Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 15 December 2012 15:48

ቅ/ሲኖዶሱ ተመራጩ ፓትርያርክ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ብቻ እንዲኾን ወሰነ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

‹‹የጳጳሱ ቅሌት›› መጽሐፍ ጸሐፊ በ‹‹የጳጳሱ ስኬት›› መጽሐፍ ይቅርታ ጠየቀ
በፓትርያርክ ምርጫ ሕግ ረቂቅ ላይ ውይይት እያካሄደ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ* የተመራጩ ፓትርያርክ ዜግነት ኢትዮጵያዊ ብቻ መኾን እንደሚገባው ወሰነ፡፡
በሃይማኖቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታይ ኾኖ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን ጠንቅቆ ያወቀ፣ በትምህርተ ሃይማኖት በቂ ችሎታ ያለውና በግብረ ገብነቱ የተመሰገነ፣ በትውልዱም በዜግነቱም የውጭ ዜጋ የኾነ አባት* ለፓትርያርክነት በተቀመጠው መመዘኛ መሠረት በዕጩነት ለመቅረብ የሚችልበት ዕድል እንዳለ በሲኖዶሱ መጤኑን የስብሰባው ምንጮች ተናግረዋል፡፡

በቤተ ክርስቲያኒቱ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ አገልግሎት በተደራጁት ከሰባት በላይ አህጉረ ስብከት በርካታ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት መቋቋማቸውን ያስረዱት የስብሰባው ምንጮች* በተጠቀሰው ደረጃ መስፈርቱን አሟልቶ ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግል፣ በትውልዱም በዜግነቱም ኢትዮጵያዊ ያልኾነ አባት ለማግኘት አዳጋች ኾኖ መታየቱ ተዘግቧል፡፡
በሌላ በኩል በትውልዳቸው ኢትዮጵያዊ ኾነው የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው በቁጥር ከአራት ያላነሱ ጳጳሳት እንዳሉ ተጠቁሟል፡፡ ከእኒህም ውስጥ የምርጫ ሕግ ረቂቁን መጽደቅ ተከትሎ በሲኖዶሱ እንደሚቋቋም በሚጠበቀው አስመራጭ ኮሚቴ አማካይነት ይካሄዳል በተባለው የስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫ* በዕጩነት ሊቀርቡ የሚችሉ አባቶች በዜግነት መመዘኛው ምክንያት ከውድድር ውጭ መኾናቸው ያላስደሰታቸው ወገኖች መስፈርቱን ተቃውመዋል፡፡ ተቃዋሚዎቹ ቤተ ክርስቲያን* ሰዎች በክርስቲያናዊ እምነትና ሥነ ምግባር እንጂ በዜግነት የማይለዩባት ዓለም አቀፋዊት (ኵላዊት) መኾኗን በመጥቀስ ይከራከራሉ፡፡ የአንቀጹን መካተት የሚደግፉቱ ደግሞ የኢትዮጵያዊነትን መንፈሳዊ እሴት፣ ኦርቶዶክሳዊነት ከኢትዮጵያዊነት ጋራ ያለውን ታሪካዊና ትውፊታዊ ቁርኝት፣ በሃይማኖት አባትነት ከራስ ምቾትና ፍላጎት አኳያ ዜግነትን መቀየር ለትውልድ ያለውን አርኣያነት በመጥቀስ ለክርክሩ ምላሽ ይሰጣሉ፡፡
ታኅሣሥ አንድ የተጀመረውና ጋዜጣው ለኅትመት እስከገባበት ሰዓት ድረስ ያላበቃው የሲኖዶሱ ስብሰባ በጥቅምት ወር በተቋቋመው የፓትርያርክ ምርጫ ሕግ አርቃቂ ኮሚቴ ተዘጋጅቶ በቀረበለትና 15 አንቀጾች ባሉት ረቂቅ ላይ መወያየቱን ቀጥሏል፤ 12 ያህል አንቀጾችንም ማጽደቁ ተገልጧል፡፡ በምልአተ ጉባኤው ከፍተኛ ክርክር ተደርጎባቸው ከጸደቁት የምርጫ ሕግ ረቂቁ አንቀጾች መካከል* በፓትርያሪክ ሥያሜው፣ ምርጫ ወይም ዕጣ እንደ ሥርዐት የሚካተትበት ኹኔታ አንዱ እንደነበር ተነግሯል፡፡
