በ2002 ምርጫ የተወሰኑ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውና ታዛቢዎቻቸው እንደታሰሩና እንደተባረሩባቸው በመግለፅ ቅሬታ አቅርበው እንደነበር ያስታወሰው ምርጫ ቦርድ፤ በዚያው ጊዜ ጉዳዩን አጣርቶና የተባለው ችግር አለመፈጠሩን ተገንዝቦ ምላሽ እንደሰጠበት ገልጿል።
“በከፍተኛ ማጭበርበር 99.6 ውጤት የተገኘበት ዓይነት ምርጫ እንዲደገም አንፈቅድም” ያሉት ፓርቲዎቹ፤ “በዘመነ ኢህአዴግ ከተደረጉ ምርጫዎች ሁሉ በዘረፋውና በኢ-ዲሞክራሲያዊነቱ የ2002 ምርጫን ተወዳዳሪ የለውም” ሲሉ በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል፡፡ የተሰራ ጥናት ጠቅሰው አስረድተዋል፡፡
ጥያቄያቸውን ከአንድ ወር በፊት ማቅረባቸውንና የቦርዱ ሃላፊዎች ባለፈው ዕሮብ በፅ/ቤታቸው ሲጠሯቸው ለውይይት መስሏቸው እንደነበር የጠቆሙት ፓርቲዎቹ፤ ሃላፊዎቹ ግን ‹‹ያነሳችኋቸው ጥያቄዎች አግባብ አይደሉም፤ ይህንኑ ለህዝብ ይፋ አድርጉት›› የሚል ምላሽ በቃል ሰጥተውናል፤ ይህም ፓርቲዎችንና የኢትዮጵያ ህዝብን መናቅ ነው ሲሉ ነቅፈዋል፡፡
ፓርቲዎቹ ባለፈው ሳምንት ባለ 18 ነጥቦች ቅሬታ ለጠ/ሚ ጽ/ቤት ማስገባታቸውን ገልጸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት የኢህአዴግ መንግስት 18ቱ ነጥቦች ትክክል መሆናቸውን ከምርጫ ቦርድ የበለጠ ያውቁታል፤ እንደ ምርጫ ቦርድ ሽምጥጥ አድርገው ይክዱታል ብለን አናስብም ብለዋል፡፡ ምርጫ ቦርድ ገዥውን ፓርቲም ሆነ እኛን እኩል ማስተዳደር ሲገባው ይሄን ሃላፊነቱን አልተወጣም ሲሉም ትችታቸውን ሰንዝረዋል - ተቃዋሚዎቹ፡፡
በሚያዝያ ወር በሚካሄደው የአዲስ አበባና የአካባቢ ምርጫ ላይ ይሳተፉ እንደሆነ የተጠየቁት ፓርቲዎቹ፤ ገና ውሳኔ ላይ አለመድረሳቸውን ገልፀዋል፡፡ “ህዝብንና ተቃዋሚን በናቀ ስሜት ወደ ምርጫ እንገባለን ብሎ ማሰብ ያስቸግራል፤ ግን ተስፋ አንቆርጥም፤ የመብት ጉዳይ ስለሆነ ከህዝብ ጋር ሆነን ህገ-መንግስቱ በሰጠን መብት እንጠቀማለን” ብለዋል፡፡
ፓርቲዎቹ መድረክን ይቀላቀሉ እንደሆነ ተጠይቀውም፤ “መድረክ ለዚህች አገር የሚጠቅም ከሆነ አባል እንሆናለን፤ እንቀላቀላለን” በማለት መልሰዋል፡፡