Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 22 December 2012 10:04

ቅ/ሲኖዶስ የሠየመው የፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ ዓለም አቀፍ ተቃውሞ ቀስቅሷል

Written by 
Rate this item
(11 votes)

‹‹ዕርቀ ሰላሙ ይቅደም›› የሚሉ ጳጳሳት የሲኖዶሱን ውሳኔ አንቀበለውም ብለዋል
የላሊበላው ውዝግብ ወደ አላስፈላጊ ግጭት እንዳያመራ ተሰግቷል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የስድስተኛውን ፓትርያሪክ ምርጫ ዝግጅት የሚመራና እስከ ጥር መጨረሻ ዕጩዎችን የሚያቀርብ አስመራጭ ኮሚቴ መሠየሙ በቤተ ክርስቲያኒቱ ካህናትና ምእመናን ዘንድ ዓለም አቀፍ ተቃውሞ መቀስቀሱ ተገለጸ። ‹‹የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ያገባኛል›› በሚል መርሕ በዋናነት በማኅበራዊ ሚዲያዎችና ብሎጎች እየተገለጸ ያለው ይኸው ተቃውሞ፤ የቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት የሚረጋገጥበት የዕርቁ ጉባኤ ‹‹የአባቶች ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ ምእመናኑን ያገለለ ሊኾን አይገባም›› በሚል የካህናቱና ምእመናኑ ድምፅ እንዲደመጥ የሚወተውት ነው፡፡