በረቂቁ መሠረት ከሰባት ያልበለጡ ከሦስት ያላነሱ ዕጩዎች 19 አባላት ባሉት አስመራጭ ኮሚቴው አማካይነት ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤው ይቀርባሉ፡፡ የመጨረሻዎቹ ዕጩዎች በምልአተ ጉባኤው ከተለዩ በኋላ፤ በሲኖዶሱ አባላት፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጀምሮ በየደረጃው በሚገኙ ሓላፊዎች፣ በአገር ውስጥና ከውጭ አህጉረ ስብከት በተወከሉ የገዳማት አበምኔቶችና እመምኔቶች፣ የካህናት፣ ሰንበት ት/ቤት፣ ምእመናንና ዕውቅና በተሰጣቸው መንፈሳውያን ማኅበራት ተወካዮች አማካይነት በምስጢር በሚሰጠው ድምፅ ከፍተኛ ድጋፍ ያገኘው ዕጩ ለፕትርክናው ይበቃል፡፡ በሲኖዶሱ ውሳኔ መሠረት ምርጫ ዋነኛው ሥርዐት ኾኖ የተወሰደ ሲሆን ከዕጩዎቹ መካከል እኩል ድምፅ ያገኙ ቢኖሩ በዕጣ የሚለዩበትና ተመራጩ ፓትርያርክ የሚታወቅበት አሠራር እንደሚኖር ተገልጧል፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ የሥርዐት መጽሐፍ መሠረት ለፕትርክና በዕጩነት የሚቀርበው ጳጳስ ዕድሜ ኀምሳ ዓመትና ከዚያ በላይ መኾን ስለሚገባው፣ በረቂቁ የቀረበው የ45 ዓመት መነሻ መለወጡ ተመልክቷል፡፡ በሕጉ ረቂቅ የገዳም መነኵሴን ጨምሮ ኤጲስ ቆጶስ፣ ጳጳስና ሊቀ ጳጳስ በዕጩነት መቅረብ እንደሚችሉ ተገልጦ የነበረ ቢሆንም መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት በመፈጸም በቂ የአስተዳደር ችሎታና ልምድ ከማካበት አንጻር የገዳም መነኵሴ የሚለው እንዲወጣ መደረጉ የሂደቱን ተከታታዮች አነጋግሯል፡፡ በሰሜን አሜሪካ የስደት ሲኖዶስ ካቋቋሙ ጳጳሳት ጋራ ከኅዳር 26 - 30 ቀን 2005 ዓ.ም በዳላስ ቴክሳስ የተካሄደው ውይይት ተስፋ ሰጪ የሰላምና አንድነት ፍላጎት በታየበት መልኩ መቋጨቱ በተነገረበት ወቅት* ቅ/ሲኖዶሱ በፓትርያርክ ምርጫ ሕገ ደንብ ላይ የሚያካሂደው ውይይት የበለጠ ጊዜ እንዲሰጠውና ትዕግሥት እንዲደረገበት ለአዲስ አድማስ አስተያየታቸውን የሰጡ የጠ/ቤተ ክህነቱ አካላት ጠይቀዋል፡፡
በሌላ በኩል የቀድሞው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ በነበሩት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ላይ ‹‹የጳጳሱ ቅሌት›› በሚል ርእስ መጽሐፍ የጻፈውና ‹‹ተከሥተ ዘሪሁን›› በተባለ ኅቡእ ስም የሚታወቀው ጸሐፊ* ‹‹የጳጳሱ ስኬት›› በተሰኘ ሌላ መጽሐፍ፣ ሊቀ ጳጳሱንና በቀደመው መጽሐፉ ‹‹አለስማቸውና አለግብራቸው ተጠቅሰዋል›› ያላቸውን ግለሰቦች በመዘርዘር ይቅርታ ጠይቋል፡፡ በ‹‹የጳጳሱ ቅሌት›› መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹት ‹‹ሳሙኤል›› ከሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ጋራ በምንም መልኩ ግንኙነት የሌላቸው ናቸው ያለው ጸሐፊው* ‹‹የሊቀ ጳጳሱን ስም ለማጥፋት፣ ዘመኑን በአስተሳሰብና በተግባር በመዋጀት በሰጡት ከፍተኛ አመራር ለቤተ ክርስቲያን ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ለማጠልሸት ብሎም ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመናፍቃን አሳልፎ ለመስጠት ያሤሩ ናቸው›› ባላቸው ግለሰቦች ፍላጎት በመገዛቱ መጸጸቱንና ሊቀ ጳጳሱን አቡነ ሳሙኤልን ይቅርታ እንደሚጠይቅ ገልጧል፡፡

Read 4786 times