋጣሚዎቿ ላይ 28 ጎል በማግባት እና 54 ጎሎችን ያስተናገደችበት ታሪክ አላት፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለዘጠኝ ጊዜያት በአፍሪካ ዋንጫ ሲሳተፍ በ1962 እኤአ ላይ በ3ኛው አፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን ከመሆኑም በላይ ካበ1957 እ.ኤ.አ ሁለተኛ ደረጃ፣ በ1959 እ.ኤ.አ ሦስተኛ ደረጃን በ1963 እና በ1968 እ.ኤ.አ አራተኛ ደረጃ ን አግኝቷል፡፡ በኦልታይምሶከር ድረገፅ የቀረበው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የውጤት ታሪክ እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ ከዛምቢያ ጋር በታሪኳ 8 ጊዜ ተገናኝታለች፡፡ አራት ጨዋታዎችን በሜዳዋ፤ 3 ጨዋታዎችን በዛምቢያ ሜዳ እንዲሁም አንዱን ጨዋታ በሌላ አገር ከዛምቢያ ጋር ያደረገችው ኢትዮጵያ 2 ጊዜ ስታሸንፍ በሁለቱ አቻ ወጥታ በአራት ግጥሚያዎች ተሸንፋለች፡፡ ኢትዮጵያ ከቡርኪናፋሶ ጋር በሁሉም ውድድሮች 2 ጊዜ ተገናኝታለች፡፡ ግጥሚያዎቹ 1 በሜዳዋ ሌላው በቡርኪናፋሶ ሜዳ የተደረጉ ሲሆን እኩል 1 ጊዜ ተሸናንፈዋል፡፡ ከናይጄርያ ጋር ደግሞ በ5 ግጥሚያዎች ተገናኝታ የምታውቀው ኢትዮጵያ ሁለት በሜዳዋ፣ ሁለት በናይጀሪያ ሜዳ፣ 1 በሌላ ሀገር የተፋለመች ሲሆን 1 ጊዜ ድል፣ 1 ጊዜ አቻ፣ 3 ጊዜ ሽንፈት በውጤቷ አስመዝግባለች፡፡ በኢንፎስትራዳ ድረገጽ እንደቀረበው መረጃ ኢትዮጵያ ከምድብ 3 ቡድኖች በተገናኘችባቸው ጨዋታዎች ዛምቢያን 35.71%፤ ናይጀሪያን 16.67% እንዲሁም ቡርኪናፋሶ 50% የማሸነፍ እድል እንደሚኖራት ተሰልቷል፡፡
የጐል ድረገጽ አንባቢዎች በሰጡት የውጤቶች ትንበያ መሰረት ኢትዮጵያ በምድብ 3 ያሉ ተቀናቃኞችን በመርታት ወደ ጥሎ ማለፍ የመግባቷ ዕድሏ አጋድሏል፡፡ ከአንድ ሳምንት በፊት በድረገፁ አንባቢዎች ለኢትዮጵያ የተነበዩት ውጤቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡
ዛምቢያ ከኢትዮጵያ
ዛምቢያ 1-2 ኢትዮጵያ -44.4 %
ዛምቢያ 3-1 ኢትዮጵያ -14.82 %
ዛምቢያ 0-2 ኢትዮጵያ - 11.11%
ቡርኪናፋሶ ከኢትዮጵያ
ቡርኪናፋሶ 1-3 ኢትዮጵያ - 66.67%
ቡርኪናፋሶ 1-2 ኢትዮጵያ -33.33%
ናይጀሪያ ከኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ 2-2 ናይጀሪያ - 33.33%
ኢትዮጵያ 1-0 ናይጀሪያ - 22.22%
ኢትዮጵያ 8-0 ናይጀሪያ - 11.11%

Read 6528 times Last modified on Wednesday, 19 December 2012 14:03

Latest from