Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 22 December 2012 09:48

‘ጭድ’ና ዘመን…

Written by 
Rate this item
(6 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…‘ጄኒዩን’ የሚባል ኦሪጂናሌ ነገር ማግኘት እየከበደ ነው፡፡ ብዙ ነገር አስመስሎ እየተሠራ ግራ እየተጋባን ነው፡፡ ብዙዎቻችን በተለያዩ ነገሮች…አለ አይደል…‘ጦጣ’ ነገር እየተደረግን ነው፡፡
“የፒያሳ ልጅ ነኝ፣ ሌላውን አሞኛለሁ እንጂ አልሞኝም…” “የመርኬ ልጅ ሆኜማ የፈለገ የጨስኩ ብልጥ ነኝ ያለ እኔን አያታልለኝም…” ምናምን ብሎ ፉከራ ዘንድሮ አይሠራም፡፡
የብልጥነት ነገር ካነሳን ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው ልጃቸውን ሂሳብ ነገር ሊያስተምሩት ሦስት ማንጎ ጠረዼዛ ላይ ያስቀምጡና ልጁን ምን ብለው ይጠይቁታል…“እነኚህን ሦስት ማንጎዎች ለአራት ሰው እንዴት አድርገህ ታከፋፍላለህ?” ይሉታል፡፡ ልጁ ምን ብሎ መለሰ መሰለችሁ… “ማንጎዎቹን ጁስ አደርጋቸዋለሁ…” አሪፍ አይደል! የዚህን ልጅ አይነት ‘ብልጥነት’ ያብዛልንማ!
ምን ይገርምሀል አትሉኝም…ይሄ የ‘ፎርጀሪ’ ነገር እንዴት እየተሻሻለ እንደሄደ! (በዛ ሰሞን ኪሱ ሞላ ባለ ሰሞን የውስኪ ወዳጅ የሚሆን ወዳጄ ምን አለኝ መሰላችሁ…“በፊት ብራንዲ ከሌላ ጠርሙስ በሲሪንጅ እየተመጠጠ ውስኪ ጠርሙስ ውስጥ እየተከተተ ውስኪው ‘ይወጋ’ ነበር፡፡

አሁን፣ አሁን መውጋት ምናምን ሳያስፈልግ ኦሪጂናሌ የስኮትላንድ ውስኪ አድርጎ ማሸግ እየተለመደ ነው እየተባለ በወረቅ ውሀው ሰፈር ይወራል” አለኝ፡፡) 
እናላችሁ… “ፎርጀሪና ኦሪጂናሌ የመለየት ጥበብ የሦስት ወራት ኮርስ እንሰጣለን…” ምናምን የሚል ተቋም የሚያስፈልገን ጊዜ ላይ ልንደርስ ምንም የቀረን አይመስልም፡፡
እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…እነዚሀ ሀብታሞች ሰፈር ነገርዬው ሁሉ እየተለወጠ ነው አሉ፡፡ (ምን አለ በሉኝ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ሀብታሞቻችን ‘ኤክስትራቴሬስትያል’ የሚባሉት የሌላ ዓለም ፍጡራን ነገር ባይመስሉን ምን አለ በሉኝ፡፡) እናላችሁ… ሀብታሞቹ ሰፈር እርስ በእርሳቸው ‘ቢዙ’ ሲያጧጡፉ እንደ ድሮ ሦስት ሚሊዮን ብር፣ አምስት ሚሊዮን ብር ብሎ ነገር እየቀነሰ ነው አሉ፡፡
ታዲያማ… ምን ይባባላሉ መሰላችሁ…“በጭዱ ከሆነ አልፈልግም፡፡” ‘ጭዱ’ ምን መሰላችሁ…መከረኛው ብራችን! ነገርዬው ሁሉ በዩሮ እየሆነ ነው አሉ፡፡ ጭድ! እኛ “…ሳይወደድ ሁለት ኪሎ በርበሬ የምገዛበት አንድ መቶ ብር ይኖርሀል?” ብለን ወዳጅ ለወዳጅ ለመጠያያቅ እንሳቀቃለን…ጭራሽ አንደኛውን ጭድ ተባለና አረፈው!
ለነገሩማ…የነገርዬዋ አቅም ማነስማ የሚያስገርም ነው፡፡ ፐርሰንት ማውራት ከጠዋትና ማታ ፀሎት በበለጠበት አገር ምነዋ ነገርዬዋ ቁጥሯ ብዙ አቅሟ ኢምንት ሆነሳ! ቀደም ሲል በመስከረም የገዛችሁት ነገር ጨመረ ሲባል በሚያዝያ ሀያ ሦስት ብር ሊገባ ይችላል፡፡ ዘንድሮ መስከረም ሦስት በሀያ ብር የገዛችሁት ነገር መስከረም ሰባት ሠላሳ ብር ከሰባ አምስት ሳንቲም ሊሆን ይችላል፡፡
እናላችሁ… እነሱ ‘ጭድ’ ቢሉት ለእኛ ደግሞ ገና ማኛ ጤፍ ነው— ምንም እንኳን መቶ ብር አንድ ትንሽ ፌስታል ቆስጣና ሰላጣ መሙላት ቢያስቸግራትም፡፡
(ሆድን በጎመን ቢደልሉት…ምናምን የሚለው ተረት ይቀየርልንማ፡ ልክ ነዋ…ተረት የሚኖረው መጀመሪያ ‘ጎመኑ’ ሲገኝ ነዋ!)
