Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 22 December 2012 09:49

3ቱ የፖለቲካ አጀንዳዎች - ለኢህአዴግና ለተቃዋሚዎች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የፖለቲካ ነገር ጭራና ቀንዱ መግቢያና መውጫው የማይታወቅ፤ በዚህ በኩል ሲይዙት በዚያ የሚያፈተልክ ውስብስብ ጉዳይ የሚመስላቸው ሰዎች ጥቂት አይደሉም - አንዳንዶቹ ውስብስብነቱ ቢማርካቸውም ብዙዎች ይሸሹታል። ግን ከፖለቲካ የሚያመልጥ የለም። በታክስ ጫና ወይም በዋጋ ንረት ኑሯቸው የሚናጋው፤ በ97ቱ አይነት የምርጫ ቀውስ ወይም በሃይማኖትና በብሄረሰብ ግጭት ህይወታቸው አደጋ ላይ የሚወድቀው በፖለቲካ ምክንያት ነው። ሙስናና አድልዎ፣ ፕሮፓጋንዳና አፈና... የፓለቲካ ጉዳይ ናቸው። ከፖለቲካ መሸሽ፣ የትም አያደርስም። ደግሞምኮ ፖለቲካ ውስብስብ አይደለም። በእርግጥ፤ ዋናውን የፖለቲካ ጥያቄ ትተን፣ ቅርንጫፍና ቅጠሉን ዝርዝርና ምንዝሩን እየነካካን ለመምዘዝና ለመተርተር ከሞከርን፤ እዚያው ተተብትበን መቅረታችን አያጠራጥርም።

ከመስረታዊው ጥያቄ የምንነሳ ከሆነ ግን፤ ለማሰብ የመፈለግና ያለመፈለግ ጉዳይ ካልሆነ በቀር የፓለቲካ ነገር እጅግ በጣም ቀላል ነው።
“እያንዳንዱ ሰው፣ በራሱ ሃሳብና ውሳኔ፣ በራሱ ፈቃድና ምርጫ፣ የራሱን ሕይወት የመምራት ነፃነት ሊኖረው ይገባል ወይስ አይገባም?” ...ይሄው ነው ዋናው የፖለቲካ ጥያቄ። ለጥያቄው የምንሰጠው ምላሽ ደግሞ፣ ጠቅላላ የፖለቲካ አቋማችንን ይወስናል። ሌሎቹ የፖለቲካ አጀንዳዎች... መርሆችና ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂና ህጎች በመሉ ከዚህ ጥያቄ ዝርዝርና ምንዝር ናቸው። ጥያቄውን ገልብጠን ልናየው እንችላለን። “የሌሎችን ሕይወት እንዳሻው የማዘዝ ስልጣን የያዘ አካል መኖር አለበት ወይስ የለበትም?”... የፖለቲካ መሰረታዊ ጥያቄ የዚህን ያህል ቀላል ነው። ጥያቄው፣ ጥቅም የሌለው ጊዜ ማሳለፊያ ወይም ጊዜ ማጥፊያ እንደሆነ አድርገን የምንቆጥረው ከሆነ፤ ጥርት አድርገን ለማሰብ አለመፈላጋችንን ያመለክታል። ራሳችንን ለመሸወድ ስንፈልግ ነው፤ ጥያቄውን የምናጣጥለው። አመቺ መስሎ ሲታየንማ፤ “መብቴ ነው፤ ንብረቴ ነው፤ ነፃነቴ ነው፤ በራሴ ሃሳብና ምርጫ የራሴን ሕይወት መምራት መብቴ ነው” ብለን እንከራከራለንኮ። ግን ይህንን ሃሳብ ከምር መሰረታዊ የፖለቲካ መርህ አድርገን ልንቀበለው አንፈልግም። ለምን ቢባል፣ ያልተመቸን ጊዜ፣ “ከግለሰብ መብትና ነፃነት በፊት የአገር ልማት፣ የህዝብ ጥቅም፣ የብሄር ብሄረሰብ ተዋፅኦ ይቀድማል” እንላለን። ለአገር ልማት በሚል ሰበብ ቅድሚያ ብድር ለማግኘት፣ ለህዝብ ጥቅም ተብሎ በሌሎች ሰዎች ላይ የዋጋ ተመን እንዲታወጅ፣ የብሄር ብሄረሰብ ተዋፅኦ በሚል ሰበብ ስልጣን ለመሻማት ስንፈልግ፤ የግለሰብ ነፃነትን እናጣጥላለን። አመቺ ሆኖ ሲታየን፤ “የሃሳብና የሃይማኖት ነፃነት፣ የመደራጀትና የመምረጥ መብት ይከበር” እንላለን። የማይመቸን ሃሳብ ለማፈንና በሰዎች ህይወት ላይ ለማዘዝ ስንፈልግ ደግሞ፤ “ከግለሰብ ነፃነት በፊት፣ አገራዊ መግባባትና የሃይማኖት ትዕዛዝ ይቀድማል” እንላለን። የነፃነት ነገር... እንደሁኔታው የምንጥለውና የምናነሳው፤ እንደአስፈላጊነቱ የምንክበውና የምንረግጠው፤ እንደአመቺነቱ የምንጮህለትና የምንጮህበት እንዲሆን እንፈልጋለን። ለዚህ ነው፤ መሰረታዊውን ጥያቄ የምናጣጥለው፤ ብዙም ልናስብበት የማንፈልገው። ነገር ግን፤ ልናስብበት ስላልፈለግን ብቻ መሰረታዊ ጥያቄነቱ አይሰረዝም። ሰው እስካለ ድረስ መሰረታዊው ጥያቄ ሁሌም ይኖራል። የነበረ፣ ያለና የሚኖር ጥያቄ ነው - በማንኛውም ጊዜና በየትኛውም አገር - ዛሬ በዘመናችንና እዚ በአገራችን ጭምር።
የአገራችንና የዘመናችን ዋና ዋና የፖለቲካ አጀንዳዎች ብዬ የማስባቸው ርዕሰ ጉዳዮችም፣ ከዚሁ መሰረታዊ የግለሰብ ነፃነት ጋር የተያያዙ ናቸው - ከሃሳብ ነፃነት፣ ከመደራጀት ነፃነትና ከመምረጥ ነፃነት ጋር የተያያዙ። በአንድ በኩል ከመንግስት የሚነጩ ሶስት ፈተናዎች አሉ። የሰዎችን ሃሳብ በማፈን የሚካሄድ መንግስት ፕሮፓጋንዳ የግለሰብ የሃሳብ ነፃነትን ይጥሳል። 1ለ5 የተሰኘው አደረጃጀትን ጨምሮ በመንግስት የሚካሄድ የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ የግለሰብ የመደራጀት ነፃነትን ይጥሳል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ፉክክር የሌለበት የአንድ ገዢ ፓርቲ ገናናነት፣ የግለሰብ የመምረጥ ነፃነትን ይጥሳል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ከተለያዩ ፓርቲዎች ወይም ቡድኖች የሚመነጩና የግለሰብ ነፃነትን የሚጥሱ ተጨማሪ ሶስት ፈተናዎች አሉ - የሃይማኖት አክራሪነት፣ በብሄር ብሄረሰብ የመቧደን ዘረኝነት፣ ለፖለቲካ ስልጣን ተብሎ የሚካሄድ አሸባሪነት።
ከላይ የተጠቀሱት ሶስት ሶስት ፈተናዎችን፣ መንታ መንታ አድርገን ልናያቸው እንችላለን። የመንግስት ፕሮፓጋንዳም ሆነ የሃይማኖት አክራሪነት የመጠንና የስልት ልዩነት ቢኖራቸውም፤ “እኛ የነገርንህን ሃሳብ የግድ መከተል አለብህ” በማለት የግለሰብን የሃሳብ ነፃነት ይጥሳሉ። የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካና የዘረኝነት ቅስቀሳም እንዲሁ፤ “የትውልድ ሃረግ እየቆጠርክ ተደራጅ” በሚል የሚያስገድዱ ናቸው። የአንድ ገዢ ፓርቲ ገናናነትና የፖለቲካ አሸባሪነትም እንዲሁ፤ “የመምረጥ መብት የለህም፤ ያዘዝንህን ፈፅም” በሚል የፈላጭ ቆራጭ መንፈሳቸው ይዛመዳሉ። በሌላ አነጋገር፤ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ናቸው።
ፈተናዎቹ፣ ለኢትዮጵያ የሰላምና የግጭት ጉዳይ መሆናቸውን ለመገንዘብ የሚያስቸግሩ አይመስሉኝም። በዚያው መጠን፣ የግለሰብ ነፃነት መከበርና አለመከበር፣ በሕይወት የመኖርና ያለመኖር፣ የብልፅግናና የድህነት ጥያቄ ነው ማለት ይቻላል - ለአገሪቱ የሰላምና የግጭት ጉዳይ ጋር የተቆራኘ ነውና። ለነገሩ፤ ኢህአዴግ “ዲሞክራሲ ለኢትዮጵያ የህልውና ጥያቄ ነው” እያለ በተደጋጋሚ እንደሚናገርና እንደሚፅፍ ይታወቃል። “የግለሰብ ነፃነት ለኢትዮጵያ የህልውና ጥያቄ ነው” ቢባል ይበልጥ ትክክለኛ ይሆናል።
