Saturday, 15 December 2012 15:50

አንድነት የክልሎች የህዝብ አደረጃጀትን አጠናክራለሁ አለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የደቡብና ሰሜን ቀጠና አስተባባሪዎችን መድቦ ትናንት ሽኝት አደረገ፡፡
የፓርቲው ህዝብ አደረጃጀት ጉዳይ ኃላፊ ኢንጅነር ዘለቀ ረዲ ትናንት ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ፓርቲው አገሪቱን አዲስ አበባን ጨምሮ በአምስት ቀጠናዎች በመከፋፈል የህዝብ አደረጃጀቱንና የማስተባበር ሥራውን ለመሥራት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በዚሁ መሰረት በሰሜን እና በደቡብ ቀጠናዎች ህዝቡን የማደራጀትና የማስተባበር ሥራ እንዲሰሩ ሁለት ኃላፊዎችን መድቦ፣ ወደ ቦታው የላከ ሲሆን አቶ ግርማ አማረን ለደቡብ ቀጠና፣ አቶ አዕምሮ አወቀን ደግሞ ለሰሜን ቀጠና አስተባባሪነት በመመደብ ትናንት ሽኝት አካሂዷል፡፡ ይህም በአገሪቱ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ታሪክ ከዚህ ቀደም ያልተደረገና አዲስ አሰራር ነው ብለዋል፡፡

ገዢው ፓርቲ በአገሪቱ ውስጥ ራሱን ብቻ አንሰራፍቶ እንደልቡ እንዲሆን ያደረገው የተቃዋሚ ፓርቲዎች በየክልሉ አለመድረስና ከህዝቡ ጋር አለመገናኘት ነው ያሉት ኢንጅነሩ፤ ሁኔታውን ለመቀየርና ከዚህ ቀደሙ በተለየና በተጠናከረ ሁኔታ የህዝብ አደረጃጀትና የማስተባበሩን ሥራ ለመሥራት ዝግጅታችንን አጠናቀናል ብለዋል፡፡ በቀጣይም በምዕራብ፣ በምሥራቅና በመሃል አገሪቱ ላይ አስተባባሪዎችን በመላክ የህዝብ አደረጃጀት ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ኢንጅነር ዘለቀ ገልፀዋል፡፡በተያያዘ ዜና ፓርቲው በነገው እለት በሚያካሂደው ስብሰባ፣ በምርጫው ላይ ሰፋ ያለ ውይይትና ክርክር በማካሄድ አቋም እንደሚይዝና አቋሙንም ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

Read 2204 times