ስሙኝማ…‘ጭድ’ የምትለው ነገር እንደ ሀብታሞቹ አተረጓጎም ባይሆንም፣ በሌላ በኩል እንዴት አሪፍ አባባል መሰለቻችሁ! ብዙ ነገር የ‘ጭድ’ ያህል እንኳን ዋጋ እያጣብን ነዋ! (“…ሰውም ጭምር…” የሚለው በቅንፍ ውስጥ እንደተካተተ ልብ ይባልልንማ!)
እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ፣ ይቺን ስሙኝማ…እዚሁ አዲስ አበባ የሚገኝ ስም ያለው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው አሉ፡፡ እናላችሁ…አስተማሪነት ለመቀጠር ካመለከቱት መሀል የተመረጡት የፈተና ቀን ተሰብሰበዋል፡፡ ታዲያማ፣ ፈተናው ከመጀመሩ በፊት ተፈታኞቹ (የወደፊቶቹ ‘አስተማሪዎች’) ምን ጥያቄ አቀረቡ መሰላችሁ… “ፈተናው በአማርኛ ይሁንልን…” አሉላችሁ! አይገርምም! እናማ…የሥራ ማመልከቻ ለመጻፍ እንኳን እርዳታ የሚጠይቁ ተመራቂዎች ቢበዙ ምን ይገርማል! (አንዳንድ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሰልጠኛ ተቋማት አካባቢ ከፍ ባለ ደረጃ እንኳን ማብራሪያ የሚሰጠው በአማርኛ ነው ሲባል የምንሰማው እውነት ከሆነ የምር አስገራሚ አይደለም!) እናላችሁ… ብዙ ነገሮች የ‘ጭድ’ ያህልን እንኳን ዋጋ ሲያጡ የምር ያሳስባል፡፡
እናማ… በየቦታው የ‘ጭድ’ ያህል እንኳን ዋጋ የማያወጡ ነገሮች እየበዙብን ነው፡፡
“ፈተና በአማርኛ ይሁንልኝ…” የሚል የከፍተኛ ደረጃ አስተማሪ ባለበት አገር የተማሪዎቹ ችሎታ “ኸረ የአገር ያለህ…” ቢያሰኝ አይገርምም፡፡
ይቺን በቀደም አንድ ወዳጄ የነገረኝን ነገር ስሙኝማ…ሰውዬው “…እስከ አፍንጫው” የተማረ ሰው ነው አሉ፡፡ እና ብዙ ቦታ ሲሠራ ኖሮ ለተሻለ ደሞዝ የሆነ ቦታ ይወዳደርና ፎርም እንዲሞላ ይሰጠዋል፡፡ ፎርሙ ላይ Marital Status (ያገባ/ያላገባ ለማለት) የሚል ክፍል አለ፡፡ እናላችሁ ሰውየው ባለትዳር ስለነበር እዚህ ቦታ ላይ ምን ብሎ መለሰ መሰላችሁ… “Wifed.” ደስ አይልም! ሀሳብ አለን…ተረቱ ይለወጥና የ‘አንኮበር ቅጠል’ ነጻ ትውጣልን! ልክ ነዋ…“ጉድ በል የሀበሻ ልጅ…” የሚያስብሉ መአት ነገሮች እያሉ ዘላለም “ጉድ በይ የአንኮበር ቅጠል…” እያሉ መኖር ‘ፌይር’ አይደለማ! ለነገሩ ቅጠሏስ ‘ዲፎርስቴሽን’ ምናምን እስካሁን ባያጠፋት ነው! (እንትናዬ አንቺ ደግሞ... አለ አይደል… “Husbanded” በዪና ግጥም አድርጊውማ! ማን ከማን ያንሳል! ከፈለግሽኝ በፈረንጅ አፍ “ሁ ማይነስ ሁ?” ማለት ትችያለሽ፡፡ ልክ ነዋ…መቼስ ከ “Wifed” ሳይሻል አይቀርም፡፡)
እናላችሁ…እንዲህ አይነት የ‘ጭድ’ ያህል ዋጋ የሚያወጡ ነገሮችና የ‘ጭድ’ ያህል ዋጋ የማናወጣ ሰዎች የበዛንበት ዘመን ላይ ደርሰንላችኋል፡፡