ኢትዮጵያ ላይ ላዩን ስትታይ፤ የተረጋጋች ሰላማዊ አገር ትመስላለች። ነገር ግን፤ በቀላሉ ልትቃወስ የምትችል አገር ነች። የአፈና ፕሮፖጋንዳ፣ የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካና የአንድ ገናና ፓርቲ ስርዓት አገሪቱን ለሃይማኖት አክራሪነት፣ ለዘረኝነት ቅስቀሳና ለፖለቲካ አሸባሪነት እጅጉን የተጋለጠች እንድትሆን አድርጓታል።

የአፈና ፕሮፓጋንዳ ለሃይማኖት አክራሪነት ያመቻል
የአገራችን የሃይማኖት ተቋማትና ቡድኖች፣ ከአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር በጥብቅ የተሳሰሩ ናቸው። ለዚህም ነው፤ የፖለቲካ ለውጥና አለመረጋጋት በሚፈጠርበት ወቅት፤ በሃይማኖት ተቋማትና ቡድኖች ውስጥም የተለያዩ ቀውሶችና አዳዲስ እንቅስቃሴቶች የሚቀጣጠሉት። ኢህአዴግ ስልጣን ሲይዝ፣ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ሲኖዶስ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ከመነከሩም በተጨማሪ አወዛጋቢ ሹም ሽር እንደተካሄደበት ይታወሳል። በየአካባቢው ግጭት፣ እስርና ግድያ ሲፈጠሩ መቆየታቸውም አይዘነጋም። ከስልጣን የተሻሩት ፓትሪያርክ ከአገር ወጥተው በአሜሪካ ከሌሎች የሃይማኖት ተቋም መሪዎች ጋር ስደተኛ ሲኖዶስ አቋቁመዋል፤ ጳጳሳትን ሾመዋል። ውዝግቡ ለ20 አመታት መፍትሄ ባለማግኘቱ እርቅ አልወረደም። የአገር ቤቱ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ባለፈው ነሃሴ ወር ህይወታቸው ቢያልፍም፣ እስካሁን ሲኖዶሱ አዲስ ፓትሪያርክ ሳይመርጥ ወራት ተቆጥረዋል።
ኢህአዴግ ስልጣን ሲይዝ ጀምሮ ከውዝግብ ያላመለጠው የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትም እንዲሁ፣ በየጊዜው አወዛጋቢ በርካታ ሹም ሽሮችን እንዳካሄደ፣ ከዚሁም ጋር በየጊዜ ግጭት፣ እስር፣ ግድያ እንደተከሰተ ይታወቃል። የካቲት 1987 ዓ.ም በአዲስ አበባ የዘጠኝ ሕይወት ያለፈበትን ግጭት መጥቀስ ይቻላል። የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በዘንድሮው ምርጫም ከውዝግብ አልዳነም። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልሎች ግጭቶች ተከስተዋል። የፕሮቴስታንት ቤተክርስትያናት ውስጥ የፖለቲካ መልክ ያላቸው እንቅስቃሴዎች አነስተኛ ቢመስሉም፤ ከፖለቲካው አየር ጋር በውዝግብና በክፍፍል እንደሚታመሱ፣ ኢህአዴግ ስልጣን በያዘበት ወቅት ታይቷል።
በእርግጥ፣ ኢህአዴግ ገናና ፓርቲ እንደመሆኑ፣ በየጊዜው የሚከሰቱ ግጭቶችን መቆጣጠር ችሏል። ነገር ግን፣ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥም ሆነ፣ ሃይማኖትን ሰበብ አድርገው በተሰባሰቡ ቡድኖች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች በጣም አስቸጋሪ እንደሆኑ አይካድም። በጂማ በርካታ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡበት ግጭት አንድ ምሳሌ ነው። የግጭቶቹ መነሻና መድረሻ አስቀድሞ ለመገመት ያስቸግራል። ግን ለመቀጣጠል ዝግጁ የሆነ ቤንዚን በአንዳች ምክንያት