የቅ/ሲኖዶሱ አባላት የኾኑ ሊቃነ ጳጳሳትን ጭምር ያካተተው የዚህ ተቃውሞ መነሻ÷ የአስመራጭ ኮሚቴው መቋቋም በሀገር ውስጥ በሚኖሩትና በውጭ አገር በስደት በሚገኙት አባቶች መካከል ለሚካሄደው የዕርቀ ሰላም ውይይት መሰናክል ይኾናል በሚል ነው፡፡
የቅ/ሲኖዶሱ የዕርቀ ሰላም ልኡክ በመኾን ወደ አሜሪካ ከተጓዙትና በዳላስ ቴክሳስ ከኅዳር 26 - 30 ቀን 2005 ዓ.ም በሰላምና አንድነት ጉባኤ አመቻችነት በተካሄደው የዕርቀ ሰላም ውይይት ላይ የተሳተፉት የደቡብ ወሎ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ ከትናንት በስቲያ ምሽት ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ በሰጡት አስተያየት÷ ቅ/ሲኖዶሱ እንደላካቸውና በሰላሙ ጉዳይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገሩ ‹‹ስንዝር ያህል መራመዳቸውን›› ገልጸዋል፡፡ የዕርቀ ሰላም ልኡካኑ ይህን እያደረጉ ባለበት ኹኔታ ስለ ፓትርያሪክ ምርጫ መወያየትና አስመራጭ ኮሚቴ ማቋቋም ‹‹ኾኗል ብለን አናምንበትም፤ ኾኖ ከተገኘ ግን አንቀበለውም፤ እንቃወመዋለን›› ብለዋል - በቅ/ሲኖዶሱ ውሳኔ ቅር የተሰኙት ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ፡፡
በሰሜን አሜሪካ የዋሽንግተን ዲሲ እና ካሊፎርኒያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በበኩላቸው÷ የጥቅምት ቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የወሰነው የፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንብ ተዘጋጅቶ የአሁኑ ስብሰባ እንዲጠራ እንጂ አስመራጭ ኮሚቴ ማቋቋም አዲስ ሐሳብ መኾኑን ለሬዲዮው በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል፡፡ በጥር ወር አጋማሽ በካሊፎርኒያ ሎሳንጀለስ ቀጣይ የሰላም ጉባኤ ለማካሄድ ቀጠሮ መያዙን ያስታወሱት ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል፤ የኮሚቴው መቋቋም የዕርቁን ሂደት እንዳያበላሸው ስጋት እንዳላቸው በመግለጽ ቅ/ሲኖዶሱ ከዕርቀ ሰላም ጉባኤው በፊት ሰፋ ያለ ሥራ ከማከናወን እንዲከለከል አሳስበዋል፡፡
የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምንጮች ለአዲስ አድማስ እንደገለጹት÷ ቅዱስ ሲኖዶስ የስድስተኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ ባቋቋመበት ስብሰባ ላይ የተገኙ አንዳንድ ሊቃነ ጳጳሳት÷ ‹‹አስመራጭ ኮሚቴውን ከመሠየማችን በፊት ቢያንስ ወደ አሜሪካ የተጓዘው ልኡክ እስኪመለስ መታገሥና ሪፖርቱን መስማት አለብን›› በማለት የቅ/ሲኖዶሱን ውሳኔ ተቃውመዋል፡፡ የተቃውሞውን አቋም ለማስቀየርና በውሳኔው ቃለ ጉባኤ ላይ ለማስፈረም እንዲሁም ውሳኔው ለብዙኀን መገናኛ እንዲገለጽ ለማድረግ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱና ከመንግሥት ተወክለዋል የተባሉ ከፍተኛ ሓላፊዎች በተለይ በቅ/ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ላይ ጠንካራ ጫና በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ምንጮቹ ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ በመንፈሳዊ ልዕልናዋ፣ ለትውልድ ባላት አርኣያነትና ለዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ተልእኮዋ መጠናከር ልታስቀድመው ከሚገባት የዕርቅና ሰላም አጀንዳ አንጻር ‹‹ከፓትርያሪክ ምርጫው በፊት አንድነቱ ይቅደም›› በሚል የተያዘው አቋም ‹‹መደገፍ ይኖርበታል›› የሚሉት ምንጮቹ÷ የሊቃነ ጳጳሳቱን አቋም ለማስቀየር የሚካሄደውን ርብርብ በጣልቃ ገብነት ነቅፈዋል፡፡ የዕርቀ ሰላም ልኡካኑ ሪፖርታቸውን ለማቅረብ ዘግይተዋል የሚሉ ሌሎች ወገኖች በአንጻሩ÷ አስመራጭ ኮሚቴ መቋቋሙ የዕርቀ ሰላሙን ሂደት ሊያደናቅፈው እንደማይችል በመጥቀስ የፓትርያሪክ ምርጫ ሂደቱ መቀጠል እንደሚገባው ይከራከራሉ፡፡
በዳላስ ቴክሳስ ለሦስተኛ ጊዜ በተዘጋጀው ጉባኤ አበው ላይ ከኢትዮጵያና ከሰሜን አሜሪካ ቅዱስ ሲኖዶስ በተሠየሙ የሰላም ልኡካን ኅዳር 30 ቀን 2005 ዓ.ም የወጣው ባለሰባት ነጥብ የጋራ መግለጫ÷ አራተኛው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ ኢትዮጵያ ስለሚመለሱበት ኹኔታ ከሁለቱም ወገኖች የተሰጡ ምክንያቶች በዝርዝር ታይተውና ተጠንተው እየተመከረባቸው የመጨረሻ ውሳኔ እንዲያገኙ፤ የሰላሙ ጥረት ለፍጻሜ እስከሚደርስ ድረስ ሁለቱም ወገኖች ለሰላሙ መሰናክል የሚኾኑ ማናቸውንም ሥራዎች ከመሥራት ተቆጥበው ትዕግሥት እንዲያደርጉ፤ ከጥር 16 - 18 ቀን 2005 ዓ.ም በካሊፎርኒያ ሎሳንጀለስ ለሚካሄደው አራተኛው ዙር የዕርቀ ሰላም ውይይት የሰላምና አንድነት ጉባኤው ልኡካን ወደ ሁለቱም ወገኖች ተልከው የማግባባትና የማቀራረብ ሥራ እንዲሠሩ ከስምምነት ላይ መደረሱን ያመለክታል፡፡
ይኹንና ከታኅሣሥ 1 ቀን ጀምሮ ከሳምንት በላይ ሲካሄድ የቆየው የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የፓትርያሪክ ምርጫ፣ ሕገ ደንብ አጽድቆ ምርጫውን የሚያስፈጽም 13 አባላት ያሉት አስመራጭ ኮሚቴ መሠየሙ ተገልጧል፡፡ የኮሚቴው አባላት ከቅ/ሲኖዶስ አባላት፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መምሪያዎች፣ ከታላላቅ ገዳማትና አድባራት፣ ከሰንበት ት/ቤቶች እና ከማኅበረ ቅዱሳን እንዲሁም ከታዋቂ ግለሰቦች የተውጣጡ ናቸው ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል÷ በሰሜን ወሎ ሀ/ስብከት በደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም ከብልሹ አሠራርና ሙስና እንዲሁም እየተባባሰ ነው ከሚባለው የቅርሶች ጉዳት ጋር ተያይዞ÷ አስተዳደሩ ከካህናቱና ምእመናኑ ጋር የገባበት ያልተፈታ ውዝግብ ከቁጥጥር ውጭ ኾኖ ወደ አላስፈላጊ ግጭትና ደም መፋሰስ እንዳያመራ ታላቅ ስጋት እንዳላቸው የከተማው ምእመናን ገልጸዋል፡፡ በቁጥር ከአንድ ሺሕ በላይ በሚደርሱ የገዳሙ ካህናትና ምእመናን ፊርማ የተደገፈውን አቤቱታቸውን በአዲስ አበባ ተገኝተው በድጋሚ ለቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት ያቀረቡት የምእመናኑ ተወካዮች÷ ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹በርግጥ አንድ ሰው በአንድ ቦታ ለስምንት ዓመት መቀመጡ አግባብነት የለውም፤ እንጀራም ይሻግታል›› ያሉት ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ፤ ከሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ጋር በመነጋገር መፍትሔ እንደሚሰጧቸው እንደነገሯቸው ምእመናኑ ለዝግጅት ክፍሉ አስታውቀዋል፡፡
በደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም በደማቅ ኹኔታ የሚከበረውና በቱሪስት መስሕብነቱ የሚታወቀው የገና (ቤዛ ኵሉ) እና የቅዱስ ላሊበላ ልደት በዓል በቀረበበት ኹኔታ በአስከፊ አስተዳደራዊ በደላቸውን መቀጠላቸው የሚነገርባቸው የገዳሙ አለቃ÷ አቤቱታ አቅራቢ ምእመናን እንዲታሰሩና እንዲንገላቱ ማድረጋቸውን፣ ካህናቱንና ምእመናኑን ከደመወዝና ከሥራ ማገዳቸውን እንደቀጠሉ መኾኑ ከከተማው ጸጥታ አንጻር ስጋት እንደሚፈጥር፣ ከሀ/ስብከቱና ከተማው አስተዳደር አቅም በላይ ኾኗል የተባለው ይኸው ጉዳይም በሰሜን ወሎ ዞን የፍትሕ፣ የፖሊስ እና የጸጥታ ጽ/ቤቶች እንደሚታወቅና በእነርሱም በኩል የክልሉ መንግሥት እንዲያውቀው መደረጉ ተመልክቷል፡፡

Read 5520 times