እኔማ…እንግዲህ የልብ ጨዋታም አይደል ‘ቦተሊካው’ ራሱ የ‘ጭድ’ ያህል እንኳን ዋጋ እያጣሁበት ተቸግሬያለሁ፡፡ አለ አይደል… ነገሩ ሁሉ ‘ዘ ሴም ኦልድ ስቶሪ’ ‘ዘ ሴም ኦልድ ፒፕል’ እና ‘ዘ ሴም ኦልድ ኢትየዽያ’ ምናምን ነገር እየሆነብኝ ‘ቦተሊካ’ ነገር ሲነሳ የ‘ቶም ኤንድ ጄሪ’ ፊልም ምናምን ትዝ ሊለኝ ምንም አይቀረው፡ ወጡ ያው ቢሆን እንኳን ብረት ድስቱ እንኳን ወደ ሸክላ ድስት ይለወጥልን! ቂ…ቂ…ቂ…ስሙኝማ…የ‘ጭድ’ ነገር ደህና ደህናው ነገር እንዳማረን እያዛጋን እንድንቀር እያደረገን ነው፡፡
ይኸው ኪሎ ሥጋ እስከ 200 ብር እየተጠየቀበት አይደል! እናላችሁ…አንዳንድ ቦታ ሥጋ ልትገዙ ስትሄዱ ምን ይሏችኋል መሰላችሁ…“ሎካሉን ነው ወይስ ፎሪኑን?” ኮሚክ አይደል! ለ‘ስታንድ አፕ ኮሜዲ’ የሚሆነው ነገር ምን መሰላችሁ… ‘ሎካሉ’ም ‘ፎሪኑ’ም ሥጋ ከአንዱ በሬ መገኘቱ! እናማ… ‘የቁርጥ አገር’ እንዳልነበረ ሁሉ…አለ አይደል…በሆዳችንም የ‘ጭዱን’ ልብ ልቡን እያጣነው ነው፡፡ሀሳብ አለን… የልጆች የታሪክ መጻሕፍት ይከለሱልንማ! ልክ ነዋ “በድሮ ጊዜ እከሌ ይባሉ የነበሩ ንጉሥ ኢትዮዽያን ይገዙ ነበር…” ምናምን እንደሚባለው ሁሉ “በድሮ ጊዜ አብዛኛው የኢትዮዽያ ሕዝብ ሥጋ የሚባል ከከብት የሚገኝ ምግብ እየገዛ ይመገብ ነበር…” ምናምን የሚባል ነገር ለማካተት ልንገደድ እንችላለና!
እና ‘ጭድ’ ነገሮች እየበዙ ‘ኦሪጂናሌ’ ነገሮችና ‘ኦሪጂናሌ” ሰዎች እያነሱ ነው፡፡ መድኃኒት ስንገዛ ‘ጭድ’ ይሆናል ብለን እየተሳቀቅን ሆኗል፣ ልብስ ስንገዛ ‘ጭድ’ ይሆናል ብለን እየተሳቀቅን ሆኗል፣ የታሸገ ነገር ስንገዛ ‘ጭድ’ ይሆናል ብለን እየተሳቀቅን ሆኗል፡፡ ልክ ነዋ…ድሮ እኮ ‘ሜድ ኢን’ ምናምን የሚለውን እያየን ደረታችንን ነፋ አድርገን “ይሄ ትክክለኛው ነው…” ምናምን ብለን እንመርጥ ነበር፡፡ ልጄ ዘንድሮ አስመስሎ የማይሠራ ‘ጭድ’ ምርት ስለሌለ ስንገዛ “አንተ ብቻ ጠብቀን…” እያልን እየጸለይን ሆኗል፡፡
ይቺን ስሙኝማ…ባልና ሚስት እየተነጋገሩ ነው፡፡
“ለጓደኛህ ያገባኋት ምግብ በማብስል ባለሙያ ስለሆነች ነው ብለኸዋል እንዴ?”
“አዎ፣ ብየዋለሁ፡፡”
“ለምንድነው እንደዛ ያልከው? እኔ… አይደለም ማብሰል፣ እንቁላል መጥበስ እንኳን አልችልም አይደል እንዴ!”
“ታዲያ አንቺን ለማግባቴ ሌላ ምን ምክንያት ልስጠው”
ከዚህ ሰውረን ማለት ነው፡፡ እሷዬዋ እኮ ከ‘ጭድ’ የተሻለ ዋጋ የሚያወጣ ባል አለኝ ብላ…አለ አይደል…ይሄኔ እኮ “ስስቅ መንግሥተ ሰማያት የገባ ያህል ነው ደስ የሚለው…” “በስዊሚንግ ልብስ ሲያኝ እንዴት ልቡ እንደሚጠፋ አልነግርሽም…” ምናምን ስትል ከርማ ሊሆን ይችላል፡፡ እናማ የ‘ጭድ’ ያህል እንኳን ዋጋ የማያወጡ ነገሮች እየበዙብን ተቸግረናል፡፡ አንድዬ ‘ጭዱ’ን ቀንሶ እህሉን ያብዛልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 7962 times