መቀጣጠሉ አይቀርም። ከወልቃይት ስኳር ፋብሪካና ከዋልድባ ገዳም ጋር በተያያዘ ምን ያህል ግርግር እንደተፈጠረ አይታችኋል። የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምርጫና ከአወልያ ትምህርት ቤት ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባና በተለያዩ የክልል ከተሞች የተከሰተውን ግጭት ታዝባችኋል። አንዳንዱ ከሃይማኖት ነፃነት ጋር፣ አንዳንዱ ደግሞ ከሃይማኖት አክራሪነት ጋር የተያያዘ ነው።
በሃይማኖት ሰበብ የሚፈጠር ውዝግብና እና የአክራሪነት ግጭት በቀላሉ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን የሚችል ከፍተኛ የፖለቲካ አደጋ ነው። በጣም አሳሳቢው ነገር፣ የሃይማኖት ነፃነትንና የሃይማኖት አክራሪነት ለይቶ ለግለሰብ ነፃነት በፅናት የሚቆም ብዙ ሰው የለም። የሃይማኖት ነፃነትን መደገፍና የሃይማኖት አክራሪነትን መከላከል የሚቻለው፣ ለሃሳብ ነፃነት (ለግለሰብ ነፃነት) ከፍተኛ ክብር ሲኖረን ነው። ነገር ግን የሃሳብ ነፃነትን በሚጥስ የመንግስት ፕሮፓጋንዳ ተጥለቅልቀን እየኖርን፤ ለሃሳብ ነፃነት በፅናት የመቆም ብርታት እንዴት ሊኖረን ይችላል?
ከላይ እንደጠቀስኩት፤ መሰረታዊው የፖለቲካ ጥያቄ፤ እያንዳንዱ ሰው፣ የማሰብ፣ የመደራጀትና የመምረጥ ነፃነት ሊኖረው ይገባል ወይ?” የሚል ነው። “የግለሰብን ነፃነት የመጣስ ስልጣን የያዘ አካል መኖር አለበት ወይ?” ነው ጥያቄው። የመንግስት ስልጣን የያዙ ሰዎች የግለሰብን ነፃነት (የሃሳብ ነፃነት) የመጣስ መብት አላቸው የምንል ከሆነ፤ አክራሪዎችም መብት አለን ይላሉ።
ስልጣን የያዙ ሰዎች፣ ለነሱ የማጥማቸውን ሃሳብ በማፈን አገሬውን በፕሮፓጋንዳ የሚያጥለቀልቁት ለምንድነው? “ለአገር እድገትና ለህዝብ ጥቅም የሚበጅ ልማታዊ አስተሳሰብ እንዲሰፍን እንፈልጋለን” ይላሉ። ... ይህንንም አገራዊ መግባባት (national consensus) ይሉታል። እያንዳንዱ ሰው የማሰብና ሃሳቡን የመግለፅ ነፃነት ተከብሮለት፤ ተወያይቶና ተከራክሮ... አብዛኛው ሰው ተቀራራቢ አስተሳሰብ ቢይዝ ችግር የለውም። የተለያዩ ሃሳቦች እንዳይገለፁ በማፈን፣ ሁሉም ሰው በባለስልጣን የተነገረውን ሃሳብ እንዲይዝ በፕሮፓጋንዳ መጠዝጠዝ ግን ሌላ ጉዳይ ነው። የሃይማኖት አክራሪዎችምኮ ከዚህ የተለየ ብዙም ክፋት የለባቸውም። “ለሰው ልጅ ፅድቅ የሚበጅ፣ ገነት ለመውረስ የሚያስችል የፈጣሪ መንገድ እንዲሰፍን እንፈልጋለን” ይላሉ። ... ይህንንም “የሃይማኖት እምነት” ይሉታል። የመንግስት ፕሮፖጋንዳን በዝምታ የሚቀበል ስርዓት፤ አክራሪዎችን የመከላከል አቅምና መከራከሪያ መርህ አይኖረውም። ብቸኛው መከላከያ የግለሰብ የሃሳብ ነፃነት እንዲከበር ማድረግ ነውና።

የብሄር ብሄረሰብ ፓለቲካ፣ ለዘረኝነት ቅስቀሳ ይመቻል
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከሲዳማ ዞን ተነጥሎ ይዋቀራል በሚል ወሬ ሰበብ በከተማዋና በዙሪያዋ ተፈጥሮ የነበረውን ስጋት ታስታውሳላችሁ - ከተማዋ የእገሌ ብሄር ነች፤ የእነእከሌ ነች በሚል።
ከጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ህልፈት በኋላ ኢህአዴግ ሶስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮችን ለመፍጠር ወራት ፈጅቶበታል - የብሄር ተዋፅኦ ለመቀመር። ለነገሩ፤ ኢህአዴግ አንጋፋ መሪዎችን በአዳዲስ መተካት ሲጀምር ጎልቶ የተነሳው የመጀመሪያ ጥያቄ ከብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነው - የእገሌ ብሄረሰብ ስልጣን አላገኘም፤ የእንቶኔ ተጎዳ በሚል። ለነገሩ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ወሬ በተነሳ ቁጥር፤ ወዲያውኑ ብቅ የሚለው ጉዳይ የዘርና የብሄር ብሄረሰብ ተወላጅነት ሆኗል - ከሙስና ጋር ተቆራኝቶ። በብሄር ብሄረሰብ ስም በመቧደን የሚፈጠር የስልጣን ሽኩቻና ግጭት አገሪቱን ሊያናውጥ የሚችል ሌላኛው የፖለቲካ አጀንዳ ነው። የግለሰብ የመደራጀት ነፃነትን የሚጥስ የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ፤ የግለሰብ ነፃነትን ለሚጥስ የዘረኝነት ቅስቀሳ ያጋልጣል።
ገናና መንግስትና የፖለቲካ አሸባሪነት
ሶስተኛው የፖለቲካ አጀንዳ የመንግስትን ስልጣን ሙሉ ለሙሉ ጠቅልሎ እድሜ ልክ እንደ ርስት የመቆጣጠር አባዜ ነው። ኢህአዴግ ቢያንስ ለሚቀጥሉት ሃያ አመታታ ያለ ተቀናቃኝ ስልጣንን በብቸኝነት ይዞ ለመቆየት ቆርጧል። ብዙ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ኢህአዴግን በማስወገድ ስልጣን ለመያዝ የሚመኙ ናቸው። የጠላትነትን መንፈስ ያሰፍናል - አሁን የምናየውን አይነት። ለምሳሌ ከ2002 ዓ.ም ወዲህ ኢህአዴግ በፌደራልና በክልል፤ በወረዳና በቀበሌ ከ99.5% በላይ በማሸነፍ ሙሉ ለሙሉ ስልጣን መቆጣጠሩ አገሪቱን ወደ አለመረጋጋት ይወስዳታል ብለው እንደሚያስቡ የአሜሪካ እና የአውሮፓ መንግስታት በተደጋጋሚ ገልፀዋል።
የስልጣን ጉዳይ ውስጥ ከመግባት በእጅጉ የሚጠነቀቀው የአለም ባንክ ሳይቀር ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ሪፖርት ውስጥ፤ ኢህአዴግ ከላይ እስከ ታች ስልጣኑን አስፋፍቶ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቦታ ማጣታቸውን መዳከማቸው፤ ውጥረትን አስከትሏል ሲል ፅፏል። የፓርቲዎች የምርጫ ፉክክር ሲጠፋ፤ ስልጣን ለመሻማት የፓርቲዎች መቆራቆስና መጋጨት ስለሚከተል፤ ትልቅ አጀንዳ መሆን ይገባዋል። ነገር ግን የፓርቲዎች ፉክክር ከዜጎች የመምረጥ መብት ውጭ ትርጉም የለውም። ነገር ግን ዋናው ጥያቄ የፓርቲዎች ቦታ ማጣት ሳይሆን፤ ዜጎችን አማራጭ የማሳጣትና የመምረጥ መብታቸውን ያለማክበር ገዳይ ነው። አድራጊ ፈጣሪ ፈላጭ ቆራጭ ገናና መንግስት የመሆን ጉዳይ ነው። ግለሰቦች የራሳቸውን ሕይወት በራሳቸው ምርጫ የመምረጥ ነፃነታቸውን እንዲያጡ የሚያደርግ ገናና መንግስት ሊፈጠር የሚችለው፤ የዜጎችን የሃሳብ ነፃነትና የመደራጀት ነፃነት በመርገጥ ነው። የፖለቲካ አሸባሪነትም ተመሳሳይ መንገድ የሚከተል ነው። በሌላ አነጋገር፤ ሶስቱ የፖለቲካ አጀንዳዎች እርስ በርስ የተሳሰሩ የግለሰብ ነፃነት አጀንዳዎች ናቸው።

Read 7294 times